Sunday, October 20, 2013

እውነቱ ስንናገር ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዘብ አልቆሙም!!



የካህናቱና ጡረተኞች የተሰገሰጉበት የሰበካ ጉባዔ ምእመናን ተወካዮች በዓመት አንድ ጊዜ ተሰብስበው በሚመሰጋገኑበትና የድግስ ጋጋታ በሚያስተናግዱበት የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባዔ ላይ ስለመቻቻል የቀረበውን አጀንዳ አስታከው ጳጳሳቱ ስሜታቸውን መግለጻቸውን ሰምተን ጥቂት ተደነቅን። እንዴት ወንድ ወጣቸው? ብለንም ጥቂት አድናቆትን ቸርናቸው። ለካስ ከቀሚሳቸው ስር ሱሪ ታጥቀዋል?  ይሁን እንጂ  ሱሪ ነገረ ስር አይሆንምና ነገሩ አጋጣሚን የመጠቀም እንጂ የወንድነት አይደለም።
  በዚያች የመቻቻል መድረክ ለመተንፈስ ከመፈለጋቸው በስተቀር በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለመፍታት አንዳችም ህልምና ርእይ እንደሌላቸው የተገነዘብንበት ሁኔታ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደተቋም የት ነበረች? አሁንስ የት ነው ያለችው? ወደፊት እንዴትና የት ትራመዳለች? ለሚለው አንኳርና ቁልፍ የመንፈሳዊ ጉዞ መልህቅ መጣያ የሚሆን የሃሳብ ወደብ አንዳችም ሳናይ በማለፉ ግንፍል ንግግራቸውን ታዘብነው። አንድም አባል ቢሆን ሲጎዳ ማየት ልብን እንደሚሰብርና መንፈሳዊ ልማት ማካሄድ የሚቻልበትን አንድም ጋት ይዞታን ማጣቱ ቢያንገበግብም  የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ችግር በመሬት ተወሰደብኝና አንድ አባል ታሰረብኝ በሚል አቤቱታ የሚገለጽ አልነበረም። ይሁን እንጂ ጳጳሳቱ ሲጮሁ የሰማነው ንግግር በቁራሽ መሬትና በአንድ ምእመን መጎዳት ላይ ማተኮሩ የችግሩን ስፋት ለመመልከት አለመቻላቸውን ያመላከተ ሆኖ አልፏል።

በጳጳሳቱ ሊታይ ያልቻለውና መታየት የነበረበት የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥና የውጪ ችግር፤
  1/ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል፤ ሲዘረፍ፤ ምእመናንና ምእመናት ሲሰደዱ፤ በአሸባሪና በአክራሪዎች ሲገደሉ መቆየታቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን አንድም ጊዜ የጳጳሳቱን የድፍረት ሱሪ በንግግር አላየንም። ለምን? አንድም የፍርሃት ቆፈን ወሮአቸዋል። አለያም የመንፈሳዊነት እንጥፍጣፊ አልቆባቸዋል። የመቻቻል ፖለቲካ ዲስኩር ሲፈነዳ አብሮ ማንዳዳት ያስተዛዝባል እንጂ አባቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ዘብ ቆሙላት አያሰኝም።

2/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንግሥታዊ ሃይማኖት ሆና ለዘመናት በመቆየቷ ብቻ ጊዜ አመጣሾች እንደጠላት ቢመለከቷትም ዘመንና ወቅት እንደዚያ ሆና እንድታልፍ ያደረጋትን ከመቀበል ውጪ «መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው» የሚል ሕግ ለመቅረጽ ስለማትችል ይህንን ሁሉ አስልተው እንደባላንጣ ለሚቆጥሯት ወገኖች ለመንግሥት አካላትም ሆነ ለሌሎች የሃይማኖት ተቋሟት መናገር፤ ማስረዳትና ማሳመን የሚችል አቋም በቤተ ክህነቱ ፕሮግራም ውስጥ ባለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነፍጠኞችና የትምክህተኞች መናኸሪያ ተደርጋ በሌሎች ዘንድ በተሳለው ስዕል የተነሳ አጋጣሚውን ጠብቀው ብድር የመመለስ ጨለምተኛ አካሄድ ሲታይ ያንን በመጠቆም ብቻ ችግሩን መግፈፍ አይቻልም። ስለዚህም ጳጳሳቱ መናገር የሚገባቸውን  ሰዓት ቀድሞ አሳልፈውት ዛሬ ለችግሩ ማልቀስ የቤተ ክርስቲያን ዘብ አያሰኝም።
  3/ ዋናው ችግር ከውስጥ መንፈሳዊ ማንነትን መታጠቅ ያስፈልጋል። ታሪክና ዘመን የሰጣቸውን ሥልጣንና እድሜ ሊሰሩበት እንደሚገባ የሚረዳ ውስጠት ሊኖራቸው የግድ ይላል። ውጪያዊ ተጽእኖን ለመጋፈጥና ለማሸነፍ መንፈሳዊ ትጥቅ የሌለው ሹም በጦር አውድማው ላይ የመጠቃትና የተሸናፊነት ድምጽ ማስተጋባቱ አይቀርም። ተመሪዎቹንም ለጥቃት ያጋልጣል። አሁንም ያየነው ያንን ጩኸት ነው።  ጳጳሳቱ ይህንን የመንፈሳዊ ማንነትን ትጥቅ በተዋቡባቸው አልባሳት ለመካካስ ይፈልጋሉ። ክብሩ ግን በመንፈሳዊ ስብእና እንጂ በመልክና በቁመና ስለማይገኝ ድፍረት፤ መንፈሳዊ ቅንዓትና ጥብዓት የራቃቸውም ለዚህ ነው።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ዘረኝነትን፤ አድመኝነትን፤ ሙስናን፤ አድልዎን፤ ብቀላን፤ ዘረፋን፤ ግለኝነትን፤ ስብእናን የሚያጎድፍ አስነዋሪ ተግባራትን በማድረግም ይሁን የሚያደርጉትን ባለመገሰጽ፤ ይልቁንም ስር እንዲሰድና እንዲስፋፋ ምክንያት በመሆን ግምባር ቀደሞቹ ራሳቸው ጳጳሳቱ ናቸው። ጳጳሳቱ ራሳቸውን ያውቃሉ፤ ካህናቱም በትክክል ያውቋቸዋል።  ሌላው ቀርቶ ምእመናንም ጭምር። ምንም እንኳን እንዲህ ማለቱ ቢያሳፍርም እውነቱን አለመናገር በራሱ ወደፊት ሊቀጥል በሚችለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መገፋት ላይ መፍትሄ እንዳይኖር ማድረግ ነውና ከመናገር ውጪ ሌላ መንገድ የለንም። ሰው ድካሙን አውቆ፤ በንስሀ ተመልሶ፤ ብርታት በሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለመሥራት እስካልተጋ ድረስ በልብስ ውስጣዊ ማንነትን ቢሸፍኑት ተግባር ማንነትን፤ የኃጢአት ዋጋ እዳን ሲያስከትል በግልጽ መታየቱ አይቀርም። የጥቃቱ መብዛት የኃጢአትን ደመወዝ እየተቀበሉ የመገኘት ምልክት ነው እንጂ እግዚአብሔር በፈተና ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ስለተዋት አይደለም።
   ከዚህ በፊት ስለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባወጣነው ጽሁፍ ስንጠቁም  «የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ቅጠል የሌለው ዛፍ አንድ ናቸው» ለማለት እንደሞከርነው ጉዳዩን በሂደት ስንመለከት ዛፍነቱ ከቅጠል አልባነት በከፋ መልኩ እየበሰበሰ በመሄድ ላይ እንዳለ በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ጭብጥ ማቅረብ የሚቻልበት ሲሆን  በአጠቃላይ ጳጳሳቱ ከውጪያዊ ተግዳሮቶች በከፋ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን እየገፉ ወደ ገደል በመንዳት ላይ እንደሚገኙ የሚያስረዳን እውነታ ነው። አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸመው የቤተ ክርስቲያን የዐመጻ ተግባር ጊምቢ ላይ ዋጋ አያስከፍላትም ያለው ማነው?

ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ችግር የበሰበሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመነኮሳት አባቶች አመራር ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ማለት ይቻላል። በዚህ መልኩ ከቀጠለ በወለጋ ወይም በጋሞጎፋ መሬት ተወሰደ አለያም ገበሬ ተገረፈ ከሚለው ጩኸት ይልቅ ከውስጥ በሚመጣው የዐመጽ ተግባር  የተነሳ የሚከሰተው ጥፋት የከፋ ይሆናል።
  ከሰሞነኛው የሰበካ ጉባዔው ስብሰባ ላይ የማቅ ቀኝ ክንድ አቡነ ቄርሎስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድምጽ እንደሆኑ የተደሰኮረ ቢሆንም አቡነ ቄርሎስን የምናውቃቸው በዘመነ ሥራ አስኪያጅነታቸው ቤተ ክህነቱን ላስታ ላሊበላ ማድረጋቸውን እንጂ ዘረኝነትን ስለመዋጋታቸው አይደለም። ሌሎቹን በስምና በቦታ መጥራት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጊዜና ቦታ የማይበቃን ስለሆነና ተግባራቱን በውል የሚያውቁ ስለሚያውቁት ሾላ በድፍን ማለቱን መርጠነዋል። ሌሎቹ ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው!!

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአቡነ እስጢፋኖስን የሙስና ስፋትና ጥልቀት፤ የሰው ሽያጭና ከስራ ማፈናቀል ተግባር በማስረጃ አስደግፈን በሌላ ዓምድ እንመለስበታለን።
  ስናጠቃልል ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሽመድመድ ዋና ተጠያቂዎች ናቸው። የተቀበሉትን አደራ እስከሞት ድረስ የመወጣት አለያም ካልቻሉ ደግሞ ወደበረሃቸው የመግባት ግዴታ እንዳለባቸው ስለማያውቁ አሁን ደርሶ በመቻቻል ፖለቲካዊ መድረክ ላይ ወኔ የታጠቁ መስሎ መታየት አንድም እንደዚህ አልኩኝ ለማለት አለያም የማኅበረ ቅዱሳንን መነካት በተዘዋዋሪ መንገድ በችግሮች ሽፋን ለማካካስ ከመፈለግ የመነጨ ከመሆን አይዘልም። ጥያቄአችንም የሚነሳው ከዚህ ነው። ይህ «መቻቻል» የሚለው መድረክ ሳይመጣ በፊት የት ነበራችሁ? ነው ጥያቄያችን። በእነ አቡነ ገብርኤል ዓይነቶቹ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን መቼም ከችግር አትጸዳም።

እውነታውን ስንናገር ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያን ዘብ አልቆሙም ነው የምንለው!!!

Tuesday, October 15, 2013

«እስኪ በቁጣ ሳይኾን በጥሞና ነገሩን አስተውሉት!»

(ይህ ጽሁፍ በአባ ሰላማ መካነ ድር ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ያቀረበው ሲሆን ስለማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ ሁኔታ በአጭሩ ስለገለጸ ማቅረቡን ወደነዋል።)

የማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ ትልቁ ችግር ይኽ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፣ የነገረ መለኮት ዕውቀት የላቸውም፡፡ ኹለተኛ፣ ራሳቸውን የቤተክርስቲያን ወታደሮች አድርገው ይስላሉ፡፡ እነርሱ የቤተ ክርስቲያቱ ወታደሮች ናቸው የሚለውን ሐሳብ የተቀበለ ኹሉ ከእነርሱ ጋር የማይተባበር ኹሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው የሚለውን አቀንቅኖት መቀበሉ አይቀርለትም፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ነው! የቤተ ክርስቲያኒቱ የመከላከያ ሠራዊት ነው!” የሚለው ዐረፍተ ነገር በራሱ የጽንፈኝነት ወጥመድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ጠበቃ የምንፈልገው የተጠቂነት ፍርኀት ሲኖርብን ነውና፡፡ ምናልባት ይኽ ነገሮችን ጥቁር ወይም ነጭ ብቻ ናቸው ከሚለው ጽንፈኝነት ከሰፈነበት ባህላችን የተወለደ ይመስለኛል፡፡ አለማወቅ ላይ ፍርኀት ሲጨመርበት ጽንፈኝነት መወለዱ አይቀርም፡፡ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን “ምስክሮቼ ናችኹ፡፡” እንጂ “ጠበቆቼ ናችኹ፡፡” አላለም፡፡)
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አላስተዋለው እንደኾነ እንጃ እንጂ የተናገረው ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን ጽንፈኝነት በደንብ ያሳያል፡፡ ማኅበሩንም በመንግሥት በደንብ ሊያስመታው ይችላል፡፡ እኛ የምንለውን የማይሉ፣ በእኛ ቅኝት ያላቀነቀኑ ኹሉ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህልውና ለማጥፋት የሚታገሉ ናቸው ከማለት በላይ ጽንፈኝነት አለን? ዳንኤል ይኽን በማለቱ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነት ዐደባባይ አውጥቶታል፡፡ ጽንፈኛ ደግሞ ከራሱ ውጪ ማንንም ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡

Friday, October 11, 2013

«የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች የሰሞኑ የአዞ እንባ የማኅበረ ቅዱሳንን ማንነት አይለውጠውም»


አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳንን ስናነሳ ለምን ተነክቶ በሚል ቁጣ ወባ እንደያዘው ሰው ይንዘፈዘፋሉ። በእርግጥ በማኅበሩ የድንዛዜ መንፈስ የተወጉ ሰዎች እንደዚያ በመሆናቸው ከያዛቸው የወባ ዛር የሚያድን ምሕረት እንዲመጣላቸው እንመኝላቸዋለን እንጂ አንፈርድባቸውም። ሌላው ቀርቶ ማኅበሩ ራሱ ከእውነት ጋር ታርቆና ራሱን በንስሐ ለውጦ ከስለላና ከከሳሽነት ማፊያዊ ሥራ ተላቆ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለራሱ አቋም ከመጠምዘዝ ቢታቀብ ሁላችንም አብረነው በቆምን ነበር።  ከወንጌል እውነት ጋር እየተላተመ በተረት ዋሻ ሥር አናቱን ቀብሮ ከኔ ወዲያ ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የለም ከሚለው ትምክህት ቢወጣ እንዴት ባማረበት ነበር። ዳሩ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ገና ከመሠረቱ የቆመበት የህልውናው መንፈስ በደምና በማስመሰል በመሆኑ ከዚያ አቋሙ ፈቀቅ ይላል ተብሎ አይታሰብም። ጉዳዩ የታጠቀው የእልህና የበቀል መንፈስ እስኪያጠፋው ድረስ አይለቀውምና ሄዶ ሄዶ መጨረሻው እስከዚያው ድረስ መሆኑን ደጋግመን ስንለው ቆይተናል። ያ ሰዓት የደረሰበት መሆኑን ያሸተተው ይህ ማኅበር በቀንደኛ ሰዎቹ በኩል የአዞ እንባውን ማፍሰስ ጀምሯል።

 ከማኅበሩ ቀንደኛና ተላላኪ ሰዎቹ መካከል ታደሰ ወርቁ፤ ዳንኤል ክብረት፤አባ ኃይለማርያም( የጵጵስና ተስፈኛው)፤ ሐራ ዘተዋሕዶና አንድ አድርገን ብሎጎች የመሳሰሉት ሁሉ እየተቀባበሉ የቃጠሎው እሳት የደረሰባቸው ያህል የአድኑን ጩኸታቸውን ሲያሰሙ እያየን ነው። የሁሉም ጩኸት በአጭር ቃል ሲገለጽ በክርስትና አክራሪነት ቦታ የለውም ወይም ለማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የመሳሰለ ስም ሊጣበቅበት ተገቢ አይደለም የሚል ድምጸትን የያዘ ሆኖ አግኝተናል። ይሁን እንጂ ሰዎቹ በገደል ማሚቱ ድምጻቸው እየተቀባበሉ እውነታውን ለማዳፈን ቢፈልጉም እውነቱ በማስረጃ ሊገለጥ ይገባዋልና በዚህ ዙሪያ ጥቂት የምንለው አለን። ይከተሉን።

1/ ክርስትና፤

ክርስትና ክርስቶስ የሞተለት እምነት ስለሆነ ከሚሞቱለት በስተቀር ሌሎችን ሊገድሉለት፤ ሊደበድቡበትና ሊያሳድዱበት የተገባው ስላይደለ በእርግጥም ክርስትና ወግ አጥባቂነት፤ አክራሪነትና፤ ጽንፈኝነትና አይመለከተውም።