Saturday, October 5, 2013

የተሻለ የሥራ ጊዜ እንዲሆንልን ጸልዩልን!

 
በሃሳባችሁ፤ በምክራችሁ፤ በእውቀታችሁ፤ በገንቢ አስተያየታችሁ አብራችሁን ለዘለቃችሁ ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ!
በዘለፋ፤ በፉከራ፤በስድብና በኢ-ክርስቲያናዊ ጽሁፎቻችሁ ለቆያችሁም አስተዋይ ልቡና ይስጣችሁ! ከጥላቻ የራቀ ማንነት እንዲሰጣችሁ እንመኛለን።
አግዚአብሔር ኢትዮጵያችንን ይባርክ
                                    ደጀብርሃን

Tuesday, October 1, 2013

“መስቀል የሚያቃጥል አይደለም”

ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ሲኖዶሱ ውሣኔ ይሰጣል - አቡነ እስጢፋኖስ

(ከደጀ ብርሃን ) ከሰማይ ወረደ ስለተባለው ሰሞነኛ ወሬ ብዙ ብዙ ተብሏል። እንደዚህ ዓይነት ደብተራዊ ቁመራ የተለመደ ሆኖ መታየቱ ለክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ፈላጊነት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ቀጥሏል። ከሰማይ ለወረደውና ወደሰማይ ለወጣው ለአብ አንድያ ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ በእምነት ልብን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ከሰማይ ወረደ ለተባለው ቁራጭ ብረት መንጋጋት አሳፋሪም አሳዛኝም ነው።  በእርግጥ ይህ ትውልድ በክርስቶስ አምኖ ልቡን ከማሳረፍ ይልቅ ምልክት እንደሚሻ ዕለት ዕለት እናያለን። ለኃጢአት ሥርየት የተሰነጠቀ ድንጋይ ሲሾልክ፤ የማያየውን የተቀበረ መስቀል ፍለጋ ከወሎ ተራራ ሲንከራተት፤ ይቅርታን ለማግኘት ፍርፋሪና ዳቦ ለመብላት ሲሻማ ማየቱ በክርስቶስ ደም ሥርየትን፤ ንስሐ በመግባት ብቻ ይቅርታን በማግኘት ማረፍ እንዳልቻለ ያሳያል። እረፍት ፍለጋ ምልክት መከተል መፍትሄ አይደለም። በእውነታው  ሰዎቹ እንደሚሉት እግዚአብሔር የተመሳቀለ እንጨትም፤ ብረትም ከሰማይ እርሻ ማሳ ውስጥ በመወርወር ከሰው ልጆች ጋር ይጫወታል ማለት ባህርይውን አለማወቅ ነው። ድንጋይ በመሹለክም፤ ፍርፋሪ በመብላትም፣ ተራራ በመውጣትም፤ ደረትን በመድቃትም ሆነ ጸጉርን በመንጨትም ኃጢአት አይደመሰስም። ሥርየትም አይገኝም። «በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት» እንደሆነ ወንጌል ቢናገርም (ኤፌ 1፤7) ይህንን ወደጎን ገፍቶ በሰንጥቅ ድንጋይ ለመሹለክ መሽቀዳደም ምልክት ፈላጊዎችን ከማብዛቱም በላይ ወንጌል ከስሙና ከንባቡ በስተቀር ለመታወቅ ብዙ እንደሚቀረው ነው።  ከዚህ ዓይነቱ እርባና የለሽ ሰሞነኛ ወሬዎች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ እርሻ ማሳ ውስጥ ወድቆ ተገኘ ስለተባለው መስቀል ብዙ መወራቱ እንዳለ ሆኖ አንስተው፤ ወደመቅደስ አስገብተውታል የሚባሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ስለእውነታው በሲኖዶስ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚል ዜና ስናነብ እጅጉን ገረመን። ምክንያቱም የነደብተራ ገለፈት ፈጠራ እንደቁም ነገር ሊቆጠር አይገባውም። እንዲያውም እንደዚህ ዓይነቶቹን ጸረ ወንጌል አጭበርባሪዎች ማስወገድ ይገባ ነበር።  ለማንኛውም የአቡኑን የአዲስ አድማስ ዘገባ እንዲያነቡት እነሆ ብለናል።
 
በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ እስኪያስተላልፍ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ የአዲስ አበባና የጅማ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አሣሠቡ፡፡ “መስቀል ከሠማይ ወርዷል አልወረደም? ትክክለኛ ነው አይደለም?” የሚለውን ለመመለስ የግድ ቅዱስ ሲኖዶሡ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔ ሊያስተላልፍበት ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ይህን ለማድረግም ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቋሚ አባላት እንዳሣወቁ ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ እንደተባለው ከሠማይ የወረደ አለመሆኑ ከተረጋገጠም የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች ይጠየቁበታል ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡
መስቀሉ ከሠማይ ወረደ በተባለ በ4ኛው ቀን ነሐሴ 27 ቀን 2005 ከሠአት በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት ተገቢውን የፀሎት ስርአት ከካህናቱና ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር ካደረሡ በኋላ መስቀሉን ከወደቀበት መሬት አንስተው ወደ ቤተመቅደሡ እንዲገባ ማድረጋቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ መስቀሉ ከሠማይ ስለመውረዱ በአይናችን አይተናል ካሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደማንኛውም ሠው መስማታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት መሬት ያነሱት ብፁዕነታቸው፤ “መስቀሉ ያቃጥላል፤ ብርሃናማ ነፀብራቅ አለው” የሚባለውን አለማስተዋላቸውን ጠቁመው፤ “መስቀል የሚያቃጥል ሣይሆን የድህነት ሃይል ነው ያለው፣ የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ ከመሬት ላይ ማንሣት ባልተቻለ ነበር” ብለዋል፡፡ ወረደ የተባለውን መስቀል ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን ለምን እንዳይመለከቱት ተከለከለ የሚል ጥያቄ ያነሣንላቸው ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶሡ ተጣርቶ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያጤነው በማሠብ ነው” ብለዋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)

 

Saturday, September 21, 2013

የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!


ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።

(ክፍል አራት)

በክፍል ሦስት ጽሁፋችን በአውሮፓ ሀገራት የእምነት መላሸቅ ስላስከተለውና በለውጡ ገፊ ምክንያትነት በቁጥር አንድ ስለተመዘገበው ነጥብ  ጥቂት ለማለት ሞክረናል። በሥራ ውጥረትና በጊዜ ማጣት የተነሳ የሰው አእምሮ በመባከኑ ሳቢያ በማኅበራዊ ኑሮው ያለውን ግንኙነት አላልቷል። ቤተሰባዊ ፍቅሩን የሚያሳልፍበትን ሰዓት አጣቧል። ከፍላጎት ማደግና ከወጪ ዓይነት ንረት ጋር ለመታገል በሚያደርገው ሩጫ የተነሳ ማንነቱን ለዚህ ዓለም ኑሮ አሳልፎ በመስጠቱ ለሰማያዊ እሱነቱ የሚገባውን እሳቤ ሸርሽሮታል። በዚህም የተዳከመ የእምነት ሰው አለያም እምነት ማለት ሰርቶ ኑሮን ማሸነፍ ብቻ ነው ወደሚል እሳቤ ወስዶታል። ከመላው አውሮፓ የክርስቲያን ቁጥር ውስጥ 45% ክርስትናውን ትቶታል ወይም ክዶታል። በፈረንሳይ ብቻ 40% እምነት የለሽ ወደመሆን የወረደው በክፍል ሦስት ያየነው ለለውጡ ገፊ ምክንያት በሆነው አንዱ ነጥብ የተነሳ ነው። ያንንም ምክንያት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን የት ነበርን? የት ደረስን? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን? አሉታዊ ጎኑን ለማስወገድ የወስድናቸው ርምጃዎች ካሉም ያንን በማንሳት ጥቂት ለመዳሰስ ሞክረን ነበር። በዚህ ጽሁፋችን ደግሞ ሁለተኛውን ምክንያት በማንሳት ጥቂት እንላለን።

2/ ኢንዱስትሪው በየጊዜው በሚፈጥረው ትንግርታዊ እድገትና ጥበብ የሰው ልብ መማረኩ፤ ያልነበሩና የማይታወቁ ልምዶችን፤ ባህሎችንና ሥነ ምግባርን የሚያላሽቁ ክስተቶች መምጣታቸው፤

ኢንዱስትሪው ረጅም የሥራ ጊዜና ኃይል እንደመውሰዱ አእምሮን ሁሉ ለእውቀትና  ለእድገት ሽግግር ጋብዞታል። በዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂው መጥቆ ትንግርት እስኪሆን ድረስ ፈጠራና ክሂሎት ተመንድጓል። የመረጃ መረብ መዘርጋት፤ በመረጃ መረብ ላይ የሚተላለፉ የድምጽ፤ የምስል፤ የጽሁፍና የፈጠራ ውጤቶች ሉላዊውን ዓለም እንደማቀራረቡ መጠን የሰውን ሁሉ ልብ ሰርቆታል። ይህ ሰፊና ቁጥጥር የለሽ መረጃ መረብ የሚያስተናግደው ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን ጸያፍና ጋጠ ወጥ የሆነው ሁሉ የሚለቀቅበት በመሆኑ የሰው ልብ በሚታይ ነገር እንዲማረክ፤ የማያውቀውን ልምምድ እንዲለማመድ፤ የነበረውን ባህል እንዲያራግፍ፤ ሥነ ምግባሩ እንዲላሽቅና የሥራ ውጥረቱን በሚያባብስ የክዋኔ ሂደት ውስጥ በማስገባቱ የተነሳ መንፈሳዊውን ዓለም በገሃዳዊው ዓለም የደስታም ይሆን የኅሊና ስካር እንዲለውጥ አስገድዶታል። ለልቅ ወሲብ/Pornography/፤ ለግብረ ሰዶም፤ ለአደንቋሪ ዘፈንና ጫጫታ፤ በስፖርት ሽፋን መንፈሳዊ ልብን ለሚሰርቅ የዓይን ጫወታ ስሱዕ መሆን፤ ለዕጽ ተጠቃሚነት፤ ለአስገድዶ መድፈር፤ ለሰው ጉልበት ሽያጭ ወዘተ ድርጊቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ተገዢ እንዲሆን አድርጎታል።