«እስከ ጥቁር ዉሃ ሄዶ የተቀበለ ሕዝብ እስከ ጥቁር ውሃ ተሰደደ» (ደጀ ብርሃን)
በሀዋሳ በግፍ የተሰደዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ብፁዕ አቡነ ገብርኤል "ኑ ልጆቼ ወደ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተመለሱ" ሲሉ ላደረጉት ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ምዕመናኑ ለአቡነ ገብርኤል በአድራሻ፣ ለ17 የቤተክርስቲያንና መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ በግልባጭ ያሠራጩትን ደብዳቤ በብሎጋችን ፖስት እንድናደርግላቸው ለዝግጅት ክፍላችን በኢሜይል ልከውልናል፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ይዘት የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም
ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል
የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ
ሀዋሳ፣
ጉዳዩ: ̶ "ወደ ቤተክርስቲያን እንድትመለሱ" በማለት ለተጻፈልን ደብዳቤ ምላሽ ስለመስጠት
በቀን 25/1/171/2005 (ቀኑን ከደብዳቤው ላይ ማየት እንደሚቻለው) በቁጥር 1459/171/2005 የተጻፈ ደብዳቤ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት በሁለት ፖሊሶች እጅ ተልኮልን ወንጌል ከምንማርበት ሥፍራ ተጠርተን መተማመኛ ፈርመን በመቀበል በአንክሮ ተመልክተነዋል፡፡ ቀጥሎም ለምዕመናን ተነቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የጋራ አቋም የተወሰደበት ሲሆን፣ ጥሪ ማድረግዎን በስምንቱም አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ዐውደ ምሕረቶች እንዲነበብ እንዳደረጉት ሁሉ ይህንን የምላሽ ደብዳቤያችንንም ለሰፊው ምዕመን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲያስነብቡልን አደራ እንላለን፡፡ የሰጠነውም ምላሽ የሚከተለው ነው፡፡
አንደኛ፣ ደብዳቤውን እንደ ወንጀል ክስ መጥሪያ በፖሊስ እጅ መላኩ እና ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ ከምሽቱ 1፡30 ከሆነ በኋላ መምጣቱ፣ እንዲሁም መተማመኛ ፈርመን እንድንቀበል መደረጉ ከሕግ አንፃር ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የጥሪው አካሄድ የፍቅር እንዳልሆነ ተገንዝበናል፡፡ በተጨማሪም ደብዳቤው ቅንነትና እውነት ያለበት ሳይሆን ማስመሰልና ውሸት የተሞላበት ከመሆኑም በላይ እርቅ፣ ሠላምና አንድነትን ከማምጣት ይልቅ ራስን ከሕዝብ (ከታሪክ) ፍርድ ለመከላከልና ለገጽታ ግንባታ (ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ) ሲባል ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን ተረድተናል፡፡
በደብዳቤው ውስጥ "የተወደዳችሁ ልጆቻችን ምዕመናንና ወጣቶች" የሚል ሐረግ ተደጋግሞ ይታያል፡፡ ልጆቻችሁ እንደሆንን ሲነግሩን ከእርስዎ ሳይሆን ከሌላ አካል የሰማነው ያህል መስሎ ነው የተሰማን፡፡ ምክንያቱም እኛ ልጆችዎ እንደሆንን ባንክድም ከእርስዎ ዘንድ ግን የአባትነት ወግ ፈጽሞ አይተን ስለማናውቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የደብዳቤውን ይዘት ስንመረምረው የተረዳነው ነገር ቢኖር ̶ አንዳንዴ በግልጽ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በስውር በሀገረ ስብከታችን የሚካሄዱትን ሕገወጥ ሥራዎች ለመሸፋፈንና "ለምን አሳደዳችኋቸው? ለምን አትመልሷቸውም"? ብሎ ለሚጠይቃችሁ አካል "ይኸው፣ በደብዳቤ ጠርተናቸውም እምቢ ብለውናል" በማለት በብልጣብልጥ አካሄድ ሪከርድ ለማስያዝ እና ወደፊት ለምታደርጉት የተለመደ እንቅስቃሴ ምክንያት ለማመቻቸት መሆኑን ለማወቅ ልዩ ጥበብ አያስፈልገውም፡፡
ጥሪዎ ቅንነት ቢኖረው ኖሮና እኛን "ልጆቻችን" እንዳሉን ሁሉ እርስዎም አባትነትዎን አምነውበት ቢሆን በአባትና በልጅ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ልጅ ቤቱን ለቆ ቢኮበልልና አባትም በበኩሉ የኮበለለው ልጅ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ቢፈልግ ደብዳቤ ጽፎ በፖሊስ በኩል መላክ ትክክለኛው መንገድ አለመሆኑን ለእርስዎ መንገር ለእናት ምጥ እንደማስተማር ይቆጠራል፡፡
በተጨማሪም፣ ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተባርረን ከወጣን ሁለት ዓመታት እስኪቆጠሩ ድረስ ከሀገረ ስብከቱ ውጪ ያሉ ካህናትና አገልጋዮች መጥተው ሲባርኩንና ሲያፅናኑን እርስዎና ከእርስዎ ሥር ያሉ አባቶች ግን የጠፉትን በጎች ፍለጋ ሳትወጡ ኖራችሁ፣ ዛሬ ከረፈደና ከመሸ፣ ጉዳዩም ከእጃችሁ ወጥቶ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤትና በቅዱስ ሲኖዶስ ከተያዘ በኋላ ድንገት ይህንን ኦፊሴላዊ ጥሪ ለማድረግ የተገደዳችሁበትን ሚስጥር ስናሸተው ጠረኑ የሚነግረን ሌላ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ደብዳቤው ሆን ተብሎ እውነታውን ለማዛባት የተደረጉ ጥረቶች እንዳሉበት ከማሳየቱም በላይ "እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላ ግፋው" እንደሚባለው ለይተበሀል ያህል ብቻ የተጻፈ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ሁለተኛ፣ በደብዳቤው የመጀመሪያ መሥመር ላይ፣ "ከቤተክርስቲያን ተባረናል በሚል . . . እየተሰባሰባችሁ የምትገኙ ልጆቻችን ምዕመናንና ወጣቶች . . . " የሚል ሐረግ ሰፍሯል፡፡ ይህ የሚያሳየን እኛ ተባረናል እንላለን እንጂ እናንተ ማባረራችሁን አምናችሁ ለመቀበል እንደማትፈልጉና ዛሬም እንኳን ፀፀት እንዳልተሰማችሁ ያመለክታል፡፡ ታዲያ ከእናት ቤተክርስቲያናችን ውጪ ለመገኘታችን ምክንያቱ እርስዎ፣ የእርስዎ አስተዳደር እና እርስዎ ያደራጁት ማኅበር ካልሆነ፣ ቤተክርስቲያንና ቅጥሯ አስጠልቶን አካባቢ ለመለወጥና ለሽርሽር የሄድን መስሎዎት ይሆንን? ይሁን እንጂ እንዳባረራችሁን መላው የሀዋሳ ምዕመናን ምሥክር ናቸው፡፡