በእንግሊዝኛ የአማርኛው ስም «ቸርች» ተብለው ከሚጠሩት ባንዱ የተፈጸመ ድርጊትና እሮሮ ነው። ምሬት የበዛበት ይህ ሰው «ሐዋርያዬ» በሚለው የዘመኑ ሰው የደረሰበትን ሰቆቃ ሲያሰማ አገኘነውና ራሳቸውን የክርስቶስ ባለሟል አድርገው እውቀት የጎደለውን ሰብስበው እንዴት እንደሚያጃጅሉ ከማሳየቱም በላይ በግራም በቀኝም በክርስቶስ ስም የሚፈጸመውን ዐመጻ ልናካፍላችሁ ወደድን። በወዲህ ሰባኬ ወንጌልና ማኅበር፤ በወዲያ ደግሞ ሐዋርያና ፓስተር ገንዘብ አምላካቸውን ይነግዳሉ። ከረጅሙ ትርክት ውስጥ ቆንጥረን አቀረብን።
የጽሁፉ ባለቤት ኢዮብ ደምሴ ነው።
ይሄን ጽሑፍ ለምታነቡ ወገኖች ልጠይቅ የምፈልገው ነገር፣
1ኛ. “መልሱኝ” ብዬ ያልጠየቅሁና በብዙ ውትወታና ንግግር ቤተ ክርስቲያን ጥሪ ያደረገችልኝ ሆኖ ሳለ፣
2ኛ. በቤተ ክርስቲያኒቱን ባገለገልኩበት ጊዜ ሁሉ በትጋት በማገልገሌ ውጤታማና ፍሬያማ መሆኔ በራሱ በሐዋርያው እጅ በምስጋና የተጻፈ ያማረ የመሸኛ ደብዳቤ ተሰጥቶኝ እያለ፣
3ኛ. የእረኞች አለቃ የሆነው ጌታ “ጠብቁልኝ” ያለውን መንጋ “ምስጢሩን አያውቅም” በሚል እሳቤ ብቻ፣ በሐሰት ንግግር በማሳሳት ለተሳሳተ ዓላማ እንዲሰለፉ እንዳደረገው ሳይሆን፣ መንጋው እንዳያዝንና እንዳይበተን፣ በመጠንቀቅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ካቆምኩበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን በአደባባይ እስከገለጠበት ጊዜ ድረስ የማውቀውን የሐዋርያውን ችግር በአመራር ክፍሉ ብቻ እንዲያልቅ በምስጢር ይዤ የቆየሁ መሆኔ እየታወቀ፣
4ኛ. እግዚአብሔር ሰፊ የአገልግሎት በር ከፍቶልኝ ከጌታ ምሕረት የተነሳ ተቀባይነትም ባገኘሁበት ጊዜ የተበላሸውንና የፈረሰውን ነገር መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ራሴን መስጠቴ ስሕተቱ ምንድን ነው?