Tuesday, April 23, 2013

እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ( ክፍል ስድስት )

 ክፍል ስድስት (የጽሁፉ ባለቤቶች ለእስልምና መልስ አዘጋጅዎች ነው)
(www.answering-islam.org)

ሙሶሊኒና የሳውዲው የግመሎች ግዢ
 
በግንቦቱ ስምምነት መሰረት የሳውዲና የጣሊያኖች ግንኙነት በጣም እየተቀጣጠለ ሄደ፤ በዚያው ወር የጣሊያን ወኪል የሆነውና በጣሊያን የወታደራዊ ስለላ ውስጥ የሌተናንት ኮሎኔልነት ማዕረግ ያለውሴልሶ ዖዴሎባለቤቱና ሴት ልጃቸው ጅዳ ደረሱ፡፡ እርሱም እራሱን የተለያዩ የጣሊያን የንግድ ድርጅቶች ወኪል እንደሆነ አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱም ወዲያውኑ የጅዳ ሕይወት ማዕከል ሆነና ከምሁራን እንዲሁም ከያሲን ጋር ጥብቅ ወዳጅነትን መሰረተ፡፡ በሐምሌም ወር ዖዴሎና ያሲን በኤርትራ ውስጥ እየተከማቸ ላለው የጣሊያን ሰራዊት አስፈላጊ ስለሆኑት 12,000 ግመሎች ለጣሊያን የመግዛት ጉዳይ ላይ ውይይት አደረጉ፡፡ሴልሶ ዖዴሎምከመደበኛ ዋጋቸው ሦስት እጥፍ እንደሚከፍል ሐሳብን አቀረበ፡፡ ዓለም አቀፉ ውጥረት እየተፋፋመ ነበርና ሳውዲ አረቢያ ከመቼውም በላይ ከሙሶሊኒ ጋር ባደረገችው ድርድር ብሪቴንን የሚያስቆጣና በመካከላቸው ማለትም በብሪቴንና በጣሊያን ጦርነት ያስከትላል በማለት በጣም ተጨንቃለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከሳውዲ የጦር ወታደር እንዳይመለመል አግዳለች፣ ይሁን እንጂ ሌሎች ነገሮች የምግብ ግዢዎችና ግመሎች ግዢዎች ላይ ምንም ችግር አልነበረም፡፡
በዖዴሎም አማካኝነት ለጣሊያኖች አትክልቶች ይሸጡላቸው ነበር፣ ምፅዋ ላይ በሚደርሱበት ጊዜ ከጥቅም ውጭ ይሆኑ የነበረ ቢሆንም፡፡ አሁን የጣሊያን ጦር መሳሪያዎች የሚፈልጉት ግመሎችን ነበር፤ ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት እንደቀጠለ ከባድ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ማጓጓዝ በጣም ችግር እንደነበረ በጣም ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተራራዎች አካባቢዎች መሳሪያዎችን ለማጓጓዝና አስፈላጊ ነገሮችን ለማግኘት የጣሊያን ሰራዊት በግመሎች ላይ መደገፍ ነበረበት፡፡ በእርግጥ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም እንኳን የተረጋገጠው ነገር የግመሎች አስፈላጊነት ነበር፡፡

Monday, April 22, 2013

«ኩሉ ዐረየ ወኅቡረ ዐለወ፤ አልቦ ዘይገብራ ለሠናይት፤ አልቦ ወኢአሐዱ»

ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም።
የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።
ሁሉ በደሉ፥ አብረውም ረከሱ አንድ ስንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም።
ሕዝቤን እንጀራ እንደሚበላ የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም። መዝ ፶፫፤፩-፬

ማንም በማንም ኃጢአት አይጠየቅም። ማንም ራሱን ጻድቅ አድርጎ በሌላ ሰው ድካም መፍረድ አይገባውም። ይህ የእግዚአብሔር ቃል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የተሰጠ መመሪያ ነው። በትክክልም እንገነዘባለን። ይህን ማለት ግን መንጋውን ለመምራት ሥልጣንና አደራ ተረክበው፤ በሌላ መልኩም ከእግዚአብሔር ጋር ቃለ መሐላ በመፈጸም በጎችህን እንጠብቃለን ብለው አዋጅ ተናግረው ሲያበቁ በማጭበርበርና ወደ ሥርየት ከማቅረብ ይልቅ በጎቹን ኃጢአት በማስተማር የተካኑ፤ ቤቱን በማፍረስ የተሠማሩ የዐመጻና የየበደል ማኅደሮችን በተቀመጡበት ቦታ ተሸክመናቸው እንዞራለን ማለት ባለመሆኑ አንድም አልታወቀብኝም ከሚሉት ዐመጻ ወጥተው በንስሐ እንዲመለሱ፤ አለያም ያንን የጣፈጣቸውን ዐመጻ ቤቴ ብለው እንዲኖሩበት ለማድረግ ሲባል እውነቱ ሊነገራቸው ይገባል ብለን እናምናለን። የክርስቶስ ቤተሰቦች በተናጠል ብዙ ኃጢአት ይኖረናል። የግላችንን ኃጢአት ግን ወስደን ለቤተክርስቲያን የኃላፊነት መድረክ ማዋል ግን የበደል በደል ነው። ከተራራ ላይ የተቀመጠችን መብራት መሸሸግ አይቻልምና ለተቀመጥንበት የከፍታ ስፍራ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጳጳስ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አባ ኤዎስጣቴዎስን የተመለከተ መረጃ ከዚህ ቀደም ማውጣታችን ይታወሳል። የዚያ የመልካም ነገር ሁሉ እንቅፋት የሆነው ማኅበር የ/ማቅ/ ፓትርያርክ ሆነው ከሲኖዶስ በማፈንገጥና እንደአሜባ ቤተክርስቲያንን እየሰነጣጠቁ ባርኬ ሰጥቼሃለሁ በማለት ችግር ሲፈጥሩ እንደነበር ዘግበንበታል። በዳላስ ቅ/ሚካኤልን በሰባኬ ወንጌሉ በኩል ሁለት ቦታ በመሰንጠቅ በሥላሴ ስም የማቅ አዳራሽ የተባረከው በኚሁ የማቅ ፓትርያርክ ነበር። ያም ሆኖ አባ ኤዎስጣቴዎስን የነካቸው ማንም አልነበረም። ይሁን እንጂ የመሰነጣጠቅ ልምዳቸው፤ እየተከተለ እነሆ ብፁዕ ነኝ የሚሉበትን የእረኝነት ቀሚሳቸውን የሚሰነጥቅ ነውር ተከትሎ ለጥፋት ዳረጋቸው።

መሸከም ያልቻሉትን ድስት አስቀምጠው የሚችሉትንና የፈለጉትን የማድረግ መብት እንዳላቸው እናምናለን። ኃጢአቱ ያልተሰጣቸውን ጸጋ ለማግኘት መፈለግ እንጂ «ጋብቻ ክቡር ነው መኝታውም ንጹህ ነው» ያለው የእግዚአብሔርን ቃል መፈጸም አይደለም። ክፋቱ ያንን የእግዚአብሔር ቃል አልፈልግም ብሎ ሊጠብቃቸው የተሰጡትን በጎች እያጋደሙ በዝሙት ሰይፍ ማረድ አይደለም። ለዚህም እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነውና ንስሐ ይግቡበት። ሚስት ማግባትም በደል አይደለምና የማይችሉትን ሰው ሰራሽ ድስት በመሸከም ከመንገዳገድ የሚችሉትን አግብተው የሥጋን ሸክም እያቀለሉ መኖር ይሻላልና ይህንኑ ይተግብሩ ምክራችን ይህ ነው።
ለነገሩ የኃጢአት ዋጋው ሳይታሰብ እንደዚህ ዓይነት ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ እንጂ  የብፁዕነት ስያሜን ያለአቅማቸው ተሸክመው የሚንገዳገዱ ስንኩላን  ሹማምንት ብዙዎች ናቸው። የመገለጡ ዕጣ ቀድሞ ለአባ ኤዎስጣቴዎስ ከመውጣቱ በስተቀር ይህ ድርጊት የእሳቸው ብቻ አይደለም። ሌሎቹንም በዚህ አጋጣሚ የምንመክራቸው እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አይጠላምና በስመ ብፁዕ የሸፈናችሁትን ኃጢአት ተሸክማችሁ፤ ለራሳችሁ ሞትን፤ ለቤተ ክርስቲያን ውርደትን፤ ለእግዚአብሔር መንጋውን መጠበቅ ያለመቻል ቅጥረኝነት ለመላቀቅ ንስሐ ግቡ፤ ጋብቻችሁን መስርቱ፤ ንግድና ገንዘብ የመሰብሰብ ክፋታችሁን አራግፉ እንላለን። ኃጢአታችሁ ከራሳችሁ አልፎ ሀገር ሁሉ አውቆታል። ሰምቶታል። ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ስለሚያጠቃው ገመናችሁን ሸፈነው እንጂ ፈረንጅ ቢሆን ኖሮ በጋዜጣ ላይ አውጥቶ ንስሐ የመግባት እድላችሁን በማፋጠን ይተባበራችሁ ነበር። ያ ጊዜ ከመድረስ በፊት ለራሳችሁም፤ ብፁዕ አለመሆናችሁን እያወቃችሁ ብፁዕ መባላችሁ እንደማይገባችሁ አምናችሁ እንደዚያ እንደቀራጭ ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ለንስሐ አዘጋጁ።
ለአባ ኤዎስጣቴዎስ የተጻፈው ሴት አዳኝና አደገኛ የወሲብ ቀበኛ የተባሉበትን ደብዳቤ አስፍተው/zoom/አድርገው እንዲያነቡ አቅርበነዋል።

እዚህ ላይ ይጫኑና አስፍተው ይመልከቱ

Friday, April 19, 2013

«እኛ ኢትዮጵያውያን ያለነው የት ነው? ተስፋችንስ ምንድነው?»

የሰው ልጅ ሁሉ የአዳምና የሔዋን ዘር ነው። ከዚህ የወጣ የለም።  ሰው ክቡርና በእግዚአብሔር አምሣል የተፈጠረ ስለሆነ እንስሳ አይደለም። ሰው በተፈጥሮው እንስሳ ነው የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም እንኳን ሰው ግን እንስሳ አይደለም። በእርግጥ በተፈጥሮው ሰው ቢሆንም በአስተሳሰቡ ከእንስሳ ያልተሻለ ሰው ይኖራል። እንደባለጤና አእምሮ ሰው፤ ሰውኛ ማንነቱን ገላጭ አስተሳሰብ ሊኖረው የግድ ነው። እንስሳ አስተሳሰብ ማለት በሰው አምሣል ተፈጥሮ እንስሶች የሚሰሩትን የሚሠራ ወይም እንደእንስሳ የሚያስብ ማለት ነው። ዳዊትም በመዝሙሩ ይህን ኃይለ ቃል ሲገልጸው እንዲህ አለ። «ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ»               (መዝ ፵፱፤፲፪)

አዎ ሰው ክቡርነቱን ትቶ በሃሳቡና በግብሩ፤ ነፍስያቸው ምናምንቴ እንደሆኑት እንስሶች መሰለ። ሁሉም ሰው የአንድ ዘር ምንጭ ቢሆንም ቅሉ ለሰይጣን ፈቃድ አድሮ በልዩነትና በክፍፍል መኖርን መርጧል። በክፍፍሉም እርስ በእርሱ ይባላል። ምክንያቱም አእምሮው ወደእንስሳነት አስተሳሰብ በወረደ ማንነት ተመርዟልና ነው። እንስሳት እርስ በእርሳቸው ይጠላላሉ። ነገን የሚጠብቁት አድነው ስለሚበሉት እንስሳ እንጂ በተስፋ ስለሚገነቡት ሕይወት አይደክሙም። ከዚያ ባለፈ እንስሳት ተስፋ የሚያደርጉት ዘላለማዊ ነገር ምንም የላቸውም። የማይሞት ተስፋ የተሰጠው የሰው ልጅ ግን በሚሞት ምድራዊ ተስፋ ላይ ራሱን አጣብቆ ይኖራል።ዳዊትም በመዝሙሩ ላይ ቃሉን በማስረገጥ  ድኩማነ አእምሮው ሰዎችን በእንስሳ ይመስላቸዋል። «አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ» (መዝ ፵፱፤፳)

ጠቢቡስ «ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም» ማለቱ ምን ማለቱ ነበር?  አዎ! ያን ማለቱ በአንጻራዊ ትርጉም አዲስ ነገር ያለው ከፀሐይ በላይ ነው ማለቱ ነበር። ከፀሐይ በላይ አዲስ ነገር እንዳለ እየተናገረን እንደሆነ እንረዳለን።  ስለዚህም ነው ተስፋችን በማይጠፋና ዘላለማዊ በሆነው ከፀሐይ በላይ ባለው ነገር ላይ እንዲሆን አበክሮ በመናገር ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም የሚለን። እንዲያውም ከፀሐይ በታች ባለው ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ነፋስን እንደመከተል ነው ይላል። «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው» (መክ ፩፤፲፬) ነፋስን ማን ሊከተል ይችላል? ነፋስስ መሄጃው ወደየት ነው? መኖሩን እናውቃለን እንጂ ወደየት እንደሚሄድ አንረዳም፤ መቆሚያውም የት እንደሆነ አናውቅም፤ ልንከተለውም ማሰብ ከንቱ ድካም ነው። ከፀሐይ በታች ያለውን ነገር ሁሉ መከተል እንደዚሁ ይለናል። የቀደመው  ነገር አልፏል፤ ያኔ ግን እንደአዲስ ይቆጠር ነበር። ዛሬ ደግሞ ነገ ቀድሞ ይሆናል። ቀድሞም ሆነ ዛሬ የምንላቸው ነገሮች ደግሞ ነገ የሉም። ሁለቱን የሚከተል ተስፋ የለውም።  ቀድሞና፤ ዛሬ የሚባልለት ሁኔታ በሌለው ከፀሐይ በላይ ባለው አዲስ ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ይሻላል። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ያስተምረናል። «እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው» (፩ኛ ዮሐ ፪፤፳፭)

የማይጠፋውን የዘላለም አዲስ ተስፋ በእምነቱ የሚጠባበቅ እንደምናምንቴ ሰው ተስፋ በሌለው በዚህ ዓለም ከንቱ ነገር ላይ ራሱን አያጣብቅም። ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በዚህ ምድር ላይ መኖራቸውን እንደመጨረሻ ምዕራፍ ቢቆጥሩት አያስገርምም። መዝሙረኛው እንደተናገረው በአሳባቸው የሚጠፉ እንስሳትን መስለዋልና።

በእምነት ተስፋ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከፀሐይ በላይ ያለውን አዲስ ነገር ይጠባበቃሉ። ስለሆነም በዚህ ምድር ላይ እስካሉ ሁላቸውም በእምነት አንድ ናቸው። ልዩነትን አይሰብኩም። ጳውሎስም እንዲህ አለ። «በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ» (ገላ ፫፤፳፮-፳፱)