በአሸናፊ ደምሴ
ሰንደቅ ጋዜጣ ረቡዕ 9/8/2005 ዓ/ም
የፌዴራሉ አቃቤ ህግ የማይገባትን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በመንቀሳቀስ ሰዎችን በማታለል “እኔ ማርያም ነኝ፤ እንደኢየሱስም በጅራፍ ተገርፌያለሁ፤ ከሞትም ተነስቻለሁ፤ የወለድኳቸውንም ልጆች ያገኘሁት በመንፈስ ነው” ስትልና የዓለም ፍፃሜ ደርሷል በሚል የሰዎችን የግል ሀብት ለራሷ ስታደርግ ደርሼባታለሁ ሲል ክስ የመሰርተባት የ34 ዓመቷ ትዕግስት ብርሃኑ ወ/ጊዮርጊስ፤ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል ችሎት ፊት ቀርባ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ በ2 ዓመት ከ4 ወራት ፅኑ እስራትና በአንድ ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ባሳለፍነው ሳምንት ወሰነ።
እንደአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ከሆነ ግለሰቧ በአራት የተለያዩ ክሶች የተወነጀለች ሲሆን፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ለሰው ህይወት ማለፍ ሳቢያ ነች” ሲል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ ያልተሟላ ነው ሲል ውድቅ ሲያደርገው በተቀሩት ሶስት ክሶች ግን ጥፋተኛ ነች ብሎ እንድትከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር።
ተከሳሿ ጥፋተኛ የተባለችበት አንደኛ ክስ በየካቲትና በመጋቢት ወራት ውስጥ 1999 ዓ.ም የማይገባትን ጥቅም ለማግኘት አስባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 21 ልዩ ቦታው ኪዳነምህረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ300 በላይ ሰዎችን በመሰብሰብ “እኔ ማርያም ነኝ፤ እንደኢየሱስም በጅራፍ ተገርፌ፤ ከሞትም ተነስቼያለሁ” የሚል የሀሰት ወሬ በመንዛትና የዓለም ፍፃሜ ደርሷል ንብረት አያስፈልግም በሚል ያላችሁን ንብረት አምጡ ስትል ከተለያዩ የግል ተበዳዮች ጥሬ ገንዘብና ወርቅ የተቀበለች ሲሆን፤ በአጠቃላይም 40ሺ ብር ለግል ጥቅሟ አውላለች ሲል በክስ መዝገቡ ያስረዳል።