Tuesday, April 2, 2013

ድኅነት በሂደት ወይስ በቅጽበት? ለሚለው የዳንኤል ክብረት ስብከት የተሰጠ ምላሽ



ደግመን ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እንላለን። ማቅና አገልጋይ ወኪሎቹ ጊዜና እድል ስላረገደላቸው ብቻ በጠለቀ እውቀት ውስጥ  ሆነው የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ይመስላቸዋል። ከእነዚህ መንጋና ጎጋ ሰባኪዎቹ መካከል አንዱ የተረት አባት የሆነው ዳንኤል ክብረት የተባለው ሰው ነው። ለስሙ፤ ለክብሩና ለዝናው ዘወትር የሚተጋ፤ ነገር ግን የአስተውሎት ደኃው ዳንኤል ክብረት በአንድ ስብከቱ ላይ እንዲህ በሚል ርእስ ስህተቱን ለተከታዮቹ ሲረጭ ተመልክተነዋል።

«መዳን በሂደት ወይም በቅጽበት?

በዚህ ርእስ ላይ ዳንኤል «መዳን» ባመኑበት ሰዓት በቅጽበት የሚሰጥ ሕይወት ሳይሆን በሂደት የሚገኝ ሀብት ነው ይለናል። ስለዚህም ክርስቲያኖች ለመዳን  ከፈለግን ለድኅነት የሚያበቃ ተጋድሎ እየፈጸምን መቆየት የግድ አለብን በማለት ድነት/መዳን/ በቅጽበት የመሰጠቱን ነገር ክዶ ሊያስክድ ያባብላል። እውነት፤ ዳንኤል እንደሚለው መዳን በቅጽበት የሚሰጥ ጸጋ ሳይሆን ክርስቲያኖች ለመዳን ሂደትን መጠበቅ አለባቸው?  የእግዚአብሔርስ ቃል እንደዚያ ያስተምረናል? ሰው ለድኅነት ስንት ዘመን መቆየት አለበት? በስንት እድሜው ላይ ሊያረጋግጥ ይችላል? ድነኻል ብሎስ ማን ይነግረዋል? ዳንኤል ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሆን ማብራሪያ መስጠት አልፈለገም፤ እንዲያው ሾላ በድፍኑ ብሎ ፤ ድኅነት በጥረትና በትግል ሂደት የሚገኝ እንጂ በቅጽበታዊ እምነት የሚሰጥ አይደለም ለማለት አጋዥ ምክንያቶቹን በመፈለግ ሊያሳምነን ይሞክራል። ይህንን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል ወይም መናፍቃን ናቸው ሲልም የራሱን ትክክለኛነት ለራሱ ነገሮ ስሙኝ ይላል።  ከየትኛውም ትምህርት ቤትና መምህር እንደዚህ የሚል ቃል እንዳገኘ አይነገረንም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በ«ቅዳሴ እግዚእ»  ቅዳሴ ወቅት በእርገተ እጣን ሰዓት በኅብስቱና ጽዋዕ ላይ ካህኑ እንዲህ እያለ በማጠን ይጸልያል።
«ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም፤ ሐመ ከመ ሕሙማነ፤ ያድኅን እለ ተወከሉ በላዕሌሁ»  ትርጉም፤  «እጆቹን ለሕማም ዘረጋ፤ በእርሱ የታመኑትን ያድን ዘንድ እንደ ሕሙማን ታመመ» ይለናል።  እንግዲህ ክርስቶስ ሕማምና ስቃይን ተቀብሎ እንዳዳነን ይህ ቃል ያረጋግጣል። ሰባኪው ዳንኤል በክርስቶስ ስቃይ እኛ መዳናችን በጊዜ ሂደት የሚረጋገጥ እንጂ በሞተልን ሰዓት የተቀበልነው አይደለም የሚለው ከየት አምጥቶ ነው?
ይህንን የዳንኤልን አሳሳች ስብከትና የጥፋት መርዝ ትምህርቱን  በወንጌል ቃል ገላልጠን  ለማሳየት እንፈልጋለን። አንባቢም የዳንኤልን ስብከት ፈልጎ እንዲያዳምጥ እንጋብዛለን ወይም በስተግርጌ ያስቀመጥነውን ሊንክ በመጫን ይህንን ጽሁፍ አንብቦ እንደጨረሰ አዳምጦ እንዲያገናዝብ ለሚዛናዊ ፍርድ አስቀምጥነዋል። ለወደፊቱም እሱንና እሱን መሰል ስሁታን አረፋ እየደፈቁና እየተንዘፈዘፉ በየመድረኩ የሚወራጩ  የሐሳውያንን  የጥፋት መንገዶች ለማሳየት እንመረምራለን። ሕዝቡን ወደጥፋት የሚነዱ የጠላት መልእክተኞች የሆኑበትን ስብከት እንደዚሁ እየመዘዝን ለማሳየት እንሞክራለን።

Saturday, March 30, 2013

ንስሐ ለአብያተ ክርስቲያናት




የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ መጋቢት 20/2005 ዓ.ም.

ከዛሬ ሠላሣ ሁለት ዓመት በፊት በጎጃም ይኖሩ የነበሩ 40 ዓመት የዘጉ አንድ ባሕታዊ ከዘጉበት በኣት/ቤተ ጸሎት/ ወጥተው ለሕዝቡ ታዩ፡፡ ታይተው የማያውቁ እኚህ አባት ዛሬ መውጣታቸው ሕዝቡን አስደንግጦታል፡፡ ለሰንበት ቅዳሴ ለተሰበሰበው  ሕዝብ እንዲህ በማለት ተናገሩ፡- “በሕልሜ ቤበ- መኩ- እፍ- ጸጉ የሚሉ ቃላትን ያሳየኛል፡፡ ተጨንቄአለሁና እባካችሁ ፍቱልኝ” አሉ፡፡ ሕዝቡም፡- “አባታችን እኛ ምኑን እናውቀዋለን? ለእርስዎ እንዳሳየ ይፍታልዎ እንጂ” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም ሕልሙን ሲተረጕሙ፡-
ቤበ  - ማለት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ማለት ነው፡፡
መኩ - መሥዋዕት ኩበት ሆነ ማለት ነው
እፍ -  ዕጣን ፍግ ሆነ ማለት ነው፡፡
ጸጉ - ጸሎት ጉባዔ/ ታይታ/ ሆነ ማለት ነው በማለት ተረጎሙ፡፡
ሕልምም ሆነ ትንቢት በፍጻሜው ይታወቃል፡፡ እኝህ አባት ያሳያቸው እውነት እንደሆነ ዛሬ እያየነው ነው፡፡ በረት ቆሻሻ የበዛበት፣ ንጽሕና የጎደለው፣ ሥነ ሥርዓት የሌለበት፣ የሕያው ነፍስ ሳይሆን የደመ ነፍስ /የእንስሳት/ መከማቻ፣ ነጻነት የማይሰጥ፣ በውስጡ የሚኖሩት የሕሊና፣ የሰብአዊና የመንፈሳዊ ሕግ የማያዛቸው፣ ዙሪያው የሚበርድ ክፍት የሆነ ስፍራ ነው፡፡ እኝህ አባት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ይለኛል አሉ፡፡ ንስሐን የመሰለ የሕይወት ውኃ የሚነገርባት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ  ያልታጠቡባት፣ ንስሐን ተሸክመው ንስሐ የሚቀበሉባት፣ በዓለም የሌለ ነውር በእርስዋ የሚሰማባት፣ ቅድስና የራቃት፣ ሁሉም በፊቱ ደስ ያለውን የሚያደርግባት፣ የደፈረ የሚኖርባት፣ እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት የማይሰማቸው አገልጋዮች የተሰበሰቡባት፣ ትሩፋት የሚሠራ አይደለም የታዘዘውን የሚፈጽም የታጣባት፣ ለሚያያቸው ዕረፍት የማይሰጡ ያልተገሩ ሠራተኞች የሞሉባት፣ ለእግዚአብሔርና ለአገር ሕግ የማይገዙ የተከማቹባት፣ ሲያስቧቸው ብርድ ብርድ የሚሉ ሥርዓት አልበኞች የነገሡባት ስፍራ ሆናለች፡፡


ከደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካቴድራል ኮለምቦስ ኦሃዮ የተሰጠ መግለጫ



ከሁሉም በላይ በሆነች ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፤ አሜን። ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለው የኢ ሕ አ ዴ ግ  መንግሥት በኃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በመንፈሳውያን አባቶች፤ በካህናትና በምዕመናን መካከል ልዩነት በመፍጠር ፤ ይህንኑ ልዩነት በማስፋትና በማራገብ ለዘመናት የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ እምነት አገልግሎት ያለአንዳች እንከን እየተካሄደ ባለበት ዘመን  በተቀደሰና በተከበረ ዓውደምህረት፤ ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ እንዲሰፍንና በኦርቶዶክሳውያን መካከል ሰላም እንዲደፈርስ፤ ብሎም የቡድንና የጐጥ ስሜት እንዲስፋፋ ያላቋረጠ ሴራ ሲሸርብ መቆየቱ ይታውሳል። ይህንን ኃላፊነት የጐደለውን እኩይ ተግባር መላው ሕዝበ ክርስቲያን ተረድቶ በተገቢው ጊዜና ሰዓት አፋጣኝና ሥርነቀል የሆነ ምላሽ ካልሰጠበት፤ የሁለት ሺሕ ዓመታት እድሜ ባለፀጋ የሆነችውን ቤተክርስቲያናችን ሕልውናዋን በፅኑ መሠረት ላይ እንደተጠበቀ ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ  ውስብስብ መሰናክሎች እንደሚገጥሙት ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
በመሆኑም ጥቂት የችግሩን አስከፊነት በጥልቀት የተረዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት በቅን ልቦና ተነሳስተው፤ ተግባብተውና ተቀራርበው በመወያየት በተለይም አሁን በአገራችን የታየው የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት፤ የኦርቶዶክስ አማኞች አሳፋሪ የመለያየት ፈተና፤ የእምነት ክፍፍል፤ በተለይም የአራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስት ዘኢትዮጵያ በመንግሥት ጫናና ግፊት ያለ በቂ ምክንያት ከመንበረ ከፕትርክናቸው በግፍ እንዲነሱ የተደረገበትን ሁኒታ ለአንዴና ለመጨረሻ  ጊዜ እልባት እንዲያገኝ ሰፊ ጥረት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት፤ አባ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ ይህም ወደ አንድነት የማምጣቱን ሂደት  መልካም አጋጣሚ በመፈጠሩ፤  የሰላሙ ኮሚቴ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ለሦስተኛ ጊዜ በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር ያሉትን የቤተክርስቲያን አባቶች ፊት ለፊት አገናኝቶ እንዲነጋገሩና  ለተፈጠረው ችግሮች መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የሚይስችል ዕድል አመቻችቶ ነበር።