ደግመን ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እንላለን። ማቅና አገልጋይ
ወኪሎቹ ጊዜና እድል ስላረገደላቸው ብቻ በጠለቀ እውቀት ውስጥ ሆነው
የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ይመስላቸዋል። ከእነዚህ መንጋና ጎጋ ሰባኪዎቹ መካከል አንዱ የተረት አባት የሆነው ዳንኤል ክብረት የተባለው
ሰው ነው። ለስሙ፤ ለክብሩና ለዝናው ዘወትር የሚተጋ፤ ነገር ግን የአስተውሎት ደኃው ዳንኤል ክብረት በአንድ ስብከቱ ላይ እንዲህ
በሚል ርእስ ስህተቱን ለተከታዮቹ ሲረጭ ተመልክተነዋል።
«መዳን በሂደት ወይም በቅጽበት?
በዚህ ርእስ ላይ ዳንኤል «መዳን» ባመኑበት ሰዓት በቅጽበት የሚሰጥ
ሕይወት ሳይሆን በሂደት የሚገኝ ሀብት ነው ይለናል። ስለዚህም ክርስቲያኖች ለመዳን ከፈለግን ለድኅነት የሚያበቃ ተጋድሎ እየፈጸምን መቆየት የግድ አለብን በማለት
ድነት/መዳን/ በቅጽበት የመሰጠቱን ነገር ክዶ ሊያስክድ ያባብላል። እውነት፤ ዳንኤል እንደሚለው መዳን በቅጽበት የሚሰጥ ጸጋ ሳይሆን
ክርስቲያኖች ለመዳን ሂደትን መጠበቅ አለባቸው? የእግዚአብሔርስ ቃል
እንደዚያ ያስተምረናል? ሰው ለድኅነት ስንት ዘመን መቆየት አለበት? በስንት እድሜው ላይ ሊያረጋግጥ ይችላል? ድነኻል ብሎስ ማን
ይነግረዋል? ዳንኤል ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሆን ማብራሪያ መስጠት አልፈለገም፤ እንዲያው ሾላ በድፍኑ ብሎ ፤ ድኅነት በጥረትና በትግል
ሂደት የሚገኝ እንጂ በቅጽበታዊ እምነት የሚሰጥ አይደለም ለማለት አጋዥ ምክንያቶቹን በመፈለግ ሊያሳምነን ይሞክራል። ይህንን የሚሉ
ካሉ ተሳስተዋል ወይም መናፍቃን ናቸው ሲልም የራሱን ትክክለኛነት ለራሱ ነገሮ ስሙኝ ይላል። ከየትኛውም ትምህርት ቤትና መምህር እንደዚህ የሚል ቃል እንዳገኘ አይነገረንም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ«ቅዳሴ እግዚእ» ቅዳሴ ወቅት በእርገተ እጣን ሰዓት በኅብስቱና ጽዋዕ ላይ ካህኑ እንዲህ እያለ
በማጠን ይጸልያል።
«ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም፤ ሐመ ከመ ሕሙማነ፤ ያድኅን እለ ተወከሉ
በላዕሌሁ» ትርጉም፤ «እጆቹን ለሕማም ዘረጋ፤ በእርሱ የታመኑትን ያድን ዘንድ እንደ ሕሙማን ታመመ»
ይለናል። እንግዲህ ክርስቶስ ሕማምና ስቃይን ተቀብሎ እንዳዳነን ይህ
ቃል ያረጋግጣል። ሰባኪው ዳንኤል በክርስቶስ ስቃይ እኛ መዳናችን በጊዜ ሂደት የሚረጋገጥ እንጂ በሞተልን ሰዓት የተቀበልነው አይደለም
የሚለው ከየት አምጥቶ ነው?
ይህንን የዳንኤልን አሳሳች ስብከትና የጥፋት መርዝ ትምህርቱን በወንጌል ቃል ገላልጠን ለማሳየት እንፈልጋለን። አንባቢም የዳንኤልን ስብከት ፈልጎ እንዲያዳምጥ እንጋብዛለን
ወይም በስተግርጌ ያስቀመጥነውን ሊንክ በመጫን ይህንን ጽሁፍ አንብቦ እንደጨረሰ አዳምጦ እንዲያገናዝብ ለሚዛናዊ ፍርድ አስቀምጥነዋል።
ለወደፊቱም እሱንና እሱን መሰል ስሁታን አረፋ እየደፈቁና እየተንዘፈዘፉ በየመድረኩ የሚወራጩ የሐሳውያንን የጥፋት መንገዶች ለማሳየት እንመረምራለን። ሕዝቡን ወደጥፋት የሚነዱ የጠላት
መልእክተኞች የሆኑበትን ስብከት እንደዚሁ እየመዘዝን ለማሳየት እንሞክራለን።