ፕሮፌሰር መሥፍን ወ/ማርያም
(ክፍል ሁለት)
የዛሬዎቹ ባለሥልጣኖች በደርግ ጊዜ አልነበሩም፤ የደርግን ስሕተት በማየት አልተማሩም፤ ትምህርታን አቋርጠው ወደጫካ የገቡት ከትምህርት የሚበልጥባቸው ምኞት አጋጥሟቸው ነው፤ የትምህርት ገዜያቸውን በጫካ ባለሥልጣን በመሆን፣ እነሱው ሕግ አውጪና ዳኛ፣ እነሱው የጫካ አስፈጻሚ ሆነው ቀዩ፤ ደርግ በጠራራ ጸሐይ የሚሠራውን እነሱ በጫካ ጭለማ ሲሠሩ ቆዩ፤ በሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላም በጣም ቆይተው ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን በትንሹ ተገነዘቡ፤ በጣም የተማሩ ሰዎች ጋር ሲገናኙ ማፈር አስጨነቃቸው፤ ስለዚህም ቀላሉ ነገር የተማሩ ሰዎችን አለማቅረብ፣ ትምህርታቸውን በጠባያቸው ካላጠቡ የተማሩ ሰዎች ጋር በቀር አለመገናኘት፣ እንዲያውም የትምህርትን ዋጋና ጥራት በማዋረድ አዲስ የሚመረቁት ሁሉ ለባለሥልጣኖች አንገታቸውን የሚደፉ ዓይነት እንዲሆኑ ማድረግ ዓላማ ሆነ።
የተማሩና የሠለጠኑ የጦር መኮንኖችም ተሸናፊዎች በመሆናቸው ትምህርታቸው ዋጋ እንደሌለው ማረጋጋጫ እያደረጉ የወያኔ መሪዎች በአደባባይ ተናገሩ፤ ትንሽዋ ቢምቢ ሰውን መግደል እንደምትችል ያልተገነዘቡት ከጫካ የመጡ ሰዎች በመግደል ማሸነፍን የትምህርትን ዋጋ-ቢስነት ማረጋጋጫ አደረጉት፤ የተማሩ ሰላማዊም የጦር መኮንኖችም ዋጋ-ቢስነታቸው ኑሮአቸውን በማናጋቱ በችግር ወደሌላ ሥራ ተሰማሩ፤ ወይም አገር ጥለው ተሰደዱ፤ በሰላማዊውም ሆነ በፖሊስና በጦር ሠራዊቱ የተማረ ሰው እጥረት መፈጠሩ ለወያኔ መግቢያና መደላደያ ምቹ ሁኔታን ፈጠረ።