Monday, March 18, 2013

«ቦኪሜ ነህ ኢየሱስ» ዘማሪት ምርትነሽ

«የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፦ እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ»መሣ 2፤1-5



Sunday, March 17, 2013

ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ማዳን ሲችል ለምን ሥጋ መልበስ አስፈለገው?


የብዙ ሃይማኖቶች መምህራን «ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው ነው» በማለት ይመሰክራሉ። ይህም እውነት ነው። ነገር ግን ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን ሲችል ለምን ሥጋ በመልበስ በሞቱ አዳምንና ልጆቹን ማዳን አስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ የላቸውም። ሥጋ መልበስ ማለት አምላካዊ ስልጣኑን በመተው ራሱን ባዶ ማድረግ እንደሆነ ለመቀበል ሲቸገሩ ይስተዋላሉ። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል በትክክል ገልጾታል።

«እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ» ፊልጵ ፪፤፮-፯ 

ፍጹም ሰው ሆነ ስንልም መለኮታዊ ማንነቱን ተወ ማለት ሳይሆን አምላካዊ ሥልጣኑን ሸሸገ ማለታችን ነው። ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደእኛ የተፈተነውም ለዚህ ነው። መለኮታዊ ስልጣኑን የመሸሸጉ ምክንያትም ፍጹም ሰው በመሆን ከአብ ጋር ያለውን መለኮታዊ ዕሪናውን  እንደተወ ሳይቆጥር እንደልጅ ለመታዘዝ ነው።  ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የሆንን ሰዎች ልጅ ሆኖ መታዘዙን ልክ፤ ከአብ  ያነሰ አድርጎ እንደመቁጠር ስለምናስብ እንደነግጣለን። አማለደ፤ አስታረቀ፤ ታዘዘ የሚሉ ቃላትን መስማማት የወልድን ባሕርይ ህጹጽ አድርጎ  የሚያወርድ ነው በማለት ለመቀበል የማይፈልጉ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። አምላካዊ ባህርይውን ለመጠበቅ ሲባል ፍጹም ሰው የሆነበትን ምስጢር በመሸርሸር ከማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ የመሆን ማንነቱ ለመሸሽ መሞከር  ምስጢረ ሥጋዌን በሽፍንፍኑ እንደመሻር ይቆጠራል። 

 ማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ከሌለ ፍጹም ሰው እንደሆነ ማመን በፍጹም ሊመጣ አይችልም። በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን እየቻለ ሥጋ መልበስ ያስፈለገው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ከኃጢአት ሁሉ ንጹህ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከል እንዲገባ በማስፈለጉ እንደሆነ አምኖ መቀበል የግድ ነው። ያለበለዚያ ነገረ ድኅነት የሚባል አስተምህሮ አይመጣም።
ቀድሞ ሰውና እግዚአብሔርን ሲያገናኝ የቆየው ሕግ ነበር። ሕጉ የሚያዘውን ሁሉ የሚያስፈጽሙ መካከለኞች ደግሞ ካህናቱ ናቸው። በሕግ ተቀባዮች በሕዝቡና በሕግ ሰጪው በእግዚአብሔር መካከል ያሉት መካከለኛ የሕግ አስፈጻሚዎቹ ራሳቸው ንጹህ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር።  ይህንንም የስርየት መስዋዕት በማቅረብ መንጻት ግዴታቸው ነው። ከዚያም የሕዝቡን ሥርየት ሕጉን በመተግባር ያስፈጽማሉ። እንግዲህ ይህ መስዋዕት ዕለት ዕለት የሚደረግ ነው። እንደዚያም ተደርጎ ለሕጉ ፈጻሚዎች  ዘላለማዊ የሆነ ስርየትን ማስገኘት አይችሉም። ይህ መስዋዕት ምድራዊ ነው። ምክንያቱም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ትዕዛዝን የማፍረስ የጥል ግድግዳ በቀዳማዊው ሰው ጥፋት የተነሳ ተተክሎ ነበርና። 

ይህ የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍረስ ነበረበት። በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በብቃት ለማፍረስ ደግሞ ኃጢአት የማያውቀው ሰው ያስፈልጋል። ክህነቱም ፍጹም ሊሆን ይገባል። ይህንንም ለማሟላት አምላክ ሰው በመሆን ያንን ደካማ ሥጋችን በመልበስ ከውድቀት ማዳን ነበረበት። በዚህም የተነሳ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በፈቃዱ የአብ የባህርይ ልጅ ሆኖ ሥጋችንን ለመልበስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አደረ። እንደሰውነቱ ኃጢአት አያውቀውም። እንደካህንነቱ ዘላለማዊ ካህን ነው። እንደአዳኝነቱ ሞት አያሸንፈውም። እንደልጅነቱ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እንደስርየት መስዋዕትነቱ አንዴ፤ ግን ለሁል ጊዜ  የሚሆን ነው። ይህም የነበረውን ጥል አፍርሶ በአብ የተወደደ መካከለኛና ለሕዝቡ ኃጢአት ዘላለማዊ ሥርየትን ማስገኘት የሚችል ሊቀ ካህን ሆኗል።

Saturday, March 16, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ለመብት ጥያቄ እየጮሁ ናቸው፤ሰሚ አላገኙም!

  •  
  •  ቤተ ክህነትም አካባቢውን በፌዴራል ፖሊስ እያስጠበቀች ነው።
  •  
  • የምግብ አቅርቦት ከተቋረጠባቸው ሦስተኛ ቀኑ መሆኑ ተሰምቷል።

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአስተዳደር ጉድለት፤  የትምህርት ጥራትና የመምህራን ብቃት ጉዳይ ተማሪዎቹን ለዓመታት እያስጨነቀ የቆየና አቤቱታ ቢያቀርቡበትም መፍትሄ የራቀው ሆኖ መዝለቁ ይታወቃል። ሙስና የተስፋፋበት ሆኖ ቆይቷል። ለተማሪዎች ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ  ኃይል፤ ዛቻና ከትምህርት ገበታ ላይ ማባረር ሆኗል። ብዙ ጊዜ የተነገረለትን የአስተዳደርና የመብት ጥያቄ ጉዳይ ቤተ ክህነት ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለትዋም በላይ መፍትሄ ብላ የያዘችው ጉዳይ ጣቷን ወደሌላ አካል መቀሰርና በሙስና ለበሰበሱ ሹመኞቿ ጋሻ በመሆን መከላከል ነው። አባ ጢሞቴዎስ የበላይ ጠባቂነቱን ወንበር እንደግል ርስት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ተማሪዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ለተማሪዎቹ አንድም ነገር ጠብ ካለማለቱም በላይ ችግሩ እንተንከባለለ ቀጥሏል።