ብዙዎች ስለማኅበረ ቅዱሳን በምንጽፋቸው ጠጣር መልዕክቶች በጣም ሲያዝኑ እንመለከታለን። በኢሜል ወቀሳና ከዚያም ሲያልፍ ስድብ የሚልኩልን አሉ። በጽሁፎቻችን ውስጥ
ማኅበሩን ነካ ባደረግን ቁጥር የሚያማቸውና ጸያፍ አስተያየቶችን የሚሰጡንም አጋጥሞናል። አንዳንዶች ስለማኅበረ ቅዱሳን የምንጽፋቸውን
እውነትነት አላቸው ብለው እንደሚቀበሉን ሁሉ ተቃራኒውን አመለካከት እንደተለየ ሃሳብ ቆጥረን በአክብሮት
እኛም ስንቀበላቸው ቆይተናል። ወደፊትም እንደዚሁ! የሃሳብ ልዩነት በዱላ ማስገደድ እስካልተቀላቀለበት ድረስ ለበጎ ነው እንላለን።
እኛ የሚታየንና እውነት ነው ብለን የተቀበልነው ነገር ለእነርሱ እንደስህተት
ቢቆጠር አያስገርምም። እኛም ያላየንላቸው የእነርሱ እውነት ሊኖር እንደሚችል አስበንላቸው ተቃራኒ ሃሳባቸውን እናከብራለን። በዚሁ
መንገድ የሁለት ወገን እሳቤን ተቀብለን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እናምራ።
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ተመሠረተ? ብለን የዓመታቱን መታሰቢያ
የልደት ሻማዎችን ለመለኮስ ወይም አስልቺ የሆነውን የልደት ትረካ በመዘብዘብ ጊዜ ለማባከን አንፈልግም። ግብሩን ለመናገር ጥያቄዎችን
እንጠይቅና እንመርምር።
፩/ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ ነው ወይ?
ማኅበረ ቅዱሳንን እንደምናየው በጠለቀ ደረጃ ባይሆንም በተወሰነ
መልኩ በቤተ ክህነቱ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ያለፉ ሰዎችን ለመያዝ ሞክሯል። አብዛኛው ግን የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያቃጠላቸው
እንደሆኑ የሚናገሩ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ያቀፈና ዘግየት ብሎም ከሰንበት ት/ቤትም ሆነ ከፈለገ ሕይወት ት/ቤት ቅርበት ያልነበራቸውን
ለመያዝ የሞከረ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንና ይህንን የመሳሰሉ ሰዎችን
ይዞ እየተጓዘ እዚህ የደረሰው ማኅበር በነማን ምን ሰራ? ምንስ አበረከተ? የሚለውን ልክ ስንመለከት ማኅበሩ እንዳዋቀሩት ሰዎች የማንነት ደረጃ አለኝ የሚለውን
የእውቀት ልክ ከነድርጊቶቹ እንመዝናለን እንጂ ዝም ብለን በጥላቻ
አንፈርጅም።
ከዚህ አንጻር ማኅበሩ ሌላውን የሚመለከትበት ዓይን ራሱን ባዋቀረበት
አቅምና ባለው የእውቀት ልክ ሳይሆን ነገሮች እየገጠሙ ስለተጓዙለት ብቻ ራሱን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ አድርጎ ማስቀመጡ
አስገራሚ ይሆንብናል። በማኅበረ ቅዱሳን ሠፈር ራስን በማሳበጥ የእውቀትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት አብጠርጥሮ የማወቅ ችግር
እንደሌለ ትልቅ ሥዕል አለ። መድረክ ላይ ቆሞ የማስተማር እድልና
የእውቀት ጥማት ባላቸው ብዙ ምእመናን ጉባዔ ላይ ተገኝቶ የመናገር
እድል በመግጠሙ ብቻ ማኅበሩ የእውቀት ርካታ የማካፈል ብቃት እንዳለው አድርጎ ራሱን አግዝፎ ማየቱን ስናይ ይገርመናል። ብዙዎቹን የማኅበሩ አንጋፋ ተናጋሪዎቹን ትምህርት
በአካልና በድምጽ ወምስል መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች የማየት እድሉ ነበረን። አንዳንዶቹ የእውቀት ሳይሆን የንግግር ችሎታ ያላቸው
ናቸው። አንዳንዶቹ የእውቀትም፤ የንግግር ችሎታ የሌላቸው ነገር ግን እድል የከነፈችላቸውና የሰው ወፍ የሚረግፍላቸው ስለሆኑ ብቻ መምህራን መሆናቸውን ለራሳቸው የነገሩ ናቸው። አንዳንዶቹ እውቀት
ያላቸው ቢሆኑም ነገር ግን እውነቱን በማጣመም ልክፍት የተያዙ ጠማማዎች
ሲሆኑ አረፋ እየደፈቁ ለጉባዔ ሲናገሩ ከማንም በላይ የደረሱበትን
እውቀት የሚያስተምሩ ይመስላቸዋል። ሌሎቹም እውቀቱ እያላቸው ለማስተማር የማይፈልጉ ጥገኞች/Parasitic/
ሆነው ተጎልተዋል። ከምንም ከምኑም ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ክፋትና
ሴራ በመጎንጎን የተካኑ የጥፋት መንፈስ ያሰገራቸው ሰዎችንም ተሸክሟል።
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ማኅበር ውስጥ በተለየ መደብ
በቅንነት፤ በየዋህነትና በእምነት የተሰለፉ አያሌዎች ደግሞ የማኅበሩ ቀኝ እጅ ሆነው እያገለገሉ መገኘታቸው እውነት ነው። አለማወቅ በራሱ ችግር ቢሆንም ቅኖችና የዋሃን ከማኅበሩ ጋር በመቆማቸው የማኅበሩ
ድክመት እንደጥንካሬ በመቆጠሩ ብቻ ቅን ማኅበር ነው ሊሰኝ አይችልም።