Monday, March 4, 2013

ጥንቆላ - በሀገራችን ፣ በቤተ ክርስቲያናቸን እንዲሁም በእያንዳንዳችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ


ክፍል ሁለት         (www.abaselama.org)


ባለፈው ጽሑፌ ጥንቆላ ምን እንደሆነ ጥቂት ለማሳየት ሞክሬያለሁ፤ በሰፊው ግን አልገለጥሁትም። የሰይጣንን ክፋት በሰፊው ከመግለጥ የእግዚአብሔርን ደግነት አጉልቶ መግለጥ ይሻላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። ነገር ግን ወገኖቼ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጥንቆላን እንደቀላል ልማድ በማየት በጨለማው ገዢ ሥር ሲወድቁ እያየሁ ስለማዝን እውነታውን ለማሳየት ምክሬያለሁ። ዛሬ ደግሞ አንዳድ መናፍስት ጠሪዎችና ደጋሚዎች የሚያጠምቁበትን ዘዴ ከአንድ ደብተራ ጓደኛዬ ያገኘሁትን ምስጢር በጥቂቱ መግለጥ እሞክራለሁ።


አስማቱ በመስቀል፤ በጣት ቀለበት እና በመቁጠሪያ ሊሠራ ይችላል። በመስቀል ቅርጽ እንዲሁም በመቁጠሪያነት ለድግምቱ የሚያገለግሉ እጸዋት ሁለት ናቸው። አንደኛው አርግፍ የሚባል ሲሆን ሁለተኛው ጠንበለል ይባላል። እጸዋቱ በደጋማ ሥፍራዎች ይገኛሉ። በትክል ድንጋይና በሰከላ በብዛት ይገኛሉ። የአስማቱ ባለሙያዎችም ከላይ በጠቅስሁአቸው ቦታዎች አሉ። በተለይ አርግፍ የሚባለውን እንጨት በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች እየጠረቡ ለሕጻናት ከሰይጣን እና ከቡዳ ይጠብቃል እያሉ ባንገታቸው ያደርጉላቸዋል።

 ይህ እንጨት የማይሰራበት አስማት የለም ይባላል፤ ሰዎችን ለክፉዎች አሳልፌ እንዳልሰጥ ሁሉን ከመግለጥ እቆጠባለሁ። ለማጥመቅ ሲጠቀሙበት ግን የሚያደርጉትን መናገር ግድ ሆኖብኛል። እንጨቱን ሲቆርጡት የሚደግሙት አላቸው። ሰባት ቀን ሲደግሙ ቆይተው የዶሮ ወይም የሰው ደም ቀብተው ይቆርጡታል። ቅጠሉን በአዲስ ሸክላ[ውሃ ወይም እህል ያልነካው] ዘፍዝፈው አርባ ቀን ከደገሙበት በኋላ ዋናው ለማጥመቅ የተዋረሰው ግለሰብ ይጠመቅበታል። አጥማቂው አርባ ቀን በተደገመበት ውሃ ሲጠመቅ መናፍስት ያለ ከልካይ በብዛት እንደሚያድሩበት ይነገራል።

Sunday, March 3, 2013

ጥቁር ይሁን እንጂ ማንኛውንም ቀለም መቀባት ትችላላችሁ”

 (Addis Admas)
የዱር አራዊት ተሰብስበው ግብረ - ገብነታችንንና ሥነ-ምግባራችንን የሚያርቅ፣ መሠረታችንን የሚያበጅ፣ ደህና ጠባይ ያለው እንስሳ እንምረጥ ይባባላሉ፡፡
አንበሳ፤ የአራዊቱ ሁሉ ንጉሥ ነውና “ምርጫው ይሳካ ዘንድ ጦጣን፣ አህያንና ነብርን ስጡኝና የአመራረጡን ሥነ ስርዓት አስቀድመን እናበጃጀው!” ይላል፡፡ አራዊቱ፤ “መልካም ሀሳብ ነው፡፡ እነዚህን ሶስቱን ወስደህ ምከሩበት፡፡ አስቀድመህ ግን፤ ለምን እነሱን እንደመረጥክ ምክንያቱን አስረዳ” አሉት፡፡
አንበሳም፤
“መልካም፡፡ በአዘጋጅ ኮሚቴነት ሶስቱን ስመርጥ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሥራ ሀላፊነት፡-
አንደኛ - ብልሃተኛ መሆን ነው፡፡ ለዚህ ጦጣን መረጥኩ፡፡
ሁለተኛ - ሸክም የሚችል ትከሻ ያስፈልጋል፡፡ እንደምታውቁት ለዚህ ከአህያ የተሻለ መሸከም የሚችል አይገኝም፡፡
ሦስተኛ - ፈጣን መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደነብር ጥይት የለም፡፡
ምክንያቴ ይሄ ነው፤ አለ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡
“ጥሩ፡፡ በሉ ምርጫውን አሳኩት” ተባሉ፡፡
አንበሳ አስመራጮችን ሰብስቦ “እህስ? እንዴት እናድርግ ትላላችሁ?” አለ፡፡
አህያ፤ “ማናቸውንም በሸክም ዙሪያ ያለ ሥራ ለእኔ ይሰጠኝ” አለች፡፡
ነብር፤ “በፈጣንነቴ የትኛውም የጫካው ድንበር ድረስ ሮጬ የተሰጠኝን መልዕክት አደርሳለሁ” አለ፡፡
አያ አንበሶም፤ “እሺ እመት ጦጣስ? ምን እናድርግ ትያለሽ? መቼም መላ የሚጠበቀው ካንቺ ነው?!” አላት፡፡ ጦጣም፤
“መቼም አያ አንበሶ! የአህያም ሥራ ሸክም መሆኑ በሙያዋ ነው፡፡ የነብርም ሩጫ የተፈጥሮ ክህሎቱ ነው፡፡ እጅግ ከባዱ ጥያቄ ግን በእኔና በእርሶ በጌታዬ በአያ አንበሶ ጫንቃ ላይ ነው የወደቀው፡፡”


አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗል!


አዲስ አድማስ፤  መጋቢት 23/2005 -March 3, 2013


በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ ሢመት ፕትርክናውን አውግዟል


‹‹ዕርቀ ሰላሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በተናገረው መሠረት ይቀጥላል››

/ተመራጩ ፓትርያርክ/


አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች ለውድድር በቀረቡበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ሌሎች ዕጩዎችን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉበት ውጤት የምርጫውን ተሳታፊዎችና ተከታታዮች እያነጋገረ ነው፡፡

አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የምርጫው ተሳታፊዎችና በተለያዩ መንገዶች የምርጫውን ሂደት የተከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን÷ የምርጫው አሸናፊ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሊኾኑ እንደሚችሉ ከወራት በፊት በሰፊው ሲነገር የቆየ ነበር፡፡ ይኹንና በምርጫው ድምፅ ከሰጡ 806 መራጮች መካከል 60 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉበት ውጤት÷ በዕጩነት ከተካተቱትና ለፓትርያርክነት ይበቃሉ የተባሉት ሌሎች ዕጩ ፓትርያሪኮች በተናጠል ካገኟቸው አነስተኛ ድምፆች አንጻር የምርጫውን ሂደት መለስ ብለው ለማጤን እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ፡፡

ስማቸውና የተወከሉበት አህጉረ ስብከት እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት መራጮች፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተከናወነውን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅርበት መከታተላቸውን፣ በአፈጻጸሙ ግልጽና ቀልጣፋ ከመኾኑም ባሻገር ለትችት የሚዳርግ የጎላ ችግር እንዳላዩበት አስረድተዋል፡፡ ይኹንና ከምርጫው ቀን በፊትና ምርጫው ከተካሄደበት አዳራሽ ውጭ ተፈጽመዋል የሚሏቸው ተግባራት ለተጠቀሰው የውጤት መራራቅ በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡