Sunday, March 3, 2013

ጥቁር ይሁን እንጂ ማንኛውንም ቀለም መቀባት ትችላላችሁ”

 (Addis Admas)
የዱር አራዊት ተሰብስበው ግብረ - ገብነታችንንና ሥነ-ምግባራችንን የሚያርቅ፣ መሠረታችንን የሚያበጅ፣ ደህና ጠባይ ያለው እንስሳ እንምረጥ ይባባላሉ፡፡
አንበሳ፤ የአራዊቱ ሁሉ ንጉሥ ነውና “ምርጫው ይሳካ ዘንድ ጦጣን፣ አህያንና ነብርን ስጡኝና የአመራረጡን ሥነ ስርዓት አስቀድመን እናበጃጀው!” ይላል፡፡ አራዊቱ፤ “መልካም ሀሳብ ነው፡፡ እነዚህን ሶስቱን ወስደህ ምከሩበት፡፡ አስቀድመህ ግን፤ ለምን እነሱን እንደመረጥክ ምክንያቱን አስረዳ” አሉት፡፡
አንበሳም፤
“መልካም፡፡ በአዘጋጅ ኮሚቴነት ሶስቱን ስመርጥ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሥራ ሀላፊነት፡-
አንደኛ - ብልሃተኛ መሆን ነው፡፡ ለዚህ ጦጣን መረጥኩ፡፡
ሁለተኛ - ሸክም የሚችል ትከሻ ያስፈልጋል፡፡ እንደምታውቁት ለዚህ ከአህያ የተሻለ መሸከም የሚችል አይገኝም፡፡
ሦስተኛ - ፈጣን መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደነብር ጥይት የለም፡፡
ምክንያቴ ይሄ ነው፤ አለ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡
“ጥሩ፡፡ በሉ ምርጫውን አሳኩት” ተባሉ፡፡
አንበሳ አስመራጮችን ሰብስቦ “እህስ? እንዴት እናድርግ ትላላችሁ?” አለ፡፡
አህያ፤ “ማናቸውንም በሸክም ዙሪያ ያለ ሥራ ለእኔ ይሰጠኝ” አለች፡፡
ነብር፤ “በፈጣንነቴ የትኛውም የጫካው ድንበር ድረስ ሮጬ የተሰጠኝን መልዕክት አደርሳለሁ” አለ፡፡
አያ አንበሶም፤ “እሺ እመት ጦጣስ? ምን እናድርግ ትያለሽ? መቼም መላ የሚጠበቀው ካንቺ ነው?!” አላት፡፡ ጦጣም፤
“መቼም አያ አንበሶ! የአህያም ሥራ ሸክም መሆኑ በሙያዋ ነው፡፡ የነብርም ሩጫ የተፈጥሮ ክህሎቱ ነው፡፡ እጅግ ከባዱ ጥያቄ ግን በእኔና በእርሶ በጌታዬ በአያ አንበሶ ጫንቃ ላይ ነው የወደቀው፡፡”


አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗል!


አዲስ አድማስ፤  መጋቢት 23/2005 -March 3, 2013


በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ ሢመት ፕትርክናውን አውግዟል


‹‹ዕርቀ ሰላሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በተናገረው መሠረት ይቀጥላል››

/ተመራጩ ፓትርያርክ/


አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች ለውድድር በቀረቡበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ሌሎች ዕጩዎችን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉበት ውጤት የምርጫውን ተሳታፊዎችና ተከታታዮች እያነጋገረ ነው፡፡

አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የምርጫው ተሳታፊዎችና በተለያዩ መንገዶች የምርጫውን ሂደት የተከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን÷ የምርጫው አሸናፊ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሊኾኑ እንደሚችሉ ከወራት በፊት በሰፊው ሲነገር የቆየ ነበር፡፡ ይኹንና በምርጫው ድምፅ ከሰጡ 806 መራጮች መካከል 60 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉበት ውጤት÷ በዕጩነት ከተካተቱትና ለፓትርያርክነት ይበቃሉ የተባሉት ሌሎች ዕጩ ፓትርያሪኮች በተናጠል ካገኟቸው አነስተኛ ድምፆች አንጻር የምርጫውን ሂደት መለስ ብለው ለማጤን እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ፡፡

ስማቸውና የተወከሉበት አህጉረ ስብከት እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት መራጮች፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተከናወነውን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅርበት መከታተላቸውን፣ በአፈጻጸሙ ግልጽና ቀልጣፋ ከመኾኑም ባሻገር ለትችት የሚዳርግ የጎላ ችግር እንዳላዩበት አስረድተዋል፡፡ ይኹንና ከምርጫው ቀን በፊትና ምርጫው ከተካሄደበት አዳራሽ ውጭ ተፈጽመዋል የሚሏቸው ተግባራት ለተጠቀሰው የውጤት መራራቅ በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡

Friday, March 1, 2013

አዲሱ ፓትርያርክ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል!


በዚህም ተባለ፤ በዚያ አቡነ ማትያስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል። ባለፈው ግድፈትና እውነት ላይ  እያነሳንና እየጣልን ጊዜ አናጠፋም። ይልቅስ ብዙዎች የታገሉለት የምርጫው ስኬት እንዳሰቡት ጥሩ የሥራ ጊዜ ይዞ ይመጣላቸው  እንደሆነ የምናይበት፤  ገሚሶቻችንም የምናያቸው የቤተ ክህነት ተግዳሮቶች የሚቀረፉበት፤ ሰናይ የአስተዳደርና መንፈሳዊ ዘመን ናፍቆታችንን ተስፋ በማድረግ እንደዚህ በፊቱ አስቀድመን አንዳንድ ነገሮችን ለማመልከት ወደድን።
የአዲሱ ፓትርያርክ አዲስ የሥራ ዘመን ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። የተጠራቀሙ የቤተ ክህነቱ ችግሮችና ብዙ እንከኖች  ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። የችግሮቹ ዓይነቶች፤ ደረጃና ጥልቀት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የተለያየ ውሳኔና እርምጃንም የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህ የተዘጋጀ የአእምሮ ዝግጁነት፤ የእውቀት በሊህነት፤ ድፍረትና ማስተዋል እንደሚጠይቁም አይጠረጠርም።  ያንን ዓይነት ሰው ከየት እናገኛለን ብለን አናሳብም። ምክንያቱም ምርጫው /ከተባለ/ ትልቅ አባት ሰጥቶናልና። ስለዚህ ወደችግሮቹ እንንደርደር።

1/ የቤተ ክህነቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር ማሻሻል

የቤተ ክህነቱ ቀዳሚው ችግር ሥራና ሠራተኛ የተገናኘበት ተቋም አለመሆኑ ነው። ሥራና ሠራተኛ ካልተገናኘ ደግሞ  በየትኛውም መልኩ የቤተ ክህነቱ የሥራ አፈጻጸም «ከርሞ ጥጃ» መሆኑ አይቀርም። ሥራና ሠራተኛ ማለት ለተገቢው ሥራ ተገቢ ባለሙያ ወይም ተቀራራቢ ችሎታ ያለው ሰው ማለት ነው። እንደዚህ ባለው ሰው ላይ የተቋሙን ዓላማና ግብ በደንብ ካስጨበጡት ከችግሮቹ ብዛት አንጻር ባንድ ጊዜ ፈጽሞ ባይወገድም፤ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። በዘመድ አዝማድ የተለጣጠፉና የተደረቱ ክፍሎችን ይዞ መቀጠል ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናልና አሁን ያለን የሥራና ሠራተኛ አቋም የችግሩ ዋና ምንጭ ነው ባይባልም የችግሩ አካል ነውና ከጥገናዊ ለውጥ ወይም ከማስመሰል /pseudo/ የራቀ ለውጥ ያስፈልገዋል። ከአቅም በታች ለመሥራት የእድሜ ጣሪያ የገደባቸውም  በየመልኩ ቦታቸውን መያዝ  ካልቻሉ ቤተ ክህነት የዘመዳ ዘመዶች የጡረታ ተቋም ሆኖ ይቀጥላል እንጂ የሥራ ብቃት መለኪያ ስፍራ ሊሆን አይችልም። 

ሀገር አቀፍ ተቋም የሆነው ቤተ ክህነት ሀገር አቀፍ አደረጃጀት ሊኖረው የግድ ነው። ከላይ እስከታች አደረጃጀቱ መሻሻል አስፈላጊ ከሚባልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ብለን እናምናለን። በአንድ ወቅት በአሁኑ ሰዓት የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በድሉ አሰፋ የቤተ ክህነቱን የአቅም ግንባታ ክፍል ሆነው ጥናት አቅርበው እንደነበር አስታውሳለሁ። ቤተ ክህነትና የዘመኑ ጥናት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ቤተ ክህነትም በአሮጌ ልምዷ ስትቀጥል፤ አቶ በድሉም አሮጌው ጎዳና አላሰራ ስላላቸው ትተውት የተሻለ ቦታ ሄደዋል። ስለዚህ ቤተ ክህነትን ከአሮጌ መዋቅር ወደዘመነ ሥርዓት ለማስገባት አዲሱ ፓትርያርክ ትልቁ ሥራቸው መሆን አለበት  እንላለን። የተደረተውን በመጠገን  ላይ ካተኮሩ ግን ልባቸው ወልቆ እርጅናቸውን ከማፋጠን በስተቀር ለእርሳቸውም ይሁን ለቤተ ክህነቱ ቀጣይ አስተዳደር አንዳችም  ነገር ጠብ ሳይል ይቀጥላል ማለት ነው። ይህን ማስተካከል የአዲሱ ፓትርያርክ ፈታኝ ሥራ ነው ብለን እናስባለን።


2/  እርምጃ አወሳሰድ፤ የሥራ ብቃት መለኪያና አፈጻጸሙን የመቆጣጠሪያ ስልት፤

 ቤተክህነትን በብቃት የሚመራ ሕግ፤ መመሪያና ደንብ የለውም። ያለውንም በሥራ የሚያውል አካል አልነበረም። ነገሮች ሁሉ በልምድና በስምምነት የሚሰራበት ሆኖ ቆይቷል። ሥልጣንና ተግባር ለክቶ የሚሰጥ መመሪያ ባለመኖሩ ሥራና ኃላፊነት ተደበላልቀው በባለሥልጣን ይጣሳል፤ ወይም በመሞማዳሞድ ይሸፈናል።  መመሪያው ሕግ ሳይሆን ሹመኛው ራሱ ሕግ ሆኖ ያገለግላል። የአድርግና አታድርግ፤ የጌታና የሎሌ አስተዳደር እንጂ የ21ኛው ክ/ዘመን የተጠያቂነት አሠራር በቤተ ክህነት  የለም። ባለሥልጣናቱ ከፈለጉ ከአፈር ይቀላቅሉሃል፤ ከወደዱም ጣሪያ ላይ ይሰቅሉሃል። ሰው  የሚያድገውም  ይሁን  ድባቅ የሚመታው ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቆይቷል።  ለሠራው ሥራ ብቃትና ጉድለት መለኪያ  ሚዛን የለም። ሌላው ይቅርና የፓትርያርክ የምርጫ ሕግ እንኳን ከእንከን የጸዳ ባለመሆኑ በነቶሎ ቶሎ ቤት ጥበብ  ተለክቶ የተሰፋው በቅርቡ መሆኑን ልብ ይሏል።  እንግዳነቱ ብዙ ጭቅጭቅና ክርክር ማስነሳቱም  አንዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑ አይዘነጋም።  ነገም ይህ ችግር ላለመደገሙ ዋስትና የለም። ስለዚህ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ  ወጥነት ያለው ሕግ፤ መመሪያና ደንብ ሊኖር ይገባል።  ይህንን ችግር አጥንቶ የተሻለ መፍትሄ በማምጣት ላይ አዲሱ ፓትርያርክ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

3/ መንፈሳዊ ሲመት/ሹመት/ በተገቢው መለኪያ ማከናወን

ከጵጵስናው ጀምሮ እስከ እልቅና ድረስ ያለው የሲመት አሰጣጥ ሲባል እንደቆየውና እንደምናውቀው ወይ ገንዘብ ያለው፤ ወይ ዘመድ ያለው እንጂ በችሎታና በብቃት ልኬት የሚገኝ አልነበረም።  ጉልበት ስር መንበርከክን ዝቅ ሲልም ትቢያ መላስን እንደመስፈርት ሲሰራበት ቆይቷል። መከባበር ተገቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ትሕትናን ገንዘብ በማድረግ ያይደለ ሥጋዊ ክብርን ከመፈለግና ለሹመት ሲባል ወደአምልኮ የተቀየረ ስግደት የመስጠት ትእቢታዊ  ግብር ማላቀቅ ተገቢ ነው። ጵጵስናውንም እንደሲሞን መሰርይ ሽጡልኝ ወደሚባልበት ደረጃ ማውረድ ወይም በአማላጅና በሽማግሌ የሚረከቡት ንብረት መሆኑ መቆም አለበት።   መሪው በተመሪው የተመሠከረለት ቢሆን እንዴት ባማረ ነበር? ጳውሎስም የመከረን ይህንኑ እንድናደርግ ነበር።  ብዙ ጊዜ እንደሚታየው መሪውን ገንዘብ ይመርጥና ወደተመሪው ሕዝብ ይላካል። እዚያም እንደደረሰ መሪው ለሚመራው ሕዝብ ሳይሆን አገልጋይነቱ ለመደቡት ክፍሎች ይሆናል። ሕዝቡም በሚወርድበት የዐመጻ ሥራ የተነሳ እምነቱን እንዲጠላ፤ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ ብሎም እንዲኮበልል ይገደዳል። ሕገ ወጥነት የሰለጠነበት የቤተ ክህነት ሥልጣን እንደገና መበጠር ይገባዋል።  ሕዝቡ መጣብን ሳይሆን መጣልን የሚል መንፈሳዊ መሪ ይፈልጋል። በመጡበት ተላላኪዎች እስከዛሬ መሮታል። እናም አዲሱ ፓትርያርክ ይህንን ሁሉ ችግር ተረክበው የጣፈጠ ሥራን ሊያሳዩት ይጠበቃል።  ያለፈውን ችግር ተሸክመው በምን ቸገረኝነት ይቀጥላሉ ወይስ ይህንን የሚሸከም ጀርባ የለኝም ይሉ ይሆን? እሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የምንጠይቃቸው  መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ትልቁ ፈታኝ ሥራቸው እንደሆነ ግን በበኩላችን አስምረንበት እናልፋለን።