እመሰ አማን ጽድቀ ትነቡ...
ይድረስ ለነ አባ እንቶኔ፦(geezonline.org)
“ሰላም ለክሙ” እንዳልላችኍ፤ እንደ እኔ ያለ አንድ ምስኪን እንደ እናንተ ላሉ ታላላቆች ከታች ወደላይ ሰላምታ ማቅረብ የማይገባው መስሎ ስለሚታያችኍ፤ ላስቀይማችኍ አልሻምና ይቅርብኝ። “ሰላምክሙ ይብጽሐኒ” ብየ እንዳልማጠናችኍም፤ ስንኳን ለሌላ የሚተርፍ ለራሳችኍ የሚበቃ ሰላም እንደሌላችኍ እያየኍ የሌላችኍን ነገር በመለመን እንዳሳቅቃችኍ ኅሊናየ አይፈቅድልኝም። ስለዚህ የሰላምታን ነገር በዚሁ እንለፈው።
ሰላምታውን በዚሁ ካለፍነው ዘንድ ነገሬን በቀጥታ ልጀምር። ከቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ባገኘኹት ላይ ተመርጉዤ። በሊቃውንት ቋንቋ እንድገልጠው ከፈቀዳችኹልኝ፦ ጳጳሳት አይደላችኍ? ከብሉይ ታሪክ ምሳሌ አምጥቼ ግሥ ልገሥሥላችኍ ነው።
ርግጥ ነው ብዙዎቻችኍ ትርጓሜ መጻሕፍትን በወንበር ተምራችኋል ብየ አላስብም። እውነት ለመናገር ረ ከመካከላችኍ አንዳንዶቹ ተነሹን ከወዳቂ፥ እሚጠብቀውን ከሚላላው፥ በፍቅደት የሚነበበውን በውኅጠት ከሚነበበው በሚገባ ለይታችኍ ማወቃችኍን ስንኳ እጠራጠራለኍ። አዛኜን። ይኹን እንጂ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እንዲሁም የዐጤ ኀይለ ሥላሴ ስም አጠራራቸው የተመሰገነ ይኹንና አቡኑ አእምሮ፥ ንጉሡ ገንዘብ ኾነው በረድኤተ እግዚአብሔር ያሳተሙትን የዳዊት አንድምታ ከመጽሐፍ መደርደሪያችኍ ፈላልጉና (ድንገት ለነ አቦይ መልእክት ስትፋጠኑ ጊዜ አላደርስ ብሏችኍ እስከዛሬ ያልገዛችኹት ከኾነም፤ ስንኳን አንድ መጽሐፍ አገር ምድሩን የሚገዛ ገንዘብ በየባንክ ቤቱ ስለሞላችኍ ዛሬውኑ ልካችኍ አስገዙና) የምገሥሥላችኍ ግሥ ተስማሚ መኾን አለመኾኑን አረጋግጡ።
የምተኩረው በዳዊት መዝሙር ላይ ነው። በ57ኛው። ትርጓሜው የመቃብያንን ታሪክ ያስተርካል። ከታሪኩ አኹን የያዝነውን መዝሙር ለመረዳት የሚያሻው ክፍል፦ ስምዖን፥ እልፍሞስ፥ መባልስ የተባሉ ሦስት ንኡሳን ካህናት ለሹመት ሲሉ እስራኤልን የአሕዛብ ንጉሥ አንጥያኮስ እጅ እንዲያደርጋት መምከራቸውን፤ እሱ ስንኳ “አኹን የተናገራችኹትን ነገር ሳላስበው ውየ ዐድሬ አላውቅም። ነገር ግን እስራኤል ሰዎቹ ጽኑዓን ናቸው፤ አምባቸውም ጽኑ ነው ሲሉ እሰማለኍ። ፈጣሪኣቸውም ይረዳቸዋልና መቅረቴ ስለዚህ ነው እንጂ።” ቢላቸው፤ “እኛ ባወቅነ እናስገባኻለን። አንተም አመንኍ ብለኽ ዐዋጅ ነግረኽ ምስዋዕተ እሪያውን በዃላ በዃላ እያስጎተትኽ ላሙን በጉን በፊት በፊት እያስነዳኽ ና” ብለው መክረውት ኺደው የከተማዋን ቅጥር “ክፈቱልን” ያሏቸውን ይመለከታል። በዚህም ምክንያት "ፈጣሪየ የሃይማኖት አብነት ቢያደርገኝ የክህደት፥ የጥብዓት አብነት ቢያደርገኝ የፍርሃት፥ የበጎ አብነት ቢያደርገኝ የክፋት አብነት እኾናለኹን? አይኾንም" ያለው እውነተኛ ካህን አልዓዛር ሰባት ልጆቹ በሰይፍ ሲመቱ ሚስቱም በጡትና በጡቷ መኻል በኩላብ ተሰቅላ በሰይፍ ተቀልታለች። እሱም ይኽን ኹሉ እያየ ስንኳ ከጽናቱ የማይመለስ በመኾኑ በሰም የተጠማ የጋለ ብረት ምጣድ በራሱ ላይ ተደፍቶበት ተንጠቅጥቆ ሙቷል። በዚያኑ ጊዜ ከእስራኤል አራት ዕልፍ ዐብረው ዐልቀዋል፤ አራት ዕልፍ ተማርከዋል፤ አራቱን ዕልፍ ይሁዳ መቅብዩ እየተዋጋ ይዟቸው ወጥቷል። ስለዚህ በዚያን ጊዜ በሃይማኖታቸው የጸኑት ባባታቸው በመቃቢስ መቃብያን ተብለዋል። ዕጉሣን በስደት ጽኑዓን በምግባር ወበሃይማኖት ማለት ነው።