Monday, February 25, 2013

ያሳዝናል! ያሳዝናል! ያሳዝናል!...... (የሐራ ዘተዋሕዶ ዘገባ)

 (To read in PDF please Click here )

አንድ ጥያቄ እናስቀድም፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካዊ ዜጋ ስለመሆንና አለመሆን ጉዳይ ይመለከተው ይሆን? ለማንኛውም «ሐራ ዘተዋሕዶ» መሳጩን የሲኖዶስ ውይይት በቦታው የነበረ ያህል በአስደማሚ ዘገባ አቅርቧልና እንዲያነቡት እነሆ!

‹‹ቤተ ክርስቲያን ስትጠራኝ እምቢ እላለኹ ወይ ! ! !›› /ብፁዕ አቡነ ማትያስ/

    ‹‹አጃቢ ነን!›› /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል/

    ‹‹እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ እኔ እጠፋለኹ›› /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/

    ‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው›› /ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ/

    ‹‹ነገ በታሪክ የሚጠየቅና የሚወገዝ ሲኖዶስና አባት መኖር የለበትም›› /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

ከላይ በዋናው ርእስ የተመለከተው÷ ቁጭት እንጂ አቅም ያነሳቸው ንግግሮች የተሰሙት ትላንት፣ የካቲት 16 ቀን 2005 . በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ለመወያየት የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውል ያለው ግልጽ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ከቀትር በኋላ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡

በስብሰባው ሂደት÷ ለፕትርክናው የተሠየሙትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ተሳትፎ በነበራቸው ብፁዓን አባቶች መካከል የነበረው የከረረ የቃላት ልውውጥ፣ ተሳትፎ ባልነበራቸው ብፁዓን አባቶች ላይ የታየው ስጋትና ድብታ፣ በኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ምትክ የኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረበው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ለቅ/ሲኖዶሱ ጠረጴዛና ለአጀንዳው ታላቅነት የማይመጥን፣ ውክልናውና ያጸደቀለትን ማኅበር የሚያስንቅና የሚያስወቅስ ደርዝ የሌለው ንግግር፣ በዋናነትም ስብሰባው የተጠናቀቀበት ውል አልባ ኹኔታ ነው ይህን የሐዘን ንግግር ያናገረው፡፡ በዚህ ቃል ሲናገሩ ከተሰሙት አረጋውያኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቂቱን ለመጥቀስ÷ አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ኤርሚያስ፣ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ኤፍሬም እና ከዕጩዎች አንዱ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡

ስብሰባው ጠዋት 300 ላይ በውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ እና መልክአ ማርያም ጸሎት ከተከፈተ በኋላ ዐቃቤ መንበሩ የዕለቱን የስብሰባ አጀንዳ ሲያስተዋውቁ፣ ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴውን ሪፖርት ሰምተን ለማጽደቅ ነው፤›› በሚል ነበር ያስጀመሩት፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተጠርተው ገብተው በሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በኩል የዕጩዎች አመራረጥ፣ ዝርዝርና ማንነት በንባብ ከተሰማ በኋላ የነበረው የስብሰባው ድባብ ግን፣ ሰምቶ ማጽደቁ ቀርቶ የተጋጋሉ ውይይቶችንና ትችቶችን ያስተናገደ፣ ከሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በቀር ብዙኀኑ የኮሚቴው አባላት አንዳች የውስጥ ክፍፍልን በሚያሳብቅ አኳኋን (በተለይም ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ) በእጅጉ አዝነውና ተክዘው የታዩበት፣ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የተረጋገጠ መልስ ሊሰጥ ያልቻለበት አሳዛኝ ኹኔታ ነበር፡፡

ኮሚቴው የተረጋገጠ ወይም በቂ ያልኾነ ምላሽ ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸውና ለተካረረ መንሥኤ የኾኑ ዋነኛ ነጥቦች፣ የመጀመሪያው÷ ዕጩ ፓትርያሪኮች የቀረበቡበት መንገድ የምርጫ ሕገ ደንቡ ተሟልቶ ያልተፈጸመበት መኾኑ ነው፤ ሁለተኛው÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይሎች ተጽዕኖ እና ለውስጥ ቡድኖች ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ እኒህን አከራካሪ ነጥቦች በየጊዜው ባወጣናቸው ዘገባዎች እያጋለጠናቸው ቆይተናል፤ እስኵ አሁን ደግሞ በስብሰባው ሂደት ከተንሸራሸሩት ሐሳቦች አንጻር በመጠኑ እንመልከታቸው፡፡

በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ከዋነኛ አነጋጋሪ ነጥቦች አንዱ÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይል ተጽዕኖ እና ለውስጥ ኀይሎች ጥቅማዊ ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ የውጭ ኀይል ሲባል ሌላ ማንም ሳይኾን የመንግሥት ተጽዕኖ ማለታችን ነው፡፡


«በር ድብደባን ያየ፤ እስኪያፈጡበት አይጠብቅም»


ምሁራን ታሪክ ራሱን ይደግማል ይላሉ። አቡነ መርቆሬዎስን የደርግ ጳጳስ በማለትና ከእርስዎ ጋር ከእንግዲህ አብረን ልንሰራ አንችልም ማለቱ የሚነገርለት ኢህአዴግ ዛሬ ደግሞ ያንኑ ታሪክ ደግሞ የኢህአዴግን ፓትርያርክ ለመሾም የቤት ሥራውን ማጠናቀቁን ስናይ ኢህአዴግ ዘመናዊ ደርግ ሆኗል ወይም ደርግ ራሱ ተመልሶ መጥቷል የሚያሰኝ ነው። በአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ምርጫ ላይ የኢህዴግ ድጋፍ መኖሩ ባይካድም እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ግን በፍጹም አልነበረም። በወቅቱ ሥልጣኑን በለቀቁት ፓትርያርክ ላይ ቅሬታና ኩርፊያ የነበራቸው ወገኖች ብዙ ስለነበሩ የአዲስ ፓትርያርክ ፊት ለማየት ተፈልጎ ስለነበር አብዛኛው ሰው ስለአቡነ ጳውሎስ ትምህርት፤ችሎታ፤በደርግ እስር መሰቃየትና የመሳሰለውን የህይወት ታሪካቸውን ከግንዛቤ አስገብቶ ድምጹን የሰጠው ወገን ብዙም ውትወታና ልመና አላስፈለገውም  ነበር። በመንግሥትም በኩል ከፈቃደኝነቱ በዘለለ እንደዘንድሮው ዓይነት ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት ሳያደርግ ምርጫው መጠናቀቁን እናስታውሳለን።  በቀድሞው ዓይን የዛሬውን ስናየው ደርግ የራሱን ፓትርያርክ ሲያስመርጥ ከነበረው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኢህአዴግ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁለተኛው ደርግ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ከሁሉም ነገር ሊገባን ያልቻለው ጉዳይ ኢህአዴግ አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ በመሾም የሚያተርፈው ምንድነው? አቡነ ማትያስስ ፓትርያርክ ስለሆኑ ኢህአዴግን የሚጠቅሙት እንዴት ነው፤ የሚለው ጥያቄ ግልጽ አልሆነልንም።
«አትረፍ ያለው በሬ ቆዳው ከበሮ ይሆናል» እንዲሉ ሆኖ ይመሩታል ከሚባለው የምእመናን ኅብረት ጋር  የመረጥነው አባታችን ተብለው ፍቅርና ክብር ካልተቸራቸው፤ እንዲሁም ርዕሰ መንበር ለሆኑለት ቅዱስ ሲኖዶስ  በኢህአዴግ ፓትርያርክነት ተፈርጀው በረባ ባልረባው አተካሮ በማስተናገድ ሰላምና እረፍት በማጣት  የተነሳ ዘወትር ያለኢህአዴግ ድጋፍ መኖር የማይችሉ የዘመመ ቤት ሆነው እሳቸውን ለመደገፍ በመታገል ጊዜውን ከሚጨርስ በስተቀር ኢህአዴግ ምንም ዓይነት ትርፍ  ከአቡነ ማትያስ አያገኝም። አቡነ ማትያስም ኢህአዴግን በምንም ጉዳይ ደግፈው ሊያቆሙት አይችሉም። ጉዳዩ በኢህአዴግ በኩል እኔ የፈለግሁት ፓትርያርክ ይሁን ከሚልና አቡነ ማትያስም ከምእመናን የምርጫ ድጋፍ ይልቅ የኢህአዴግን ጥሪ እንደመንፈስ ቅዱስ ምርጫ አድርጎ የመቀበል የሥልጣን ጥማት  ውጤት ነው።  በማንኛውም ሚዛን የወረደ የደካሞች አእምሮ የፈጠረው ስሌት ከመሆን ውጪ አይደለም። 

Sunday, February 24, 2013

ደግመን ደጋግመን የምንቃወመው ነገር ዐድማና ዘመቻው ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለግለሰቦች ጥቅም የሚውል በመሆኑ ነው!


የአቡነ ማትያስን ፓትርያርክ መሆን ኅሊና እንዳለው ሰው ምልከታ በራሱ ጉዳት አለው ብለን አስበን አናውቅም። ችግሩ የሚመጣው አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ ለማስደረግ የሚደረገውን ሩጫ ስንመለከትና ሯጮቹን ስንመረምር እጅግ ያሳስበናል፤ ያስፈራናልም። የአቡነ ማትያስን ፓትርያርክነት የሚፈልጉ ቡድኖች ሁለት ስልት ይዘው የሚንቀሳቀሱትን  እነማን መሆናቸውን ስናይ ምርጫውን አጥብቀን ለመቃወም እንገደዳለን። በምርጫ ሚዛን ከአቡነ ሳሙኤል ይልቅ አቡነ ማትያስ የተሻለ ኳሊቲ ሊኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አቡነ ሳሙኤልን የሚጠሉ ቡድኖች በአንድ በኩል የጥቅሞቻችን ጠላት የሚሏቸው አቡነ ሳሙኤልን ለመጣልና በሌላ በኩል የራሳቸውን ጥቅሞች ለማስከበር ሲሉ ለአቡነ ማትያስ መመረጥ ዐመጽና ዘመቻ ውስጥ መግባት ለቤተ ክርስቲያን ከጉዳት በስተቀር ትርፍ ካለማምጣቱም በላይ ተገቢም፤ መንፈሳዊም አይደለም። እንደዚሁ ሁሉ የአቡነ ማቴዎስ መመረጥ በብዙ ሚዛን ቢለካ ፓትርያርክ ለመሆን የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው እናምናለን። ይህን ብቃት ለማግኘት የግድ የቡድንና የዐድማ ዘመቻ ውስጥ መገባት አለበት ብለንም አናስብም። የአቡነ ማቴዎስን ፓትርያርክ መሆን የሚፈልጉ ቡድኖች አቡነ ማቴዎስ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ ፈልገው ሳይሆን በር ከፋችና ዘጊ ሆነው በቤተ ክርስቲያን ጉያ ዐቃቤ ኆኅት አድርገው ራሳቸውን ለመትከል ከመፈለግ የመነጨ በመሆኑ አሁንም እንቃወማለን። የአቡነ ሕዝቅኤልንም ፓትርያርክነት እንዳንቀበል የሚያደርገን ጉልህ ችግር አለ ብለን አስበን አናውቅም። ችግሩ ያለው አቡነ ሕዝቅኤል ፓትርያርክ እንዲሆኑ የሚፈልጉ ወንዘኞች የመራወጣቸው ነገር ነው።  ምንም እንኳን ከሰው ልጅ ጉድለት የመኖሩ ነገር ጠባይዓዊ መሆኑ ባይካድም ከጉድለታቸው ይልቅ ብቃታቸው ያመዝናልና ፓትርያርክ ሆነው ሁሉም መታጨታቸው በራሱ ችግር ላይኖረው ይችላል። ችግሩ የሚነሳው እነሱን ፓትርያርክ ለማድረግ የሚራወጡት ኃይሎችና ቡድኖች እያደረጉት ያለው ጉዞ ነው። የማያውቋት ቤተ ክርስቲያን አሳስቧቸው ሳይሆን በዚህም ይሁን በዚያ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ከታቀደ ዓላማ የመነጨ በመሆኑ ድርጊታቸውን አጥብቀን እንጸየፈዋለን። በሌላ መልኩም ራሳቸው እጩዎቹ እነዚህን ዙሪያቸው ተሰልፈው እናነግስዎታለን ባዮችን በመቃወም ምርጫው በመንፈሳዊ ዓይን ተካሂዶ የሚመጣውን ውጤት በቅንነት ከመጠበቅ ይልቅ ከተሰላፊዎቹ ጋር መቆም ወይም ሰልፉን በዝምታ መቀበላቸው በራሱ ፓትርያርክ የመሆን ብቃታቸውን ያወርደዋል። በዚህም የተነሳ ለፓትርያርክነት የቆሙበትን መንገድ አጥብቀን እንቃወመዋለን።
 በዐድመኞቹና ሰልፈኞቹ የተቀነባበረ መንገድ ለምርጫው ይቀርባሉ የተባሉ የ880 የመራጮች ድምጽ ጥራት እንደሌለው የቻይና እቃ በርካሽ ዋጋ ገዝተው ወይም እጅ ጠምዝዘው ሲያበቁ አስቀድሞ የታወቀውን የራሳቸው ፓትርያርክ በምርጫ አሸንፈዋል ለማለት መዘጋጀት እንኳን እንደ ሃይማኖት ሰዎች ይቅርና ኅሊና እንደፈጠረበት ኢአማኒ ለመቀበል  የሚያስቸግር አሳፋሪም፤ አሳዛኝም  ነገር ነው። አቅማቸው ፈቅዶ ዐድመኞችን ማስተባበር የማይችሉት እነ አቡነ ኤልሳዕ እና አቡነ ዮሴፍ የመሳሰሉት አንድም እንደ ሕጻን ፓትርያርክ ልናደርጋችሁ አጭተናችኋል ብሎ ማታለል ነው፤ አለያም መራጭ እንደሌላቸው በማስላት ለጫወታ ሜዳው ውበት ለመስጠት የተፈለጉ አዳማቂዎች  አድርጎ ማቅረብ ነው። እኛ አጫዋች አንሆንም ብለው ራሳቸውን ቢያገሉ ቢያንስ ለፓትርያርክ መወዳደር ማለት ምን ማለት እንደሆነና ዋጋ እንዳለው ማሳየታቸው ነው፤ ቢበዛም የነጋዴዎቹን የኮንትሮባንድ መንገድ ወደሕግ መስመር እንዲገባ ጫና መፍጠራቸው ስለሆነ ውሳኔአቸውን እናደንቃለን።