ምሁራን ታሪክ ራሱን ይደግማል ይላሉ። አቡነ መርቆሬዎስን የደርግ ጳጳስ በማለትና ከእርስዎ ጋር ከእንግዲህ አብረን ልንሰራ አንችልም ማለቱ የሚነገርለት ኢህአዴግ ዛሬ ደግሞ ያንኑ ታሪክ ደግሞ የኢህአዴግን ፓትርያርክ ለመሾም የቤት ሥራውን ማጠናቀቁን ስናይ ኢህአዴግ ዘመናዊ ደርግ ሆኗል ወይም ደርግ ራሱ ተመልሶ መጥቷል የሚያሰኝ ነው። በአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ምርጫ ላይ የኢህዴግ ድጋፍ መኖሩ ባይካድም እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ግን በፍጹም አልነበረም። በወቅቱ ሥልጣኑን በለቀቁት ፓትርያርክ ላይ ቅሬታና ኩርፊያ የነበራቸው ወገኖች ብዙ ስለነበሩ የአዲስ ፓትርያርክ ፊት ለማየት ተፈልጎ ስለነበር አብዛኛው ሰው ስለአቡነ ጳውሎስ ትምህርት፤ችሎታ፤በደርግ እስር መሰቃየትና የመሳሰለውን የህይወት ታሪካቸውን ከግንዛቤ አስገብቶ ድምጹን የሰጠው ወገን ብዙም ውትወታና ልመና አላስፈለገውም ነበር። በመንግሥትም በኩል ከፈቃደኝነቱ በዘለለ እንደዘንድሮው ዓይነት ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት ሳያደርግ ምርጫው መጠናቀቁን እናስታውሳለን። በቀድሞው ዓይን የዛሬውን ስናየው ደርግ የራሱን ፓትርያርክ ሲያስመርጥ ከነበረው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኢህአዴግ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁለተኛው ደርግ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ከሁሉም ነገር ሊገባን ያልቻለው ጉዳይ ኢህአዴግ አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ በመሾም የሚያተርፈው ምንድነው? አቡነ ማትያስስ ፓትርያርክ ስለሆኑ ኢህአዴግን የሚጠቅሙት እንዴት ነው፤ የሚለው ጥያቄ ግልጽ አልሆነልንም።
«አትረፍ ያለው በሬ ቆዳው ከበሮ ይሆናል» እንዲሉ ሆኖ ይመሩታል ከሚባለው የምእመናን ኅብረት ጋር የመረጥነው አባታችን ተብለው ፍቅርና ክብር ካልተቸራቸው፤ እንዲሁም ርዕሰ መንበር
ለሆኑለት ቅዱስ ሲኖዶስ በኢህአዴግ ፓትርያርክነት ተፈርጀው በረባ
ባልረባው አተካሮ በማስተናገድ ሰላምና እረፍት በማጣት የተነሳ ዘወትር
ያለኢህአዴግ ድጋፍ መኖር የማይችሉ የዘመመ ቤት ሆነው እሳቸውን ለመደገፍ በመታገል ጊዜውን ከሚጨርስ በስተቀር ኢህአዴግ ምንም ዓይነት
ትርፍ ከአቡነ ማትያስ አያገኝም። አቡነ ማትያስም ኢህአዴግን በምንም
ጉዳይ ደግፈው ሊያቆሙት አይችሉም። ጉዳዩ በኢህአዴግ በኩል እኔ የፈለግሁት ፓትርያርክ ይሁን ከሚልና አቡነ ማትያስም ከምእመናን
የምርጫ ድጋፍ ይልቅ የኢህአዴግን ጥሪ እንደመንፈስ ቅዱስ ምርጫ አድርጎ የመቀበል የሥልጣን ጥማት ውጤት ነው። በማንኛውም ሚዛን የወረደ የደካሞች አእምሮ የፈጠረው ስሌት ከመሆን ውጪ አይደለም።