Friday, February 22, 2013

ሰበር ዜና – ለዕጩ ፓትርያርክነት የተመረጡት ሊቃነ ጳጳሳት ታወቁ !!


ከዚህ ቀደም ስንል እንደቆየነው ከብዙ እጩዎች መካከል አምስቱን የመለያው መስፈርት ግልጽ ባለመሆኑ የአስመራጭ ኮሚቴው መልካም ፈቃደኝነት የሚወስነው እንደሚሆን በነበረን ግምት መሠረት ለ6ኛ ፓትርያርክነት የታጩትን አምስት ጳጳሳት አስመራጭ ኮሚቴው ለይቶ ለቋሚ ሲኖዶስ ማቅረቡ ተሰምቷል። በዚህ መካከል ሌላ አዲስ ክስተት እስካልተፈጠረ ድረስ የአባ ሳሙኤልና የአባ ገብርኤል እጩ ሆኖ የመቅረብ ነገር ውድቅ ሆኗል። በእርግጥም የጭለማው ቡድን ተብሎ የሚጠራው ክፍል የትግሉን ድል እያጣጣመ ወደሚገኝበት እርከን ተሸጋግሯል። በሌላ መልኩም ጥላወጊ የሆነው  ያ ክፉ ማኅበርም የስኬት ደረጃውን አሳድጓል ማለት ይቻላል። ከእንግዲህ የሚኖረው ወሳኙ ፍልሚያ በጥላ ወጊው ማኅበርና በጭለማው ቡድን መካከል ይሆናል ማለት ነው። ያ ማለት ደግሞ በሁለት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ወደሚደረግ ውድድር ተሸጋግሯል ማለት ነው። የሰልፉን ብርታት አይተን ግምታችንን ስንወስድ ሌሎቹ እጩዎች ለማሟያነት የቀረቡ ናቸው። ምናልባትም የእነ ኤልያስ አብርሃ ፓርቲ የሆነው የጭለማው ቡድን  ሥልጣንን መከታ አድርጎና ከኋላ የድጋፍ ኃይሉን አስታኮ ያንን ጥላ ወጊ ማኅበር ሊያሸንፍ እንደሚችል አስቀድሞ መገመት ይቻላል። ረጂም እጅ እንደገባም ዘግይቶ የወጡ መረጃዎች ይናገራሉ። በምርጫው ውስጥ የሰዎች ምርጫ እንጂ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር በጭራሽ የለም።

                                                                                                                          

        የእጩዎች የምርጫ ሂደት ሐራ ዘተዋሕዶ እንዲህ ዘግቦታል።

  •     ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል አልተካተቱም
  •     ሁሉም የኮሚቴው አባላት በውሳኔው ስለመስማማታቸው አጠራጣሪ ኾኗል
  •     የፓትርያሪክነት መመዘኛ መስፈርቱ ከዕጩዎች ማንነት ጋራ በአግባቡ ይረጋገጥ
  •     ‹‹ዕጩዎቹን ስታውቅ ፓትርያሪኩን ታውቃቸዋለኽ››› /ሰሞንኛ አባባል/
የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ለዕጩ ፓትርያሪክነት አጣርቶ የለያቸውን አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቋሚ /ሲኖዶሱ ማቅረቡ ተሰማ፡፡ ከየካቲት ዘጠኝ ቀን ጀምሮ የዕጩዎች ልየታ ሲያካሂድ የቆየው አስመራጭ ኮሚቴው÷ ለፓትርያሪክነት ለመመረጥ ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸው የአምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ዝርዝር፡-

1)  ብፁዕ አቡነ ማትያስበኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ

2)  ብፁዕ አቡነ ማቴዎስየወላይታ ዳውሮ /ስብከት ሊቀ ጳጳስ

3)  ብፁዕ አቡነ ዮሴፍየባሌ /ስብከት ሊቀ ጳጳስ

4)  ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልየከፋ ሸካ ቤንች ማጂ /ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ

5)  ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕየሰሜን ጎንደር /ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

«የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው» ፪ኛ ቆሮ ፲፩፤፳፰


 በዘመኑ የግንኙነት መሣሪያ በሆነው መረጃ መረብ ላይ ተቀምጠን ከውድ ጊዜያችን ላይ ቀንሰን የምናካፍለውን መልእክት አንዳንዶች እነሱን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንድናስተላልፍ  ይፈልጋሉ። ገሚሶቹ ደግሞ የሆነ ስውር ዓላማ አንግበን የተሰለፍን  አስመስለው ይስሉናል። አንዳንዶቹም በእግዚአብሔር መንግሥትና አሁን ባለው ምድራዊው የቤተክህነት አስተዳደር መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ያልተረዳን አድርገውም ይገምታሉ። በተለይም የሰሞኑን የፓትርያርክ ምርጫን በተመለከተ የምናወጣቸውን ዘገባዎች የሚያስከፋቸው ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል። በዚህም ይሁን በዚያ የእግዚአብሔር እቅድና ዓላማ እንዳይሆን የሚከለክል ምንም ኃይል እንደሌለ እያመንን የእኛ ዓላማና ፍላጎትም ምን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራና ዘመን  እንዲመጣ ከመፈለግ የመነጨ ትግል ለማድረግ ብቻ እንደተሰለፍን ለሚጠሉንም ሆነ ለሚወዱን ማሳወቅ እንፈልጋለን።
ይህንንም አቋማችን ከሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ተውሰን በአጭር ቃል ስናስቀምጠው ««የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው» ፪ኛ ቆሮ ፲፩፤፳፰ እንዳለው የቤተ ክርስቲያናችን ነገር ብቻ ያሳስበናል።
አንዳንዶችን ቅር የሚያሰኝ፤ ሌሎችን ደግሞ የሚያሳዝን፤ ለገሚሱም ደስታን የሚሰጥ መረጃ ስናወጣ በእኛ በኩል ያለው ስሌት ግን አንድ ሃሳብ ብቻ ነው፤ እሱም የእግዚአብሔር መንግሥት እንዳይስፋፋ መንገድ ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን እየነቀስን በማሳየት ሰው በመረጃና በእውቀት እውነቱን እንዲረዳ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከዓለም ቀደምት ቤተክርስቲያን ተርታ የምትመደብ ቤተክርስቲያን ናት። በእውቀት የበለጸገች፤ በአስተምህሮ የዳበረች፤ በትውፊትና በታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የያዘች መሆኗም ለማንም የሚሰወር አይደለም።  ይሁን እንጂ እንደቀደምትነቷ ወደኋላ እየሄደች፤ በአስተምህሮዋ እየደከመች፤ በአስተዳደሯ እየወደቀች፤ በትውፊቷ እየኮሰመነች፤ በታሪኳ እየተሸፈነች መሄዷ በገሃድ የሚታይ እውነት መሆኑንም መካድ አይቻልም።
በቁጥር 75 የእስልምና ሰዎች መካና መዲናን ለቀው ወደኢትዮጵያ ሲሰደዱ ክርስትና የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሃይማኖት ነበር። መንግሥቱንም፤ ጉልቱንም፤ሕዝቡንም ትቆጣጠር የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ከኋላዋ የመጣው እስልምና አንድም የዐረብ ተወላጅ ሳይኖረው የሸሪአ መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችል ኃይል አለኝ እስከማለት የደረሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ እድገት እንደመሠረቱ ከፍ እያለ መጓዙን ሳይሆን እያቆሽቆለቆለ  የመሄዱ አንዱ ማሳያ ነው ብሎ መጥቀስ ይቻላል። እንደዚሁ ሁሉ ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ብቅ ጥልቅ ይል የነበረው የአውሮፓውያን የወንጌል ሰዎች እንቅስቃሴ በስውር የነበረው ስርጭት ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን ማፍራት የቻለው ይህችው ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ቤተ መንግሥቱን፤ ቤተ ክህነቱንና ሕዝቡን እስከጉልተ ርስቱ  የመቆጣጠር አቅም እያላት መሆኑን አይተን ዛሬ ላይ የደረሰችበትን ደረጃ ስንመረምር ሽቅብ ሳይሆን እያቆለቆለች መጓዟን ቢመረንም የሚታየውን እውነታ መቀበል የግድ ይለናል።
በተለይም ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን የክብር ሥፍራና መንፈሳዊ ኃይል ቀስ በቀስ እያጣች በዝናና በስም ብቻ ወደመኖር የደረሰችው ዘርዓ ያእቆብ የተባለውን ሰው ንጉሥ አድርጋ ከተቀበለች ወዲህ ባሉ ዘመናት ውስጥ ስለመሆኑ፤ እውነት በሀሰት ሰርዶ ተሸፍኖ የሌለ ታሪክ እውነት እንዲመስል ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ታሪክ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ይገኛል።  ዛሬ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ  በአንድ በኩል  ከቅዱሳኖቿ እንደ አንዱ አድርጋ የምትቆጥረው ፤ በሌላ መልኩም በተደለዘው ገድሏ ከሰውነት ተርታ አውጥታ ከውሾች መድባ የምትረግመው ሰማእቱ አባ እስጢፋኖስንና ደቀ መዛሙርቱን እያሳደደች ለ100 ዓመት ባሳረፈችባቸው ሰይፍ የፈሰሰው ደም በዐውደ ምሕረቷ ላይ እየጮኸ እነሆ የሰማይ ክሳት ተለቆባት እየከሳችና እየደከመች በመሄድ ላይ ትገኛለች። የግራኝ ወረራ፤ የድርቡሽ፤ የግብጽ፤ የቱርክ፤ የጣልያን ሰይፍ የወረደው ሳያንስ እርስ በእርስ ስንበላላ ኖረናል።

Thursday, February 21, 2013

መንግሥት የፓትርያርክ ምርጫውን እድል ለ50 ሚሊዮኑ ምእመን ይሰጥ!!

  •       መንግሥት እንደፓርቲ ሹም ራሱ ያስቀምጥበት፤ አለበለዚያም ምእመኑ የፈለገውን እንዲመርጥ ጳጳሳቱን አደብ ያስገዛ!!
  • አሁን በተያዘው መንገድ ሄዶ አንዱ ቢመረጥ፤ መንግሥት የፈገለውን ሾመ መባሉ ወይም በቡድን ዘመቻ የተደረገ ምርጫ መሰኘቱ አይቀርም!!
  • ጳጳሳቱ ወደየ ሀገረ ስብከቶቻቸው ተበትነው ሕዝቡ ራሱ ተወያይቶ ይምረጥ!!
አንዳንዶች የአዲስ አበባውን የፓትርያርክ ምርጫ ከእርቅ በፊት መደረጉን ይቃወማሉ። እንደገና ተመልሰው እነ አቡነ እገሌ ወደምርጫው መግባት አይገባቸውም ነበር ይላሉ። ምርጫውን መቃወም አንድ ነገር ነው። እነ አቡነ እገሌ መመረጥ የለባቸውም ማለት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። « በማንኪያ ሲፋጅ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ» የሚባለው ይሄ ነው።  እንኳን ሰው ዝንጀሮም ቢሾም ከምርጫ በፊት እርቅ ይቅደም ባዮችን አይመለከታቸውም። በምርጫው ላይ እነማን ይታጫሉ ብሎ ወደመከራከር ከተገባ የምርጫውን አስፈላጊነት እንዳመኑ ያስቆጥራልና። አለበለዚያም ቀድሞውኑ እርቅ ይቅደም ማለት የተፈለገው ለማምታት ነበር ማለት ነው። በአጭር ቃል ሲነገር እርቅ ይቅደም ባዮች በሀገር ቤት ውስጥ ያለውን ምርጫ ሙሉ በሙሉ ከመቃወም በስተቀር እነማን ይወዳደራሉ ብሎ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ የለባችሁም።
በሌላ መልኩ ምርጫ መደረግ አለበት ባዮችን የሚያሳስበው ነገር እስከ አሁን ድረስ ከተደረጉ የፓትርያርክ ምርጫዎች ይኽኛው የከፋ ገጽታን የማስተናገዱ ጉዳይ ነው። የአቡነ ሳሙኤል ቡድን በአንድ በኩል፤ የአቡነ ጢሞቴዎስና የመሐመድ ሚስት በሌላ በኩል፤ የማኅበረ ቅዱሳን ቡድን በሦስተኛ ረድፍ፤ የወሎ ማኅበር በዐራተኛ ሰልፍ፤ እንዲሁም ሌሎች በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ቡድኖች ያቺን አንድ ወንበር ለማግኘት ወጥረው ይዘዋል። ገንዘብ ይረጫል፤ ጦርና የጦር ወሬ ይሰበቃል፤ አፋኝና ስለላ ይዋቀራል። ባሎቻቸውን የማስለቀስ የዳበረ ልምድ ያላቸው መበለቶች ቤተ ክህነቱንም ለማስለቀስ ቤት ሽያጭ ድረስ ፉከራ ማሰማታቸው ቤተ ክህነቱ ወደሞት እያዘገመ መሄዱን እንጂ ታታሪ ሰዎች መሰለፋቸውን አያሳይም።
ሐራ ተዋሕዶ እንደዘገበው «በስመ ደኅንነት ያጭበረበሩ 40 ግለሰቦች ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፤ እነንቡረ እድ ኤልያስ የመራጮች ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጫና እየፈጠሩ ነው። ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እየተደረገ በሚገኘው ቅድመ ዝግጅት፣ የየራሳቸውንምርጥይዘው የቡድን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አካላትን ያስተባብራሉ ለተባሉ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መንግሥት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተሰማ፡፡ ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ በማለት አስንብቦናል።
እንግዲህ ቀደም ሲል እንደቆየው ሁሉ ዛሬ ሁከቱና እሳቱ ተባብሶ ቤተ ክህነት ግቢ እየነደደ ለመሆኑ ማሳያ ነው።ጥንቱንም ቢሆን የቡድን ዘመቻ  እጅ ያልተለየው ቤተ ክህነት፤ ከምርጫ ቦርድ እውቅና በሌለው የጳጳሳት ፓርቲ እየታመሰ መገኘቱ አስገራሚም፤ አሳዛኝም ነው።  ጥቅመኞችና ሥልጣን ፈላጊዎች አባ ሳሙኤልን ይላሉ። ሌቦችና ማጅራት መቺዎች የቤተ ክህነት ችግር በረጂም ጢም የሚፈታ ይመስል አባ ማትያስን ይላሉ፤ አድባዮችና ወላዋዮች ዘክልዔ ልብ አባ ገብርኤልን ይላሉ። ዘረኞችና ነገር ጠምጣሚዎች አባ ማቴዎስን ይላሉ። መንታ መንገድ ላይ የቆሙ አስመሳዮች ደግሞ አባ ሉቃስ ይሁኑልን ይላሉ። ከሥር ደግሞ ፍልፈሎች፤ አይጦችና ወሮበሎች የየድርሻቸውን ሲጥ ሲጥ ይላሉ። ቤተ ክህነት በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተከባለች። «ከነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ» የሚባለው ለዚህ አይደል? እየታየ ያለው የሰዎቹ ግብር፤ ማንነታቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው።