- መንግሥት እንደፓርቲ ሹም ራሱ ያስቀምጥበት፤ አለበለዚያም ምእመኑ የፈለገውን እንዲመርጥ ጳጳሳቱን አደብ ያስገዛ!!
- አሁን በተያዘው መንገድ ሄዶ አንዱ ቢመረጥ፤ መንግሥት የፈገለውን ሾመ መባሉ ወይም በቡድን ዘመቻ የተደረገ ምርጫ መሰኘቱ አይቀርም!!
- ጳጳሳቱ ወደየ ሀገረ ስብከቶቻቸው ተበትነው ሕዝቡ ራሱ ተወያይቶ ይምረጥ!!
አንዳንዶች የአዲስ አበባውን የፓትርያርክ ምርጫ ከእርቅ በፊት መደረጉን ይቃወማሉ። እንደገና ተመልሰው እነ አቡነ እገሌ ወደምርጫው መግባት አይገባቸውም ነበር ይላሉ። ምርጫውን መቃወም አንድ ነገር ነው። እነ አቡነ እገሌ መመረጥ የለባቸውም ማለት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። « በማንኪያ ሲፋጅ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ» የሚባለው ይሄ ነው።
እንኳን ሰው ዝንጀሮም ቢሾም ከምርጫ በፊት እርቅ ይቅደም ባዮችን አይመለከታቸውም። በምርጫው ላይ እነማን ይታጫሉ ብሎ ወደመከራከር ከተገባ የምርጫውን አስፈላጊነት እንዳመኑ ያስቆጥራልና። አለበለዚያም ቀድሞውኑ እርቅ ይቅደም ማለት የተፈለገው ለማምታት ነበር ማለት ነው። በአጭር ቃል ሲነገር እርቅ ይቅደም ባዮች በሀገር ቤት ውስጥ ያለውን ምርጫ ሙሉ በሙሉ ከመቃወም በስተቀር እነማን ይወዳደራሉ ብሎ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ የለባችሁም።
በሌላ መልኩ ምርጫ መደረግ አለበት ባዮችን የሚያሳስበው ነገር እስከ አሁን ድረስ ከተደረጉ የፓትርያርክ ምርጫዎች ይኽኛው የከፋ ገጽታን የማስተናገዱ ጉዳይ ነው። የአቡነ ሳሙኤል ቡድን በአንድ በኩል፤ የአቡነ ጢሞቴዎስና የመሐመድ ሚስት በሌላ በኩል፤ የማኅበረ ቅዱሳን ቡድን በሦስተኛ ረድፍ፤ የወሎ ማኅበር በዐራተኛ ሰልፍ፤ እንዲሁም ሌሎች በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ቡድኖች ያቺን አንድ ወንበር ለማግኘት ወጥረው ይዘዋል። ገንዘብ ይረጫል፤ ጦርና የጦር ወሬ ይሰበቃል፤ አፋኝና ስለላ ይዋቀራል። ባሎቻቸውን የማስለቀስ የዳበረ ልምድ ያላቸው መበለቶች ቤተ ክህነቱንም ለማስለቀስ ቤት ሽያጭ ድረስ ፉከራ ማሰማታቸው ቤተ ክህነቱ ወደሞት እያዘገመ መሄዱን እንጂ ታታሪ ሰዎች መሰለፋቸውን አያሳይም።
ሐራ ተዋሕዶ እንደዘገበው «በስመ ደኅንነት ያጭበረበሩ 40 ግለሰቦች ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፤ እነንቡረ እድ ኤልያስ የመራጮች ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጫና እየፈጠሩ ነው። ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እየተደረገ በሚገኘው ቅድመ ዝግጅት፣ የየራሳቸውን ‹ምርጥ› ይዘው የቡድን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አካላትን ያስተባብራሉ ለተባሉ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መንግሥት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተሰማ፡፡ ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ በማለት አስንብቦናል።
እንግዲህ ቀደም ሲል እንደቆየው ሁሉ ዛሬ ሁከቱና እሳቱ ተባብሶ ቤተ ክህነት ግቢ እየነደደ ለመሆኑ ማሳያ ነው።ጥንቱንም ቢሆን የቡድን ዘመቻ
እጅ ያልተለየው ቤተ ክህነት፤ ከምርጫ ቦርድ እውቅና በሌለው የጳጳሳት ፓርቲ እየታመሰ መገኘቱ አስገራሚም፤ አሳዛኝም ነው።
ጥቅመኞችና ሥልጣን ፈላጊዎች አባ ሳሙኤልን ይላሉ። ሌቦችና ማጅራት መቺዎች የቤተ ክህነት ችግር በረጂም ጢም የሚፈታ ይመስል አባ ማትያስን ይላሉ፤ አድባዮችና ወላዋዮች ዘክልዔ ልብ አባ ገብርኤልን ይላሉ። ዘረኞችና ነገር ጠምጣሚዎች አባ ማቴዎስን ይላሉ። መንታ መንገድ ላይ የቆሙ አስመሳዮች ደግሞ አባ ሉቃስ ይሁኑልን ይላሉ። ከሥር ደግሞ ፍልፈሎች፤ አይጦችና ወሮበሎች የየድርሻቸውን ሲጥ ሲጥ ይላሉ። ቤተ ክህነት በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተከባለች። «ከነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ» የሚባለው ለዚህ አይደል? እየታየ ያለው የሰዎቹ ግብር፤ ማንነታቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው።