Wednesday, February 20, 2013

የኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያንን አንድ ሊያደርግ የሚችል የመፍትሄ ሃሳብ!

                                                                         ግርማ ካሳ   
     muziky68@yahoo.com
     የካቲት 12 2015 .

«በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ! »

የአቡነ ጳዉሎስን ሕልፈት ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ የተፈጠረዉን መከፋፈል ለማስቀረት፣ በመንፈሳዊ አባቶች መካከል፣ የሰላምና የእርቅ ዉይይቶች ተደርገዋል። ለሃያ አመታት የዘለቀዉ፣ ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የወረደው የመከፋፈል እርግማን ተወግዶ፣ ቤተ ክርስቲያኒቷ አንድ ሆና፣ «ሂዱና አሕዛብን እያስተማራችሁ፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅድስ ስም እያጠመቃችሁ፣ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸዉ» የሚለዉና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠዉ፣ ታላቅ ተልእኮን መፈጸም ትችል ዘንድ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየአብያተ ከርስቲያናቱ፣ በየጸሎት ቤቱ በየገዳማቱ ሲጾምና ሲጸል ነበር።
ነገር ግን ከተጠበቀዉና ከተገመተዉ ዉጭ አስደንጋጭና አሳዛኝ መግለጫዎችን አነበብን። የክርስቶስ መድሃኔአለም ስም ተሰደበ። የዲያብሎስ ስም ገነነ። የትህትሃ የፍቅር እራስን የማዋረድ ክርስቲያናዊ መንፈስ ጠፋ። የእልህ የስደብ የመወጋገዛና የትእቢት መንፈስ ሰፈነ።
በአገር ደረጃ ካያን የከተማ፣ የክልል የፌደራል መንግስት ሕጎች ይኖራሉ። ነገር ግን ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነ ሕገ-መንግስት የሚባል ሕግ አለ። ፈረንጆች “The Supreme Law of the Land” ይሉታል።
ቤተ ክርስቲያንም የምትተዳደርበት ሕገ ደንብ ወይንም ቀኖና አላት። ካህናት ገዳማት፣ የሰንበት አስተማሪዎች ወዘተረፈ የሚታዳደሩበት ስርዓት/ሕግ/ቀኖና አለ። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሕጎችና ቀኖናዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መመሪያ የሆነዉን፣ የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የሚያግዙ እንጂ፣ የሚተኩ አይደለም። ወንጌል ከሁሉም በላይ ነዉ። ለዚህም ነዉ በቅዳሴ ወቅት ወንጌልን ቄሱ በሚያነቡበት ወቅት፣ ምእመኑ በአክብሮትና በፍርሃት ቆሞ የሚያዳምጠው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶችን እያጨቃጨቀ ያለ አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ የቀኖና መጽሃፍ የተጠቀሱ፣ ፓትሪያርክ እንዴት እንደሚሾምና እንደሚተካካ የሚገልጹ አንዳንድ አንቀጾች ናቸዉ። በዶክትሪን ወይንም በሃይማኖት ጉዳዮች አልተለያዩም። በአስተምህሮ አልተለያዩም። ልዩነታቸው፣ ቅንነትና ትህትና የተሞላ ልብ ካለ፣ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል፣ የአሰራርና ማን መሪ መሆን አለበት የሚለዉ ላይ ነዉ።

አራተኛዉ የቤተ ክርስቲያኒቷ ፓትሪያርክ በሕይወት እያሉ አምስተኛ ፓትሪያርክ ይሾማሉ። «አምስተኛዉ ፓትሪያርክ የተሾሙት አራተኛዉ ፓትሪያርክ በፍቃዳቸው ሃላፊነታቸዉን ስለለቀቁ ነዉ» ያላሉ አንዳንዶች። ሌሎች ደግሞ «አይደለም በአቶ ታምራት ላይኔ ተገደው ነዉ» ሲሉ በፓትሪያርኩ ላይ ተደረገ የሚሉትን ግፍ በምሬት ይገልጻሉ። ይሄ እንግዲህ ከሃያ አመት በፊት የሆነ ነገር ነዉ። ጠባሳዉ ግን ለሃያ አመታት ይኸዉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት አደረሰ። ቤተ ክርስቲያኒቷ ተከፈለች። ለሃያ አመታት ጠብ ነገሰ። ተፋቅረን ተያይዘን በአንድ ላይ ወንጌልን ማስፋፋት የሚገባን ክርስቲያኖችን፣ ከፋፍሎና አጣልቶ ሆድና ጀርባ አደረገን።
እንግዲህ አስቡት፣ የመጽሃፍት ሁሉ የበላይ፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነዉ ወንጌልን ያካተተዉ መጽሃፍ ቅዱስ ነዉ። መጽሃፍ ቅዱስ የሚያዘው ፍቅርን፣ ይቅር መባባልን፣ አንድነትን፣ ትህትና የመሳሰሉትን ነዉ። የቀኖናዎች ሁሉ የበላይ ከሆነዉ፣ ከማያልፈዉና ከማያረጀዉ ሕያዉ የእግዚአብሄር ቃል ዉስጥ «እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ የኔ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን ሌሎች ያዉቃሉ» « እራስህን ከሌላ የተሻለ አድርገህ አትቁጠር» «አንተ የሌላዉን ጉዳፍ ለማወጣት የምትቸኩል በአይን ያለዉ ያለዉን ትልቅ ምሰሶ መጀመሪያ ተመልከት» ‹‹በመጀመሪያ መባህን በመሰዊያው ላይ ትተህ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ›› «ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ወፍጮ ባንገቱ ታስሮ ባህር ዉስጥ ቢወረወር ይቀለዋል» «ሌላዉን የሚያሰናክል ከሆነ ስጋ ባልበላ ለዘላለም ልቀር» «እኔ መምህር ጌታ ሆኜ ይሄን ካደረኩ ( የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ) እናንተም እንዲሁ አደርጉ» የመሳሰሉትን ትእዛዛት እናነባለን።
የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ በኩል ለክርስቲያናዊ ሕግና ቀኖ ቆመናል እያልን፣ በሌላ በኩል ከቤተ ከርስቲያን ሕግና ቀኖና በላይ የሆነዉን የጌታ ክርስቶስን ትእዛዝ ወደ ጎን እያደረገን፣ ያለ ይመስለኛል። ቀኖና፣ ወንጌልንም መደገፍ እንጂ ከወንጌል በተቃራኒ መቆም እንደሌለበት የዘነጋን ይመስለኛል። ዋናዉን ረስተን ትንሹ ነገር ላይ ስናከር ነው የሚታየዉ።
እንግዲህ «ንስሐ እንግባ ክርስትናችንን የክርስቶስ ተከታይና አገልጋይነታችንን፣ በምንለብሰው ካባ ሳይሆን በስራችን አናሳይ» እላለሁኝ። ከወንድሞቻችን ጋር መስማማት አቅቶን፣ ይቅር መባባል ከብዶን፣ «እኔ ነኝ ፓትሪያርክ መሆን ያለብኝእርሱ ነዉ መሆን ያለበት ..» እየታባባልን፣ በእልህ መንፈስ ተሞልተን፣ በአኮቴተ ቁርባን ወቅት ስጋ ወደሙን በእጃቸችን ለመያዝ መቆማችን መቅሰፍት ነዉ» እላለሁ።

Tuesday, February 19, 2013

ስለ መንበረ ፕትርክናው ዕጩዎች የቅድመ ምርጫ ግምት


   source: Haratewahido.wordpress.com
ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም ረቡዕ አዲስ አበባ ይገባሉ

ኀምሳ አራት ዓመት ወደ ኋላ፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያሪክ ለኢትዮጵያ የተገኘው ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ዕጨጌ ወጳጳስ ሰኔ 21 ቀን 1951 . 116ኛው የእስክንድርያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ በተቀቡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው ለከፍተኛው ማዕርግ በበቁበት የፓትርያሪክነት ሢመታቸው ወቅት እዚያው ግብጽ ካይሮ ይገኙ በነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፊት ካሰሙት ታሪካዊ ንግግር መካከል÷ ‹‹ወደዚህ ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ለመድረስ ሲፈቀድልኝ ለግርማዊነትዎ ያለኝን የታማኝነት ቃል ኪዳን በፊትዎ ቆሜ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ምክንያት አግኝቻለኹ፤›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ 1951 – 62 . በፓትርያሪክነት ሲያገለግሉ ቆይተው በተወለዱ 73 ዓመታቸው ጥቅምት 2 ቀን 1962 . በደብረ ሊባኖስ ተቀብረዋል፡፡ ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ፓትርያሪክ እየተመራች ኤጲስ ቆጶሳትን ትሾማለች፡፡ 


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ካረፉና መዋዕለ ሐዘኑ በመላ ኢትዮጵያ ለአርባ ቀናት ከተፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የመጀመሪያውን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሁለተኛውን ፓትርያሪክ ለመሾም መጋቢት 29 ቀን 1963 . ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት ቀረቡ፡፡ የሦስቱ አባቶች ስም ዝርዝር ከመጋቢት 26 – 29 ቀን 1963 . በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ተቀምጦ ጸሎተ ቅዳሴ ሲደረግበት ቆይቶ መጋቢት 29 ቀን በመንበረ ፓትርያሪኩ በተደረገው ምርጫ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደራሴና የሐረርጌ /ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከፍተኛውን ድምፅ ማለትም 80 በመቶ አግኝተው ተመርጠዋል፡፡ ምርጫው ለንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡

በፍጥነት ወደፊትጥር 6 ቀን 2005 .ም፤ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ በዳላስ ቴክሳስ ስለተደረገው ሦስተኛው ዙር ጉባኤ አበው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት ለማዳመጥ፣ በቀጣይነት በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ስለታቀደው አራተኛው ዙር ጉባኤ አበው ለመወሰን በተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጠረጴዛ ‹‹ከፓትርያሪክ ሹመት በፊት ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ አባቶች በብዛትም በአቋምም የበላይነቱን ይዘው ጠንክረው እየወጡ ነው፡፡ ከስብሰባው መካከል በሹልክታ የወጡ አንድ አባት ‹‹አግዙን እንጂ›› ሲሉ እንዳስተላለፉት በተዘገበው የስልክ ጥሪ፣ በዚያው ዕለት ቀንና ምሽት ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠንክረው ሲከራከሩ በዋሉ አባቶች ላይ በተለያዩ መንገዶች ርብርብ ተደረገ፡፡

በስብሰባው መጀመሪያው ላይ ጠንክረው የተሰሙ የዕርቀ ሰላሙ ይቅደም ድምፆች በቀጣዩ ቀን ስብሰባ ላይ ጸጥ ረጭ አሉ፤ ‹‹በስብሰባችን በአካል የተገኘ ባለሥልጣን አልነበረም፤ ቀደም ሲናገሩ የነበሩ አባቶች በሁለተኛው ቀን አስቀድመው ዝም ሲሉ ግን መንግሥት በአንዳች መንገድ ሰተት ብሎ እንደገባበት ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፡፡ በዚህ ኹኔታ ታኅሣሥ 10 ቀን አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም የተጀመረው የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዝግጅት እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ጥር 30 ቀን 2005 . ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት÷ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የካቲት 21 ቀን 2005 . ይካሄዳል፤ በዓለ ሢመቱም የካቲት 24 ቀን 2005 . በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ ከምርጫው ቀን ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚያሳልፈው ውሳኔ ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙ አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 . ለሕዝቡ በይፋ ይገለጻሉ፡፡