source: Haratewahido.wordpress.com
ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም ረቡዕ አዲስ አበባ ይገባሉ
ኀምሳ አራት ዓመት ወደ ኋላ፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያሪክ ለኢትዮጵያ የተገኘው ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ዕጨጌ ወጳጳስ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም በ116ኛው የእስክንድርያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ በተቀቡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው ለከፍተኛው ማዕርግ በበቁበት የፓትርያሪክነት ሢመታቸው ወቅት እዚያው ግብጽ ካይሮ ይገኙ በነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፊት ካሰሙት ታሪካዊ ንግግር መካከል÷ ‹‹ወደዚህ ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ለመድረስ ሲፈቀድልኝ ለግርማዊነትዎ ያለኝን የታማኝነት ቃል ኪዳን በፊትዎ ቆሜ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ምክንያት አግኝቻለኹ፤›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከ1951 – 62 ዓ.ም በፓትርያሪክነት ሲያገለግሉ ቆይተው በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ጥቅምት 2 ቀን 1962 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ተቀብረዋል፡፡ ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ፓትርያሪክ እየተመራች ኤጲስ ቆጶሳትን ትሾማለች፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ካረፉና መዋዕለ ሐዘኑ በመላ ኢትዮጵያ ለአርባ ቀናት ከተፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የመጀመሪያውን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሁለተኛውን ፓትርያሪክ ለመሾም መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት ቀረቡ፡፡ የሦስቱ አባቶች ስም ዝርዝር ከመጋቢት 26 – 29 ቀን 1963 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ተቀምጦ ጸሎተ ቅዳሴ ሲደረግበት ቆይቶ መጋቢት 29 ቀን በመንበረ ፓትርያሪኩ በተደረገው ምርጫ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደራሴና የሐረርጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከፍተኛውን ድምፅ ማለትም 80 በመቶ አግኝተው ተመርጠዋል፡፡ ምርጫው ለንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡
በፍጥነት ወደፊት – ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም፤ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ በዳላስ ቴክሳስ ስለተደረገው ሦስተኛው ዙር ጉባኤ አበው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት ለማዳመጥ፣ በቀጣይነት በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ስለታቀደው አራተኛው ዙር ጉባኤ አበው ለመወሰን በተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጠረጴዛ ‹‹ከፓትርያሪክ ሹመት በፊት ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ አባቶች በብዛትም በአቋምም የበላይነቱን ይዘው ጠንክረው እየወጡ ነው፡፡ ከስብሰባው መካከል በሹልክታ የወጡ አንድ አባት ‹‹አግዙን እንጂ›› ሲሉ እንዳስተላለፉት በተዘገበው የስልክ ጥሪ፣ በዚያው ዕለት ቀንና ምሽት ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠንክረው ሲከራከሩ በዋሉ አባቶች ላይ በተለያዩ መንገዶች ርብርብ ተደረገ፡፡
በስብሰባው መጀመሪያው ላይ ጠንክረው የተሰሙ የዕርቀ ሰላሙ ይቅደም ድምፆች በቀጣዩ ቀን ስብሰባ ላይ ጸጥ ረጭ አሉ፤ ‹‹በስብሰባችን በአካል የተገኘ ባለሥልጣን አልነበረም፤ ቀደም ሲናገሩ የነበሩ አባቶች በሁለተኛው ቀን አስቀድመው ዝም ሲሉ ግን መንግሥት በአንዳች መንገድ ሰተት ብሎ እንደገባበት ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፡፡ በዚህ ኹኔታ ታኅሣሥ 10 ቀን አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም የተጀመረው የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዝግጅት እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡
የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት÷ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ይካሄዳል፤ በዓለ ሢመቱም የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ ከምርጫው ቀን ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚያሳልፈው ውሳኔ ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙ አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝቡ በይፋ ይገለጻሉ፡፡