Sunday, February 17, 2013

የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ያለው የት ነው?



የ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ እርግጥ መሆኑ ከተነገረበት በፊት አንስቶ ብዙ ተወርቷል፣ ብዙም ተብሏል። ግማሹ ከምርጫው ይልቅ እርቁ ይቅደም ይል ነበር። ገሚሱም በተለይ ከሀገር ቤት እርቅ ማለት አንድ ማኅበር፤ አንድ መንጋ ማለት እንጂ ያረጀ ስልጣን ማደስ አይደለም ማለቱም አይዘነጋም። ከምርጫው ይልቅ እርቁ ይቅደም ከሚለው ወገን የሚመጣው ሃሳብ አብዛኛው በቅንነትና ለቤተክርስቲያን አንድነት ከማሰብ ልባዊ ስሜት እንደሆነ ይገመታል። አንዳንዱም እርቅ የሚለው ነገር ከግቡ እንደማይደርስ እያወቀ ወይም ስውር ዓላማውን ከኋላው አድርጎ ሐቀኛ መስሎ ለመታየት የሚያደርገው ጫወታም እንደሆነ ካለፉት እንቅስቃሴዎች ተነስቶ ግምት ማስቀመጥ ይቻላል። በዚህም ይሁን በዚያ እርቅ የተባለውን ነገር ገቢር ለማድረግ ከስሜትና ከቅናት በፊት ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ብዙ ሥረ ነገሮች መኖራቸውን አለመረዳት ቅን ሃሳቦች ሁሉ ትክክለኞች ቢሆኑ እንኳን  አፈጻጸማቸውን አርቆ መመልከት አለመቻል በራሱ ችግር ነው። እንደምንሰማው የውጪው ሲኖዶስ መፈንቅለ ፓትርያርክ ያደረገው ወያኔ ነው እያለ ወያኔ በሚመራው ሀገር እንዴት ሆኖ ነው ተመልሶ ፓትርያርክ መሆን የሚችለው ለሚለው ግዙፍ ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ይመስለኛል። የውጪው ሲኖዶስ መፈንቅለ ፓትርያርክ አድርጎብኛል ካለው መንግሥት ጋር የእርቅ ድርድር ያደርጋል ወይስ መንግሥት ጥፋቱን አምኖ እንዲመለሱ በመፍቀድ ዋስትና ይሰጣል? ብለንም ተጨማሪ ጥያቄ ለማቅረብ እንገደዳለን።
    የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ብቻውን ፈነቀለኝ ባሉት መንግሥት ሀገር ለመመለስ የሚያስችል አዲስ ግኝት ነው ወይ? እርቅ ለም? ከማን ጋር? እንዴት? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኝ እየተጠራሩ መነጋገር ብቻውን መፍትሄ እንደማይሆንና ከሚጠየቁት ነጥቦች አንጻር መሳካት አለመቻሉን አስቀድመን በመገመት  በዚህ ዙሪያ ጽፈንበት ነበር። ወደፊትም የውጪ ሲኖዶስ ሳይሆን  የውጪ ጳጳሳት ተብሎ ወደሀገር ቤት ተመልሶ ባለው አንድ ሲኖዶስ ስር ከሚኖሩ በስተቀር እንደአቻ ሲኖዶስ የሚደረግ ድርድር ሊኖር እንደማይችል ከመጻዒ አመለካከቶች አንጻር አስቀድሞ መተንበይ ይቻላል።  የሚነሳው እውነታ ሲኖዶስ ያለው የት ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። እልህና ቁጣ በሚፈጥረው ስሜት እስካልተመራን ድረስ  የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ያለው አዲስ አበባ ነው። ኢትዮጵያውያን አሜሪካ በመኖራቸው ብቻ አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ ልትባል አትችልም።
     ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት አንባ ገነን ይሁን ዲሞክራሲያዊ ሀገሪቱ ከዓለም ካርታ ላይ እስካልጠፋች ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ይባላል። ሲኖዶሱም መንግሥት ባለበት ሀገር የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ይባላል። እውነታውን ለመቀበል ባንፈልገውም እንኳን አለመቀበላችን እውነታውን አይለውጠውም። አንዳንዶች ታሪክ እያጣቀሱ ስለስደት ሲኖዶስ ስነሞገት ለመግጠም ይዳዳሉ።
 ከ50 ሚሊዮን በላይ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናንን የሚመራው ማነው? ብንል ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚናገረው በሀገረ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖዶስ መሆኑን ነው።

Friday, February 15, 2013

የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው ማምሻውን መግለጫ አወጣ




ኮሚቴው ከሳምንት በፊት በሰጠው ይፋዊ መግለጫ መሠረት ለፓትርያርክነት እጩ ሆነው የሚቀርቡትን አባቶች  ጥቆማ ከተለያየ አቅጣጫ እየቀረበለት መቆየቱን በማውሳት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅማትን መንፈሳዊ አባት እንዲሰጣት የጾምና የጸሎት ጊዜውን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል በማለት ለመላው የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች በመግለጫው ላይ በድጋሚ አበክሮ አሳስቧል።
በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዛሬ የካቲት 8/ 2005 / የእጩ ተጠቋሚዎች የመቀበያ ጊዜ ማብቃቱን በመግለጽ ከእንግዲህ የሚቀረው ሥራ  ሲኖዶሱ በሰጠው ደንብ ላይ ተመርኩዞ ከየካቲት 9 እስከ 14 2005 / ድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የሚቀርቡ 5 እጩዎችን መመልመል መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ይቀርባሉ ከተባለው ብዙ ተጠቋሚዎች መካከል ውስጥ እንዴትና በምን ስሌት መልምሎ 5ቱን እጩ ተጠቋሚዎች ብቻ እንደሚያቀርብ ኮሚቴው የዘረዘረው ነገር ባይኖርም መርጦ ለሲኖዶስ የማቅረብ ስልጣኑ የኮሚቴው መሆኑን ግን ሳይገልጽ አላለፈም።
የኮሚቴውን የምልምላ ስልት ያሟላሉ የተባሉ 5 እጩዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ ሲኖዶሱ ከየካቲት 16 ጀምሮ በሚያደርገው ጉባዔ ላይ የቀረቡለትን የእጩ ፓትርያርኮች  ዝርዝር  በይሁንታ በማጽደቅ፤ የካቲት 18/ 2005 / ለሕዝብ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ምርጫውም የካቲት 21 ቀን እንደሚደረግና በእለቱ ማምሻው ላይ የድምጽ ብልጫ ያገኘው አባት በይፋ ተገልጾ የካቲት 24/ 2005 / ሥርዓተ ሲመቱ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም  ከዚህ በፊት የተገለጸ መሆኑ ይታወሳል። ብዙ ጊዜ ሲባል እንደቆየው የመንግሥት ጫና አለ የሚባለው ነገር እስካሁን በኮሚቴው ላይ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
የአስመራጭ ኮሚቴውን የዛሬውን መግለጫ ለማንበብ (እዚህ ላይ ይጫኑ )
 
እግዚአብሔር የወደደውንና የፈቀደውን ያድርግ!

የቤተክህነቱ የጭለማው ቡድን እየተባለ የሚጠራው ክፍል በፓትርያርክ ምርጫ ላይ እየሰራ መገኘቱ ታወቀ!

 ዘሐበሻ የድረ ገጽ ጋዜጣ የቀጣዩ ፓትርያርክ እጩዎች
/ አባ ሳሙኤል ፪/ አባ ገብርኤል ፫/ አባ ሉቃስ ፬/ አባ ማቴዎስ ፭/ አባ ዮሴፍ ናቸው ሲል የደረሰውን መረጃ በመጥቀስ ዝርዝሩን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ የአባ ሳሙኤል 6ኛ ፓትርያርክነት አይቀሬ መሆኑን ተናግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኃይለ ኢየሱስ የተባለ ተሳታፊ ስለጨለማው ቡድን የሚነግረን ስላለው ጽሁፉን አቅርበነዋል።
ኃይለ ኢየሱስ አምኃ ከአራት ኪሎ



ከዚህ በፊት በቤተክህነቱ ግቢ ውስጥ ሊቃነ ጳጳሳቱን በመደብደብና በማስደብደብ ወንጀል ሰፊ ልምድ ያለው የቤተክህነቱ የጭለማው ቡድን እየተባለ የሚጠራው አካል የቆየበትን የተሰሚነትና የኃይል ሥፍራ ላለመልቀቅ ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚመቸውን ሊቀጳጳስ ወደ ወደፓትርያርክነት ሥልጣን ለማምጣት ሌሊትና ቀን እየሰራ እንደሚገኝ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።

ጠላትና ባላጋራ ይላቸው ከነበሩት ከአቡነ ጢሞቴዎስ ጋር በምን ምክንያትና ሰበብ ለመስማማት እንደቻለ ባይታወቅም ይህ የጭለማው ቡድን ከሟቹ ፓትርያርክ ጋር ሰፊ ውዝግብ ውስጥ የነበሩትን አባ ጢሞቴዎስን ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑም ተገልጿል። እነዚህ እርስ በእርሳቸው ይናጩ የነበሩት ሁለት ተጻራሪ ኃይሎች ዛሬ ድንገት ሰምና ፈትል ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው አይታወቅም። ይሁን እንጂ  የቤተክርስቲያኒቱ ችግር ስላንገበገባቸው እንዳልሆነና በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደመዥገር ተጣብቀው ሲመጠምጡ የቆዩት የንዋይና የሥልጣን ብልግና ዘመናቸው ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ማብቂያቸው እንዳይሆን የሚያደርጉት  ትግል መሆኑን  ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች እየተናገሩ ነው።  ወይዘሮ ማንትስ በመባል የምትጠራውና ቤተክህነቱን ስታተራምስ የቆየችው ባል አልቦ ሴትዮ በዙሪያው ላይ የተጠናከረ ዘመቻ እያደረገች ሲሆን ረዳቶችዋም «የመጠጥ ቤት በር ዝጉ» በማለት ልምድ ያላቸው የሰካራሞች ማኅበር አባላትም በትወናው ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

አፈትልከው የወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጭለማው ቡድኖች ለፓትርያርክነት አጭተው ለማቅረብ የፈለጉት አባት ከእነዚህ ግብረ በላ ቡድን ጋር የሃሳብ፤ የዓላማና የግብ ዝምድና ምንም የሌላቸው መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን አባት ለማሾም መሯሯጥ ያስፈለገበት ምክንያት  «ከበጣም ክፉ፤ ክፉ ይሻላል» ከሚል እሳቤ የተነሳ እንደሆነም ምክንያታዊነቱን የገመገሙ ሰዎች ይናገራሉ።  

 በአንድ ወቅት በእነ አቡነ ቄርሎስ ላይ ቤተክህነቱን የባድሜ ጦርነት አድርጎ የቆየው የጭለማው ቡድንና  የአቡነ ሳሙኤል ድጋፍ ሰጪ አካል በዚህ የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የመጨረሻ እልባት  እንደሚያገኝ ከግምት በላይ እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክተው ነገር የቅድስት ሥላሴ ኰሌጅ ደቀመዛሙርት  ለእጩ ፓትርያርክነት አቡነ ሳሙኤልን በማቅረባቸው ነው።

 ይህም በጭለማው ቡድን ላይ የፈጠረው ድንጋጤና ፍርሃት ጦርነቱን የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል።