Monday, February 4, 2013

የሚበልጠውን ይዘናል!!

 ከዲ/ን አሸናፊ መኰንን «የኑሮ መድኅን» መጽሐፍ ገጽ 32 ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ

ዲዮጋን የተባለ የግሪክ ፈላስፋ ኑሮው ጎርፍ በሸረሸረው ፈፋ ውስጥ ነበር። ንብረቱም አንዲት መንቀል /የውሃ መጠጫ ቅል/ ስትሆን አንዲት ውሻም ጓደኛው ነበረች። ታላቁ እስክንድር ዓለምን አስገብሮ ሲመለስ ዲዮጋን የተባለውን ፈላስፋ ማየት አለብህ ስላሉት ሊያየው መጣ። ዲዮጋን ግን ከቤቱ አጠገብ በጀርባው ተኝቶ ፀሐይ ይሞቅ ነበር። ታላቁ እስክንድር አጠገቡ መጥቶ ቢቆም ስንኳ ዲዮጋን ማነው? ብሎ ዓይኑን አልገለጠም። እስክንድርም፤ ዲዮጋን ሆይ፦ ተነስ! እኔ ታላቁ እስክንድር ነኝ። ዓለሙን ሁሉ አስገብሬ ተመልሻለሁ፤ የምትሻውን ለምነኝ፤ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሃለሁ» አለው። ዲዮጋን ግን ዓይኑን እንደከደነ «ይልቅስ አንተ ልትሰጠኝ የማትችለውን ፀሐይ እንዳልሞቅ አትከልክለኝ» አለው ይባላል። ንጉሥ እንኳን የማይሰጠውን ብዙ ስጦታ ስለተቀበልን እግዚአብሔር ይመስገን!
  ሰውዬው  «እግር የሌለውን ሰው እስካይ ድረስ ጫማ ስላልነበረኝ አዝን ነበር» ብሏል። ሰውዬው መለስ ብሎ ራሱን ሲመለከት የሚበልጥ ነገር አገኘ ጫማን ገንዘብ ይገዛዋል፤ እግርን ግን ገንዘብ አይገዛውም።  ጫማም ያማረው እግር ስለነበረው ነው። ለማማረርም የበቃነው ስላለን ነው። ለማማረር እንኳን እድሜ ስላገኘን ልናመሰግን ይገባል። በሣጥናቸው ብዙ ልብስ አጭቀው  ከአልጋዬ ተነሥቼ አንድ ቀን እንኳን በለበስኩት እያሉ የሞቱ ሰዎችን አውቃለሁ። የሚበላው እያለው የሚሞት፤  እንዲሁም የሚበላውን አጥቶ የሚኖር ብዙ ሰው አለ። ባለጠጎች በገንዘባቸው አንድ ቀን እድሜአቸውን ማስረዘም አይችሉም። እናት ለምትወደው ልጇ ቀንሳ የማትሰጠው እድሜ ስላለንና ሰው የማይሰጠውን ስለተቀበልን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል።

Friday, February 1, 2013

«የበላ ዳኛ…………………………..እንዲሉ!!»



ከጥቁሩ የአፍሪካው ዓለም በምድረ እስራኤል ይዞታ ያላት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። መረጃዎች እንደሚያሳዩን ኢትዮጵያ በምድረ እስራኤል 7 ያህል ገዳማት ያሏት ሲሆን በዐረቦችና በእስራኤል መካከል በተደረገው የ6ቱ ቀን ጦርነት ምክንያት የተዘጋው የዮርዳኖስ ዳርቻውና በሃሽማታዊው የንጉሥ ሁሴን ግዛት ያለና ምንም ያልተሰራበት ይዞታ ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ 5ቱ ይዞታዎች ክፍት ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ይዞታዎች ውስጥ በእስራኤል አሮጌው ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ይዞታ የሆነውና በአረብኛው «ዴር ኤል ሡልጣን» ተብሎ እስካሁን የሚጠራውና በአማርኛው ትርጉም «የመንግሥት ገዳም» የሚባለው በጎልጎታ መካነ መቃብር አጠገብ ያለው ይዞታ ዋነኛው ነው። 
ይህ ይዞታ ለ1600 ዓመታት ያህል በጳጳሶቻቸው ሲመሩን ከነበሩት ከግብጾች ጋር በይገባኛል ጥያቄ እያጨቃጨቀ ሲቆይ  ከ230 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ጉዳዩም እስካሁን ማብቂያ ሳይበጅለት ተወዝፎ ይገኛል። የገዳሙ ባለቤት ማን እንደሆነ እስራኤል ብታውቅም በግብጽ መንግሥት ከፍተኛ የፖለቲካ ድጋፍ ካለው ከኮፕቶች ገዳም ኃላፊዎች ጋር ለመጋጨት ስለማትፈልግ ጉዳዩን ያዝ ለቀቅ እያደረገች መያዙን እንደስልት አድርጋ ትጠቀምበታለች።
ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በቦታው ላይ እየኖሩ ያለው አኗኗር እጅግ አሳዛኝና አስከፊ ከመሆኑ ጋር ገዳሙን በማሻሻል ለኑሮና ለሰው እይታ እንዲመች አድርገው ለመስራት ፈጽሞ የማይችሉ ሲሆን  ግብጾቹ  እያንዳንዷን እንቅስቃሴ  እየተከታተሉ በእስራኤል ፖሊስ እየገዛ  እንዲቆም ያስደርጋሉ።  ካገኘነው መረጃ እንደተረዳነው ከሆነ ማንኛውንም ልማትና እድሳት ለማከናወን እንዳይቻል የሚቀርበው ብቸኛ ምክንያት በጎልጎታ ዙሪያ ያሉ ቅዱሳን መካናት ሁሉ ቅርጽና ይዘታቸውን ሳይለውጡ ባሉበት ሁኔታ እንዲረጉ የሚያስገድድ ስታተስ-ኮ /Status-quo/ የሚባል ሕግ አለ በማለት ኢትዮጵያውያንን ያግዷቸዋል። 

Sunday, January 27, 2013

በቅ/ላሊበላ ገዳም በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች በቃጠሎ ወደሙ



አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ጥር 18/2005 ዓ/ም

  • ·        ቤቶቹ ከቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ዐማኑኤል አጠገብ የተሠሩ ነበሩ።

  • ·        በልደት ክብረ በዓል የቱሪስቶች ቁጥር መቀነሱ ኅብረተሰቡን አስደንግጧል።

በቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም ከዐሥራ አንዱ ውቅር አብያተ መቅደስ ጋር በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት ጥንታውያን ቤቶች በእሳት ቃጠሎ መውደማቸው ተገለጸ፡፡ ባለፈው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ መንሥኤው ባልታወቀ ምክንያት በተነሣው የእሳት ቃጠሎ የወደሙት አራት ቤቶች የሣር ክዳን ያላቸው ፎቅ ቤቶች ሲኾኑ፣ የላሊበላን ጥንታዊ የቤቶች አሠራር የሚያሳዩ በመኾናቸው እየተጠገኑ እንዲጠበቁ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ በቃጠሎው የወደሙት ጥንታውያኑ ቤቶች፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርቶች መካከል በቅኔና ዜማ ትምህርት መስጫነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ ተገልጧል፡፡ ገኛ ቦታቸውም ከዐሥራ አንዱ አብያተ መቅደስ መካከል በታላቁ ቤተ መድኃኔዓለም እና በቤተ ዐማኑኤል አጠገብ 20 - 30 ሜትር ርቀት ላይ መኾኑ፣ የገዳሙ አስተዳደር /ቤት ለቅርሶቹ ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ በቂ ጥበቃና ክብካቤ እንደማያደርግ በካህናቱ እና ምእመናኑ የሚነሡበትን ስጋቶችና ተቃውሞዎች ያጠናከረ ነው ተብሏል፡፡ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት÷ የቃጠሎ አደጋው በደረሰበት ዕለት ሌሊት በሁለቱም አብያተ መቅደስ አካባቢ የገዳሙ ጥበቃ አባላት አልነበሩም፡፡

ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚነሣባቸውና ላለፉት ስምንት ዓመታት በአስተዳዳሪነት የቆዩት የገዳሙ መምህርም ቃጠሎው በደረሰበት ስፍራ የተገኙት ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ቤቶቹ ሰው በማይኖርበትና ‹‹ኮር ዞን›› ተብሎ በዩኔስኮ በሚታወቀው ለቅርሶች የተለየ ስፍራ የሚገኙ ኾነው ሳለ የተከሠተው ይኸው አደጋ፣ ‹‹በአስተዳደሩ ላይ እየተጠናከሩ የመጡትን ተቃውሞዎች ትኩረት ለማስቀየስ የተፈጠረ›› አድርገው እንደሚወስዱት የስፍራው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅ/ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም በአንድ ጊዜ በተደረገው 160 በመቶ የቱሪስቶች ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ዘንድሮ በተከበረው የልደተ ክርስቶስ (ቤዛ ኵሉ) እና ጥምቀት በዓላት ላይ የተገኙት የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት ቀንሶ መስተዋሉን የዜናው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡