ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ባለች አንዲት ምኩራብ ሲያስተምር በቆየበት ወቅት ከፈሪሳዊያን አንዳንዶች ቀርበው እንዲህ ሲሉ መናገራቸውን አንብበናል።
«በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት» ሉቃ 13፤31
ጌታችንም ሲመልስላቸው «እንዲህም አላቸው፦ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት» ሉቃ 13፤32 አላቸው።
እንግዲህ በሰይጣን መንፈስ የሚነዳው ሄሮድስ፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ለመግደል ቢፈልግም በጉ ከመታረዱ በፊት የፈውስና የማዳን ጊዜ እንዳለው በማመልከት የበግ ጠላት የሆነው፤ ቀበሮው ሄሮድስ ጥቂት እንዲታገስ በቀበሮ መስሎ መናገሩን እንመለከታለን።
እንደዚሁ ሁሉ «ኢትክሉ ገቢር ተቀንዮ ለክልዔ አጋእዝት» እንዳለው መጽሐፉ ለጌታ ከመገዛት ይልቅ መንግሥተ ንዋይ ራሳቸውን በግልጽ ያስገዙና ከሥጋ አልፈው አጥንት ዘልቀው ይግጣሉ ለሚባሉት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የአዲስ አበቤው ካህን «አቶ ኑረዲን» የሚል ስመ ተቀጽላ አውጥቶላቸዋል።
«ንቡረ እድ» የሚለውን የማእርግ ስም ወደ «ኑረዲን» ቀይሮ «ኑረዲን ኤልያስ» በማለት ይጠራቸዋል። ለምን? ቢሉ ኑረዲን ኤልያስ ከዚህ ቀደም የነበረውን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለቅጥር የሚከፈል የጉቦ ዋጋ እንደዘመኑ የኑሮ ውድነት አሳድገውት ስለሚገኙ እንደሆነ ሰለባዎች ያስረዳሉ። መምህር ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ ዘግተውት የነበረውን የጅቦችን አፍ አቶ ኑረዲን በደብዳቤ ክፍት ሆኖ የዘረፋ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በደብዳቤ ከማዘዙም በላይ በሥራ ምክንያትና በጉብኝት ሰበብ ወደ አድባራት ከወረደ ለአቶ ኑረዲን ከ15ሺህ ብር ያላነሰ ጉርሻ እንደሚሰጠው ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ሰው ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አውግቷል።
ከአንድ ሺህ ብር ለማይበልጥ ደመወዝ ለመቀጠር አንድ መነኩሴ አስራ ስምንት ሺህ ብር ጉቦ የከፈሉ ሲሆን መነኩሴው የተጠየቀውን ክፍያ ለማሟላት ባለመቻላቸው ይህንን የጉቦ ገንዘብ ከወዳጅና ዘመድ በማዋጣት ያስተባበረ አንድ ዲያቆን የኑረዲንን ገፈፋ በምሬት አውግቶናል።
አቶ ኑረዲን ለቢሮ የስራ መደብ ከሰላሳ ሺህ እስከ ስልሳ ሺህ ብር ጉቦ እንደሚቀበሉ የተገለጸ ሲሆን የጉቦው ዋና አቀባባዮችና ግብረ አበሮቻቸው ኪሮስና ዘካርያስ የሚባሉ ነፍሰ በላዎች እንደሚባሉም ይታወቃል። አቶ ኑረዲን ክፍት የስራ መደብ ማግኘት ካልቻሉ እንደሚያፈናቅሉና ያለፍላጎት ሰራተኛውን በማዘዋወር ክፍት ቦታ እንደሚፈጥሩ ተያይዞ ተገልጿል።
የአክሱም ጽዮን ንቡረ እድና፤ የአክሱም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል የሚታወቁት ንቡረ እድ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደተመደቡ የሙዳየ ምጽዋት ገልባጮችን አፍ በመሸበብ ህግና ስርዓት እንዲያዝ በማድረግ፤ ኢፍትህና ግፍ እንዲቆም በመታገላቸው ከጅቦቹ መንደር ጩኸትና ማጓራት ተሰምቶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ አይዘነጋም። የጅቦቹን ጩኸት በማስተባበር ፊት አውራሪ የነበረው ቀንደኛው መሪና እድሜውን በክፋት የጨረሰ፤ ንስሐ ለመግባት የማይፈልግና ከመልካም ነገር ጋር ዘወትር የተጣላው የሽማግሌው ነውረኛ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሲሆን ለንቡረ እድ ገ/ማርያምን መነሳት በማስተባበር፤ የአድማ ፊርማ በማስፈረም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።