source: dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ ገብርኤል ወደ ሀዋሳ በሥራ ተመድበው ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ሠላምና ዕረፍት አግኝተው አያውቁም፡፡ ልባቸው ከሠላምና ከዕርቅ ርቋል፡፡ ከቤተክርስቲያን የተባረሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንን ጥያቄ በመመለስ ፈንታ ሕልምና ሃሣባቸው ለጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎችና ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እየተሸነፈ ማንኛውም ዕርቅ እንዳይደረግ ከማገድ ውጪ ምንም ነገር አይታያቸውም፡፡
በሺዎች ከሚቆጠሩ ምስኪን ምዕመናን ይልቅ ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉት ከጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎችና ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" እንደሆነ ራሳቸውን አሳምነውታል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሁለት አካላት አቀነባባሪነት በድሃዎቹ የሀዋሳ ምዕመናን ላይ ጥቃት ሲፈጸም፣ አይተው እንዳላየ፣ ሰምተው እንዳልሰማ በመሆን ፍትሕን ከሀገረ ስብከቱ የሰማይ ያህል አራቁት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እንዳይሰበክ ሲታፈን ነገሮችን ሁሉ በፊርማና በማኅተማቸው እያፀደቁ የድኆቹ የአምልኮ ነፃነት በጠራራ ፀሐይ ሲቀማ ምንም አልተሰማቸውም፡፡
ይሁንና በዚህ ሁኔታ የተማረሩት የሀዋሳ ምዕመናን ስለመልካም አስተዳደርና ስለ ፍትሕ ጮኹ፡፡ ቁጣቸውን በተለያዩ መንገዶች ገለጹ፡፡ ግጭቱ ተጋግሞ ሀገረ ስብከቱን አልፎ በመላው ሀገሪቱ በተለይም በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ቋሚና ቅዱስ ሲኖዶሶች ተከታታይ ስብሰባዎችን በማድረግ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፉ፡፡ ይሁን እንጂ አቡነ ገብርኤል ያላወረዱትን ዕርቅ፣ ዕርቅ አውርጃለሁ፣ ያልመሠረቱትን ሠላም፣ ሠላም መሥርቻለሁ፣ ያላመጡትን አንድነት፣ አንድነት አምጥቻለሁ እያሉ ጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ ቢዋሹም ሐቁ ግን እየገዘፈ መጥቶ ለስድስት ወራት (ጥር/2003 -ሐምሌ/2003) ያህል ለሕይወታቸው በመስጋት ሸሽተው አዲስ አበባ ላይ መቀመጥ ግዴታ ሆነባቸው፡፡
ይሁን እንጂ፣ ከእትብቱ እንደተቆረጠ ጽንስ መተንፈስ የተሳናቸው ጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎቹና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እንደምንም ተሟሙተው ሐምሌ 18 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት በአንዲት አሮጌ ሃይላክስ ፒክ አፕ መኪና በስውር ወደ ሀዋሳ መልሰው ወሰዷቸው፡፡
ከዚያም ዙሪያውን ጥበቃ ተጠናከረላቸው፡፡ ሲወጡም ሲገቡም በግል ሴኪዩሪቲ ማሠልጠኛ የሠለጠኑ ጠባቂዎችን በመመደብ፣ ብርሃን ቀርቶ አየር እንኳን እንዳያገኙ እፍንፍን አድርገው አጀቧቸው፡፡ ዐውደ ምሕረቱ በልዩ ልዩ መሰናክል ታጥሮ ምዕመናን በቅጡ ማስቀደስ ተሳናቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ይላሉ ውስጥ ዐዋቂዎች፣ በዚህን ጊዜ የአቡነ ገብርኤልን መንፈስ ለማረጋጋት ሲባል፣ በአግባቡ የተመዘገበ ስለመሆኑ እንኳን በቅጡ የማይታወቅ ለራስ መጠበቂያ የሚሆን አንድ ሽጉጥ ከጥገኛ ነጋዴዎቹ በአንዱ በእጅ አዙር ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተነቃቁት ሊቀጳጳስ ምስኪኖቹን የሀዋሳ ምዕመናንን ለግል የወሲብ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ቀበሮዎች ናቸው" ብለው እስከመሳደብ ደረሱ፡፡ በሠላም የሚመጣውን በእጅ መስቀላቸው፣ በኃይል የሚመጣባቸውን ደግሞ በተሰጠቻቸው ራስ መጠበቂያ ቀልጥመው ሊያሳርፉት ንቁ ሆነው መጠበቅ ያዙ፤ በሠለጠነ ዘመን ማን ይሞታል ታዲያ?
አቡነ ገብርኤል እንዲህ እንዲህ እያሉ፣ ልባቸው ዕርቅና አንድነትን እየተፀየፈች፣ ልታረቅ ቢሉ እንኳን ጥገኛ ነጋዴዎቹና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እንዳይታረቁ እያከላከሏቸው የሠላም መንፈስ አንድ ቀን እንኳን በውስጣቸው ሳትገባ፣ ሀዋሳ ላይ ሥራ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው አንድ ሁለት ወራት ብቻ ቀራቸው፡፡ ታዲያ በአንድ ዕድለ ቢስ የነሐሴ 2004 ዓ.ም የተረገመች ቀን፣ ያቺ ለራስ መጠበቂያ የተሰጠቻቸው ሽጉጥ ጠፋችባቸው፡፡ ከሁኔታው መረዳት እንደተቻለው አቡነ ገብርኤል ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ሽጉጣቸውን መኝታ ክፍላቸው ውስጥ ረስተውም ይሁን አስቀምጠው ያገኘ ሰው እንደወሰደባቸው ተገምቷል፡፡
በዚህ ሁኔታ የተበሳጩትና የተቆጡት አቡነ ገብርኤል ከእነርሱ በስተቀር አንስቶ ሊወስድብኝ የሚችል የለም በማለት የጠረጠሯቸውን ፍጹምን (ተላላኪያቸው) እና ሊቀመዘምራን ልሳነወርቅን (ሾፌራቸው)፣ በቅርብ እንዲከታተሉላቸውና እንዲያጠኗቸው የጥገኛ ነጋዴዎችንና የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን ጥምር ኮሚቴ አይሉት ስብስብ ነገር ይመድቡባቸዋል፡፡ የሽጉጧ ነገር የውሃ ሽታ ሆነ ቀረ፡፡ ፍጹም ሲጠየቅ ከልሳነወርቅ በስተቀር ሊወስድባቸው የሚችል የለም እርሱን ጠይቁት ይላቸዋል፡፡ ልሳነወርቅ ደግሞ በበኩሉ "አብሯቸው የሚያድር ማን ሆነና ነው እኔን የምትጠይቁት? ለመሆኑ ለእርሳቸው ከፍጹም የቀረበ አለ እንዴ? ፍጹምን መርምሩት" ይላቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ያችን ውድ ዕቃ ሳያገኟት መስከረም ወር እንደዋዛ ሊጠናቀቅ ተቃረበ፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት በእነዚህ ሁለት ሰዎች መጠቃታቸው ያንገበግባቸዋል፡፡ በተለይ የፍጹም እንዲህ መጨከን ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ፍጹም እኮ ሁለ- ነገራቸው ነው፡፡ ቃል አቀባያቸው፣ ጠባቂያቸው፣ አስገቢና አስወጪ አጋፋሪያቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ እንደሚሉት፣ የላመ የጣፈጠ ምግባቸውን ቀምሶ ለይቶ የሚያስቀርብላቸው ወጥ ቀማሽ እልፍኝ አስከልካያቸው፣ ኧረ ስንቱ . . . ? የፍትሕ ጥያቄ ለማቅረብ ወደ መንበረ ጵጵስናው የሚመጡትን የሀዋሳ ምዕመናንን "እርሳቸው የሉም"፤ "ተኝተዋል"፤ "ዕረፍት ላይ ናቸው"፤ "አሁን ሊያነጋግሯችሁ አይችሉም" እያለ የሚያባርርላቸው አለኝታቸው ነው፡፡ ሲያስፈልግም ከእርሳቸው ቀደም፣ ቀደም እያለ ምዕመናኑን ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ሳያገኙ አፍ አፋቸውን እያለ ወደ መጡበት ይመልስላቸዋል፡፡ እርሱን እንደ እሳት መከላከያ አስቤስቶስ ነው የሚጠቀሙበት፡፡ እንደሻንጣቸው ሁልጊዜ የትም ነው ይዘውት የሚዞሩት፡፡ በተለይ ረፋድና አመሻሽ ላይ በፌስታልና በብብቱ ሥር በጋዜጣ የተጠቀለሉ የሚበሉና የሚጠጡ ፍሬሽ ፍሬሽ ነገሮችን ባሻው መንገድ በማቅረብ እርሱን የሚተካከለው አንጀት-አርስ የለም፡፡ ፍጹም እኮ በፍጹም ተተኪ የሌለው ረዳታቸው ነው፡፡
ሲያሻው ደግሞ "ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ" ብለው በሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ ወረዳዎችና ከተማዎች እየወከሉት ልዩ ልዩ ካህናትን እየሰበሰበ ይገስጽላቸዋል፡፡ የተበላሹ አሠራሮችን ያስተካክልላቸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ሆኖ የሚገባቸውን ግብዣ ስለእርሳቸው ይጋበዝላቸዋል፡፡ ታዲያ "ፍጼን" ምን ነካው? ደግሞ እኮ እርሱን ላለማጣት ቃለ ዐዋዲን ሽረው በመዋቅር የሌለ የሥራ መደብ ፈጥረው "የጳጳሱ የመልዕክት ክፍል" የሚል የሥራ መደብ መጠሪያ አውጥተው በወር ብር 930 ከአሮጊቶች መቀነት ከሚሰበሰብ ገቢ ወርሃዊ ደመወዝ እንዲከፈለው ቆርጠውለታል፡፡ ይህም ብቻም አይደለም፤ እርሱን ከመውደዳቸው የተነሳ ቅጥሩ ያለ ማስታወቂያና ያለ ነፃ ውድድር በመስከረም 2004 ዓ.ም ሆኖ፣ ደመወዙ ደግሞ ከቅጥሩ ቀን በፊት አንድ ወር ወደ ኋላ ተደርጎ ከነሐሴ 2003 ዓ.ም ነው የተደረገለት፡፡ እርሳቸው ይህንን ሁሉ ሕግን እየተላለፉለት፣ እየጣሱለት፣ እንዲህ ጉድ ያደርጋቸዋል? ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ! ሰውየዉ . . . !!