አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳንን የሕይወታቸው አንድ
አካል አድርገው ይመለከቱታል። የማኅበረ ቅዱሳን ሞት ሞታቸው፤ ሕይወቱ ደግሞ ሕይወታቸው አድርገው ስለሚመለከቱ ሲወቀሱ ወይም ሲተቹ
ኅሊና እንዳለው ሰው ሳይሆን ዛር እንደሰፈረበት ሰው ያንዘፈዝፋቸዋል፤ ያወራጫቸዋል። እስከለሞት ስለሚሟገቱለት ማኅበር፤ ማንነት ተረጋግተው አሳማኝና ማስረጃ ያለው መልስ በመስጠት
በግንዛቤ የተሳሳተ ካለ በመመለስ ወይም እንደጠላት የሚቆጥሩትን ክፍል
የሚንቁ ከሆነም ዝም ብለው እንደትቢያ ቆጥረው ከማለፍ ይልቅ ስድብ፤
ዛቻና ማስፈራሪያ፤ ጴንጤ፤ ተሐድሶ፤ መናፍቅ፤ አህያ፤ ውሻ፤ ደደብ፤ ከሐዲ፤ ሌባ ወዘተ ቃላቶችን በመጠቀም ተቀናቃኝ ነው ለሚሉቱ ሁሉ መጠቀምን ባህላቸውና የእምነታቸው
አንዱ ክፍል በማድረግ ሲጠቀሙበት መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። ከአፍቃሬ ማኅበሩም ይሁን የማኅበሩ አንድ አካል ከሆኑት አባላቶቹ
የሚሰጡን አስተያየቶች የሚያሳዩን ያንን ነውና።
ከዚህ ሁሉ አስተሳሰቦቻቸው የምንረዳው ነገር ቢኖር
የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ይሁኑ የደጋፊዎቹን ማንነት ሲሆን ከእነሱ የተለየ ሃሳብ ላለው ሁሉ መልስ መስጠት የማይችሉ፤ ነገሮችን ሁሉ በኃይልና
በዘለፋ ለመፍታት የሚመኙ፤ «ሁሉም መንገዶች ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ያመራሉ» ካልሆነ በስተቀር ሌላ መስማት የማይፈልጉ ስታሊናዊ አመለካከት
የታጠቁ ሰዎች ስብስብ መሆናቸውን ብቻ ነው።
አሁንም ስለማኅበረ ቅዱሳን መሠሪ ማንነት የምናቀርባቸውን
አንዳንድ ነጥቦችን ተከትለው ያንኑ የተለመደ አፋቸውን በመክፈት ከዚያ አልፎ ያለውን የአእምሮአቸውን በር ከፍተው እንደሚያሳዩን በመጠበቅ፤ የማኅበሩን መሠሪነት የሚጠቁሙ ጭብጦችን በአስረጂ
ለማስቀመጥ እንሞክራለን።
1/ ስውር ሚዲያዎችን የመጠቀም መሠሪነት፤
ማኅበሩ በግልጽ የሚታወቁ የራሱ የሆነ የሚዲያ
ኃይሎች አሉት። የጽሁፍና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎቹ በየጊዜው በሚለዋወጡ
አገልጋይ ሰዎቹ አማካይነት ሌሊትና ቀን ለማኅበሩ የስም ግንባታ ይሰራሉ። እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ስለማኅበሩ ማንነት በሰፊው መረጃ
ማድረስ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩን በማጠናከር ለፖለቲካ ጡንቻ ግንባታ
የሚያግዝ የገቢ አቅሙንም ያሳድጉለታል። የሕትመት ውጤቶች እንደ ስምዓ ጽድቅና ሐመር መጽሔት፤ መጻሕፍቶች፤ ካሴትና ሲዲ፤ እንዲሁም
ሱቆች፤ ሆቴሎች፤ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኰች፤ የመዋጮና የበጎ አድራጎት ገቢዎች በየፈርጁ የተመሰረቱ የገቢ መንገዶች ስለመሆናቸው
ሁሉም የሚስማማበት እውነት ነው። ዘመኑ ደግሞ «ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚል ፈሊጥ የነገሠበት እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ
ዓለማዊ ብሂል በደንብ የተረዳው ማኅበሩ፤ የሚፈልገውን አፍ በሚገባው ቋንቋ ለማናገርም ይሁን ያስቸገረውን አፍ ደግሞ በአንድ ወቅት ፍልስጤማውያን የይስሐቅን ምንጭ በድንጋይ እንደጠረቀሙት፤
እሱም ለመጠርቀም የሚያስችል የኃይልን ምንጭ አድርጎ ይገለገልበታል። ዘፍ 26፤18
ይህ እንግዲህ የሚታይ የሚጨበጥ የአደባባይ እውነት
ነው። በነዚህ ሁሉ መንገዶች ማኅበሩ ስለመልካም ስሙ ሚዲያዎቹን አይጠቀምም ወይም የገቢ አቅሙን እያሳደገበት አይደለም የሚለን ቢኖር
ይሁንልህ ብለን ከማለፍ ባሻገር ለማሳመን መሞከሩ ነጩን ነገር ጥቁር
ነው ብሎ ከሚከራከር ሰው ጋር መታገል ስለሚሆንብን እናልፈዋለን።
ማኅበሩ ይህን ሁሉ በግልጽ የሚጠቀምበት መንገድ
ሲሆን በስውር የሚገለገልባቸው መንገዶች፤
ዋናው የማኅበሩ ድረገጽና በዓለም ዙሪያ ያሉ የክፍል
ድረ ገጾች በተጨማሪ፤
ሀ/ ደጀ ሰላም
ለ/ አንድ አድርገን
ሐ/ አሐቲ ተዋሕዶ
መ/ አደባባይ
እና ሌሎች መካነ ድሮችን ለዓላማው መሳካት በግልጽና
በስውር ይጠቀምባቸዋል። ደጀ ሰላም ብሎግ ሥራውን ሲጀምር /dejeselam owned by mahibere kidusan/ሲል የነበረውን
ቢቀይረውም ጉግል በኢንዴክስ ውስጥ የመዘገበውን ይኽንኑ ስም ያሳይ እንደነበር አይዘነጋም። እነዚህ ብሎጎች ለማኅበረ ቅዱሳን ተግተው
እንደሚሰሩ የሚያረጋግጠው አንድም ትችት ወይም ነቀፋ በማኅበሩ ላይ አያቀርቡም ብቻ ሳይሆን በቀሳፊው ማኅበር የተጨነቀው ዲ/ን ዳንኤል
ክብረት የደረሰበትን ወከባና የማኅበሩን ማንነት በመዘርዝር በደጀ ሰላም ላይ ያወጣውን ጽሁፍ በሰዓታት ልዩነት መደምሰሳቸው ከምንም በላይ አረጋጋጭ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የሰዎች እንጂ የቅዱሳን መላእክት
ማኅበር ባለመሆኑ አንዳችም ማኅበራዊ ስህተትም ይሁን ግድፈት እንደሌለው በመቁጠር የእርምት ወይም የትችት ዘገባ አለማቅረባቸው እንዲሁም የቀረበበትን ማውረዳቸው፤
ማንነታቸውን ከምንም በላይ የሚያረጋግጥልን ይሆናል። እንዲያውም ማኅበረ ቅዱሳን ሲነካ ወይም ስሙ ሲነሳ አንድ ላይ እየተቀባበሉ
መንጫጫታቸው አስገራሚነቱን ከፍ ያደርገዋል። በገለልተኝነት መታዘብም
የነበረ ወግ ቢሆንም እነርሱ ግን ከዝምታ ባለፈ ልክ ዓይናቸው ውስጥ ጉድፍ እንደገባ ህጻን
ከዳር እስከዳር ጩኸታቸውን እንደማኅበሩ ሕጋዊ ወኪል ማስተጋባታቸው ለራሳቸው የማይታወቃቸውና ሌላውም ይታዘበናል
የማይሉ መሆናቸው ይገርመናል ። ምንም እንኳን መደገፍም ሆነ መቃወም
መብታቸው ቢሆንም እነርሱ ግን በአንድ ድምጽ አንድም ቀን ሳይቃወሙ ሁል ጊዜ በመደገፍ መቆማቸው የማን ተልእኰ ፈጻሚ መሆናቸውን
ተመልክተን ሁሉንም የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ናቸው ብሎ መናገር ይቻለናል። ከማኅበረ ቅዱሳን መሠሪ ባህርያትም መካከልም አንዱ በግልጽ ከሚታወቀው መገልገያ መንገዶቹ ውጪ በስውር
እጁ በብዙ ብሎጎች መጠቀም መቻሉ ነው። በዚህም መንገድ ዓላማውን
ያዳርሳል፤ ያስተዋውቃል፤ የሚቃወመውን ይመታበታል፤ ዜናና ዘገባ ይሰራበታል።
ይህንንም ስውር ሚዲያዎችን መጠቀሙን የማኅበሩ
መሰሪ መገለጫ ቁጥር አንድ ብለነዋል።
