Sunday, May 20, 2012

ለጠያቂያችን የተሰጠ መልስ

ALEMIN HULU YEFETERE AND AMLAK WOLDEABE WOLDEMARIAMNEW"KIDUS EGZIABHER BICHA NEW.GIN,MUZLIMOCH ALLAH (AMLK)MILUT MANIN NEW???
ከላይ በፈረንጅኛው ፊደል የቀረበው የአማርኛው ንባብ ጥያቄ፤ በጡመራ ገጻችን ላይ ባለው «ይጠይቁ» ዐምድ ላይ የተላከልን ነው።
ንባቡን ወደፊደላችን ስንመልሰው፤ ይህንን ይሰጠናል።
«ዓለምን ሁሉ የፈጠረው አንድ አምላክ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነው። ቅዱስ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ግን ሙስሊሞች አላህ(አምላክ) ሚሉት ማንን ነው?»
ጥሩ ጥያቄ ነው። ሙስሊሞች የሚያመልኩትን «የአላህ» ማንነት ከመመልከታችን በፊት እነሱ ብቻ ትክክለኛ እንደሆኑ ቆጥረው  እኛ የምናመልከውን እግዚአብሔርን በተመለከተ የሚሉንን ጥቂት ለማሳየት እንሞክራለን።
በእኛ ዘንድ የሚነገረውን አንድነት በሦስትነት ሳይከፋፈል፤ ሦስትነት በአንድነት ሳይጠቃለል፤ አንድም ሦስትም ብለን ማምለካችንን ሦስት አምላኰችን እንደምናመልክ አድርገው ይቆጥራሉ። ይህንንም «ሽርክ»شرك ይሉታል። ይህም ማለት «አጋሪ» ፤ ከአንድ በላይ  አምላኪ ማለት ነው። ከዚያም በተረፈ ጣዖት አምላኪ ማለት ነው። አላህ አንድ ገጽ፤ አንድ አካል፤አንድ ግብር ያለው እንጂ አንድም ሦስትም ሊሆን ስለማይችል ክርስቲያኖች የሚያመልኩት አላህን ሳይሆን «ፍጡርን ነው» ይላሉ። አንድና አንድ ብቻ (Oneness) ወይም توحيد ተውሂድ(ተዋህዶ) ያልተቀበለ ሁሉ አላህን አልገዛም ያለ ነው ይላሉ። (ተዋሕዶ ማለት አንድ ገጽ ማለት  እንደሆነ ልብ ይሏል?) توحيد ወይም Oneness ማለት ነውና። لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ «እሱን የሚመስል ማንም የለም፤ ሁሉን የሚሰማ፤ ሁሉን የሚያይ እሱ ብቻ አንድ ነው» ቁርዓን ሱረቱል Ashura 42፤11
( Fundamentals of Tawheed/Islamic monotheism/  Dr Abu Ameenah Bilal Philips)
ስለዚህ ተውሂድን( ተዋሕዶን) (Unification) ያልቀበሉ ሁሉ ከሀዲዎች ናችሁ ይሉናል።
በዚህም ተውሂድን ባለመቀበል የተነሳ ዛሬ በዓለም ላይ ያለው ኃጢአት ሁሉ የመጣው የሽርክና ውጤት ነው ይላሉ። ስለዚህ በእነሱ ዘንድ ክርስቲያኖች  ሽርክ አማኞች  ስለሆኑ የኃጢአቶች ሁሉ  ምንጮች ናቸው ማለት ነው። ይህ እንግዲህ እነሱ ክርስቲያኖችን የሚተነትኑበት መንገድ ነው። http://www.allaahuakbar.net/shirk/crime.htm/ይመልከቱ።
ክርስቲያኑን እንዴት እንደሚመለከቱት የብዙ ገጽ ትንታኔ ማቅረብ ቢቻልም ለማሳያነት ይህ በቂ ሆኖ ክርስቲያኖች እስልምናውን እንዴት እንደሚያየው ጥቂት ለመግለጽ እንሞክራለን።
አሊ ሲና የተባለ የቀድሞ የእምነቱ ተከታይ (Why I left Islam?)በተባለው ጽሁፉ እንዲህ ሲል ጽፏል። የእስልምና እምነት ተከታይ በዚህ ዘመን ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን በላይ መድረሱን ይገልጽና ታዲያ ይህ ሁሉ ህዝብ የሚሳሳት ይመስልሃል? ብሎ ይጠይቃል።

አህያቸውን ደጅ ያሳድሩና ጅብን ነገረኛ!

                   በፒዲኤፍ ለማንበብ ( እዚህ ላይ ይጫኑ )
ብዙዎቹ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች ድጋፋቸውን የሚገልጹት በሃይማኖታዊ እውቀት ላይ ተመስርተው ሳይሆን  ስሙን በቀባበት የቅዱሳን መጠሪያ ስር  ክርስቲያን በሚመስል ባህሪው  ካጠመዳቸው ሱስ የተነሳ ነው።
ማኅበረ ቅዱሳንን ለማወቅ ውልደቱንና እድገቱን መረዳት በጣም አስፈላጊው ነገር ነው። በዚያም ውስጥ የኖረበትን  ውስጠ ምስጢር ቀረብ ብሎ ማጥናትም በለበሰው ክርስቲያናዊ ካፖርቱ ስር ያለውን ማንነቱን ለመረዳት እጅግ አስፈላጊው ነገር ነው። ምክንያቱም  «መጽሐፍን በልባሱ፤ ሰውን በልብሱ አታድንቀው» የሚለውን ብሂል በመቀበል ገቢር ላይ አውለን ለማድነቅም ይሁን ለመንቀፍ የሚያስችል ሙሉ እውቀት እንዲኖረን ስለሚያስችለን ነው። ካገኘናቸው ጭብጦች ተነስተን ወደመንቀፉ ጥግ ስንደርስ በማኅበሩ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ምልከታ ከጭፍን ጥላቻና ምሬት የራቀ እንዲሆን ያደርገዋል። ስንደግፈውና ከፍ ከፍ ስናደርገውም ለመደገፍ የሚበቃን በጭብጥ ላይ የተመሰረተ እውቀታችን ከጭፍን ደጋፊነትና ከማኅበር አምላኪነት እንድንርቅ ያግዘናል። ስለዚህ የማኅበሩን አዎንታዊና አሉታዊ ማንነት በይፋ ለመናገር ምን ጊዜም በተሟላ መረዳት ላይ በተመሰረተ እውቀት መሆን እንዳለበት ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። እኛን የሚነቅፉና የሚሳደቡ የማኅበሩ ደጋፊዎች እኛ ስለማኅበሩ ያለንን መረዳትና እውቀት ለማወቅ ከመፈለግ ይልቅ ለደጋፊነት ያበቃቸውን መረዳት በእኛ ላይ ለመጫን እጃቸውን ሲወራጩ ይስተዋላሉ። የማኅበሩ ደጋፊዎች እንደሚያዩን ሁሉ እኛም እነሱን የምናይበት ምልከታ ያለን ስለሆነ ልዩነቱ ከጭፍን ደጋፊነትና ከጭፍን ጥላቻ የወጣና የማኅበሩን ማንነት በማወቅ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከሁለታችን ይጠበቃል።
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እንደተመሰረተ፤ እንዴት እንዳደገ፤በዘመኑ ምን እንዳደረገ ብዙ ተነግሯል። ከልደት እስከ ጉርምስናው ብዙ ተጽፏል። በማኅበሩ የተሰለሉና የሕይወት ታሪካቸው የተጠና ብዙ ሰዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል። በማኅበሩ አቅራቢነት በፖሊስ የተደበደቡ፤ ከስራ የተባረሩ፤ ሀገር ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ዛሬም በሕይወት ስላሉ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። የአንዳንዶቹንም ኃጢአትና በሥጋ ድካም የሰሩትን አበሳ  ማኅበሩ በኃጢአት መዝገቡ ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ አስፍሮ ለሕዝብ በሽያጭ አቅርቦ አስነብቦናል። ከዚህም በላይ የማኅበሩ መስራችና አባል ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስላደረሰበት መገለልና ገፍትሮ ወደዳር የማስወጣት የስውር አመራሩን ጡንቻ በተነተነበት ረጅም ጽሁፉ ያለውን የቅርብ እውቀት ምስክርነቱን  ሲነግረን ስለማኅበሩ ያለንን እውቀት የበለጠ ያሳደገልን መረዳት ነው። እዚህ ላይ ሳንጠቅሰው የማናልፈው ነገር ዳንኤል ከማንም ደጋፊ በላይ ስለማኅበሩ ያለውን እውቀት በጽሁፍ በገለጠ ጊዜ እርግማን ያዘነቡ የማኅበሩ ደጋፊዎች፤ ውጥረቱ በእርቅ ፍጻሜ አግኝቷል ሲባል ደግሞ ምርቃት ለማዥጎድጎድ ጊዜ ያልወሰደባቸው መሆኑን ስናይ ደጋፊዎቹ በማኅበሩ ላይ ያላቸው ድጋፍ በእውቀት ላይ በተመሰረተ መረዳት ሳይሆን በሱስ  ፍቅር መጠመዳቸውን እንድረዳ ጋብዞናል። ዳንኤል የማኅበሩን ማንነት በጽሁፍ ሲገልጥ፤ ማኅበሩ ያልነበረውን ማንነት ያን ጊዜ ከሰማይ ቧጥጦ የመጣ እንዳልነበረ ሁሉ ሲታረቅም ማኅበሩ የተገለጠበት ማንነት ወዲያውኑ ብን ብሎ የሚጠፋ ሆኖ አይደለም። ታዲያ ለእርግማንና ለምርቃት ለምን ተጣደፉ ስንል የምናገኘው መልስ ድሮውንም ድጋፋቸው በስሜት ስካር የተቃኘ መሆኑን ነው። ዳንኤልም ሲጣላም ይሁን ሲታረቅ ያሳደገውን ማኅበር ማንነት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምንም እንኳን ዳንኤል ራሱ የችግሩ አካል መሆኑን ብናምንም ዳንኤል ከእርቅም በፊት ይሁን ከእርቅ በኋላ በማኅበሩ ላይ ስላለው ውስጥ አወቅ እውቀት ዛሬም ቢሆን አብሮት አለ። በደንብ አውቆት የጻፈው መረዳት ቢታረቅም ባይታረቅም ከማኅበሩ ባህርይ አንጻር ማኅበሩ ያው ነው። እኛም ይህንን ጠንቅቀን እንረዳለታለን። እንግዲህ ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚኖረን ዙሪያ ገባ እውቀት የማኅበሩን ማንነት የበለጠ እንድንረዳ ስእል የሚሰጠንና ይህም፤ ይህም አለ! እንድንል የሚያደርጉን ነጥቦች ከላይ የጠቃቀስናቸውና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው ነው።

Saturday, May 19, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን የስኳር ልማቱን እንደሚቃወም ባደፈጠ ጥናቱ ውስጥ ገለጸ!


ስለዋልድባ ገዳም ጥናት አዘጋጅቻለሁ ካለ በኋላ አድፍጦ የቆየው ማቅ የመምህር ዕንቍ ባህርይ ደብዳቤ እንደደረሰው ጥናቱን ካዘገየበት ቆፍሮ በሽንፍን ካባ ለመግለጥ ተገዷል። ማቅ ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ ሆኖ የደረሰበትን የጥናት ውጤት በኦፊሴል ማቅረብ ሲገባው  ጥናት ሳይሆን ወሬ ሰብስቦ ገዳማቱ እንደዚህ ይላሉ፣ መንግሥት ደግሞ እንደዚህ እየሰራ ነው በሚል ገደምዳሜ ጎዳና ለመሸወድ የሞከረ ዲስኩር ለማቅረብ ሞክሯል።
ገዳማቱ የሚያሰሙትን ጩኸት ማንም ሰምቶታል። መንግሥትም እየሰራ ስላለው ልማትም በግልጽ ተናግሯል። ማቅ ሁለቱን ሃሳቦች ለማስታረቅ የሄደ ሽማግሌ ይመስል ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን እንደዚህ ተባለ፤ እንደዚያ ተደረገ የሚል ወሬ መለቃቀሙ ምናልባትም ያጠናውን ስውር ውጤት በይፋ ብገልጸው መምህር ዕንቍ ባህርይ በግልባጭ ባስታወቋቸው ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት፤ በፌዴራል ፖሊስ፤ በፌዴራል ጉዳዮች ወዘተ መስሪያ ቤቶች በተያዘብኝ የአሸባሪነት ጥቁር ስሜ  ወደ አደጋ ያደርሰኛል ብሎ በመስጋት በልቡ ያስቀመጣትን ሚጥሚጣ ጥናት እንደቀበረ እንገምታለን።
የመንግስትን የስኳር ልማት በግልጽ ብደግፍም ደግሞ በውጪ ሃገር ያሉ ደጋፊዎቼ ዓይንህን ላፈር ይሉኛል፤ መነኰሳቱም ለስንት ስንጠብቅህ፤ እንደዚህ ታዋርደናለህ? ይሉኛል ብሎ  እንዳደፈጠም የጫጫረው ወሬ በግልጽ ያሳብቅበታል።
አሁን ከማቅ መገለጽ ያለበት ኦፊሴላዊ መግለጫ መነኰሳቱ የሚናገሩትን ቃል መድገም  ሳይሆን ደረስኩበት ባለው ጥናት ላይ የስኳር ልማቱ የሚያደርሰው ጉዳት አለ ወይም የለም የሚል ቃል ብቻ እንጂ እንዲህ ተባለ፤ እንዲያ ተወራ የሚል ዲስኩር አይደለም።
ከዚያ ውጪ በሽብር ተግባር የተወጠረች ነፍሱን ለማቆየት ሸርተት፤ ሸርተት አያዋጣም።
 ይህንንም ያህል ለመጠንቀቅ ቢሞክርም ማቅ ባቀረበው የወሬ ዘገባ ላይ ቁና ቁና እየተነፈሰ አንዴ ስኳር ልማቱን እደግፋለሁ የሚልና በሌላ መልኩ ደግሞ ደጋፊዎቹ እንዳይቀየሙትም የስኳር ልማቱ አደገኛ ነው፤ እኔ የገባሁትን ውጥረት ተረዱልኝ የሚል ስሜት ያላቸውን የተቃውሞ ሃሳቡን አልፎ አልፎ ከዲስኩር ጽሁፎቹ መካከል ደንቅሮ ይታያል።