Monday, May 7, 2012

የሰንበት ማደራጃና መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አባ ኅሩይ ከሥልጣናቸው ተነሱ

                                source: http://awdemihret.blogspot.com
አቀርቅሮ ወጊውና የማቅ ቀኝ እጅ መሆናቸውን በይፋ ያረጋገጡት የሰንበት ማደራጃና መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አባ ኅሩይ ከሥልጣናቸው ተነሱ፡፡ በምትካቸውም መምህር ዕንቁባህሪ ተተክተዋል፡፡  እጅግ በሆነ መሰሪ አቀራረብ የሰንበት ማደራጃውን ሚስጢር ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፈው እየሰጡ ቤተክርስቲያንና ማደራጃውን ወደ ማቅ አቅጣጫ እየመሩ የነበሩት አባ ኅሩይ መነሳታቸው ለእውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች እጅግ አስደሳች ዜናና የጸሎታቸውምም ምላሽ ነው፡፡
ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በድብቅ የማቅ ተላላኪ በመሆን የሰንበት ማደራጃውን አሰራር በሙሉ ለማቅ ለማስረከብ ተዘጋጅተው የነበሩት አባ ኅሩይ ከዚህ በፊት አብረውኝ የሚሰሩ ሰዎች ሁሉ በስራዬ ላይ እንቅፋት ስለሆኑ ይነሱልኝ ብለው ጠይቀው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ በቦታው ላይ የሚተኩት ሰዎች በማቅ በኩል ተዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ እኝህ ሰው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ዜግነት እስተቀበሉባት አሜሪካ ድረስ መፍቀሬ ንዋይነታቸው በእጅጉ የታወቀ ስለነበር በሰንበት ማደራጀው ላይ በተሾሙ ጊዜ፤ ሹመታቸው ብዙዎችን የቤተክርስቲያን ልጆች አሳዝኖ  ነበር፡፡ የሰውየውን የባህሪ ክፍተት አሜሪካ ባሉ ባልደረቦቻቸው የሰሙት የማቅ አመራር አባላት አባ ኅሩይ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ በቀላሉ በማግኘትና የንዋይ ፍቅራቸውን በማርካት ከጎናቸው እንዲቆሙ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዛም ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በቅርቡ እንኳ ማቅን በሚመለከት የአሰራርን ግልጽነት ለማስረጽ የሚረዳ ደብዳቤ እንደይወጣ ማህተም ይዞ እስከመሰወር የደረሰ አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙ ሰው ናቸው፡፡ ከዛ ጊዜም በኋላ በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ሲሆን ከሰዎች ጋር ያላቸውም ግንኙነት በስልክ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ የእለት ዕለት የስራ ዕንቅስቃሴ የሚያስፈልገው የማደራጃ መምሪያው የስራ ገበታ ክፍት ስለሆነና የሰውየውም አካሄድ አደገኛ በመሆኑ መነሳታቸው አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በአባ ኅሩይ ቦታ የተሾሙት መምህር ዕንቁባህሪ ሲሆኑ እሳቸውም ከዚህ ቀደም በመምሪያው ኃላፊነት የሰሩና እስካሁንም ድረስ ደግሞ በምክትል ኃላፊነት የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ ለመምህር እንቁባህሪም የሹመቱ ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

Sunday, May 6, 2012

"ማኅበረ ቅዱሳን" በአርቤጎና ከተማ ጥዋ ማኅበራትን በአንድነት ስም ለመጨፍለቅ ያደረገው እንቅስቃሴ ተቃውሞ ገጠመው


                                     source:http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
 "ማኅበረ ቅዱሳን" በሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፣ በአርቤጎና ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሥር ያሉትን ልዩ ልዩ የጥዋ ማኅበራትን በአንድ ጥላ ሥር ለማደራጀት ሙከራ ቢያደርግም ተቃውሞ እንደተነሳበት ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የጥዋ ማኅበራት መመሥረትና መደራጀት እንዲሁም የምዕመናን መሰባሰብ እንደጦር የሚያስፈራው "ማኅበረ ቅዱሳን" በተለያዩ ፃድቃን፣ ሰማዕታትና መላዕክት ስም የተመሠረቱትን የጥዋ ማኅበራት በማፍረስ እንቅስቃሴ መጠመዱን በተጨማሪ የደረሰን መረጃ ያሰረዳል፡፡

የአርቤጎና ከተማ አማንያን በተለያዩ የጥዋ ማኀበራት ተደራጅተው ለዘመናት የቆዩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ ተደራጁ የሚለው "ማኅበረ ቅዱሳን" መመሪያ በከፍተኛ መደናገር ውስጥ እንደከተታቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" የጥዋ ማኅበራትን ለመጨፍለቅ ሙከራ ሲያደርግ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም ያሉ ወገኖች እንዳስረዱት፣ ቀደም ሲል በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ገዳምም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አድርጎ የከሸፈበት መሆኑ በተጨማሪ ታውቋል፡፡ በገዳሙ እሰከ 40 የሚደርሱ የጥዋ ማኅበራት የሚገኙ ሲሆን በቅድስት አርሴማ፣ በኪዳነ ምሕረት፣ በቅዱስ ገብርኤል እና በቅዱስ ሚካኤል ስም ብቻ እስከ አሥር፣ አሥር የሚደርሱ የጥዋ ማኅበራት ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች የጥዋ ማኅበራትም ተደራጅተው በእህትማማችና በወንድማማች መንፈስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

Friday, May 4, 2012

«አሁን ደግሞ ገፍተው፤ ገፍተው ማንን ይሆን የሚወረውሩት?»

                                                                      (by dejebirhan)
አንድ ሰሞን የዘመድኩን በቀለ ትኩሳት  «በደጀሰላምና አንድ አድርገን» እንዲሁም በሌሎቹ ውርንጭላ ብሎጎች ሳይቀር፤  ይሄ ነው የተዋህዶ ልጅ፣ ሲኦልም ቢሆን ግባ፤ ውረድ ፣ ዘመድኩን  የአባ ቢላዋ ልጅ፣ ቆራጡ፤ እሳቱ፤ አንድ ለእናቱ፤ ጀግናው ፣ ሰማእቱ ምኑ ቅጡ፤ ያልተባለ፣ ያልተወራ ነገር አልነበረም። ከወሬ አቀባባዮቹ ብሎጎች አንስቶ፤ የወሬ አቀባባዮቹ አስተያየት ሰጪዎች ሁላቸውም በአንድነት፤ በአንድ ጀምበር ዘመድኩንን አጽድቀው፣ እነሱንም የሰማእትነት ሲቃ በሚተናነቃቸው  አስተያየቶች ተዥጎድጉደው ድረ ገጾቹን በእንቶ ፈንቶ አቆሽሸው ዘመድኩንን ከእርቅ አጣልተው ሲያበቁ ለተመኙለት   የእነሱ  ሲኦል (በኛ በኩል ግን እስር ቤት) ዱለውት ሲያበቁና  ፋይሉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መልስ  ሲሆን አንድም አጨብጫቢ ቃሊቲ አብሮት ሳይወርድ ያ ሁሉ ጯሂ የራሱን ኑሮ ወደማሞቁ መመለሱን ታዝበን ተገርመናል፣ ምናልባትም ዘመድኩን ዛሬ ላይ ሆኖ የያኔውን ግፋ በለው ፤ዓይኑን ገልጦ ሲመለከት  ያን ሁሉ ጆፌ አሞራ እንደእኛው ታዝቦ  ምን እንደሚሰማው ስንገምት «ሰውን ማመን ቀብሮ ነው» በተለይም ማቅን ማመን ውሃ መጨበጥ ነው፤ ይል ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ጥሩ የትምህርትና ነገሮችን የማመዛዘን ጊዜ እንደሚሆንለት አይጠረጠርም። በዚያ መጠቀም ሳይችል ቀርቶ በከሰሱኝ  ሰዎች ላይ ቂሜ አይበርድም በሚል  ስሜት  በቀል አርግዞ የሚወጣ ከሆነም ከርቸሌ ውስጥ በችግር ተወልውሎ በተዘጋጀ የልቡ አዳራሽ፤ ከደጅ ቆመው የሚጠብቁት የቂም መናፍስት ወዲያው ገብተው የከፋ ችግር ከሚያመጡበት በቀር እሱ የሚጎዳው ወይም የሚያመጣው አንዳች ነገር እንደማይኖር ከወዲሁ ማስገንዘቡ ተገቢ ነው። ለማንኛውም ቃሊቲ የማስተዋል፣ የመማርና የማገናዘብ ጊዜ እንዲሆንለት ምኞታችን ነው።