Sunday, April 22, 2012

እንኳን ለዳግማይ ትንሳዔ አደረሳችሁ!

ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ላይ የተወሰደ፤

«የዘመኑ ምዕራፍ»


*የዘመኑ ምዕራፍ*
                    (by dejebirhan)
ከህይወት ጎዳናወጥቶ ከመንገዱ
ከወደላይ ትቶ - የምድሩን መውደዱ
ነፍስያውን ሽጦ - ውረድ መዋረዱ
ነፍሱን ከሞት ገደል - ሰቅሎ በፈቃዱ።
                  እረፍት የለሽ ኀፍረት - ተከትሎት ኋላ
                  ከጥልቁ ሰጠመሞኝ ሆኖ ተላላ
                  ብራሪው በረረ - ጥልማሞት አጠላ
                   በሀጢአት ፓራሹትበበደል ዣንጥላ።
 አረፈ በማለፍ - አለፈ በማረፍ
 ሲብከነከን ኖሮ - ሲበርና ሲከንፍ
 ኑረቱ ጨለመ - አንዳችም ሳያተርፍ
 እስከዚያው ነበረ - የዘመኑ ምዕራፍ።

Saturday, April 21, 2012

«እድሜአችን እንዴት ይሮጣል?»

                                            (by dejebirhan)
          የኢትዮጵያ ሚሊኒንየም (እስራ  ምእት) ከተከበረ እነሆ አራት ዓመታት እንደከነፉ አለፉ። አራት ዓመታትን እድሜያችን ሮጧል ማለት ነው። እያንዳንዷ ደቃቅ ሰከንድ እኰ የእድሜ የሩጫ ሰዓት ናት! የሚገርመው ደግሞ እኛ በእረፍት ዓለም እንቅልፍ ውስጥም ሆነን ቢሆን እድሜ መሮጡን አለማቆሙ ነው። ይሮጣል፣ ይሮጣል፣ ይሮጣል!!
የእድሜ ሩጫው አይታይም። አይሰማም። የሚታወቀው በእኛነታችን ላይ በሚያሳየው የሕይወት ለውጥ ብቻ ነው። እድሜ ሩጫውን የሚያበቃው ደግሞ ከዚህ ዓለም ምንም ዓይነት ሽልማት  ሳይቀበል ወይም ባለእድሜውን ሳያማክር በገዛ ሥልጣኑ የባለእድሜውን የዚህ ዓለም ሕይወት ዘመን ለሞት በማስረከብ ነው። ያኔም እድሜ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ» ብሎ ከእኛ ህልፈት በኋላ ሩጫውን ያቆማል። ሟችም ከእድሜው ሩጫ ጋር እኩል ሮጦ ከሆነ እኔም «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የጽድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» ይል ይሆናል።  የሩጫውን ውጤት የሚወስነው ሲያሯሩጠው የነበረው የእድሜውን ሩጫ ተከትሎ የሮጠበት የሩጫ ዓይነትና ይዘት ነው።
አንዳንዶች እድሜያቸው ሮጦ፣ ሮጦ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ በሌሉበትና ባልኖሩበት የዚህ ዓለም ቆይታቸው ግንኙነት የሌለው የሩጫ ዜና ይሰራላቸዋል። ከመቃብራቸው በላይ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የፅድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» የሚል ጥቅስ ይሰፍርላቸዋል። ምናልባት ከእድሜአቸው ጋር የሮጡት ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ በወለድና በአራጣ ለመክበር ሲሮጡ ሆነው ይሆናል። የተበደሩትን ቀምተው፣ በሚስታቸው ላይ ወይም በባላቸው ላይ ወስልተውም ይሆን ይሆናል። እንደክርስቲያን እያማተቡ ወይም ክርስቲያን ስለመሆናቸው አንገታቸው ላይ መስቀል አንጠልጥለው ወይም ክር አስረው ግን አንድም ቀን ክርስትናውን የሕይወታቸው አንድ አካል አድርገው አልኖሩበት ይሆናል። አንዳንዶች በ40 ቀናቸው ወይም በ80 ቀናቸው በእናታቸው ጀርባ ክርስቲያን ከተባሉ በኋላ እድሜ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ በሳጥን ተጭነው ይሆናል ከክርስትናው ጋር የሚተዋወቁት። የእድሜ ፍጻሜ ምስክርነትን ባልዋሉበት ማግኘት ደግሞ አሳዛኙ ነገር ነው።
ብዙዎች ይህንን ኑረት ኖረው በእድሜአቸው ሩጫ ከተለያዩት በኋላ ባሸበረቀ የሀዘን መግለጫ ካርድ ወይም ዝናና መልካም ገመና ገላጭ በሆነው በሕይወት ታሪክ ጽሁፍ ሲመሰገኑ፣ ሲወደሱ ይታያል። የሚያስቆጨው  ነገር ይህ ሁሉ የዝና ግርግር ለሌላኛው ዘመናቸው የማይጠቅም መሆኑን ማወቅ አለመቻል ነው።