Saturday, April 21, 2012

«እድሜአችን እንዴት ይሮጣል?»

                                            (by dejebirhan)
          የኢትዮጵያ ሚሊኒንየም (እስራ  ምእት) ከተከበረ እነሆ አራት ዓመታት እንደከነፉ አለፉ። አራት ዓመታትን እድሜያችን ሮጧል ማለት ነው። እያንዳንዷ ደቃቅ ሰከንድ እኰ የእድሜ የሩጫ ሰዓት ናት! የሚገርመው ደግሞ እኛ በእረፍት ዓለም እንቅልፍ ውስጥም ሆነን ቢሆን እድሜ መሮጡን አለማቆሙ ነው። ይሮጣል፣ ይሮጣል፣ ይሮጣል!!
የእድሜ ሩጫው አይታይም። አይሰማም። የሚታወቀው በእኛነታችን ላይ በሚያሳየው የሕይወት ለውጥ ብቻ ነው። እድሜ ሩጫውን የሚያበቃው ደግሞ ከዚህ ዓለም ምንም ዓይነት ሽልማት  ሳይቀበል ወይም ባለእድሜውን ሳያማክር በገዛ ሥልጣኑ የባለእድሜውን የዚህ ዓለም ሕይወት ዘመን ለሞት በማስረከብ ነው። ያኔም እድሜ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ» ብሎ ከእኛ ህልፈት በኋላ ሩጫውን ያቆማል። ሟችም ከእድሜው ሩጫ ጋር እኩል ሮጦ ከሆነ እኔም «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የጽድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» ይል ይሆናል።  የሩጫውን ውጤት የሚወስነው ሲያሯሩጠው የነበረው የእድሜውን ሩጫ ተከትሎ የሮጠበት የሩጫ ዓይነትና ይዘት ነው።
አንዳንዶች እድሜያቸው ሮጦ፣ ሮጦ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ በሌሉበትና ባልኖሩበት የዚህ ዓለም ቆይታቸው ግንኙነት የሌለው የሩጫ ዜና ይሰራላቸዋል። ከመቃብራቸው በላይ «ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ የፅድቅም አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» የሚል ጥቅስ ይሰፍርላቸዋል። ምናልባት ከእድሜአቸው ጋር የሮጡት ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ በወለድና በአራጣ ለመክበር ሲሮጡ ሆነው ይሆናል። የተበደሩትን ቀምተው፣ በሚስታቸው ላይ ወይም በባላቸው ላይ ወስልተውም ይሆን ይሆናል። እንደክርስቲያን እያማተቡ ወይም ክርስቲያን ስለመሆናቸው አንገታቸው ላይ መስቀል አንጠልጥለው ወይም ክር አስረው ግን አንድም ቀን ክርስትናውን የሕይወታቸው አንድ አካል አድርገው አልኖሩበት ይሆናል። አንዳንዶች በ40 ቀናቸው ወይም በ80 ቀናቸው በእናታቸው ጀርባ ክርስቲያን ከተባሉ በኋላ እድሜ ለሞት ካስረከባቸው በኋላ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ በሳጥን ተጭነው ይሆናል ከክርስትናው ጋር የሚተዋወቁት። የእድሜ ፍጻሜ ምስክርነትን ባልዋሉበት ማግኘት ደግሞ አሳዛኙ ነገር ነው።
ብዙዎች ይህንን ኑረት ኖረው በእድሜአቸው ሩጫ ከተለያዩት በኋላ ባሸበረቀ የሀዘን መግለጫ ካርድ ወይም ዝናና መልካም ገመና ገላጭ በሆነው በሕይወት ታሪክ ጽሁፍ ሲመሰገኑ፣ ሲወደሱ ይታያል። የሚያስቆጨው  ነገር ይህ ሁሉ የዝና ግርግር ለሌላኛው ዘመናቸው የማይጠቅም መሆኑን ማወቅ አለመቻል ነው።

Friday, April 20, 2012

ምን አለበት?

አዳምና ሔዋን

***********

አንተ አዳም ራስ ነህ

ብሏል ቅዱስ ቃሉ፤

አንቺ ሔዋን አንገት ነሽ

ብለው ያወራሉ

እንግዲህ ተስማሙ

አንተ ራስ፤

እርሷ አንገት፤

ብታሽከረክርህ …..

ታዲያስ ምን አለበት?
**********
ከደረጀ በላይነህ

Thursday, April 19, 2012

ማህበረ ቅዱሳንና ሰለፊያ!! ግልባጩ ማነው?

                                                                                              source:awdemihret.blogspot.com
የማህበረ ቅዱሳን ሰለባ የሆኑ ብዙ የቤተክርስቲያን አባቶችና ልጆች ማቅን በአሸባሪነት ከፈረጁት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ማቅ ግን እንዲህ የሚሉኝ ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና ስለቆምኩ ነው በሚል ራሱን ሲከላከል ቆይቷል። ማህበሩ አሸባሪ የመሆኑ ጉዳይም በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ስድበ ሲቆጠር መቆየቱ ይታወሳል። ለማኅበሩ ይህ ስም የተሰጠው በከንቱ አልነበረም። ስራው በአክራሪ ሙስሊሞች ከሚካሄደው የበለጠ እንጂ ያላነሰ ሆኖ ስለተገኘ ነበር ይህ የግብር ስም የወጣለት።

 ዕድሜ የሰጠው ሰው ብዙ ያያልና ይኸው የማህበሩ የግብር ስም ከትናንት በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ጸድቋል። በማኅበሩ ሲገፉና ሲነቀፉ ለኖሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህ እንደ አንድ ትልቅ ድል የሚቆጠር ነው። እንኳንም በትክክል የወጣለት የግብር ስም በማኅበሩ ዘንድ እንደ ስድብ ከመቆጠር አልፎ ትክክለኛ የማህበረ ቅዱሳንን ማንነት የሚገልጥ ስም ሆኖ ተነገረ! ይህን የተናገሩት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሆናቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ብቻ ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያንን ከማሸበር አልፎ አገርንም ለማተራመስ ትልቅ አላማ እንዳለው በመንግስት በኩል የተደረሰበት መሆኑን ያመለክታል።   

በአሁኑ ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው? ምንስ ነው የሚሰራው? አላማው ምንድነው ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚፈልገው የህብረተሰብ ቁጥር እየበዛ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰለፊያን አስመለክተው ሲናገሩ ሰለፊያ የማኅበረ ቅዱሳን ግልባጭ መሆኑን በግልጽ ቋንቋ እንዲህ ሲሉ ነግረውናል። “አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ይታያሉ።” ማኅበረ ቅዱሳን ለክፋት መምህር እንጂ ደቀመዝሙር እንደማይሆን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ማኅበረ ቅዱሳን ስልቶቹንና አካሄዱን ለሰለፊያ ማውረሱን በማያሻማ መንገድ ገልጸዋል፡፡
መቼም ማቅ የሚሰራውን ስራ አስተውሎ ያየ ሰው በማቅና በሰለፊያ(ወሀቢያ) መካካል ያለውን የመንፈስ አንድነት በቀላሉ ይረዳል። ለማስረጃ ያህል፡-