Sunday, April 15, 2012

መልካም የትንሳዔ በዓል ይሁንላችሁ!!!



 "ክርስቶስ ተንስአ እሙታን፣በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን'
 አሠሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፣
ሰላም' እምይእዜሰ፣ ኮነ ፍስሐ ወሰላም"




Friday, April 13, 2012

«ስቅለተ ዓርብና እርግማን!»

መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የአዳምን ልጆች በደልና የሕግ እርግማን ተሸክሞ ቀራንዮ ላይ መሰቀሉን እናውቃለን። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ኢየሱስ  ቤዛ ይሆን ዘንድ ያስገደደው ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ብቻ ነው። ይህንንም አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው «ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት» ሲል ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ገልጾታል። ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ አልነበረውም።

«ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል
ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል» 
ሮሜ ፭፣፰
እንግዲህ ይህ ፍቅር ለእኛ የተደረገው እኛ ደጎች ስለነበርን ሳይሆን የእኛ በደል ከፍቅሩ ውጪ ስላወጣን ዳግም በማያልቀው ፍቅሩ ውስጥ እንድንኖርለት ስለፈለገ ብቻ ነው። ወሰን በሌለው ፍቅሩ ውስጥ እንድንኖርለት አርአያውና ፍለጋውን ሁሉ ሰርቶ አሳይቶናልና የሕይወታችን አንድ አካል እንዲሆንለት ይሻል። ለእኛ የተሰጠው አምላካዊ ፍቅር በእኛ ውስጥ መኖር ይገባዋል። እኛ ኃጢአተኞች ሳለን ከተወደድን ልንጠላው የሚገባው የሰው ልጅ  የለም ማለት ነው። 
በክርስቶስ ደም  የተመሠረተው ወንጌል እኛን ጠላቶቹ ሳለን ወደ ፍቅሩ መመለስን ብቻ ሳይሆን «ጠላትህን ጥላ» የሚለውንም የጥል ሕግ አፍርሶ «ጠላትህን ውደድ» የሚልም ትእዛዝ ትቶልናልና ነው።

« ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና» ሮሜ ፭፣፵፫-፵፭
 የሰማዩ አባታችን ልጆች እንሆን ዘንድ ለእኛ ለተጠላነው ጥልቅ ፍቅሩን በልጁ ሞት ስላሳየ እኛም እንዲሁ በፍቅሩ የልጅነት ሕይወት ውስጥ ለመቆየት የግድ ጠላቶቻችንን መውደድ፣ የሚረግሙንን መመረቅ፣ ለሚጠሉን መልካም እንድናደርግ ይፈልጋል። ከጥላቻና ከእርግማን ጎራ ወደ ፍቅርና በጎነት መንፈሳዊ ዓለም እንድንገባ ያዘናል። ያለበለዚያማ ልጆቹ ልንሆን እንዴት ይቻላል? ፍቅርና እርግማን መቼም ቢሆን ስምምነት ይኖራቸው ዘንድ አይታሰብም። ስለዚህም የፍቅር አባት ልጆች ረጋሚዎችና ጥላቻን የተሞሉ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። 
በእርግጥ በአፋችን የሰማዩ አባታችን ልጆች ስለመሆናችን እንናገር ይሆናል። ልዩነቱን ግን  በእኛ ላይ የሚገልጠው ልጅነታችንን ስላወራን ሳይሆን የሚመሰክርብን ፍቅር የራቀው ማንነታችን  ነው። ቃሉን የሚያወሩ እንጂ የማያደርጉ ስለሆንን ስንት የእርቅ በሮችን ዘግተን በጥላቻና በእርግማን ዓለም ውስጥ ዛሬም ድረስ አለን።

Thursday, April 12, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ላይ የስለላ መዋቅሩን ዘረጋ

    • “የቤተክርስቲያን አባቶች የጻፉትን መጻህፍትም ሆነ የቤተክርስቲያን አባቶችን መቶ በመቶ አንቀበልም። መቶ በመቶ የምንቀበለው መጽሐፍ ቅዱስንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ነው።”                                                                               ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ                               source: awdemihret.blogspot.com
ማኅበረ ቅዱሳን በየወሩ በሚያካሂደው የማኅበሩ አባላት የሆኑ አገልጋዮች ውይይት  ላይ የማኅበሩ አፍ ሆኖ በተለያዩ ቦታዎች እና አዳራሾች በግንዛቤ አስጨብጣለሁ ስም፣ ያለ አንዳች ማስረጃ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችን “ተሀድሶ - መናፍቃን ናቸው” እያለ መግለጫ ሲሰጥ የነበረው ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በቤተክርስቲያን ታሪክ «አውጣኪ መናፍቅ ነው» የተባለው ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ነው ሲል ለአውጣኪ ተከላከለ።

የካቲት 29 2004 ዓ.ም. በአዲስ ቪው ሆቴል በተካሔደው በዚህ ወርሀዊ ጉባኤ ላይ ለጥናት የቀረበው ርዕስ “ቅድመ ኬልቄዶን ጉባኤ የኬልቄዶን ጉባኤ እውነታና ድኅረ ኬልቄዶን ጉባኤ” የሚል ሲሆን፣ የጽሁፉም አቅራቢ የማህበሩ ቀኝ እጅ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ነው። የጥናቱ ዋና ትኩረት የአውጣኪና የፍላብያኖስን ጠብና የአውጣኪን መወገዝ የተመለከተ ነው። ያረጋል እንዳለው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተቻለውን ያህል ልዩ ልዩ መዛግብትን ለማገላበጥ የሞከረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህም በመነሳት የደረሰበት ድምዳሜ “አውጣኪ የተወገዘው መናፍቅ ሆኖ ሳይሆን በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበሩት በነፍላብያኖስ ጥላቻ ነው” የሚል ነው። ይህም እንደ ጥናቱ ባለቤት እንደ ያረጋል አመለካከት “በወቅቱ አውጣኪ ላይ የቀረበው ክስ በእምነት ሳይሆን በጥላቻ የቀረበ ነው። ከዚህም በመነሳት ክሱ መሠረታዊውን አጀንዳ የሳተ እና በሀይማኖት ሽፋንነት የቀረበ ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል።” ብሏል።

ያረጋል ይህንን ሀሳቡን ሲያጠናክር በዋነኛነት እንደ ምክንያት የሚከተለውን አቅርቧል፤ “አውጣኪን መናፍቅ የሚያደርግ አንድም መረጃ አልተገኘም። አውጣኪ የተወገዘው በትክክለኛ እምነቱ ነው። በገዳሙ ውስጥ በእውነተኛ እምነቱ እና በትክክለኛ የምንኩስና ህይወቱ ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የመገኘት ፍላጎት አልነበረውም። በጉባኤው ላይ ላለመገኘትም ሕመምና የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርቦ እንደ ነበር ያካሄድኩት ጥናት ያስረዳል። ይሁንና ያኔ ስልጣን ላይ የነበሩት አካላት በግፍ በጉባኤው ላይ እንዲቀርብና ምንም አይነት ሀሳብ ሳያቀርብ ጥያቄም ሳይጠየቅ መልስም ሳይሰጠው መናፍቅ ነው ብለው ብዙ ጫና አድርገውበታል።” ሲል ለአውጣኪ ትክክለኛ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሯል።