Thursday, April 12, 2012

ሰባኪ፣ አስተማሪ ወይም ፖስተር (POSTER፣PASTOR) ማነው?

(BY DEJEBIRHAN)
በእውነት፣ እውነተኛ ሰባኪ ማነው? ምን ይመስላል? ምንስ መምሰል አለበት? በዚህ ዘመን ምላሽ የሚያስፈልገውና በቂ መልስም ያልተገኘለት አገልግሎት ቢኖር ይህ «ሰባኪ» የሚባለው የግብር ማንነትን የሚገልጸው ቃል ነው። መልሱ ያልተገኘው፣ መልስ ስለሌለው ሳይሆን መልስ የሚያስፈልገው የሰባኪነት ሕይወት በዘመናችን ከመጥፋቱ የተነሳ ነው። ዳዊት ሁሉም የስህተት መንገድ ሂያጆችን በሚኖሩበት ውድቀት ውስጥ « ኵሉ ዐረየ፣ ወኅቡረ ዐለወ» ሲል ያስቀምጠዋል። መዝ ፲፬፣፲፫
የሰባኪነት አገልግሎትና ሕይወቱን በተመለከተ ከታች በጥቂቱ እንመለከታለን።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው «ሰባኪ»የሚለውን ቃል እንዲህ ይፈቱታል።


ወንጌላችንም በተረዳነው እውነት ሰባኪ ማለት እንዲህ ዓይነት ነው ይለናል።


«ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው» 

ሮሜ ፲፣፰

የሚሰብክ የሚሰብከውን ያመነ ካልሆነ የሚሰብከውን ሰው እንዴት ማሳመንና በሚያምነው እውነት እንዲኖር ማድረግ ይችላል? ሰባኪ የሚሰብከውን ያመነና የሚያወራው ብቻ ሳይሆን የሚሰብከውን እምነት የወንጌል አደራ ራሱ የሚጠብቀው ካልሆነ እንዴት ሕይወትን በሰዎች ውስጥ መዝራት ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በአንድ ወቅት እንደገለጸው ስብከት ለሰባኪው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መቀበልና ይህንንም የመቀበል አደራ በተገለጠለት ቃሉ መሠረት የመጠበቅ ግዴታ መሆኑን አስረግጦ በመናገርና በዚህም አደራው  በጳውሎስ ስብከት የተነሳ ቲቶ ሃይማኖት ልጁ ለመሆን መብቃቱን እናነባለን።

«በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ
በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን»

ከዚህ ቃል የምንረዳው  ሰባኪ የሚሰብከው እግዚአብሔር እንዳዘዘውና ስብከቱም በተሰጠው የስብከት አገልግሎት ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል አደራውን  በመግለጥ ሌሎች ወደ እውነተኛ የሃይማኖት ኅብረት እንዲመጡ ማስቻል መሆኑን ነው።
ሰባኪ የታዘዘውን ቃል  በተሰጠው አደራ መሠረት ለሌሎች ማድረስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚያዩለት የሰባኪነት አገልግሎት ሕይወትም በኑሮው ሁሉ ሊታይ የግድ ነው።  ጳውሎስ ይህንን ነገር በራሱ ላይ የሰባኪነት አገልግሎት ምስክሮቹ በስብከቱ ቃል ወደ እምነት ኅብረት የመጡ ምእመናንና ምእመናት ስለመሆናቸው እንዲህ ሲል ያስረዳናል።

Wednesday, April 11, 2012

ስለ ሰንበት ወደ እሁድ መቀየር

ሰንበት የሚለው ቃል ከእብራይስጡ Shabbat (שַׁבָּת) ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም ከድካም ማረፍ ወይም ሥራን ማቆም (to cease or to desist from exertion) ማለት ነው።

ሰንበት እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ከሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ አንዱ ነው።

Quote:
ኦሪት ዘጸአት 20
8 የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።
9 ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ
10 ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ
11 እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።

የቃሉ ትርጉምና እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሰንበት ከድካምና ከሥራ ሰዎችና እንስሳት የሚያርፉበት የእረፍት ቀን ነው። በተለይ ከሰንበት ጋር ተያይዞ የተጠቀሱት ሎሌዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ባሪያዎችና ከብቶች በዚያን ጊዜ እጅግ አድካሚ ሥራ ይሠሩና ይለፉ የነበሩ ናቸው። ሰለዚህ ሰንበት በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ከሠራው ሥራ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ ሁሉ ከሥራና ከድካም ማረፍ ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህ ነው ሰውን ብቻ ሳይሆን የአምልኮ ፕሮግራም ማድረግ የማይችሉትን ከብቶችንም የሰንበት ትእዛዝ የሚያጠቃልለው።

ከዚህ በተጨማሪ ሰንበት በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል የተደረገ የምልክት ቃል ኪዳን ነው። እንደማናቸውም የብሉይ ኪዳን ሕግ ሰንበትም በማያከብሩት ላይ መርገምና ፍርድ የሚያመጣም ትእዛዝ ነው።
Quote:
ኦሪት ዘጸአት 31
12 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
13 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ።
14 ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።
15 ስድስት ቀን ሥራን ሥራ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል
16 የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ።
17 እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው

ብዙ ጊዜ ሰንበት ተብሎ በልማድ የሚታወቀው ሥራ የማይሠራበትንና የአምልኮ ፕሮግራሞች የሚካሄዱበትን ቀን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰንበት የሚባለው በእስራኤልና በእግዚአብሔር ብቻ የተገባን ቃል ኪዳን ነው። በዚያ ቀን "የአምልኮ ፕሮግራም የማይካፈል ይሙት" ሳይሆን ትእዛዙ የሚለው "በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል" የሚል ፍርድና ቅጣት ያለው ነው። በብሉይ ኪዳንም ይሁን በአሁኑ ዘመን እስራኤላውያን ሰንበትን የሚጠብቁት ቅዳሜ ነው፡፡

ክርስቲያኖች ሰንበትን ይጠብቁ ዘንድ አልታዘዙም። በእርግጥ እስራኤላዊ ሆነው ወደ ጌታ እምነት የሚመጡ ሰንበትን መጠበቅ ይችላሉ አልተከለከሉም። ነገር ግን ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም። እስራኤላዊ ባልሆኑ አህዛብ ክርስቲያኖችም ዘንድ በአዲስ ኪዳን ሰንበት ሲጠበቅ ይሁን ሰንበትን እንዲጠብቁ ሲታዘዙ አናነብብም። ይህ ብቻ አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ይጠብቁትና ያከብሩት ዘንድ የተሰጠ ምንም ዓይነት ቀን ወይም በዓል የለም። ክርስትና የቀኖችና የበዓላቶች አክብሮ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሕይወት ነውና። 

Monday, April 9, 2012

በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሚመራው የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤት በምዕራብ አሜሪካ ካሊፎርኒያና አካባቢው የተቋቋመውን የስቴት ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናቱን አስታወቀ

ከአባ ሰላማ ብሎግ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ብጹእ አቡነ ፋኑኤል ከዚህም ቀደም በየእስቴቱ ሊቃነ ካህናትን በመመደብ የአስተዳደር መዋቅራትን እያደራጁ እንደነበረው ሁሉ በተቀሩት  ስቴቶችም መዋቅራቸውን በማስፋት ተጨማሪ ሊቀካህናትና የአስተዳደር አካላትን የመደቡ መሆናቸውን ታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአህጉረ ስብከቱን ጽ/ቤት መንፈሳዊ የአስተዳደር ጉባዔ አባላትን በአዲስ መልክ እንዳዋቀሩ ዘገባው በተጨማሪ ያመለክታል። የመንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ አባላትን በአዲስ መልክ ማደራጀቱ ለአህጉረ ስብከቱ የሥራ እንቅስቃሴ የተሻለ እንደሚሆን ቢታመንም ለአንዳንድ ወገኖች ይህ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ታስቦ እንቅፋት ሊዘጋጅለት ይችላል። በተለይም እነዚህ የአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት መንፈሳዊ የአስተዳደር ጉባዔ አባላት በአዲስ መልኩ መዋቀር እጀ ረጅም ለሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ መርዶ ብቻ ሳይሆን ራስ ምታት እንደሚፈጥርበት «ደጀ ብርሃን» ብሎግ ታምናለች። ለዚህም መዋቅር መፍረስ የሚቻለውን ሁሉ ኃይልና በጀት እንደሚመድብ ከማኅበሩ ተፈጥሮ የተነሳ ግምት ይወሰዳል። ከዚያም ባሻገር  ሊቀ ጳጳሱ ምድረ አሜሪካ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በማኅበረ ቅዱሳን የጥላቻ ፈንገስ (Fungus) የተጠቃው አሮጌው ቡድን ይፈጽም የነበረው የህውከት በሽታ በዚህ ፍቱን የመዋቅር መድኃኒት የተነሳ እየመረዘ እንዳይቀጥል  ፈውስ የተሰጠበት ስለሆነ   ፈንገሱ ለመመለስ የሚያደርገውን መፍጨርጨር አብሮ መከላከያውን በመፍጠር መዋቅሩን ማጠናከር እንደሚገባ «ደጀ ብርሃን» አጥብቃ ታሳስባለች።
በተሰጠው የሊቀ ጳጳሱ የአስተዳደር መዋቅር ድንጋጤና ንዴት የተነሳ የአፈ ማኅበሩ ብሎጎች ፈንገሱን በምረዛው ለማስቀጠል ዘመቻቸውን እንደሚከፍቱ ይጠበቃል። ይህንን ዘመቻ መቋቋም የሚቻለው  መዋቅሩ ከደብዳቤ ባለፈ መሬት ላይ የሚታይ መሆን ሲችል ብቻ በመሆኑ ብሎጋችን ስለምታምን ከማሳሰቡ ጋር በጸሎት ጭምር የምታግዝ መሆኑን አቋሟን ትገልጻለች።
እስከዚያው ድረስ በሊቀጳጳሱ የተሰጠውን የአስተዳደር መዋቅር ደብዳቤዎችን ለመመልከት፤
                                           ( እዚህ ላይ ይጫኑ )