Wednesday, April 11, 2012

ስለ ሰንበት ወደ እሁድ መቀየር

ሰንበት የሚለው ቃል ከእብራይስጡ Shabbat (שַׁבָּת) ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም ከድካም ማረፍ ወይም ሥራን ማቆም (to cease or to desist from exertion) ማለት ነው።

ሰንበት እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ከሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ አንዱ ነው።

Quote:
ኦሪት ዘጸአት 20
8 የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።
9 ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ
10 ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ
11 እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።

የቃሉ ትርጉምና እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሰንበት ከድካምና ከሥራ ሰዎችና እንስሳት የሚያርፉበት የእረፍት ቀን ነው። በተለይ ከሰንበት ጋር ተያይዞ የተጠቀሱት ሎሌዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ባሪያዎችና ከብቶች በዚያን ጊዜ እጅግ አድካሚ ሥራ ይሠሩና ይለፉ የነበሩ ናቸው። ሰለዚህ ሰንበት በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ከሠራው ሥራ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ ሁሉ ከሥራና ከድካም ማረፍ ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህ ነው ሰውን ብቻ ሳይሆን የአምልኮ ፕሮግራም ማድረግ የማይችሉትን ከብቶችንም የሰንበት ትእዛዝ የሚያጠቃልለው።

ከዚህ በተጨማሪ ሰንበት በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል የተደረገ የምልክት ቃል ኪዳን ነው። እንደማናቸውም የብሉይ ኪዳን ሕግ ሰንበትም በማያከብሩት ላይ መርገምና ፍርድ የሚያመጣም ትእዛዝ ነው።
Quote:
ኦሪት ዘጸአት 31
12 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
13 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ።
14 ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።
15 ስድስት ቀን ሥራን ሥራ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል
16 የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ።
17 እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው

ብዙ ጊዜ ሰንበት ተብሎ በልማድ የሚታወቀው ሥራ የማይሠራበትንና የአምልኮ ፕሮግራሞች የሚካሄዱበትን ቀን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰንበት የሚባለው በእስራኤልና በእግዚአብሔር ብቻ የተገባን ቃል ኪዳን ነው። በዚያ ቀን "የአምልኮ ፕሮግራም የማይካፈል ይሙት" ሳይሆን ትእዛዙ የሚለው "በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል" የሚል ፍርድና ቅጣት ያለው ነው። በብሉይ ኪዳንም ይሁን በአሁኑ ዘመን እስራኤላውያን ሰንበትን የሚጠብቁት ቅዳሜ ነው፡፡

ክርስቲያኖች ሰንበትን ይጠብቁ ዘንድ አልታዘዙም። በእርግጥ እስራኤላዊ ሆነው ወደ ጌታ እምነት የሚመጡ ሰንበትን መጠበቅ ይችላሉ አልተከለከሉም። ነገር ግን ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም። እስራኤላዊ ባልሆኑ አህዛብ ክርስቲያኖችም ዘንድ በአዲስ ኪዳን ሰንበት ሲጠበቅ ይሁን ሰንበትን እንዲጠብቁ ሲታዘዙ አናነብብም። ይህ ብቻ አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ይጠብቁትና ያከብሩት ዘንድ የተሰጠ ምንም ዓይነት ቀን ወይም በዓል የለም። ክርስትና የቀኖችና የበዓላቶች አክብሮ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሕይወት ነውና። 

Monday, April 9, 2012

በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሚመራው የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤት በምዕራብ አሜሪካ ካሊፎርኒያና አካባቢው የተቋቋመውን የስቴት ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናቱን አስታወቀ

ከአባ ሰላማ ብሎግ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ብጹእ አቡነ ፋኑኤል ከዚህም ቀደም በየእስቴቱ ሊቃነ ካህናትን በመመደብ የአስተዳደር መዋቅራትን እያደራጁ እንደነበረው ሁሉ በተቀሩት  ስቴቶችም መዋቅራቸውን በማስፋት ተጨማሪ ሊቀካህናትና የአስተዳደር አካላትን የመደቡ መሆናቸውን ታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአህጉረ ስብከቱን ጽ/ቤት መንፈሳዊ የአስተዳደር ጉባዔ አባላትን በአዲስ መልክ እንዳዋቀሩ ዘገባው በተጨማሪ ያመለክታል። የመንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ አባላትን በአዲስ መልክ ማደራጀቱ ለአህጉረ ስብከቱ የሥራ እንቅስቃሴ የተሻለ እንደሚሆን ቢታመንም ለአንዳንድ ወገኖች ይህ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ታስቦ እንቅፋት ሊዘጋጅለት ይችላል። በተለይም እነዚህ የአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት መንፈሳዊ የአስተዳደር ጉባዔ አባላት በአዲስ መልኩ መዋቀር እጀ ረጅም ለሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ መርዶ ብቻ ሳይሆን ራስ ምታት እንደሚፈጥርበት «ደጀ ብርሃን» ብሎግ ታምናለች። ለዚህም መዋቅር መፍረስ የሚቻለውን ሁሉ ኃይልና በጀት እንደሚመድብ ከማኅበሩ ተፈጥሮ የተነሳ ግምት ይወሰዳል። ከዚያም ባሻገር  ሊቀ ጳጳሱ ምድረ አሜሪካ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በማኅበረ ቅዱሳን የጥላቻ ፈንገስ (Fungus) የተጠቃው አሮጌው ቡድን ይፈጽም የነበረው የህውከት በሽታ በዚህ ፍቱን የመዋቅር መድኃኒት የተነሳ እየመረዘ እንዳይቀጥል  ፈውስ የተሰጠበት ስለሆነ   ፈንገሱ ለመመለስ የሚያደርገውን መፍጨርጨር አብሮ መከላከያውን በመፍጠር መዋቅሩን ማጠናከር እንደሚገባ «ደጀ ብርሃን» አጥብቃ ታሳስባለች።
በተሰጠው የሊቀ ጳጳሱ የአስተዳደር መዋቅር ድንጋጤና ንዴት የተነሳ የአፈ ማኅበሩ ብሎጎች ፈንገሱን በምረዛው ለማስቀጠል ዘመቻቸውን እንደሚከፍቱ ይጠበቃል። ይህንን ዘመቻ መቋቋም የሚቻለው  መዋቅሩ ከደብዳቤ ባለፈ መሬት ላይ የሚታይ መሆን ሲችል ብቻ በመሆኑ ብሎጋችን ስለምታምን ከማሳሰቡ ጋር በጸሎት ጭምር የምታግዝ መሆኑን አቋሟን ትገልጻለች።
እስከዚያው ድረስ በሊቀጳጳሱ የተሰጠውን የአስተዳደር መዋቅር ደብዳቤዎችን ለመመልከት፤
                                           ( እዚህ ላይ ይጫኑ )

Saturday, April 7, 2012

ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር ማቴ ፳፩፣፱




«ሆሳዕና» ቃሉ ከሁለት አረማይክ ቃላት የተሰራ ሲሆን ትርጉም «እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው። እብራይስጡም  ይህንኑ ቃል ወርሶ «הושענא » ሆሻአና ሲል ይገኛል። አዎ «አሁን አድን፣ እባክህ እርዳን» ብሎ የአዳም ዘር ያጣውን ልጅነትና የደረሰበትን ሞት ለመላቀቅ የሚያሰማው የጩኸት ድምጽ ነው፣ «ሆሳዕና»!!!
ዳዊት ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ ተመልክቶ ማዳኑን ሲጣራና አሁን ናልን ሲል ከዘመናት በፊት አድምጠነዋል። የውስጥ ዓይኖቹ ሩቅ አይተዋል። ማዳኑንም ሽተው እንዲህ ሲል ዘምሮለታል።
«አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» መዝ ፻፲፰፣፳፭ 
ያ ማለት ደግሞ « אָנָּ֣א  יְ֭הוָה  הֹושִׁ֘יעָ֥ה  נָּ֑א  אָֽנָּ֥א  יְ֝הוָ֗ה  הַצְלִ֘יחָ֥ה  נָּֽא   » አና ያኽዌ ሆሳአና አና ያኽዌ ሆስሊኻ  ና» የሚለው የእብራይስጡ ቃል ነው።
አበው የማዳኑን ነገር አስቀድመው አይተው በተስፋ «ሆሳዕና» እያሉ ዘምረዋል። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በክርስቶስ ኢየሱስ እስኪገለጥ ዘወትር በእንባና በዝማሬ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር።
አዎ ንጉሥ ክርስቶስ ከዘጠና ዘጠኙ በጎች መካከል የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንደንጉሥ ያይደለ በአህያ፣ ለዚያውም በውርንጫ ተቀምጦ «የአሁን አድን (ሆሳዕና)»  ጩኸት ሊመልስ በጽዮን ከተማ ይመጣል፤ ይህንንም ዘካርያስ ከዘመረው ዘመናት ተቆጥረው ነበር።
«አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል» ዘካ ፱፣፱
ምንኛ ይደንቅ? ምንኛስ ይረቅ? ንጉሥ ስለመምጣቱ አስቀድመው የተናገሩለትና  ከዘመናት በፊት ማዳኑን አይተው በእልልታ የዘመሩለት!!
ሰማያዊ ንጉሥ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ከስጋችን ተዛምዶ ማዳኑን ሲጠብቁ፤ ከሩቅ አይተው ሲጣሩ፣ ሲዘምሩለትና አንድ ቀን ማዳኑ እንደሚሆን ተስፋ ሲያደርጉት የነበረው ሰዓቱ ደርሶ በመካከላቸው ሲገኝ ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ሳይሆን  ውበት የሌለውን ንጉሥ  ለመቀበል የገዛ ወገኖቹ ተቸግረው ነበር።
አዎ የደም ግባት ብቻ ሳይሆን የንጉሥ ወግ የሌለው፣ በአህያ ለዚያውም በውርንጫ የሚመጣ ንጉሥ እንዴት ይቀበሉት?