«ሆሳዕና»
ቃሉ ከሁለት አረማይክ ቃላት የተሰራ ሲሆን ትርጉም «እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው። እብራይስጡም ይህንኑ ቃል ወርሶ «הושענא » ሆሻአና ሲል ይገኛል። አዎ «አሁን አድን፣ እባክህ እርዳን» ብሎ የአዳም ዘር ያጣውን ልጅነትና የደረሰበትን ሞት
ለመላቀቅ የሚያሰማው የጩኸት ድምጽ ነው፣ «ሆሳዕና»!!!
ዳዊት
ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ ተመልክቶ ማዳኑን ሲጣራና አሁን ናልን ሲል ከዘመናት በፊት አድምጠነዋል። የውስጥ ዓይኖቹ ሩቅ አይተዋል።
ማዳኑንም ሽተው እንዲህ ሲል ዘምሮለታል።
«አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» መዝ ፻፲፰፣፳፭
ያ
ማለት ደግሞ « אָנָּ֣א יְ֭הוָה
הֹושִׁ֘יעָ֥ה
נָּ֑א אָֽנָּ֥א יְ֝הוָ֗ה
הַצְלִ֘יחָ֥ה נָּֽא » አና ያኽዌ ሆሳአና አና ያኽዌ ሆስሊኻ ና» የሚለው የእብራይስጡ ቃል ነው።
አበው
የማዳኑን ነገር አስቀድመው አይተው በተስፋ «ሆሳዕና» እያሉ ዘምረዋል። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በክርስቶስ ኢየሱስ እስኪገለጥ
ዘወትር በእንባና በዝማሬ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር።
አዎ
ንጉሥ ክርስቶስ ከዘጠና ዘጠኙ በጎች መካከል የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንደንጉሥ ያይደለ በአህያ፣ ለዚያውም
በውርንጫ ተቀምጦ «የአሁን አድን (ሆሳዕና)» ጩኸት ሊመልስ በጽዮን
ከተማ ይመጣል፤ ይህንንም ዘካርያስ ከዘመረው ዘመናት ተቆጥረው ነበር።
«አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና
አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል» ዘካ ፱፣፱
ምንኛ
ይደንቅ? ምንኛስ ይረቅ? ንጉሥ ስለመምጣቱ አስቀድመው የተናገሩለትና ከዘመናት በፊት ማዳኑን አይተው በእልልታ የዘመሩለት!!
ሰማያዊ
ንጉሥ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ከስጋችን ተዛምዶ ማዳኑን ሲጠብቁ፤ ከሩቅ አይተው ሲጣሩ፣ ሲዘምሩለትና
አንድ ቀን ማዳኑ እንደሚሆን ተስፋ ሲያደርጉት የነበረው ሰዓቱ ደርሶ በመካከላቸው ሲገኝ ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ሳይሆን ውበት የሌለውን ንጉሥ ለመቀበል የገዛ ወገኖቹ ተቸግረው ነበር።
አዎ
የደም ግባት ብቻ ሳይሆን የንጉሥ ወግ የሌለው፣ በአህያ ለዚያውም በውርንጫ የሚመጣ ንጉሥ እንዴት ይቀበሉት?