Saturday, April 7, 2012

አለ በየቦታው ዋሾና ቀጣፊ!

 
                      ዋሾ፤ ቀጣፊ
                                           (ከደጀብርሃን)
እንዲያው ቅጥፍ አርጎ የነገር አበባ
ሳይሸተው የሚያበን የዲስኩር ገለባ
የሰው አረማሞ የሆነ ፍሬ አልባ
መጎንጎን ማፍተልተል፣ተንኮልና ደባ
ሳይጠሩት የሚጮህ ፣ጣልቃ የሚገባ
በከቸቸ ዓይኑ፤ እንደአዞ የሚያነባ
ነጩን የሚያጠቁር ክፋት የሚቀባ
ሰው መሳይ በሸንጎ ፣ለብሶ የእድሜ ካባ
 አለ በሰፈሩ፣ አለ በሀገሩ፣
በዋሾ የተወጋ፣ አለ በመንደሩ፣
                        ያለቀሰም አለ፣ እንባን የፈሰሰ፣ ኑሮን ያመረረ
                        ተወግቶ የደማ ፣ ውስጡ የጠቆረ፣
                        ትዳሩ የፈረሰ፣ ሜዳ ላይ የቀረ
                     ተሰርቶበት ነገር፣ ውድቀት የቆጠረ፣
                     ጓደኛን የጠላ፣ ጸብን ያከረረ፣
                     አለ የተወጋ፣ አለ የተነካ በዋሾ ቀጣፊ
                     በሀሰት ዲስኩሩ፣ በነገር ፈልሳፊ
                   በሃይማኖት ስፍራ፣ አለ መስቀል ይዞ፣
                   እያለቃቀሰ ልክ ፣ እንደአዞ፣
                   ጸብን እየዘራ፣ በሀሰት ደንዝዞ፣
                   አለ በየቢሮው፣ ወንበር ተደግፎ፣
                   አብስሎ ሚያበላ፣ የተንኮልን ገንፎ፣
                   አለ በአስኳላው፣ ደብተር ተሸክሞ፣
                  አጋጭቶ የሚስቅ፤ በክፋት አላትሞ፣
አለ በየቦታው ዋሾና ቀጣፊ
በምታልፈው እድሜ፣ ሳይመስለው አላፊ።
በምታልፈው እድሜ ሳይመስለው አላፊ፣
                        ዛሬም ገና አለ
 ዋሾና ቀጣፊ........

Friday, April 6, 2012

ዘሪሁን ሙላቱ ከቡታጀራ፣ ዳንኤል ግርማ ከደሴ፣ "ቀኝ ኋላ ዙር" ተባሉ

                             የጽሁፉ ምንጭ፣ dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
በረጅም ምላስ እና በፈሪሳዊ ፍልስፍና ከሚታወቁት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ቀንደኛ ነውጠኞች መካከል ዘሪሁን ሙላቱ እና ዳንኤል ግርማ የተባሉት ግለሰቦች ከቡታጀራ እና ደሴ ከተሞች በመጡበት እግራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ከየሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘሪሁን ሙላቱ ከቡታጀራ የተባረረው ማንም ሳይወክለውና ሳይልከው ዓመታዊውን የመድኃኔዓለም በዓለ ንግሥ ተደግፎ ለራሱ ዝናና እና መልካም ገፅታ ግንባታ በማሰብ ዐውድ ምሕረት ላይ ለመስበክና "ኦርቶዶክስ መልስ አላት" በሚል ርዕስ ያሳተመውን ቪሲዲ ቸብችቦ ኪሱን በብር ለመሙላት አስልቶ ወደ ስፍራው በመሄዱ መሆኑን ውስጥ ዐዋቂ ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡

ዘሪሁን ከወንድወሰን ጋር በመሆን "ሀገር-አማን" ብሎ ወደ ቡታጀራ የገሰገሰ ሲሆን፣ በትላንትናው ዕለት (መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም) በቡታጀራ ደብረ ሠላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተገኝቶ ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ለመስበክ ዕድል እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በሥፍራው የነበሩ የሀገረስብከቱ ሠራተኞች፣ የደብሩ አለቆችና የልዩ ልዩ ክፍል የሥራ ኃላፊዎች ማንነቱን ይጠይቁታል፡፡ ዘሪሁንም፣ "እኔ መምህር ዘሪሁን ሙላቱ" እባላለሁ በማለት ይጀምርና ስለ ራሱ ማንነትና አስተዋጽዖ አጉልቶና አግዝፎ መተንተን ይጀምራል፡፡ ካህናቱም "ለመሆኑ ይህንን ስትለን ተዘዋውረህ ለመስበክ የሚያስችልህ ፈቃድ አለህ ወይ"? ይሉታል፡፡ እርሱም በቀጥታ "የለኝም" ሳይላቸው ታዋቂ ሰባኪ ነኝ፤ ብዙ ቦታ ተገኝቼ አስተምሬአለሁ በማለት ቀጥተኛ መልስ መስጠት ሳይችል ይቀራል፡፡ "እሺ ወደዚህ ስትመጣ ማን እንደላከህ ልትነግረን ትችላለህ? ለዛሬ እዚህ መጥተህ እንድትሰብክ የተመደብክበት ወይም የታዘዝክበት ደብዳቤ ልታሳየን ትችላለህ"? ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም አንዱንም ጥያቄ በአግባቡ ሳይመልስላቸው ይቀራል፡፡ 

Thursday, April 5, 2012

የአባ ፋኑኤልን ጵጵስና የሚሽር ደብዳቤ የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ብሎግ በሆነው «ደጀሰላም» ላይ ወጣ


 አባ ፋኑኤልን ከጵጵስና ሽረናል የሚለው የኦርቶዶክስ ወሀቢያዎችን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
አባ ፋኑኤል ወደምድረ አሜሪካ እንዳይገቡ በደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያመለከተው የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ማኅበር አባላት በጥቅምቱ ሲኖዶስ ከዳር ዳር በየብሎጋቸው ሲንጫንጩ እንደነበር ያስቀረናቸው መረጃዎች የሚያረጋግጡልን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ናቸው።
እንግዲህ አባ ፋኑኤል ወደአሜሪካ እንዳይገቡ አስቀድሞ በመዋጋት፤ ያ ሳይሆን ሲቀርና ምድረ አሜሪካ መግባታቸው ሲታወቅ ደግሞ ወደ ሀገረስብከቱ እንዳይመጡ አንድም የወፍ ዘር ዝር ሳይልና ሳይቀበላቸው ከመቅረቱም በላይ በአባ አብርሃምና በአንዲት ሴት ስም የግል ንብረትነት እንደተመዘገበ በሚነገርለት ሀገረ ስብከት መሄድ  ባይችሉና  በሩ ሁሉ ቢዘጋባቸው፣ በሰላም ጊዜ ወደተከሉት ቤተክርስቲያን ሄደው በዚያ ቢያርፉ ደግሞ በግላቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ መሽገዋል ብሎ ስም በማጥፋት፤ ሥራ የተጠመዱት የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ማኅበር (ማቅ) አባላት ይህንንም እንደኃጢአት በመቁጠር የከሳሽነት ድርሻቸውን በደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ የላኩ መሆናቸውም የሚዘነጋ አይደለም። የቆዩ ደብዳቤዎችን ለማየት ከፈለጉ ይህንን ይጫኑ
ከነዚህ የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ማኅበር (ማቅ) አቀንቃኞችና አሸርጋዶች አንዱ ይኼው ቄስ ነኝ የሚለው ዶ/ር የተሰጠውን የአገልግሎት ድርሻ እየተወጣ ወደቤቱ ወይም ወደእንጀራ መብያ ስፍራው በመመለስ ትህትናን ገንዘብ ማድረግ ሲገባው እንደወሀቢዝም ዓላማ(ማቅ) የአስተሳሰብ ሱሪውን አሳጥሮ ሁከት፤ብጥብጥ፣ የሥራ እንቅፋትና አባ ፋኑኤልን የማደናቀፍ ተልእኰውን ለመወጣት ሲባትል ሊቀጳጳሱ በምክር፣ በተግሳጽ፣ እና በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ከእኩይ ኢ-ቅስና ተግባሩ እንዲታቀብ ቢያስታምሙትም እሱ እንደፍርሃትና እጅን እንደመስጠት ስለቆጠረው በተለመደው ወሀቢያ አገልግሎቱ ቀጥሎበት ስላገኙት «ሰይፍ ዘክልዔ አፉሁ» በሆነው ስልጣናቸው በዐመጽ ያደፈ ልብሱን ከላዩ ላይ ቀደው ቢጥሉለት ሊያመሰግን ሲገባው በሌለው አቅምና ስልጣን «ረስጠብ» እንደዚህ እያለ እንደሚጠቅሰው የእርስዎም ስልጣን ተገፏል ሲል እስከ ግንቦት ሲኖዶስ የሚያደርሰንን አስቂኝ ደብዳቤ በኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ድረ ገጽ ላይ አድመኛ ተባባሪዎቹን አሰልፎ አሰንብቦናል።
እዚህ ላይ ልናነሳ የሚገባን ጥያቄዎች፣
1/ አባ ፋኑኤል በቤተክርስቲያናችን አሠራር በየደረጃው መወሰድ የሚገባቸውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ አግባብነቱን የጠበቀ አካሄድ መከተል ይቅርና በተገቢው መንገድ ያልሆነ እግድ ፈጽመው ቢሆን ኖሮስ ተበደልኩ ወይም እርምጃው ትክክል አይደለም የሚል ወገን የቤተክርስቲያኒቱ አካል ነኝ የሚል ከሆነ አቤቱታውን ማቅረብ የሚገባው ለማነው?
2/ አንድ ቄስ ነኝ የሚል ዶ/ር እርምጃ ከተወሰደበት እርምጃውን ለመከላከልና መብቱን ለማስከበር የሚችለው በህግ አግባብና መንገድ ብቻ ነው ወይስ አብያተ ክርስቲያናትን ወይም አባላትን በማሰለፍና በማሳደም?
3/ ዶ/ሩ ቄስ አላግባብ ተወሰደብኝ ለሚለው እርምጃ አድማውን ወደ ሁሉን አቀፍ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ለመውሰድ ከመፈለግ ባሻገር «ረስጠብ»ን በመጥቀስ አላግባብ ክህነትን የሚያግድ ጳጳስ ከጵጵስናው ይሻር! ብሏል በማለት ምንጭ ማጣቀሱ ጳጳሱ አሁን በነቄስ ዶ/ር ተሽረዋል ማለት ነው? ይህንን ለማለት ሥልጣኑን ከየት አገኙት?
4/ ለአባ ፋኑኤል እርምጃ አጸፋዊ ምላሽ የሆነው ደብዳቤ የተጻፈው በዋሽንግተን ዲሲና በአካባቢው አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት ማኅተም ሲሆን የአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት ኃላፊ ማነው? የስልጣነ ክህነትን እግድ ለማየት የተሰየመው ጉባኤ የት ያለው? እነማን ናቸው?
ሀገረስብከቱ ይህንን ደብዳቤ ስለ ዶ/ሩ ቄስ ጉዳይ የመመልከት ውክልናን ያገኘው ከማነው?
5/ የአብያተክርስቲያናቱ የአቋም መግለጫ በምን ስሌት ነው የስልጣነ ክህነትን ጉዳይ መመልከት የጀመረው? በአቋም መግለጫ የሚቀለበስ ወይም የሚከበር የክህነት ሥልጣን የት ሀገር ነው ያለው? ምናልባትም የሚያስቸግርህን በለው በሚለው የወሀቢዝም ፍልስፍና ይሰራ ይሆናል። ምክንያቱም ወሀቢዝም የምትቀበል ከሆነ ትቀበላለህ፣ እምቢ ካልክ ትመታለህ ፖሊሲው ስለሆነ ነው።
ስናጠቃልለው
ይህ ወሀቢያ ኦርቶዶክስ አቀንቃኝ ቡድን አባ ፋኑኤል ነገ ወደ ጅማ ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል የሚል ዜና ቢሰማ ጅማ ባሉ ተላላኪዎቹ አድማውንና ሴራውን ይተዋል ወይም የከሳሽነት አፉን ዘግቶ ዝም ይላል ብሎ ማሰብ የወሀቢያነቱን እንቅስቃሴ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመን ለጥፋት የተላከ የጥፋት መሳሪያ መሆኑን አለመረዳትም ይሆናል።
የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ብሎጎች አባ ፋኑኤልን ለማጥፋት የወሀቢያ ተግባራቸውን እንደማያቆሙ ቢታወቅም ትግላቸው ሁሉ ውሃ ወቀጣ ከመሆን ውጪ እስካሁን የፈየደው ነገር አለመኖሩን ስንመለከት የያዛቸው የዘመቻ አባዜ ግን መቼም ቢሆን ሳያጠፋው እንደማይለቀው አስረግጠን መናገር እንችላለን። በህውከት ቤቱን የሰራ መቼም አይኖርም። 
 «ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል» ምሳ 17፣11
ለዚህም ጊዜ ይስጠን ሁሉን እናየዋለን።
የራሳቸውን የኦርቶዶክስ ወሀቢያ አገልግሎታቸውን እንደቅድስና ስራ በመቁጠር የአባ ሰላማ ብሎግ የዶ/ሩን ቄስ እግድ ደብዳቤ ስላወጣ የተሃድሶ ብሎግ ብለው በመጥራትና አባ ፋኑኤልን ወደተሀድሶ ለማጣበቅ መፈለጋቸውን ስንመለከት «ይሉሽን ባልሰማሽ፣ ገበያ ባልወጣሽ» የተባለውን ተረት እንድናስታውስ ያስገድደናል። ቤተክርስቲያኒቱ የምትታወከው በኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ማኅበር (ማቅ) መሆኑን የማያውቅ ቢኖር ራሱ ማቅ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ጳጳሱን ሽረንሃል የሚል ደብዳቤ በብሎጉ ላይ ያወጣ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ የሚታየው  ከየትኛው የኦርቶዶክስ  ፍርድ በተገኘ መብት ነው?
በኦፊሴል የጻፉትን ደብዳቤ ያገኘና ድረ ገጽ ላይ ባወጣ ክፍል የተነሳ አባ ፋኑኤል የሚሰደቡበት ምክንያት ምንድነው? አባ ፋኑኤል ጽፈው ያሳወቁትን የእግድ ደብዳቤ እነማን እጅ መግባት እንዳለበትና እንደሌለበት ሲጠብቁ መኖር አለባቸው ወይ? በወሀቢዝም ደጀ አፍ ብሎግ ላይ ሲወጣ የኦርቶዶክስ የሚሆነውና ካልወጣ ደግሞ የተሃድሶ ነው የሚባለው በምን ስሌት ነው? እናንተ በተሃድሶ ብሎግ ላይ ወጣ ስትሉ  እኛ ግን እንደዚህ ልንላችሁ ስለመቻላችን አትገነዘቡም ማለት ነው?
የአባ ፋኑኤልን ጵጵስና የሚሽር ደብዳቤ የኦርቶዶክስ ወሀቢዝም ብሎግ በሆነው «ደጀሰላም» ላይ ወጣ!