Sunday, February 12, 2012

ያልገባኝ ነገር አለ!

ጥያቄ፦ እኔ ያልገባኝ ነገር አለ፤ እሱም ጌታ ፍቅር ነው እና ኃጢአት የሚሠራ ሥጋ ነው እና እሱ ራሱ ካልቅደሰኝ እንዴት ራሴ ልቀደስ እችላለሁኝ? ራሴ የምቀደስ ከሆነ ሕግ ይሆንብኛል እና እወድቃለሁ። አታድርግ ከሆነ ሰው በኋላ አይበርታም፡ ሰለዚህም ግራ መጋባት ላይ ነኝ።
 መልስ፦
ጸጋና ኃጢአት

በቅድሚያ አዲስ ኪዳን ስለ ሁለት ኃጢአቶች ይናገራል። አንደኛው ሳናውቅና ሳናስብ አንዳንዴ ስለምናደርገው ኃጢአቶች። እንደዚህ ያሉትን ኃጢአቶች ካደረግን፤ ንስሐ ገብተን ኃጢአታችንን እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን ተጽፎአል።

Quote:
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1
8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።

Saturday, February 11, 2012

የጤናማ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ!

ጠያቂ፦ ስለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዶክትሪን ብታስረዱኝ?

መልስ፦
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። የእያንዳንዳቸውን ዶክትሪን ልዩነት ለመጻፍ አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም ግን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጤነኛ መሆንዋን የሚያመለክተን ዶክትሪንዋ (አስተምህሮትዋ) ነው። ጤነኛ ዾክትሪን ያላትን ቤተ ክርስቲያንን ለመለየት የሚከተሉትን መስፈርቶች መጠቀም ያስፈልገናል፦

1. ስለመጽሐፍ ቅዱስ ያላት አመለካከት ምን ነው - Bibliology
- መጽሐፍ ቅዱስ የ እግዚአብሔር ቃል ነው ብላ የማታምን፤ እንዲሁም ለቀደመው ዘመን እንጂ ለዚህ ዘመን አልተጻፈም ብላ የምታምን ከሆነ ወይንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ አግንና የምትጠቀምበት ሌላ አይነት መጽሐፍት ያላት ከሆነ ይህች አይነቱ ቤ/ክ ጤናዋ ትክክል አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ሌላ ነገር የምታስተምር ከሆነ መስመር የሳተች ናት።
2. ሰለ ስነመለኮት (ስለ እግዚአብሔር) ያለት አስተምህሮት ምንድነው? - Theology
- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሦስትነት አንድነትን የማታስተምር ከሆነች ጤነኛ አይደለችም።
3. ስለ ክርስቶስ ያላት እምነት ምንድነው?- Christology
-ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን የምታምን ቤ/ክ ጤነኛ ቤ/ክ ናት
4. ስለመዳን ያላት እምነት ምንድነው? እንዴትስ ይዳናል ብላ ታምናለች? - Soteriology
- በክርስቶስ ከማመን ውጪ ሌላ ወይንም ተጨማሪ የመዳኛ መንገድ የምታመለክት ቤ/ክ ጤነኛ አይደለችም።
5. ስለመንፈስ ቅዱስ ምን ብላ ታምናለች? - Pneumatology
- መንፈስ ቅዱስ ከስላሴ አካላት አንዱ እንደሆነ ፣ ለቤተ ክርስቲያንን በሃይል የሚያጠምቅ፣ወደ እውነት የሚመራና አስተማሪ መሆኑን ወዘተ. የምታምን ቤ/ክ ጤነኛ ናት።
6. ስለመላዕክት ምን ብላ ታምናለች? - Angelology
- መላዕክት የእግዚአብሔር ፍጥረትና አገልጋይ መልዕክተኞች እንደሆኑ እንጂ አማላጅ እንዳልሆኑ የምታምን ቤ/ክ ጤነኛ ናት። መላእክት ከምድር እስከሰማይ በተዘረጋው መሰላል ላይ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ እንጂ ራሳቸው መውጪያና መውረጃ መሰላል አይደሉም። ናቸው የምትል ከሆነ በክርስቶስ ቦታ መላእክትን ተክታለችና ጤናማ አይደለችም።
7. ስለርኩሳን መላዕክትስ ምን ብላ ታምናለች - Demonlogy
- ርኩሳን መናፍስቶች የ እግዚአብሔርን አላማ አሰናካዮች፣ የሰውም የ እግዚአብሔርም ጠላቶች እንደሆኑ፤ በመንፈስ ቅዱ ኅይል በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሰዎች መውጣት እንዳለባቸው የምታምን ቤ/ክ ጤነኛ ናት። ከክፉ መናፍስት መካከል ክርስቲያን መሆን የሚችሉ እንዳለ የምታስተምር ከሆነ ጤናማ ቤ/ክ አይደለችም።
8. ስለቤተ ክርስቲያንስ ምን ብላ ታምናለች - Ecclesiology
- ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል፤የክርስቶስ ሙሽራ የምታምን ቤተ ክርስቲያን ጤነኛ ናት።
9 ሰለመጨረሻው ዘመን ምን ብላ ታምናለች? - Eschatology
- ቤ/ክ እንደምትነጠቅ፣የመከራው ዘመን  በምድር ላይ  እንደሚመጣ የምታምን፣ ከክርስቶስ ጋር እንደገና በክብር እንደምትገለጥና  ከንጉሡ ጋር በክብር ነግሳ እንደምትኖር የምታምንም ቤ/ክ ጤነኛ ቤ/ክ ናት።

እንግዲህ የዶክትሪን ልዩነቶች ከላይ በተጠቀሱት ዙሪያ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ሊኖር ይችላል። በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ውስጥ በአብዛኛው ተቀራራቢ መረዳት አለ ብዬ አምናለሁ። በዚህ ምሳሌ ነገሬን ልደምድም.... ጊታር የሚጫወቱ ሰዎች ይህ ምሳሌ በቀላሉ ይገባቸዋል። ጊታር ስድስት ክሮች አሉት የሁሉም ድምጽ ይለያያል። ሁሉም አይጠብቁም ሁሉም ደግሞ አይላሉም። ከሚገባው በላይ የጠበቀ ድምስ ዲስኮርድ ይፈጥራል፤ ከሚገባው በላይም የላላ እንዲሁ። በዶክትሪንም ዙሪያ ከላይ የዘረዘርኩት የሚጠብቁ ናቸው.... ይህንን ማላላት አይቻልም። ስለዚህ የሚጠብቀውን አጥብቀን የሚላላውን እናላላ። በሚያጨቃጭቁ ዶክትሪን ዙሪያ ከመናቆር አንድነታችንን ጠብቀን ወንጌልን እናሩጥ!
ከኢየሱስ.ኮም ድረገጽ የተገኘና በጥቂት ማስተካከያ የቀረበ

Friday, February 10, 2012

«ኢያሱ ወልደ ነዌ በአባቶች እግር»



«ኢያሱ ወልደ ነዌ በአባቶች እግር»

ምድራችን አንዱን በአንዱ እየተካች እዚህ ዘመን ላይ ደርሳለች። ቀድሞ የነበረው ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው ደግሞ ነገ ላይኖር ይችላል። በለውጥ ሂደት ውስጥ እንዳለን እንገነዘባለን። ዓለም እንኳን እየተለወጠች ነው። ድሮ የሌለ እምነት ዛሬ ተፈልስፏል። የነበረውም ቢሆን ገሚሱ ረስቶታል ወይም ከልሶታል አለያም ጥሩ አድርጎ አክርሮታል። ዝናባማው ዘመን በፀሐይ ተተክቷል። የሙቀት ጨምሯል ጩኸት፣ የዕለት ከዕለት ዜና ከሆነ ውሎ አድሯል። ሉላዊነት(Globalization) የሚሉት ስልጥንና በመንፈሳዊ ሀብት የሚታይ አብሮነትና አንድነት ባይኖረውም የሳይንስ ቁስ ዓለምን አቀራርቧል። ዓለምን ለመቃኘት ማጄላንን ወይም ኢብን ባቱታን መምሰል አይጠበቅብንም። ቁርስ አዲስ አበባ፣ ምሳ አቴንስ ለመመገብ ተችሏል። ድምፀትን ለመቀበል ወይም ለመስጠት ዛሬ ሁሉ ነገር የዓይንና የጆሮ ያህል ቀርቧል። ሲሰየጥኑ ይሁን ሲሰለጥኑ «ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚለው ትረካ ዓለምን እየነዳት ይገኛል። ይህ እንግዲህ ዓለም ደርሼበታለሁ የምትለው ግኝቷ ሲሆን የተቆላለፈው ችግሯ ደግሞ የትየለሌ ሆኗል።
ኤድስ የሚሉቱ አይድኔ በሽታ ብዙዎችን ወደ መቃብር ሸኝቷል። ኢቦላና የአእዋፍ ጉንፋን(BIRD FLU) ስንቱን ፈጅቶ የታገሰ ቢመስልም ጨርሶ እንዳልጠፋ ይወቃል። ካንሰር፣ ወባ፣ ስኳር፤ ግፊትና ብዛት፣ ማነስና ድክመት ልዩ ልዩ ህመሞች በርክተዋል፣ ወይም ህመምተኞችን አበራክተዋል። ከቺሊ እስከጃፓን፣ ከግሪንላንድ እስከ አንታርክቲካ የመሬት መንቀጥቀጡና የበረዶ መደርመሱ፣ የመሬት መናዱና ጎርፉ ብዙዎችን አጥፍቷል።
ሀይቲ 230,000 ሰው ሲሞትባት፤ሱናሚ ከኢንዶኔዢያ እስከ ሶማሊያ ጠረፍ ከ280,000 በላይ ሰዎችን መጥረጉን ሰምተናል። ጃፓንም ሀገር አማን ባለችበት ሀብቷን ሳይጨምር10 ሺዎችን ዜጋ አጥታለች።
ጦርነቱ፣ ፍጅቱ፣ የስልጣን ሽኩቻው፣ የሃይማኖት ፉክክሩ፣ የአሸናፊና ተሸናፊ ግብግቡ አይሏል። ያም ሆኖ ዓለም አለሁ፣ ማለቷን አልተወችም። ያለፈውን እየረሳች፣ መጪውን ትኖር ዘንድ ትጥራለች። «ገንፎ እየሞተ፣ ይተነፍሳል» እንዲሉ መሆኑ ነው። አዎ ዓለማችን እየሞተች መተንፈሷን አላቋረጠችም። ባለውና በሚታየው ነገር ለመጽናናት ትሻለች። ቁም ነገሩ ባለውና በሚታየው ነገር ፍጹም መጽናናትን ማግኘት አለመቻሏን አለማወቋ ነው። የተነገረውን አልሰማችም ወይም አልሰምቶም ሆኖባታል።
ማቴ 243-8
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
እናም ዓለም የምትወልደውን በምትወልድበት በመጨረሻው ወር ውስጥ ነው ያለችው። እንደነፍሰ ጡር ሴት በምትወልድበት በ9ኛው ወር ውስጥ እንዳለች ልትረዳና «ወልደ አብ፣ ኢየሱስ» 9ነኛው ሰዓት ያስተማራትን ጸሎት ልታሰማ ይገባታል። «
ማቴ2746
ዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።

በዚህ ጽሁፍ ስለዓለም የዳሰስኩት ጽሁፌን በዚያ ላይ ለማንተራስ እንጂ ስለዓለም ለማስተማር ስላለሆነ ዋናው ነጥቤ ዓለም ያለችበትን ደረጃ በማሳየት የዓለም አንድ ክፍል የሆንን እያንዳንዳችን ከዚህ የዓለም ጣር ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብን «የኢያሱ ወልደ ነዌ»ን አብነታዊ መንገድ ለማሳየት ነው። ኢያሱ እንደልጅ ልጅ ሆኖ ኅሊናውን ሳያባክን፣ መንፈሳዊ ልቡናውን በጊዜው ከነበረው መሳሳቻ ጠብቆ የአባቶቹን እግር እንደተረከበ በማሳየት እኛም በዚያ መሠረትነት ላይ ቆመን ዛሬ ዓለምን ከሚንጣት ወጀብ በመዳን የኃጢአት ከተማ ኢያሪኰን አፍርሰን ርስታችንን ለመውረስ እንድንችል ለማስገንዘብ ነው። ፍየል በኃጢአተኛ የምትመሰልበት ዋናው ምክንያት፣ ግልገሎቿን አድፍጦ ወደበላባት የቀበሮ ጫካ ቅጠል ለመቀንጠስ ዳግመኛ የምትመለስ በመሆኗ ነው። እንዲሁ ሁሉ ከጎናችን ብዙዎች ንስሐ ሳይገቡ መሞታቸውን እያየን፣ በቅጽበታዊ አደጋ ዓለም ብዙዎችን እንደሸኘች እየተመለከትን፣ እኛ ዘንድ እንደማይደርስ አስበንና ለእነርሱ እያዘንን በመቆየት ሰንበትበት ሲል ሁሉን ነገር ረስተን እንደነበረው የምቀጥል መሆናችን ነው።

ይቀጥላል.............