የብዙዎቻችን ምርጫ አንድ ዓይነት አይደለም። እንደየመልካችን ይለያያል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ልዩነት ውበት ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ሥጋ ያለነፍስ ምውት እንደሆነ ሁሉ ለነፍሳችን የምንሰጠው የልዩነት ውበት ነው አባባል ዋጋ የለሽ ይሆናል። በነፍስ ዘላለማዊነት ውስጥ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ታሪክ የለም። በዚህ ምርጫ ላይ ዘላለማዊ ውበትን ለማግኘት የግድ ምርጫችን አንድ ዓይነት ብቻ መሆን አለበት። የምንጊዜም ምርጫችን በሥጋ ዓለም እስካለን በክርስቶስ ላይ ካልተመሠረተ በነፍስ ዘላለማዊነት ላይ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ሥጋዊ አባባል ዋጋ የለውም። ፍላጎታችንን የሚከተል ምርጫ የህይወታችን መሠረት ላይሆን ይችላል። እምነታችንን የሚከተለው ምርጫ ግን ለዘላለማዊ ኑሮ ወሳኝ ነው። ስለሆነም ምን እናድርግ?
ማንም ሰው የእግዚአብሔርን የፍቅርና የምህረት እንዲሁም የደህንነትን ጥሪ ከተቀበለ፣ ለመዳንና ኃጢአቱ እንዲሰረይለት የሚከተሉትን እንዲያደርግ መጽሕፍ ቅዱስ ያስተምረናል::
1ኛ ንስሐ መግባት:- "ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፣ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ? አሉአቸው:: ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ...አላቸው::" ሐዋ 2፣37-38
"እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ፣ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል..." ሐዋ 17፣30
"ኃጢአታቸሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም::" ሐዋ 3፣20
ንስሐ መግባት ማለት በመጀመሪያ ኃጢአተኝነታችንና ፍርድ እንደሚጠብቀን አውቀን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአታችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲታጠብ መለመንና ከአሁን ጀምሮም በአዲስ ሕይወት እንጂ በድሮ በአጸያፊና ከእግዚአብሔር በተለየ ኑሮ ላለመኖር መቁረጥ ወይም መወሰን ነው:: ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን አዲስ ሕይወትን ለመጀመር የእኛ ውሳኔ አስፈላጊ ነው::
2ኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን:- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ለሰው ልጆችም ብቸኛ የመዳን መንገድ እንደሆነ፣ ለኃጢአታችንም ሲል በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰና እንደ ሞተ እንዲሁም በሶስተኛው ቀን እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣውና በቀኙ እንዳስቀመጠው ከልብ ማመን:: በዚህ ምድር ላይ ቢሆን ወይም ከሞት በኋላ የነፍሳችን ጌታና ጠባቂ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ፣ እርሱም ከዘላለም ፍርድ ነፍሳችንን ሊያድን የሚችል ብቸኛ አዳኝ እንደሆነ ማመን::