Friday, June 29, 2012

የፍቅር ለይኩን አላማ ማኅበረ ቅዱሳንን መታደግ ወይስ እውነትን መዋጋት?

                               ምንጭ፤ ዓውደ ምሕረት
ፍቅር ለይኩንን በግሌ በጣም አደንቀዋለሁ። በማንኛውም ርዕስ ጽሁፍ ሲጽፍ ነገሮችን በሚያይበት ዕይታ በእጅጉ እመሰጣለሁ። አገር ውስጥ ያሉ መጽሔቶች ለምን አምድ እንደማይሰጡት ሁሌም ግራ ይገባኛል። አገሩን እና ቤተክርስቲያንን የሚወድበትን ፍቅር ያንንም የሚገልጽበትን መንገድም አደንቃለሁ። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን ጋር ሲደርስ ሚዛናዊነቱን ሚዛን ያሳጠበት ምክንያት እየደነቀኝ ግን መልስ ልሰጠው ተገድጃለሁ። በመጀመሪያ አባ ሰላማ ላይ በጻፈው ጽኁፍ ካለኝ ከበሬታ አንጻር በዝምታ ላልፈው ብፈልግም ለደጀ ብርሃን የሰጠው የመልስ መልስ ግን ያለመናገር መብቴን ስለገፈፈው በጽኁፉ ላይ ያሉትን ሚዛን ያጣባቸውን ነገሮች ለመተቸት ተገድጃለሁ።
ላለፉት ስድስት አመታት አቡነ ጳውሎስ በዘረኝበት በሌብነት በተሃድሶነት ተጠርጥረው ሲሰደቡ አቡነ ገሪማ አቡነ ፋኑኤል አቡነ ሳዊሮስ ያለስማቸው ስም እየተሰጣቸው ሲሰደቡ ዲያቆን አሰግድ በሀሰት በከፍተኛ ደረጃ ስሙ ሲጠፋ ወንጌል ሰበክ ተብሎ ፓስተር ሲባል መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ለምን እውነትን አገለገልክ ተብሎ በከፍተኛ ደረጃ የስነ ምግባር ጉድለት በተቀነባበረ ካሴት ካደ ሲባል አባ ሰረቀብርሃን በህጋዊ መንገድ ሂዱ ባሉ በጠላትነት ተፈርጀው ሲብጠለጠሉ እነ አእመረ፣ ሀይለጊዮርጊስ፣ ኑብረዕድ ኤልያስ፣ ዲያቆን ትዝታው፣ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፣ በሪሁን፣ ተረፈ፣ ያሬድ፣ ታሪኩ……በተለያዩ የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች በከፍተኛ ደረጃ ሲብጠለጠሉ እንደ ተራራ የተቆለለው ትዕግስትህ ምነው አውደ ምህረትና አባ ሰላማ በጻፉት ጽሁፍ ጊዜ እንደ ገለባ ክምር ተበታተነ?

በመጀመሪያ አባ ሰላማ ላይ ላወጣኸው ጽኁፍ ለተሠጡህ ጠንካራ አስታየቶች በሰጠኸው ምላሽ እንጀምር “…የመጻፋችን ዓላማ እርስ በርስ ለመተናነጽና ለመማማር እስከሆነ ድረስ መልካም ነው እላለሁ፡፡” በማለት ጀምረሀል ፍቅር እስኪ እንደገና አባ ሰላማ ላይ ያወጣኸውን ጽሁፍ ተመልከተው በርግጥ እሱ ጽሁፍ የመመካከርና የመማማር ለዛ ነበረው? ስድብ ያልከውን ነገር በስድብ ከማወራረድ በቀር ምን አይነት ምክር ጠቅሰሃል? የጻፍከው መቅሰፍት አዘል ማስፈራሪያ መሆኑንስ ትስተዋለህ?  ጽሁፍህ ላይ “…እየተገለጸ ያለው ገመና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው።…” በማለትህ ግን ሳናመሰግንህ አናልፍህም። አንተም ቢሆን ያልሆኑትን ተባሉ አላልክምና እና ነው። በበኩላችን በጻፍነው ነገር አናፍርም ሀሰትን ላለመጸፍ እንጠነቀቃለን።
ለገመናቸው ሲሉ ግን የቤተክርስቲያን ልጆችን ለማጥቃትና ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የሚተጉትን አባቶችንና የማኅበረ ቅዱሳን አባላትን ብሎጎቻቸው ሊገነቡላቸው የሚፈልጉትን የሐሰት ገጽታ ከመናድና ትክክለኛ ማንነታቸውን ከመግለጽ ግን ወደ ኃላ እንልም። እነዚህ ሰዎች ስለ ራሳቸው ኃጢአት እየተጸጸቱ ንስሀ ከመግባት ባለፈ ንጹሀንን እያሳደዱ ሊገነቡ የሚፈልጉትን ከንቱ ዝና የመግለጽና መንፈሳዊ ሰው መስለው ሌሎችን ለመቃወም የሞራል ብቃቱና መንፈሳዊነቱ እንደሌላቸው እውነትን ለሚፈልጉ አንባቢዎቻችን የማሳየት ግዴታ አለብን።
በአስተያየትህ ላይ “እንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ እኔ የማንንም ግለሰብም ሆነ ብሎግ ስም አልጠቀስኩም፡፡” ብለህ መጻፍህ በጉዳዩ ላይ ሚዛናዊነት እንደጎደልህ ያሳያል። ሌላ አስተያየት ሰጪ በምላሽህ አዝኖ “ሁሉንም ብሎጎች ሳይሆን የጠቀስከው አባ ሰላማን እና አውደ ምህረትን ብቻ ነው። ምሳሌዎችህን በጥንቃቄ ተመልከታቸው። ቀውስ ጦስ ማን ላይ የወጣ ጽሁፍ ነው? የጉድ ሙዳይ ማን ላይ የወጣ ጽሁፍ ነው? ሁሉንም ለመውቀስ ብትፈልግ ሳይሳደቡ ውለው ከማያድሩት ከደጀ ሰላምና ከአንድ አድርገን የሚጠቀስ ምሳሌ አጣህ? ቢያንስ እንድንረዳህ ስህተትህን እመን።” ያለውን ሀሳብ አኔም እጋራለሁ። በኛ በኩል አቡነ አብርሃምን የጉድ ሙዳይ ማለታችንን አናፍርበትም ስለ እሳቸው ጉድ አይደለም ሙሉ ታሪኩን ገና መቅድሙንም አልጻፍነው። ሲጀመር መቼ የተዋህዶ ልጅ ሆኑና ነው። ለእሳቸው እኮ የቤተክርስቲያን ልጆች መወገዝ በጣም ተራ ነገር ነው። የሚመኙት ጠቅላላ ቤተክርስቲያኒቱን ማውገዝ ነው። ሲቀጥል እንዲህ እና እንዲያ ተብለው የሚጠቀሱ እንኳን ከጳጳስ ከአንድ ምዕመንም የማይጠበቁ በርካታ ጉዶች አሉባቸው። በቤተ ክህነት አካባቢ እሳቸው ሲገቡ ጳጳሳቱ  ቀስ እያሉ “ሙዳየ መና ዘጉድ ሙዳየ መና” እያሉ የሚዘምሩላቸው ማንነታቸውን በሚገቡ ስለተገነዘቡ ይመስለኛል።
 ስለአባ ሳሙኤል ስለጻፍነው ጽኁፍ ስትጽፍም እንዲህ ብለሀል “…አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተለዋውጠውታል የተባለው ለጆሮ የሚቀፍ ንግግርን በዝርዝር መዘገብ በምን መልኩ መንፈሳዊ ለዛ ያለው ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የቆመ ጹሑፍ ሊሆን እንደሚችል አንባቢ ይፍረደው…” ፍቅር እንዴት አድርገህ እንዳነበብከው አናውቅም እንጂ እኛ ግን ሚጡ የተናገረችውን ጸያፍ ንግግር … አድርገን ነው ያለፍነው ለምን አልገለጻችሁትም ከሆነ እና ምን እንዳለች ማወቅ ከፈለክ ግን ሁሌም በጽሁፍ ስር በምትገልጸው ኢሜልህ እንልክልሀን። ነገሩን ከ10 በላይ ምስክሮች እንዳዩት ስለምናውቅና የማኅበረ ቅዱሳን መሳሪያ የሆኑበት ኢየሱስ ክርስቶስ ዋናችን ነው ያለን ሰው ከእነርሱ በቀር ማንም የሚያውቀው በሌለ ፍጹም ስህተት በሆነ ልዩ የውግዘት ሀሳብ ለማውገዝ የደፈሩ ሰው መንፈሳዊነቱ ቢጎል ሰብዓዊነቱ እንኳ ያጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ደግሞ ጥፊው ለሳቸውም ለአይዞህ ባያቸው ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንም የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን እናምናለን፡፡
አስተውለኸው ከሆነ አባ ሰላማ ላይ ከቀረቡት ጽሁፍ ሁሉ በሬሽዎ ሲሰላ ያንተን ጽኁፍ ያህል ብዙ ተቃማዊ ያስተናገደ ጸሀፊ የለም ለምን ይመስልሀል? ምክንያቱም በከፍተኛ ደረጃ ሚዛናዊነት ስላጣህ ነው።
የጳጳሳትን ገመና የምንከድነው እኛ አይደለንም። ወይም እያስፈራራ ያልኩዋችሁን ፈጽሙ አሊያ…የሚለው ማኅበረ ቅዱሳንን አይደለም። እነርሱን ገመና የሚከድነው እውነተኛ ንስሀና ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ክብር መኖር ነው። እስከመውለድ ድረስ የገለጡትን ገመና እንዴት አርገን ነው የምንሸፍነው? ልጁን ለካደ ጳጳስ ጌታውን እንደማይክድ ምን ዋስትና አለን? እያደረጉት ያለውንስ ይሄንን አይደለምን?
ፍቅር አንተ ተንጠራርተህ መንካት የፈለከው የማኅበረ ቅዱሳን ተቃዋሚ ብሎጎችን ብቻ ነው። አይንህን ጨፍነህ እንኳን ብታይ በጭላንጭል ውስጥ ከቶውን ልታጣቸው የማትችላቸውንና አንተም ብትሆን  ውሸትነታቸውን ልትመሰክርላቸው የምትችላቸውን በርካታ የስም ማጥፋት ዘገባዎችን የሚያወጡ የማቅ ብሎጎችን በዝምታ አልፈህ የእነርሱን ተቃማዊሞች ግን እወቁልኝ በሚል መንፈስ ስማቸውን ተራ በተራ እየዘረዘርክ ማሻቀልህ አሳዝኖናል። ጽኁፍህ ሰው ምንም ሚዛናዊ ቢሆን ሁሌም በቀላሉ የሚነካ ስስ ብልት እንዳለው  ያሳየ ጽኁፍ ነው። 

«የታማኝ ወዳጆች መከዳዳት»


 ባንድ አገር የሚተማመኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ከነዚህም አንደኛው በሀብቱ የገነነ በሽምግልናው የተከበረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እየሠራ ከሚያፈራው ከዕለት ምግቡ ካመት ልብሱ የሚተርፈው ገንዘቡን እየወሰደ ባደራ ስም አኑርልኝ እያለ ለባለጸጋው የሚሰጥ ነበረ። ያም ታማኝ መሳዩ ሽማግሌ ያደራውን ገንዘብ እየተቀበለ ሲያስቀምጥለት ቆይቶ አንድ ቀን ባለ ገንዘቡ ለዕለት ችግሩ ካኖረው ሒሳብ ላይ ጥቂት እንዲሰጠው ቢጠይቀው ምን ሰጠኸኝና ትጠይቀኛለህ አላየሁም ብሎ ጨርሶ ካደው፤ እየተመላለሰ በማሳዘን ቢለምነውም አላዘነለትም፣ አልራራለትም። ቁርጡን ካወቀ በኋላ ላገሩ ዳኛ ክስ ለማቅረብ ሄዶ አመለከተ፤ ዳኛውም ስትሰጠው ያየህ ምስክር የሚሆን ሰው አለህን ብሎ ቢጠይቀው ከኔና ከሱ በቀር ማንም ሰው አልነበረም አለው። እንግዲያስ እኔ እጠይቅልሃለሁና ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሰህ እንድትመጣ ብሎ አስታወቀው።
ብልኁ ዳኛ አደራ አስቀማጩን ሰው ጠርቶ፣ አሁን ያስጠራሁህ እኔ በድንገት ከዚህ አገር ከሹመቴ ተሽሬ መሄዴ ነው፤ ብጠይቅ ባስጠይቅም ታማኝ ሽማግሌ ባገር ያለኸው አንተ መሆንህን ሰማሁ፡ ስለዚህ ዕቃዬንና ያለኝን ገንዘቤን በሙሉ አንድ ጊዜ አንሥቼ ለመሄድ ስለማይቻለኝ አንተ ዘንድ እንድታስቀምጥልኝና በየጊዜው ሰው ስልክ እንድትሰጥልኝ እለምንሃለሁ አለው።
ሽማግሌውም እንግዲህ ይህ ያገር ዳኛ ትልቅ ሰው ስለ ሆነ ባደራ የሚያስቀምጠው ገንዘብ በብዙ የሚቆጠር ዕቃውም ካይነቱ ብዛት ጋራ የበረከተ ይሆናልና ይኸን ተቀብዬ አላየሁም ብዬ ባለሀብት ባለገንዘብ እሆናለሁ ብሎ ደስ አለውና ለዳኛው እሺ ጌታዬ ሲል መልስ ሰጠው።
ከሦስት ቀንም በኋላ ባለገንዘብ ለዳኛው በቀጠሮዬ መጥቻለሁ ብሎ አመለከተው። እንግዲህ ሂድና አንዳችም ነገር ሳትጨምር ባገሩ ዳኛ ልከስህ ነውና ገንዘቤን ስጠኝ በለው፤ በዚያም ጊዜ ገንዘብህን በሙሉ አንድም ሳያስቀር ጨርሶ ይሰጥሃል አለው። እንደ ተባለውም ሁሉ ሄዶ ቢጠይቀው ይህን አልሰጥም ያልኩት እንደ ሆነ ለዳኛው ሲነግረው ከሓዲነቴን ያውቅብኝና የሱን ብዙውን ገንዘብና ዕቃ ያስቀርብኛል ሲል ገንዘቡን በሙሉ አውጥቶ ሰጠው ይባላል።
እንቅልፍ ለምኔ፣ 3 እትም። ከብ/ጌታ ማኅተመ ሥላሴ። 1960 አርቲስትክ ማተሚያ። /አ። ገጽ 184-185

Thursday, June 28, 2012

ሁሉም ነገር ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ይመስላሉ አንዳንድ ብሎጎች!

 
በፍቅር ለይኩን፡፡
የደጀ ብርሃን ጸሐፊዎች «አህያውን ፈርቶ ዳውላውን» እንዲሉ እባካችሁ የአባቶችን ገመና እና ኃጢአት እንዲህ ጨዋነት በጎደለው መልኩ በየአደባባዩ እያወጣንና እየዘረዘርን ከመንፈሳዊነት ሕይወት ውጭ አንሁን ይሄ ዓይነቱ መንገድ መንፈሳዊነቱ ቢቀር ኢትዮጵያዊው ጨዋነትና ባሕል አይፈቅደውም እና እንተወው ለሚል ጹሑፌ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ጹሑፍ ተነስተው አንተ በመንግሥት ተቃዋሚ ድረ ገጾች አቡነ ጳውሎስንና ቤተ ክህነቱን እንዳሻህ ስታብጠለጥል ቆይተህና በአፍቃሪ ማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ላይ እንዳሻህ ስትሆን ከርመህ ዛሬ እኛ ያሻነውን ብንል ምነው ቆጨህ በማለት፣ ያሻንን በማለት መብታችን ላይ አትምጣብን በማለት የክርክሩን ጭብጥ ለቀቀውና አይወርዱ አወራረድ ወርደው ከቆየ ጹሑፌ ጥቂት መስመሮችን ብቻ በመውሰድ የጹሑፌ አጠቃላይ ጭብጥና መንፈስ ምን መሆኑን ለአንባቢያን ሙሉ መረጃ በማይሰጥ መልኩ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ሊፈርጁኝ ደፈሩ፡፡
ደጀ ብርሃኖች ለምን እንዲህ ዓይነቱን መሰሪ አካሄድ እንድመረጡትም ግራ ገብቶኛል፣ ምላሽ ልሰጣቸው አስቤ ነበር ግን ጽንፈኝነት የሞላበትና ሚዛናዊነት የጎደለው የሚመስለው አካሄዳቸው ስላልጣመኝ ተውኩት ደግሞም አንባቢያን ለሕይወታቸው የሚተርፍ የወንጌል ትምህርት ፍለጋ በሚቃርሙበት ጊዜያቸው የእኛን ሙግት እንዲያዳምጡ መጋበዝ ሌላ የባሰ ስህተት እንደሆነ አስበኩና አሳቤን ቀየርኩ፡፡ መቼም ቀውስጦስ የተባሉትን አባት «ቀውስና ጦስ» ናቸው በማለት ተራ የሆነ የቃላት ስንጠቃ ውስጥ በመግባት የሰውን ሞራልና ሰብእና መንካት እንዴት ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ስንል ነው እንዲህ የጻፍነው የሚለው መከራከሪያ አሳብ በምን መልኩ ሚዛን እንደሚደፋ ኅሊና ያለው ሰው ይፍረደው፡፡
ከዚህ የሚብሰው ደግሞ አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተብሎ የተጻፈው ጹሑፍ እንደዛ ልክ እንደ ዓለማዊ ትረካ ልብን በሚሰቅልና ከአሁን አሁን ምን ይከሰት ይሆን በሚል እስከ አንሶላ መጋፈፍ ያለውን የጓዳ ምስጢር ለመግለጽ ዳር ዳር ያሉበትና አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተለዋውጠውታል የተባለው ለጆሮ የሚቀፍ ንግግርን በዝርዝር መዘገብ በምን መልኩ መንፈሳዊ ለዛ ያለው ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የቆመ ጹሑፍ ሊሆን እንደሚችል አንባቢ ይፍረደው ከማለት ውጭ ሌላ ምን ማለት ይቻላል፡፡