Tuesday, June 28, 2022
Sunday, May 15, 2022
Wednesday, May 4, 2022
Monday, May 2, 2022
Friday, April 22, 2022
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና 1ኛ ቆሮ 5፣7
ዕብራውያን פֶּסַח» ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው። በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል።
ደሙን ደግሞ የበሩን ሁለት መቃንና ጉበኑን ይቀቡታል። ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።
ይህ ቅርጽ የዕብራውያን ስምንተኛውን ፊደል «ኼ» የተባለውን ይወክላል። (እንደአማርኛው በጉሮሮ ሳይሆን በላንቃ የሚነበብ ነው) «ኼ» ማለት በዕብራውያን ትርጉም «ሕይወት» ማለት ነው። ዕብራውያንም በፊደላቸው በ«ኼ» ቅርጽ በሚቀቡት ደም የተነሳ ወደፈርዖናውያን ሠፈር የሚያልፈው ሞት አይነካቸውም። ምክንያቱም ሕይወት የሚል ማኅተም በራቸው ላይ ታትሟልና። ፋሲካ ማለት ይህ ነው። በደሙ ምልክት የተከለሉ በሕይወት ለመቆየት ዋስትና የያዙ ሲሆን ይህንን ማኅተም ያላገኙና ምን እየሆነ እንዳለ የማያውቁ ደግሞ በሞት የሚወስዱበት የፍርድ ምልክት ነው። ደሙ የሞትና የሕይወት መለያ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ሥርዓት እስራኤላውያንን ከባርነት፤ ከጠላት አገዛዝና ከመገደል የታደገ የዋስትና መንገድ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ ሕዝብና አሕዛብን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለም ሞት የታደገ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፤7 በማለት የሚነግረን። የእስራኤል ዘሥጋ ፋሲካ መጻጻና የቦካ ይከለክል እንደነበረው ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካም እንዲሁ ይከለክላል። በኃጢአትና በዐመጻ የቦካ የውስጣችንን ሆምጣጣ እርሾ ካላስወገድን በስተቀር በፋሲካው የሚገኘውን ሕይወት በፍጹም አናገኝም። የቀደመው ፋሲካ እርሾ ያለውን ነገር ከቤቱ ያላጠፋ ከእስራኤል ጉባዔ ተለይቶ ይጥፋ የሚል ሕግ ነበረው። ምድራዊው ፋሲካ ይህንን ያህል ከከበረ ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይከብር? ፋሲካን መናገርና ፋሲካን አውቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለፋሲካ ብዙ ማስተማርና መናገር ይቻል ይሆናል። ስለፋሲካ የመልካም ጊዜ መግለጫና ስጦታም መለዋወጥ ይቻል ይሆናል። ፋሲካ ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አይገኝም። ፋሲካ በስግደትና በወይራ ቅጠል በመጠብጠብ የሚገኝም ጸጋ አይደለም። ፋሲካ የአንድ ወቅት ራስን ማስገዛትና በጽኑ እሳቤና ጭንቅ ማለፍ ውስጥ የሚመጣም አይደለም።
ፋሲካ በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የደሙን ምልክት በመያዝ ዕብራውያን ከሞት እንዳመለጡበት የ «ኼ» ምልክት ማኅተም በመያዝ ብቻ ነው የምንድነው። ያን ጊዜ ብቻ ነው ሞት በራችን ላይ ያለውን የአዲስ ኪዳኑን ፔሳኽ አይቶ የሚያልፈን። ይህንን የደም ማኅተም ለመያዝም ከክፋት፤ ከሀሰት፤ ከግፍና ከዐመጻ እርሾ መለየት የግድ ነው። ከዝሙት፤ ከስርቆት፤ ከጉቦ፤ ከምኞትና ከኃጢአት ሁሉ እርሾ ሳንለይ ውስጣችን የሞላውን መጻጻ ተሸክመን የፋሲካ ሕይወት አይገኝም። ጳውሎስም እንዲህ አለን።
«ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም» 1ኛ ቆሮ 5፤8
እንግዲህ ከፋሲካው ተስፋ የምናደርግ ሁላችን እስኪ ራሳችንን እንመርምር። እንደመጽሐፍ ሊያነበን በሚቻለው ከፋሲካችን ክርስቶስ ፊት እስኪ ራሳችንን እናንብበው። በእውነት እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ከሌሉ ከ2000 ዓመት በፊት ለሕይወት የፈሰሰውን ደም ይዘናል ማለት ነው። ያኔም ሞት በኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አረጋግጠናል። እስራኤላውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን በቀቡ ጊዜ ሞት እንደማይነካቸው እርግጠኞች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የበለጠውንና የተሻለውን የሕይወት ደም በእምነት ስለያዝን ለዘላለማዊ ሕይወት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚያ ባሻገር በየዓመቱ በሚመጣ በዓል የሚገኝ የደም ምልክት የለም። በጥብጠባና በስግደትም የሚገኝ የሕይወት ዋስትናና የሚሻር ኃጢአት የለም። የተደረገልንን ማሰብ አንድ ነገር ሆኖ ሰው ግን ዓይኑን በዚያ በዓል ላይ ተክሎ የዓመቱ ኃጢአት ወይም ሸክም እንደሚወድቅ ማሰብ ስህተት ነው። ዓመቱን ሙሉ ከክፋትና ከግፍ እርሾ በመላቀቅ፤ አንድም ሰከንድ የማይለይ የልባችንን ጉበንና መቃን ላይ ደሙን በእምነት ይዘን መገኘት የግድ ይሆንብናል። ያኔ ነው ፋሲካችን ታርዷል የምንለው። ያኔም ነው ሁልጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ እንዳለን የምናውቀው። መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሰምርልን ዕለት፤ ዕለት መታደስ መታደስ ይገባዋል እንጂ በዘልማድ መንገድ አንመላለስ!
«ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል» 2ኛ ቆሮ 4፤16
ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን ውስጣችንን መፈተሽ የግድ ነው። በአምናው እኛነታችንና በዘንድሮው እኛነታችን መካከል የሕይወት ለውጥ ከሌለን ሞት በመጣ ጊዜ ምንም የመዳን ምልክት እንደሌላቸው ፈርዖናውያንን ወደዘላለማዊ ሞት መሄዳችን እውነት ነው። በወይራ በመጠብጠብ 30 እና 40 ለመስገድ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከሞት የማምለጫ የፋሲካው ዓርማ ክርስቶስን ከኃጢአት በጸዳ ማንነታችን ውስጥ ዘወትር ይዘነው እንኑር። የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እሁድ ነው። ከእሁድ እስከ እሁድ 8 ቀናት አሉት። ዕብራውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን የቀቡት ቅርጽ ከዕብራውያን አሌፋት መካከል የ «ኼ» ስምንተኛው ፊደል አምሳል ነው። «ኼ» ደግሞ ትርጉሟ «ሕይወት» ማለት ነው። ይህ የደም ምልክት ነው ሕይወት የሆናቸው። በሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን የአዲስ ኪዳኑ ሕይወት በክርስቶስ ትንሣዔ ለዓለሙ ሁሉ ታደለ። ይልቅስ ይህንን ደም በልባችንን ጉበንና መቃን ላይ እንደንጹሕ መስዋዕትለመቀባት እንሽቀዳደም። ያኔምክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ፍለጋ የት መሄድ ይገባናል? የእግዚአብሔር መገኛው የት ይሆን? ከምድራዊት ቤተ መቅደስ? ከገሪዛን፤ ከጌባል? ወይስ በኢየሩሳሌም?
አንዳንዶች ኢየሩሳሌምን የተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን ይሆናል ይላሉ። የቆረበ ደግሞ የበለጠ የ40 ቀን ሕጻን እንደሚሆንም ይሰበካል። ከተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን በመሆንና ከቆረበ የ40 ቀን ሕጻን በመሆን መካከል ያለው ልዩነት አይገባኝም። ኢትዮጵያ በመቁረብና ኢየሩሳሌም ከጎልጎታ ሄዶ በመቁረብ መካከልስ ያለው ልዩነት ምንድነው? ሰዎች ክርስትናን እንደሕግ ሥርዓት ማክበር ሲጀምሩ የሕግ የብልጫ ልዩነት ክርስትናውን መውረስ ይጀምረዋል። ኢየሩሳሌም ሄዶ በመሳለም ወይም በመቁረብና ኢትዮጵያ በመቁረብ መካከል ልዩነት የሚመጣውም ለዚህ ነው። መቱ ባለች ቤተ ክርስቲያን ጓሮ በመቀበርና ደብረ ሊባኖስ በመቀበር መካከል ያለው የመብት ልዩነትም ውጤቱ የሕግ ተፋልሶ ክርስትናውን በመዋጡ የመጣ ነው። የወንጌል እውነት ግን ያንን እንድንል አይነግረንም። እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቦታና በሥፍራ የሚወሰን አምላክ አይደለም። ስለዚህም እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በእምነትም፤ የመንፈስ የሆነ ሥራ በሕይወታችን ላይ ሊገለጥ ይገባዋል። ያኔ ዲላ ሚካኤል ተቀበርን፤ ደብረ ሊባኖስ፤ ደሴ ቆረብን አውስትራሊያ በማንነታችን ላይ ለውጥ የለውም። በሕይወቱ የክርስትና ማንነት የሌለው ሰው ደብረ ሊባኖስ ጓሮ መቀበሩ በፍርድ ወንበር ፊት ለውጥ አያመጣለትም። ሰው ሲሞት ይዞት የሚሄደው በምድር የነበረውን ሥራ እንጂ በሰማይ የሚፈጸም የክርክር ዳኝነት የለም። «እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ» እንዳለ ዳዊት በመዝሙር 62፤12
ስለዚህ እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በመንፈስ ይሰገድለታል፤ በመንፈስ ይታመናል እንጂ በቦታና በሥፍራ አይደለም። እሱን ይይዝ ዘንድ የሚችል ምድራዊ መቅደስ የለንም። «ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ» የሐዋ 7፤50
«ወትቤሎ፤ አበዊነሰ በዝንቱ ደብር ሰገዱ፤ ወአንትሙሰ ትብሉ ከመ በኢየሩሳሌም መካን ውእቱ ኀበ ይሰግዱ። ወይቤላ ኢየሱስ፤ እመንኒ ብእሲቶ ከመ ትመጽእ ሰዓት አመ ኢበዝንቱ ደብር፤ ወኢበኢየሩሳሌም ዘይሰግዱ ለአብ፤ አንትሙሰ ትሰግዱ ለዘኢታአምሩ፤ ወንሕንሰ ንሰግድ ለዘናአምር፤ እስመ መድኃኒት እምነ አይሁድ ውእቱ። ወባሕቱ ትመጽእ ሰዓት፤ ወይእዜ ይእቲ፤ እመ እለ በርቱዕ በአማን ሰጋድያን፤ ይሰግዱ ለአብ በመንፈስ ወበጽድቅ እስመ አብኒ ዘከመዝ የኀሥሥ እለ ይሰግዱ ሎቱ። እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ፤ እለሂ ይሰግዱ ሎቱ በመንፈስ ወበጽድቅ ሀለዎሙ ይሰግዱ ሎቱ»
ትርጉም፤
«አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» ዮሐ 4፤20-24
የኢየሱስ ስቅለት የሚታሰበው በመንፈስ መሆኑን ለማመልከት ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንዲህ አላቸው። ኢየሱስ የተሰቀለው ኢየሩሳሌም እንጂ ገላትያ አለመሆኑን እያወቀ ለገላትያ ሰዎች ግን «በዓይናችሁ ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» እያለ ይወቅሳቸዋል። ምክንያቱም ስቅለቱ በአማኞች ፊት የሚታየው በየዓመቱ ለሁለት ወር በሚደረግ ጾምና ለአንድ ሳምንት በሚታሰብ የሕማማት ሳምንት ሳይሆን በየትኛውም ቦታ ብንሆን ያለምንም ዕረፍት በዘመናችን ሙሉ ነውና።
የሕማማቱ ሳምንት ካለፈ በኋላስ? በዓለ ፍስሐ ወሀሴት፤ በዓለ ድግስ ወግብዣ፤ በዓለ ምግብ ወመጠጥ ነው? የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለሁለት ወር ከምግብ የመከልከል ማዕቀብና ለሁለት ወር ተከልክለው የነበሩ ምግቦች በተራቸው ድል የሚቀዳጁበት በዓል አይደለም። ዓመቱን ሙሉ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የምናስብበት፤ በመንፈስና በእውነት የምንሰግድለት ቋሚ የሕይወታችን መርህ እንጂ በአርብ ቀን የወይራ ጥብጣብ የሚያበቃ ዓመታዊ ልምምድ ካደረግነው ከገላትያ ሰዎች በምን እንሻላለን?
ለዚህም ነው፤ ብዙ ክርስቲያኖች ከነገሠባቸው የሥጋ ሥራ ሳይላቀቁ ፋሲካን እያከበሩ ዘመናቸውን ሁሉ የሚፈጽሙት። ጋብ ብሎ የነበረው የሥጋ ሥራ ከፋሲካ በዓል በኋላ ይደራል። ዝሙቱ፤ ውሸቱ፤ ስርቆቱ፤ ማጭበርበሩ፤ ሃሜትና ነቀፋው ያለማንነት ለውጥ እንደነበረው ይቀጥላል። ዓመቱን ሙሉ ያጠራቅሙትን ኃጢአት የፋሲካ ጾም ሲመጣ ለማራገፍ እንደሚቻልበት አመቺ ጊዜ ጠብቀው ብዙ ሰዎች ጥሬና ቆሎ ቋጥረው በየዋሻውና ፍርክታው ልክ እንደሽኮኮ ይመሽጋሉ። ሀብት ያላቸው ኢየሩሳሌም ሄደው ለመሳምና ለመቁረብ ገንዘባቸውን በየዓመቱ ይከሰክሳሉ። የክፉ ቃል ምንጭ የሆነውን አንደበቱን ሳይዘጋ ሥጋ መሸጫ ቤቱን የሚዘጋ የት የለሌ ነው። ከተማውን ሁሉ የወረረው የሚዛን መሥፈሪያ በፈሪሃ እግዚአብሔርና ያለማጭበርበር ሳይሰሩበት ጾም የሚሉትን ፈሊጥ የሚጠብቁት ለምንድነው? አቤት! የዘንድሮ ሚዛን የሚባለው የድሮና የዚህ ዘመን ሚዛን ልኬታ የተለየ ሆኖ ይሆን?
የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚዘርፉ የሕግ ፋሲከኞች ቁጥራቸው ብዙ ነው። የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል የሚከንፉ ነገር ግን የቤታቸውን የፍቅርና የሰላም ደወል የተነጠቁ ቤቱ ይቁጥራቸው። ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁ፤ በፍትህ አደባባይ ፍርድን የሚጨፈልቁ፤ በመማለጃም የእንባን ዋንጫ የሚጎነጩ የሁለት ወር ጸዋሚዎችና ተሃ ራሚዎች አያሌ ናቸው። የልምድ ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክርነት በሥራቸው ሊታይባቸው አይችልም። ስለዚህም ይመስለኛል፤ በክርስቲያን ቁጥር ብዙ ሆነን በበረከት መትረፍረፍ አቅቶን እድሜ ልካችንን ከእምነት የለሾች ምጽዋት ጠባቂ ሆነን የቀረነው። እንደእምነት የለሾቹ፤ እምነት የለሾች ብንሆን ያለእምነት ስለሚፈረድብን በሥጋ ረሃብ ባልተገፋንም ነበር። እግዚአብሔርን እየጠራን፤ እንደፈቃዱ ለመኖር ባለመቻላችን በራሳችን የእምነት ጉድለት በሥጋችን እንቀጣለን። ብዙ ባወቅህ ቁጥር ብዙ ሥራ ይጠበቅብሃል። ካልሰራኸው ግን ባታውቅ ቢቀርብህ ይሻልህ ነበር። ስለዚህ ማወቅህ ለመዳንህ ዋስትና የሆነውን ነገር ካላትርፈረፈልህ ክርስትናህ ምንድነው? ኢየሱስ በባዶ ተስፋ አልተወንም። እኛ ግን አስሮ በያዘን በገላትያውያን አዚም ፈዘን ሳለ ስለገላትያ አዚም እናስተምራለን።
የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ በየዓመቱ እየዞረ የሚመጣ በዓል ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት በፊታችን ተስሎ የሚታየን የሕይወታችን አካል ነው መሆን ያለበት። በቦታ፤ በሥፍራና በጉዞ ብዛት የሚከበር ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ እንድናመልከው የተደረገልን የማዳን ሥራ ነው። በአዲስ ሰውነት ለውጥ እንጂ በሕግ ሥነ ሥርዓት ልናሳልፈው አይገባም። ሰላምና እርጋታ በውስጡ መኖሩን መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክርለት አማኝ ሀገር ለሀገር፤ ተራራ ለተራራ ትንሣኤውን ፍለጋ ሲዞር አይገኝም። ምክንያቱም፤ ሁል ጊዜ በዓይኑ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየዋልና»! ከተያዝንበት አዚም ተላቀን በልባችን የተሳለውን ትንሣኤ፤ በኑሮአችን ፍሬ የሚታይበት እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን።
Thursday, April 21, 2022
Tuesday, April 19, 2022
Saturday, April 16, 2022
ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር ማቴ ፳፩፣፱
«ሆሳዕና» ቃሉ ከሁለት አረማይክ ቃላት የተሰራ ሲሆን ትርጉም «እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው። እብራይስጡም ይህንኑ ቃል ወርሶ «הושענא » ሆሻአና ሲል ይገኛል። አዎ «አሁን አድን፣ እባክህ እርዳን» ብሎ የአዳም ዘር ያጣውን ልጅነትና የደረሰበትን ሞት ለመላቀቅ የሚያሰማው የጩኸት ድምጽ ነው፣ «ሆሳዕና»!!!
ዳዊት ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ ተመልክቶ ማዳኑን ሲጣራና አሁን ናልን ሲል ከዘመናት በፊት አድምጠነዋል። የውስጥ ዓይኖቹ ሩቅ አይተዋል። ማዳኑንም ሽተው እንዲህ ሲል ዘምሮለታል።
«አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» መዝ ፻፲፰፣፳፭
ያ ማለት ደግሞ « אָנָּ֣א יְ֭הוָה הֹושִׁ֘יעָ֥ה נָּ֑א אָֽנָּ֥א יְ֝הוָ֗ה הַצְלִ֘יחָ֥ה נָּֽא » አና ያኽዌ ሆሳአና አና ያኽዌ ሆስሊኻ ና» የሚለው የእብራይስጡ ቃል ነው።
አበው የማዳኑን ነገር አስቀድመው አይተው በተስፋ «ሆሳዕና» እያሉ ዘምረዋል። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በክርስቶስ ኢየሱስ እስኪገለጥ ዘወትር በእንባና በዝማሬ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር።
አዎ ንጉሥ ክርስቶስ ከዘጠና ዘጠኙ በጎች መካከል የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንደንጉሥ ያይደለ በአህያ፣ ለዚያውም በውርንጫ ተቀምጦ «የአሁን አድን (ሆሳዕና)» ጩኸት ሊመልስ በጽዮን ከተማ ይመጣል፤ ይህንንም ዘካርያስ ከዘመረው ዘመናት ተቆጥረው ነበር።
«አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል» ዘካ ፱፣፱
ምንኛ ይደንቅ? ምንኛስ ይረቅ? ንጉሥ ስለመምጣቱ አስቀድመው የተናገሩለትና ከዘመናት በፊት ማዳኑን አይተው በእልልታ የዘመሩለት!!
ሰማያዊ ንጉሥ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ከስጋችን ተዛምዶ ማዳኑን ሲጠብቁ፤ ከሩቅ አይተው ሲጣሩ፣ ሲዘምሩለትና አንድ ቀን ማዳኑ እንደሚሆን ተስፋ ሲያደርጉት የነበረው ሰዓቱ ደርሶ በመካከላቸው ሲገኝ ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ሳይሆን ውበት የሌለውን ንጉሥ ለመቀበል የገዛ ወገኖቹ ተቸግረው ነበር።
አዎ የደም ግባት ብቻ ሳይሆን የንጉሥ ወግ የሌለው፣ በአህያ ለዚያውም በውርንጫ የሚመጣ ንጉሥ እንዴት ይቀበሉት?
«በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም» ኢሳ ፶፫፣፪
አባቶቻቸው ለዘመናት «ሆሳዕና፣ ማዳንህ አሁን ይሁን» ያሉለትና የዘመሩለት በዕለተ ቀጠሮው ማዳኑን ሊያሳይ ከጽዮን ደጃፍ ቀርቦ ሳለ የማያውቁት፣ ያልሰሙት፣ ትንቢቱን ያላነበቡት «ሆሳዕና» ሲሉ ትልልቆቹ ዕብራውያን ግን ዝም አሉ፣ ዝም በሉም አሉ!
«ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፣ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው፣ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት»
የማዳኑ ጌታም፣
«እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው» ማቴ ፳፩፣ ፲፭-፲፮
ኢየሱስ ክርስቶስ የእነዚህን ሕፃናት ዝማሬና ምስጋናን የሰማው ከቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም ማዳኑን ሊፈጽም በመጣ ጊዜ ነበር። ቤተ ፋጌ ከኢየሩሳሌም ከተማ ምሥራቃዊ አቅጣጫ በቢታንያና በደብረ ዘይት ተራራ መካከል የምትገኝ መንደር ነበረች። ቤተ ፋጌ ማለት በአረማይክ «ያልበሰለ በለስ ቤት» ማለት ነው። ርቀቱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት ያህል ምዕራፍ ነበር።
ጌታ ኢየሱስም ከኢያሪኰ ከተማ ወደኢየሩሳሌም ሲወጣ ካረፈባት ከቤተ ፋጌ መንደር ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ልኰ ውርንጫይቱን ከታሰረችበት ፈትተው እንዲያመጡለት አዟል።
«ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ» ማቴ ፳፩፤፪
ያን ጊዜም በቀደምት አበው የተነገረው ትንቢትና ዝማሬ ፍጻሜ አገኘ ማለት ነው።
«የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር» ማቴ ፳፩፣፱
ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም ለሆሳዕና አልተዘጋጀችም ነበር። ይልቁንም ቤተ መቅደሱ አካባቢ ስለማዳኑ ዝማሬ በማቅረብ ፋንታ የጦፈ የንግድ ገበያ ደርቶበት ነበር። ቤተመቅደሱ የጸሎት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የሻጮችና የለዋጮች መድረክ ሆኖ ነበር። ያኔ ማዳኑ የቀረበላት ኢየሩሳሌም በመቅደሱ በራፍ ስትሸጥ፣ ስትለውጥ መድኃኒቱን ሆሳዕና እያለች መቀበልን እንዳልቻለች ሁሉ የዛሬዋ ቤተክርስቲያንስ ንግድና ሸቀጥ የሌለበትን «ሆሳዕና» እያከበረች ነው ወይ? ብለን ብንጠይቅ ራስን ማታለል ካልተጨመረበት በስተቀር፣ መሸጥ መሸቀጡ የሌለበትን «ሆሳዕና» የሚያከብር የለም ነው መልሱ። ዐውደ ምሕረቱ ሱቅ በደረቴ ያልሆነበትን ሥፍራ ማግኘት ከባድ ነው።
ኢየሱስ ማዳኑን ከመፈጸሙ በፊት እነዚህን ነጋዴዎች አስወግዷል። ገበታቸውን ገልብጧል። እየገረፈ አስወጥቷል። የወንበዴዎች ዋሻ የሆነውን የጸሎት ቤት ጠራርጓል። ዛሬስ ቤቱ ስንት ወንበዴ መሽጎበት ይሆን? ወንበዴዎቹ ይዘምራሉ፣ ሆሳዕና ይላሉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ይይዛሉ፣ በጣታቸው፣ በግንባራቸው ያስራሉ። ወንበዴዎች ናቸው ተብለው እንዳይርቋቸው የአምልኰ መልክ አላቸው። ቤተመቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁ ያለው በግብር ውንብድና በመልክ ግን አገልጋይ ይመስሉ የነበሩትን የመቅደሱን ሰዎች ነበር። ዛሬም እንደዚያው!!
በሌላኛው ቀንም በዚያው በመቅደሱ ሲያስተምር ዋለ። የወይኑ ጌታ ስለወይኑ ደኅንነት የላካቸውን አገልጋይ ሠራተኞች ታሪክ አወጋቸው። የሕይወት ለውጥ ለወይኑ ባይሆንለት ይፈሩት እንደሆነ አንድ ልጁን ቢልክም ገበሬዎቹ ወራሹ ይህ ነው እንግደለው ብለው መከሩበት፣ መክረውም አልቀረም፣ ከወይኑ አውጥተው ገደሉት። ስለዚህ የወይኑ ጌታ ገዳዮቹን ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ሲል ይጠይቃቸዋል። እነሱም መልስ መለሱ። መልሱ ግን በራሳቸው ላይ የሚሆን የምስክርነት ፍርድ ነበር። «ፍታሕ በርእስከ» ማለት ይህ ነው። እነሱም እንዲህ ሲሉ በራሳቸው ፈርደው ተናገሩ።
«እርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት» ማቴ ፳፩፤፵፩
የአይሁድ ፋሲካ ከመሆኑ ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይነጋገር ነበር። ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይወድቅ የማይቀረው ለምድነው አሉት?
ስለረገማት በለስና ስለኢየሩሳሌም ጥፋት ተናገረ። ኋላም በሮማዊው ጥጦስ ትንቢቱ ተፈጸመ። ፍሬ አልባዋ በለስ እስራኤል ጠፋች።
ጴጥሮስ ደብረ ዘይት ላይ ሌላ ጥያቄ አነሳ።
«እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት» የቅርቡን ጊዜና መጨረሻውን ዘመን ምልክቶች ነገራቸው። የቅርቡ ጊዜ የኢየሩሳሌም መከበብ የበለስ መድረቋ ጊዜ መሆኑን እንዲህ አለ። «ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ» ሉቃ ፳፩፤፳ በዚህ የኢየሩሳሌም የመጥፊያ የፍርድ ቀን መድረሱን አሳይቷል።
እንደገናም የኋለኛውንም ዘመን ትንቢት ደግሞ ይህች የተረገመች በለስ ስታቆጠቁጥ በጋ እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ፤ ያኔ ደግሞ የመጨረሻው የፍርድ ቀን እንደደረሰ ምልክት ይሆናል አላቸው።
«ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፣ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ» ሉቃ ፳፩፤፳፱-፴፩
አዎ ! የመጨረሻው ዘመን ዋናው ምልክት ፍሬ አልባዋና የደረቀችው በለስ ማቆጥቆጥ መጀመሯ ነበር። ያኔ የአጨዳው መከር ስለመድረሱ ጫፏ ሲለሰልስና ማቆጥቆጥ ሲጀምር በጋ እንደደረሰ እወቁ« ተብሏል። እናም የምንዘምረው ዝማሬ ትልቅ ትርጉም አለው። ማዳኑን አይተናል። «ሆሳዕና በአርያም » እያሉ መዘመር ብቻውን ግን ዋጋ የለውም። ኢየሩሳሌም ተዘምሮባት ነበር። ግን ፍሬ የሌለባት በለስ በመሆኗ ደረቀች። በሚያምር ውብ ድንጋይ ፵፮ ዘመን የታነጸውን መቅደስ ማዳን አልቻለም። ተራሮችን ውደቁብን እስኪሉ ድረስ የወረደውን መከራ መሸሸግ የቻለ ዝማሬ አልተገኘም። መቅደሱ በወንበዴዎች ተሞልቶ ነበር። ወንበዴዎቹ ልጁን አልተቀበሉትም። የተቀበሉትም ፍሬ አላፈሩም። ስለዚህ በጭፍራ ተከበው ለሺህ ዘመናት ጠፉ። ዛሬ በኛ የሚሆን ፍሬ አልባነት ጥፋቱ ለሺህ ዘመን አይደለም። ለአልቦ ማኅለቅት እንጂ!!
በእድሜአችን ስንት «ሆሳዕና በአርያም» አሳለፍን? ማዳኑ በተደረገለት ማንነታችን ውስጥ ስንት ፍሬ አፈራን? የተራበው ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገውን ፍሬ ይዘናል? ወይስ ፍሬ አልባ ሆነን ለቁጣ የተዘጋጀን እንሆን? «ሆሳዕና በአርያም» ማለቱ ብቻውን አያድንም፣ ማዳኑንም አያመጣም። የወንበዴ ዋሻ ማንነታችንን እናጽዳ። ከዚህ ዓለም ሽቃጭና ልዋጭ ማስመሰያ ማንነት እንውጣ! በጎ ፍሬ እንዲያፈራ ለተላከው የወይኑ ባለቤት ወራሽ እንገዛ! ያኔ «ሆሳዕና በአርያም» ስንል ማዳኑ ፈጥኖ ይሆንልናል። ከኢየሱስ በቀር ማዳን የሚቻለውና ተስፋ የሚሆነን ማነው? ከሥጋ ለባሽ ማንም የለም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰው የሚታመን፣ በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
አዎ ሆሳዕና በአርያም! በዚህም አንተ ብቻ መታመኛ ነህ፣ በወዲያኛውም አንተ ብቻ! ሆሳዕና በአርያም።
ሃሌ ሉያ!!!!!!!!
Friday, April 8, 2022
ቻት ላይ ነን አትረብሹን!
ዮሐንስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።
¹² እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።
¹³ ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።
Wednesday, March 9, 2022
የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች በጉያዋ ናቸው!
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሦስት መንገድ ችግር ውስጥ ናቸው። 1ኛ/ ወደው ባልተወለዱበት ዘር ትግሬ በመሆናቸው በኦሮሙማው ኃይል የሚታዩት እንደጠላት ነው። 2ኛ/ የራሳቸው የአመራርና የሥልጣን አጠቃቀም ድክመት የተነሳ የመፈራትና የመከበር አቅማቸው አናሳ መሆኑ ሌላኛው ችግር ነው። 3ኛ/ ሊቃነ ጳጳሳቱ በራሳቸው የግል ኑሮ ምቾትና ምንግዴለሽነት የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱን ስለረሷት ከፓትርያርኩ ጋር መቆም አልቻሉም። ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁን ባለችበት መንገድ ከተጓዘች በውስጥና በውጪ ጠላቶቿ እየተገዘገዘች የመውደቋ ነገር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መፍረሷ አይቀርም። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ሦስት ምክር ያቀርባል።
1/የቀድሞው ፓትርያርክ ከዚህ ዓለም ስላረፉ አሁን ያሉት ፓትርያርክ ከእድሜ: ከህመምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳ በቂ ውሳኔ እየተሰጠ ባለመሆኑ ችግሮቹ ተደራራቢ እየሆኑ በመገኘታቸው ለቤተክርስቲያኒቱ ፈጣን አመራር መስጠት የሚችል ሰው በራሳቸው በፓትርያርኩ አቅራቢነት እንደራሴ ቢሾም:
2/ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ መሆኑ ከድግስና ከተጋነነ ሪፖርት ውጪ ችግር ፈቺ ስላልሆነ የየአህጉረ ስብከቶቹን ችግር የሚያጠናና ለእንደራሴው ቢሮ የሚያቀርብ ቡድን ተሰይሞ በየችግሮቹ ዘርፍ ፈጣን ውሳኔ ቢሰጥባቸው:
3/ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚቆረቆሩ በሙያ: በልምድና በችሎታ ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአማካሪ ቦርድ ቢቋቋም የተሻለ ይሆናል። ይህ አሰራር በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያና ተግባራዊ ሆኖ ብዙ ችግር መቃለል ተችሏል።
ከዚህ ውጪ አሁን ባሉት ጳጳሳት የሚፈታ የቤተ ክርስቲያን ችግር የለን። አይኖርምም። ራሳቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ናቸው። ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸውና በጥብዓት ይታገሉ የነበሩት ሁሉ በዐረፍተ ዘመን ሁሉን ትተው ሄደዋል።
አሁን ካሉት ጳጳስ ተብዬ ወመኔዎች አንዱ የሆነው ቅዱስ ፓትርያርኩ ለመናገር ያሰቡትን ሃሳብ እንዳያስተላልፉ የዱርዬ ስራውን እንዴት ይሰራ እንደነበር ይህ ቪዲዮ ያሳያልና ተመልክታችሁ ፍረዱ! በፕሮቶኮል ደረጃ ከፓትርያርኩ ፊት መነጋገሪያ ማይክ አይነሳም። ማፊያው ጀነራል ሦስት መነጋገሪያ ፓትርያርኩ እንዳይነጋገሩ ሲያሸሽና ለአዳነች አቤቤ ሲሰጥ ተመልከቱ።
Friday, February 4, 2022
የኦሮሙማ ህልመኞችና የኦርቶዶክስ ጳጳሳት!
የኦሮሙማ ሀገር ምስረታ ህልመኞች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን የሚቆጥሯት የአማራና የትግሬ ንብረት እንደሆነች አድርገው ነው። የሁለቱ ብሄሮች ደናቁርት የፖለቲካ ኤሊቶች ደግሞ ለስልጣን ካላቸው ጉጉት አንዱ ለአንዱ ጠላት መሆን ከጀመረና በሴራና ተንኮል መተላለቅ ከጀመረ ግማሽ ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል። ሰርቶ ከመኖር በስተቀር ስለፖለቲካው ምንም እውቀት የሌለው ደሃው ህዝብ በማያውቀው የፖለቲካ እሳት እየተጠበሰ ህይወቱን እየተነጠቀ: ሀብትና ንብረቱ ወድሞ ባዶ እጁን ቀርቷል። ይሄ እድል እጁ ላይ የወደቀው የኦሮሙማ መንግስት ከአማራና ከትግራይ እልቂትና ውድመት በኋላ ስልጣኑን አደላድሎ የተረፈችው ኦርቶዶክስን ሰባብሮ ለማጥፋት በቅጥረኞቹ በአባ ገዳ በላይ መኮንንና ወታደራዊ ሹመት ብቻ በቀረው ጀነራል አባ ዮሴፍ (እንኳን ጳጳስ የተመሰከረለት ወንበዴ ለመባል ይበዛበታል) በኩል ወጥሮ ይዟታል። ፊደል ተራራው አባ ወ/ኢየሱስ እና ቄሮ ኃይሉ ጉተታ የኦሮሙማው መንግስት ጉዳይ አስፈፃሚዎቹ ናቸው። ቤተክርስቲያኒቱ በአፄው ዘመን የአፄዎቹ አጋፋሪ ነበረች። በዘመነ ኢህአዴግ የህወሀት አለቅላቂ እንደነበረች ይታወቃል። በደርግ ዘመን ፓትርያርኩ አባ መርቆርዮስ የሸንጎ አባል ነበሩ።
ዛሬ ደግሞ የኦሮሙማው መንግስት የብልፅግና ወንጌል አራማጅ ስለሆነ ቤተክርስቲያኒቱን ለቀብር እየገነዛት ነው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ጳጳሳቱ በየወሩ ረብጣ ደመወዝ እየበሉ በወንበራቸው ላይ ተቀምጠዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ጉዲትን ቢሮአቸው ድረስ ብትጠራቸውም ሆቴል እንገናኝ ብላ አላግጣባቸዋለች። ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበትና ኦርቶዶክስ እየፈራረሰች ለምትገኝበት ሁኔታ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ በመንፈስ ቅዱስ እየመራናት ነው ብለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳለቁ እነዚህ ጳጳሳት ናቸው። መቼም ቢሆን በነዚህ ምንደኞች ቤተ ክርስቲያን ፈውስ አታገኝም። ምንደኛ ስለደመወዙ እንጂ ስለበጎቹ አይገደውምና በነዚህ ጳጳሳት ኦርቶዶክስ ከሞት አትድንም። የበጎች እውነተኛ እረኛና ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ የሰጠ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው!
Subscribe to:
Posts (Atom)