የሰው ልጅ ሁሉ የአዳምና የሔዋን ዘር ነው። ከዚህ የወጣ የለም። ሰው ክቡርና በእግዚአብሔር አምሣል የተፈጠረ ስለሆነ እንስሳ አይደለም። ሰው በተፈጥሮው እንስሳ ነው የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም እንኳን ሰው ግን እንስሳ አይደለም። በእርግጥ በተፈጥሮው ሰው ቢሆንም በአስተሳሰቡ ከእንስሳ ያልተሻለ ሰው ይኖራል። እንደባለጤና አእምሮ ሰው፤ ሰውኛ ማንነቱን ገላጭ አስተሳሰብ ሊኖረው የግድ ነው። እንስሳ አስተሳሰብ ማለት በሰው አምሣል ተፈጥሮ እንስሶች የሚሰሩትን የሚሠራ ወይም እንደእንስሳ የሚያስብ ማለት ነው። ዳዊትም በመዝሙሩ ይህን ኃይለ ቃል ሲገልጸው እንዲህ አለ። «ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ» (መዝ ፵፱፤፲፪)
አዎ ሰው ክቡርነቱን ትቶ በሃሳቡና በግብሩ፤ ነፍስያቸው ምናምንቴ እንደሆኑት እንስሶች መሰለ። ሁሉም ሰው የአንድ ዘር ምንጭ ቢሆንም ቅሉ ለሰይጣን ፈቃድ አድሮ በልዩነትና በክፍፍል መኖርን መርጧል። በክፍፍሉም እርስ በእርሱ ይባላል። ምክንያቱም አእምሮው ወደእንስሳነት አስተሳሰብ በወረደ ማንነት ተመርዟልና ነው። እንስሳት እርስ በእርሳቸው ይጠላላሉ። ነገን የሚጠብቁት አድነው ስለሚበሉት እንስሳ እንጂ በተስፋ ስለሚገነቡት ሕይወት አይደክሙም። ከዚያ ባለፈ እንስሳት ተስፋ የሚያደርጉት ዘላለማዊ ነገር ምንም የላቸውም። የማይሞት ተስፋ የተሰጠው የሰው ልጅ ግን በሚሞት ምድራዊ ተስፋ ላይ ራሱን አጣብቆ ይኖራል።ዳዊትም በመዝሙሩ ላይ ቃሉን በማስረገጥ ድኩማነ አእምሮው ሰዎችን በእንስሳ ይመስላቸዋል። «አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ» (መዝ ፵፱፤፳)
ጠቢቡስ «ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም» ማለቱ ምን ማለቱ ነበር? አዎ! ያን ማለቱ በአንጻራዊ ትርጉም አዲስ ነገር ያለው ከፀሐይ በላይ ነው ማለቱ ነበር። ከፀሐይ በላይ አዲስ ነገር እንዳለ እየተናገረን እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህም ነው ተስፋችን በማይጠፋና ዘላለማዊ በሆነው ከፀሐይ በላይ ባለው ነገር ላይ እንዲሆን አበክሮ በመናገር ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም የሚለን። እንዲያውም ከፀሐይ በታች ባለው ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ነፋስን እንደመከተል ነው ይላል። «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው» (መክ ፩፤፲፬) ነፋስን ማን ሊከተል ይችላል? ነፋስስ መሄጃው ወደየት ነው? መኖሩን እናውቃለን እንጂ ወደየት እንደሚሄድ አንረዳም፤ መቆሚያውም የት እንደሆነ አናውቅም፤ ልንከተለውም ማሰብ ከንቱ ድካም ነው። ከፀሐይ በታች ያለውን ነገር ሁሉ መከተል እንደዚሁ ይለናል። የቀደመው ነገር አልፏል፤ ያኔ ግን እንደአዲስ ይቆጠር ነበር። ዛሬ ደግሞ ነገ ቀድሞ ይሆናል። ቀድሞም ሆነ ዛሬ የምንላቸው ነገሮች ደግሞ ነገ የሉም። ሁለቱን የሚከተል ተስፋ የለውም። ቀድሞና፤ ዛሬ የሚባልለት ሁኔታ በሌለው ከፀሐይ በላይ ባለው አዲስ ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ይሻላል። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ያስተምረናል። «እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው» (፩ኛ ዮሐ ፪፤፳፭)
የማይጠፋውን የዘላለም አዲስ ተስፋ በእምነቱ የሚጠባበቅ እንደምናምንቴ ሰው ተስፋ በሌለው በዚህ ዓለም ከንቱ ነገር ላይ ራሱን አያጣብቅም። ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በዚህ ምድር ላይ መኖራቸውን እንደመጨረሻ ምዕራፍ ቢቆጥሩት አያስገርምም። መዝሙረኛው እንደተናገረው በአሳባቸው የሚጠፉ እንስሳትን መስለዋልና።
በእምነት ተስፋ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከፀሐይ በላይ ያለውን አዲስ ነገር ይጠባበቃሉ። ስለሆነም በዚህ ምድር ላይ እስካሉ ሁላቸውም በእምነት አንድ ናቸው። ልዩነትን አይሰብኩም። ጳውሎስም እንዲህ አለ። «በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ» (ገላ ፫፤፳፮-፳፱)