አዲሱ ፓትርያርክ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል!
በዚህም ተባለ፤ በዚያ አቡነ ማትያስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል። ባለፈው ግድፈትና እውነት ላይ እያነሳንና እየጣልን ጊዜ አናጠፋም። ይልቅስ ብዙዎች የታገሉለት የምርጫው ስኬት እንዳሰቡት ጥሩ የሥራ ጊዜ ይዞ ይመጣላቸው እንደሆነ የምናይበት፤ ገሚሶቻችንም የምናያቸው የቤተ ክህነት ተግዳሮቶች የሚቀረፉበት፤ ሰናይ የአስተዳደርና መንፈሳዊ ዘመን ናፍቆታችንን ተስፋ በማድረግ እንደዚህ በፊቱ አስቀድመን አንዳንድ ነገሮችን ለማመልከት ወደድን።
የአዲሱ ፓትርያርክ አዲስ የሥራ ዘመን ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። የተጠራቀሙ የቤተ ክህነቱ ችግሮችና ብዙ እንከኖች ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። የችግሮቹ ዓይነቶች፤ ደረጃና ጥልቀት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የተለያየ ውሳኔና እርምጃንም የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህ የተዘጋጀ የአእምሮ ዝግጁነት፤ የእውቀት በሊህነት፤ ድፍረትና ማስተዋል እንደሚጠይቁም አይጠረጠርም። ያንን ዓይነት ሰው ከየት እናገኛለን ብለን አናሳብም። ምክንያቱም ምርጫው /ከተባለ/ ትልቅ አባት ሰጥቶናልና። ስለዚህ ወደችግሮቹ እንንደርደር።
1/ የቤተ ክህነቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር ማሻሻል
የቤተ ክህነቱ ቀዳሚው ችግር ሥራና ሠራተኛ የተገናኘበት ተቋም አለመሆኑ ነው። ሥራና ሠራተኛ ካልተገናኘ ደግሞ በየትኛውም መልኩ የቤተ ክህነቱ የሥራ አፈጻጸም «ከርሞ ጥጃ» መሆኑ አይቀርም። ሥራና ሠራተኛ ማለት ለተገቢው ሥራ ተገቢ ባለሙያ ወይም ተቀራራቢ ችሎታ ያለው ሰው ማለት ነው። እንደዚህ ባለው ሰው ላይ የተቋሙን ዓላማና ግብ በደንብ ካስጨበጡት ከችግሮቹ ብዛት አንጻር ባንድ ጊዜ ፈጽሞ ባይወገድም፤ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። በዘመድ አዝማድ የተለጣጠፉና የተደረቱ ክፍሎችን ይዞ መቀጠል ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናልና አሁን ያለን የሥራና ሠራተኛ አቋም የችግሩ ዋና ምንጭ ነው ባይባልም የችግሩ አካል ነውና ከጥገናዊ ለውጥ ወይም ከማስመሰል /pseudo/ የራቀ ለውጥ ያስፈልገዋል። ከአቅም በታች ለመሥራት የእድሜ ጣሪያ የገደባቸውም በየመልኩ ቦታቸውን መያዝ ካልቻሉ ቤተ ክህነት የዘመዳ ዘመዶች የጡረታ ተቋም ሆኖ ይቀጥላል እንጂ የሥራ ብቃት መለኪያ ስፍራ ሊሆን አይችልም።