Monday, July 25, 2016

የሚፈውስና የሚያሳምም ስም - ኢየሱስ!!


(ከዙፋን ዮሐንስ)
የሆነ ጊዜ ፷፬ ሰው በሚይዝ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ተሣፍረን ወደክልል የሁለት ቀን መንገድ ተጓዝን። ቁርስ፣ ምሳ፣ አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመቀመጥ፣ የተነሳ ሁሉ ዘመድ ቤተሰብ ሆነ። የሆድ የሆዱን ተጫወተ። ስልክ ተቀያየረ፣ እጮኛም ያገኘ አይጠፋም። ያልተነሳ ርእስ አልነበረም። ፖለቲካ፣ የኑሮ ውድነት፣ ስለሳይንስ፣ ሃይማኖት፣ ስለታዋቂ ደራሲያን፣ ዘፋኝ፣ ፈላስፋ፣ ስለሃይማኖት አባት፣ ብዙ ብዙ….ብቻ ያልተወራ አልነበረም። አንዳንዶቹም ወሲብ ቀስቃሽ ቀልዶችን ግጥሞችን አውርተው መኪናው ውስጥ ከጫፍ እስከጫፍ አነቃቅተዋል። የወሲብ ነገር ሲወራ ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል። የሚያስቅ ከሆነ ይስቃል፣ የሚያሳፍር ከሆነም መስማት ያልፈለገ ይመስል የኮረኮሩት ያህል ግንባሩ ጥርስ በጥርስ ይሆናል። የአለቃ ገ/ሐና ነገር ሲነሳማ የአለቃን ወሲብ ወዳጅነትና ይጠቀሙ የነበረበትን የማማለል ዘዴ እያደነቀ ከልምዳቸው ብዙ የቀሰመው ነገር ያለ ይመስል ተሳፋሪው ይስቃል፣ ያውካካል።

ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ሳቅና ፍንደቃ ራሱን አግልሎ ከመስኮት ጥግ ተቀምጦ ያነብ ነበር። ድንገት ብድግ ብሎ “ኢየሱስ“ የሚለውን ስም አንስቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ አዳኝነቱን፣ ተስፋነቱን፣ አጽናኝነቱን መናገር ሲጀምር ብዙ ፊቶች ተቀያየሩ። አንዳንድ ፊቶች ቲማቲም መስለው ቀሉ። የባሰባቸው አንዳንዶች ደግሞ እንደበርበሬ ቀልተው የቁጣ ብናኛቸው በሰውየው ላይ በተኑ። ስለዝሙት ቀልድ ቦታ ሳይመርጡ ሲያውካኩ የነበረውን ረስተው ስለኢየሱስ ለመስማት ቦታ አጡና “ሰብከት ቦታ አለው“ አሉና ደነፉ። ጫወታችንን አታበላሽ አሉና አጉረመረሙ። ስለፌዝ፣ እርባና ስለሌለው ቀልድና ስለዝሙት ማውራት እንደጥሩ ጫወታ ተቆጥሮ ስለኢየሱስ መስማት ግን ጫወታን እንደማበላሸት ሆኖ ተቆጠረ።
እርግጥ ነው። የሥጋን ነገር መከተል ከእግዚአብሔር የመለየት ጉዳይ ስለሆነ ማበሳጨቱ የሚጠበቅ ነበር።

ሮሜ 8፣7
 “ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል” እንዳለው ሐዋርያው።

በየትኛውም መመዘኛ “ኢየሱስ” የሚለው ሃይለኛ ስም ሲጠራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል የሰዎች አስተሳሰብ ከሁለት ነገር ውጭ አይሆንም።
አንድም የኢየሱስን ጌትነትና አዳኝነት የሕይወቷ ቤዛ ላደረገችው ነፍስ ሃሴትን ያመጣልና በስሙ መጠራት ይኽች ነፍስ አታፍርም፣ አትቆጣም።
 ሁለትም የኢየሱስ አዳኝነት፣ ጌትነትና አምላክነት ብቸኛ ቤዛዋ ያላደረገችውን ነፍስ ያበሰጫታል፣ ያናድዳታል።

ምክንያቱም ፪ቆሮ ፪፣፲፮ “ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፣ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን“ እንደሚል ይኽ ስም ለዘላለማዊ ሕይወት ለተመረጡት የፕሮቴስታንት ይሁኑ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ አማኞች ሕይወት፣ ሕይወት የሚሸት ሰላምና እረፍት የሚያመጣ ሲሆን ለጥፋት ለተመረጡት ግን የሚያስቆጣ፣ የሚያነጫንጭ ጥርስ የሚያፋጭ ይሆናል። ዘፈንና ቀልዱ፣ ቧልትና ፌዙ ሲነገር ሁሉ ያለምንም ልዩነት አንድ ሆነው ሲስቁና ሲፈነድቁ እንዳልነበር “ኢየሱስ” የሚለው ስም ሲጠራ የሚያበሳጭበት ምክንያት ለምንድነው? እነዚህ ጴንጤዎች ቦታ የላቸውም እንዴ ማሰኘቱስ ለምን ይሆን? የራሱ የሆነውን ኢየሱስ ያዘጋጀ ሃይማኖት የለም።

ቢያንስ አዳምጦ ከወንጌል ቃል ውጪ የሆነውንና ያልሆነውን መለየት ሲቻል መቃወም ተገቢ አይደለም። ደደግሞም ፌዝና ሥጋዊ ነገርን ከማውራት ስለኢየሱስ መስማት በብዙ መልኩ ይሻላል። ለሁሉ ስለሞተው ስለኢየሱስ መናገር የተወሰኑ ሰዎች ስጦታ ሆኖ ሲያስወቅስ፣ ስለዝሙት መናገር ግን ለሁሉ የተፈቀደ መልካም ተግባር ሆኖ የሚቆጠርበት ምክንያት መኖር አልነበረበትም። ነገር ግን ይኽ ስም ሲጠራ ያስፈራቸውና ሐዋርያቱን፣ “ጀመሩ ደግሞ እነዚህ የተረገሙ!” ያስብል እንደነበር ወንጌል ያስታውሰናል።

1. ስሙን ሲጠራ ለተቀበሉ የሕይወት ሽታ የሆነላቸው። ሐዋ ፰
 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፊልጶስ ስለኢየሱስ ሲሰብክለት ልቡ ደስ ተሰኘ። አጥምቀኝ አለው እንጂ “የእናትና አባት ሃይማኖቴን ተከትዬ ከኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ድረስ ያስመጣኝና ተራራ የወጣሁበትን ታላቅ የበረከት ጉዞ አድርጌ ከመመለስ ባለፈ ያንተን ኢየሱስ ለመስማት አልመጣሁም“…ብሎ አልተቆጣም።
በሉቃ ፳፯-፳ ላይም የኤማሁስ መንገደኞች ስለኢየሱስ በመጽሐፍ የተጻፈውን ሲሰሙ ልባቸው ይቃጠልባቸው ነበር። በዚያ በነበርንበት አውቶቡስ ላይ ግን ለብዙዎች ልባቸው የተቃጠለው ለምን ይኄንን ስም ትጠራላችሁ? ብለው በመናደድ ነበር።
ሐዋ ፲-፳፬ ላይ መቶአለቃ ቆርኔሌዎስም ጭራሽ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ ስለኢየሱስ ስበኩኝ ብሎአል። ስለኢየሱስ መስማት ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ ጆሮ የሚያሳክክበት ምክንያት አይኖርም። ቢያንስ ስለአለቃ ገ/ሐና የዝሙት ጥበብና ሴቶችን እንዴት እንደሚያጠምዱ ከመስማት ይልቅ አምነው ባይቀበሉት እንኳን ስለኢየሱስ የሚነገረውን የወንጌል ቃል ማዳመጥ ለዝሙት ልብን ከማነሳሳት ከንቱ ወሬ ሳይሻል አይቀርም።
  በበዓለ ሃምሳ የተሰበሰቡት አይሁድ ስለኢየሱስ ሲወራ ልባቸው ተነክቶ ሐዋርያትን “ምን እናድርግ ?? “ብለው እርዳታ ጠየቁ እንጂ “በየመንገዱ በየአደባባዩ በየባሱ እየሰበካችሁ፣ አታስቸገሩ “ብለው በተቆርቋሪነት ሰበብ የአጋንንትን ቁጣ አልተቆጡም። እነዚህ ስሙን የሰሙና ያልተቃወሙ ሁሉ መጨረሻቸው ያመረ ክርስቲያኖች ሆነው በሰማይ የዘላለም ሕይወትን በምድርም በረከትን አግኝተው ወደጌታ ሄደዋል።

2. የሞት ሽታ የሆነባቸውና ስሙ ሲጠራ የሚያበሳጫቸው የሚያስቆጣቸው ሰዎች እንዲህ የሚሆኑት እነሱ ሳይሆኑ በውስጣቸው የተቀመጠው ክፉ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው። ይኽ ስም ሰዎችን ከሥጋዊና መንፈሳዊ ደዌ ስለሚፈታ ሰይጣን ይጠላዋል። መድኃኒትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ሰውነት መድኃኒት ለሞት እንደሚሆንበት ሁሉ ኢየሱስ የሚለውም ስም ለሞት ይኾንባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብን አምላክ እንደሚያመልክ ስለሚያምን “ኢየሱስ” የሚባለው ስም ያበሳጨው ነበር። ይኽንን ስም የሚጠሩትን ያስርና ያስገድል ነበር። ሐዋ ፬:፲፰ “በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው” “ በማለት ፈሪሳዊያን ስሙ የሞት ሽታ እንደሆነባቸው ያሳያል። “ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።“ በማለት ስሙ እንዳስገረፈ አንብበናል።

ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬም ይህንን ስም መጥራት ያስደነግጣል/ያስፈራል/ኤሌክትሪክ ያስጨብጣል። በስካር መንፈስ ናውዞ ውሃ መውረጃ ቱቦ ስር የሚያድረው ብረቱ፣ አንበሳው ሲባል ዘማዊውና አለሌው ቀምጫዩ እየተባለ ሲሞካሽ፣ ሌባው ቢዝነሳሙ፣ እሳቱ ሲሉት የኢየሱስ ስብከት ሲነሳ ግን ሃይማኖተኛ ሆኖ ሲያፈጥ ማየት በጣም ያሳዝናል። ጫትና ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሺሻ የሚያናውዘው ሱሰኛው ሰው ለጥምቀትና ትንሣኤ በአጭር ታጥቆ መንገድ ከሚጠርግ፣ ቄጠማ ከሚጎዘጉዝ፣ ምንጣፍ ከሚያነጥፍ ውስጡ ተጎዝጎዞ ከተቀመጠው ክፉ መንፈስ ኢየሱስን ንጉሡ አድርጎ ቢያኖር ኖሮ ከዐመጻ ተግባራቱ ነጻ በወጣ ነበር። የሕይወቴ መሪ ነው ያለ ሰው ንሰሃ ገብቶ ኢየሱስ ሰው አደረገኝ ይላል እንጂ “ኢየሱስ” ብሎ የሚሰብክን ሰው “መግደል ነበር“ አይልም። እህቴና ወንድሜ ዛሬ ኢየሱስ አንተና አንች ጋር የሞት ሽታ ወይስ የሕይወት ሽታ ነው? ሁላችን ራሳችንን እንመርምር።
 ክብርና ምስጋና ነፍስ ሥጋና መንፈስን ነጻ ለሚያወጣው ሰው ለሚያደርገው ትልቅ ስም፣ ለኢየሱስ ክብር ይሁን! አሜን

Friday, July 15, 2016

ትወደኛለህን?


(ከነገ ድል አለ)
ምላሽ የሚያሻው የክርስቶስ ጥያቄ - ትወደኛለህን? (ዮሐንስ 21)
ይህን ጥያቄ ስናነብ ወደ አእምሮአችን በቶሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ብለን እናስብ ይሆናል፤ ወይም ጥያቄው የአፍቃሪ ጥያቄ አንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አሊያ እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ጥያቄው ረጅም ጊዜ ዐብሮን ከኖረ ሰው፥ በጣም ከሚያውቀንና ከምናውቀው ሰው፥ ለምሳሌ፥ ከባለቤታችን ወይም ከጓደኛችን ቢመጣስ ምን ይሰማናል? ያለ ጥርጥር ምን አይቶብኝ ይሆን? ወይም ምን አይታብኝ ይሆን? ምን ሰምቶብኝ/ምን ሰምታብኝ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል።
ጥያቄው “አዎን እወድሃለሁ” የሚል ምላሽን ለማግኘት ወይም መወደድን ለማወቅ የተጠየቀ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከፍቅረኛ፥ ከትዳር አጋር ወይም ከጓደኛ የመጣ ሳይሆን ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይም ለጴጥሮስ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በ21ኛው ምዕራፍ አንደ ዘገበልን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ያህል “ትወደኛለህን?” ሲል ጠይቆታል።

እወድሃለሁ
“ትወደኛለህን?” የሚለው ጥያቄ ፍቅርን ለማወቅ ወይም ለማረጋገጥ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ጥያቄው ከዚያ የሚያልፍ መልእክት አለው። በርግጥ ትወደኛለህን? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አልወድህም የሚል አይሆንም። በክርስቶስና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን ግንኙነት መለስ ብለን ስናስታውስ፥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሥጋ ልለያችሁ ነው፤ ልሄድ ነው ብሎ በነገራቸው ጊዜ፥ ጴጥሮስ ‘ተለይተኸን ወዴት ትሄዳለህ? የትም ብትሄድ ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ ሞት እንኳ ቢመጣ ከአንተ አልለይም’ ያለው ሰው ነበር (ዮሐ. 13፥36-38)። ጌታ ለጴጥሮስ ንግግር የሰጠው ምላሽ፥ ‘እንኳ ነፍስህን ልትስጠኝ፥ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ’ የሚል ነበር።

ፍቅር እንዴት ይገለጣል?
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የፍቅር መገለጫ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፥ ከባህል ባህል ይለያያል። የፍቅር መግለጫ ቋንቋ፥ የጋለ ጭብጨባ፥ እንባ፥ የቃል ንግግር፥ አበባ ማበርከት፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ መሳሳም ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍቅር ይገለጣል። ጌታ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቀው፥ ጴጥሮስም ሦሰት ጊዜ መላልሶ እወድሃለሁ ብሎታል። እንዲሁም በኋላ ላይ ግራ የገባው በሚመስል መልክ፥ በማዘንም ጭምር እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ ብሎታል።

ፍቅርና ተግባር
በአጠቃላይ በወንጌል በተለይም በጌታችን ትምህርትና ሕይወት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የፍቅር ዋና መገለጫ ቃላት ሳይሆኑ ተግባር ነው። ጴጥሮስ “እወድሃለሁ” ቢልም በተግባር ግን ይህን ፍቅር ማሳየት አልቻለም፤ እወድሃለሁ ያለውን ጌታውን ክዶታል። ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፥13 ላይ ነፍሱን ለወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር እንደሌለና ነፍስን መስጠት የፍቅር ጣሪያ መሆኑን እንዳስተማረ፥ በተግባርም ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ነው ጌታ ጴጥሮስን “ትወደኛለህን?” ሲል መላልሶ የጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ቀድሞው፥ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም” (ማቴ. 26፥35) አላለም። የራሱን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ነበር ያለው። ጴጥሮስ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ባይችልም፥ ኢየሱስ ፍቅሩን በተግባር ከገለጠና፥ የካደውን ጴጥሮስን በዚህ ፍቅር እንደ ገና ከመለሰው በኋላ አልከሰሰውም። ይልቁንም ሲመልሰውና ወይም እንደ ገና ሲያድሰው፥ ኀላፊነትንም ሲሰጠው እንመለከታለን።

መልእክቱ

“ትወደኛለህን?” የሚለው የጌታ ጥያቄ “አዎን እወድሃለሁ” ከሚል ምላሽ ያለፈ ቀጥተኛ መልእክት አለው። መልእክቱም የምትወደኝ ከሆነ አደራዬን ተወጣ የሚል ነው። ጌታ ሦስት ጊዜ፥ “ትወደኛለህን?” ሲል ከጠየቀው በኋላ ጴጥሮስ “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ፥ ግልግሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ የሚል ግልጽ አደራ ሰጥቶታል (ዮሐ 21፥15-17)። ይህ ኀላፊነት ወይም አደራ የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጨምር እንደሚሆን ቀጥሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ እናነባለን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጒልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ።” የዚህ ክፍል መልእክት በእኛም ሕይወት ሊተገበር የሚገባው ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል። ትወደኛለህን? ለሚለው ጥያቄ በቃል “እወድሃለሁ!!” የሚለውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳችንን መልሰን መጠየቅ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። በርግጥ ጌታን እንወደዋለን ወይ?

Monday, July 4, 2016

እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም አስፈላጊዎች ናቸው!

(ከኪሩቤል ሮሪሳ ጽሑፍ ተሻሽሎ የተወሰደ)
ነገሥታቶች በሪፐብሊካዊ መንገድ ሥልጣንን በእጃቸው ካስገቡ መሪዎች የበለጠ ቅቡል ነበሩ። የሥልጣን መሠረታቸው መለኮታዊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ሕዝብ በፈቃዱ ይገዛላቸው ነበር። እነርሱም ሕዝባቸውን ይወዳሉ... ሕዝብም ይወዳቸዋል። በንጉሣዊ አገዛዝ ንጉሡ አባወራ.., ንግሥቲቱ እማወራ... ሕዝብ ደግሞ ልጆች ናቸው። አዋጅ ሲነገር "የምንወድህና የምትወደን ህዝብ ሆይ" ብለው ንግግር ይጀምራሉ። ይኼ ጭምብል ያለው ማታለያ አይደለም። እውነት ነው። በእነዚህ አካላት መካከል እውነተኛ ፍቅር ነበር። ምክንያቱም በታዛዥ ልጅና አባት መካከል ፀብ አይኖርም። ፀቡ የሚጀምረው ልጅ እምቢ ሲል ነው።
ሕዝብ ሁሉንም ነገር እሺ ብሎ በሚቀበልባቸውና ንጉሣዊ አስተዳደር ባለባቸው አገሮች የተሻለ ሰላም አለ። ሕዝብ ጠግቦ ሊበላ ይችላል። ባይበላም ከላይ ከሰማይ የተሰጠን የ40 ቀን እድል ነው ስለሚባልና የመብት ጥያቄዎች ስለማይኖሩ የአገርም አንድነት አይናጋም። እዚህም እዚያም የቦምብ ፍንዳታና ግድያ አይኖርም። የትልቅ አገር (በተለየ አተያይ) ባለቤት የመሆን እድልም ሰፊ ነው። በኛም አገር ከነበሩት የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞች መካከል ከላይ የተጠቀሱት ይገኙበታል። ስለዚህ እነኚህን የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞችን የቀመሰም ሆነ የሰማ ሰው... ዛሬ ላይ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ነኝ ቢል ላይገርም ይችላል።
ሥልጣንን የመጋራትም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምርባቸው አገሮች ላይ ሰላም አይኖርም። ስደትና እንግልቶች ይኖራሉ። የረጋና ጸጥታ የሰፈነበትን ንጉሣዊ አስተዳደር ወደ ሌላ ሥርዓት የሚቀይረው እምቢታ ነው።
እምቢታ የለውጥ መጀመሪያ ነው። የዓለምን ቅርጽ የቀየረው እምቢታ ነው። የእምቢታ መሠረቱ ደግሞ እውቀት ነው። የንጉሣዊ አስተዳደሮች አገዛዝ ማዕበል አልባ ሐይቅ ነው። የማይንቀሳቀስ ውሃ ከሩቅ ሲታይ ፀጥታው ቢያስጎመዥም ውስጡ ላሉ አሣዎች ግን መራር ነው። ማዕበል ሲቆም አሣዎች መሞት ይጀምራሉ። እንቅስቃሴ አልባ የሆነ ነገር መልካም ቢመስልም ቆይቶ ግን ይገማል... ይሞታልም። ስለዚህ ንጉሣዊ አስተዳደሮች ለለውጥ የማይጋብዙ ስለነበሩ በኃይል መቀየራቸው ግድ ነበር። ሕዝብ በፀጥታው ውስጥ ተኝቶ ነበር። ሕይወት በድግግሞሽ የተሞላች አሰልቺ ነበረች።
በንጉሣዊ የአስተዳደር ሕግ ገዢው ግለሰብ እንጂ ሃሳብ አይደለም። ንጉሣዊ ባልሆነው ዓለም ደግሞ ገዢ የሚሆነው ሃሳብ ነው። የግለሰብ መኖር አስፈላጊ ላይሆንም ይችላል። ፓርቲዎች ሃሳቦችን ሲያመነጩ ሕዝቦች ደግሞ "ገዢ" ለሆነው ሃሳብ ድምፅ ይሰጣሉ። በዚህ የሥርዓት ሂደት... ሕይወት በምርጫ ውሳኔ ውስጥ ትወድቃለች። ለመምረጥ ሁለቱም መኖር አለባቸው። ሁለቱ ነገሮች ተነፃፃሪ እንጂ ተጻራሪ አይደሉም። መጻረር የሚባል ነገር የለም። ሁለቱም ትክክል ናቸው። የተሳሳተ የሚባል ነገርም የለም። አንዱ ከሌለ ምርጫ የሚባል ነገር ይጠፋል። አንዱ ፓርቲ ወንበር ይዞ ይቀርባል። አንዱ ደግሞ ሶፋ። ሕዝብ የፈለገውን መርጦ ያስቀመጥበታል። በዚህ መሃል ፓርቲዎች "ሶፋ ለእንቅልፍ ይጋብዛል" ወይም "ደረቅ ወንበር ለኪንታሮት ሕመም ይዳርጋል" ተባብለው ልዩነቱን ማጦዝ ይችላሉ። ነገር ግን ወንበር፣ ወንበር መሆኑ ሶፋም፣ ሶፋ መሆኑ እሙን ነው። ሁለቱም ይጠቅማሉ። ይህ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ፈጠራን አበረታቶ ለለውጥ ይጋብዛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የፖለቲካ አረዳድ ሶፋ ካለ ወንበር አያስፈልግም። ወንበርና ሶፋ ተጻራሪ እንጂ ተነጻጻሪ አይደሉም። ሁለቱም ጎራዎች ውስጥ በውስጣቸው የተቀበረ ንጉሳዊ መለዮ አለ። እኔ ብቻ ነኝ፣ የሥልጣን ምንጭ የሚል። ልዩነትን እንደጠላት የማየትና የእኔ ብቻ ትክክል የማለት አባዜ አገራችንን ጠፍንጎ ይዟታል። ከንጉሣዊ አስተዳደር ተላቀን ከለውጡ ልናገኝ የነበረውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እነዚህ ሁለት ጎራዎች መና አስቀርተውታል። የለውጡ ችቦ ከተለኮሰ ከ40 በላይ ዓመታት ቢቆጠሩም ዛሬም ፖለቲካችን አዙሪት ውስጥ ነው። የአዙሪቱ ምክንያት አንድ ነው። የመቀያየር ሳይሆን የመጠፋፋት አባዜ። ገዢው የተቃዋሚው.... ተቃዋሚው ደግሞ የገዢው ጠላቶች ናቸው። አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ መንገሥ ይፈልጋል።
ይህ በሽታ ወደ አዲሱ ትውልድም እየተዛመተ ነው። ወጣቱ ልዩነትን ባየ ቁጥር፣ ስም መለጠፍ ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ፍላጎቱ አይታወቅም።
የንጉሣዊ አስተዳደርን ባሕርያት በጥልቀት በማጥናት ለውጡ አስፈላጊ እንደነበረ መረዳትና ወደኋላ ተመልሰን እሱን የምንናፍቅበት መሠረት እንደሌለ ማመን ላይ ገና ብዙ ክፍተት አለ። በዚህ ዘመን ወደኋላ ተመልሶ ንጉሥ መናፈቅ ምን ይባላል?
መነሻው ባለው ላይ በትንሽ ነገር ተስፋ መቁረጥ... እልህና አጉል ጀብደኝነት ነው። የታሰረ ሁላ ጀግና.... ተቃዋሚ ሁላ ሽብርተኛ በማለት ፈርጆ ለመጠፋፋት ምሏል። ለዚህ ሁላ ምስቅልቅል የፖለቲካ ባህል ተጠያቂው ስንፍናና ድንቁርና ነው። በየጊዜው ዓላማችን ሥርዓት ለመቀየር እንጂ እኛ ለመቀየር ፍላጎት የለንም። ያልተቀየረ አስተሳሰብ ደግሞ የተቀየረ ሕብረተሰብ ሊፈጥር አይችልም። መለወጥ ያለበት አተያያችን ነው። እሳትና ውሃን አለቦታው ለመጠቀም መፈለግ የፈጣሪ ስህተት ሳይሆን የኛ ጉድለት ነው።
ውሃን እሳት ውስጥ ብንጨምር ወይም እሳትን ውሃ ውስጥ ብናስገባ ለመጠፋፋታቸው ስህተቱ የማነው? የበረደው ሰው እሳትን በብብቱ ይይዝ ዘንድ አይጠበቅም።
ነገር ግን ውሃንና እሳትን መጥነን በመደጋገፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንችላለን። ይህ የአስተሳብ ብስለት ነው። ፖለቲካችንን ግን ለምንኖርባት ቤታችን እንደሚመጥን አድርገን አስማምተን መጠቀም አልቻልንም። አጥፊና ጠፊ መሆኑ እስካላከተመ ድረስ አዙሪቱ ደግሞ አይለቀንም። ስለዚህ መለወጥ ያለበት ወንበሩ ሳይሆን ወንበሩን የሚፈልጉ ጭንቅላቶች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚነግረን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከቀረቡ ክሶች መካከል አንዱ "ንጉሥ ነኝ ይላል" የሚል ነበር። ይኽ ንግግር ደግሞ በወቅቱ በሕዝቡ ላይ ተሹሞ ለነበረው ሰው ትልቅ ራስ ምታት ነው። ምክንያቱም ሥልጣን የሚቀናቀን ሰው ቶሎ መጥፋት አለበት። ከሳሾቹም ይኽንን ያውቃሉ። በአደባባይም የተጠየቀው "አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህን?" የሚለው መቅደሙ መልሱን ለማወቅ ነው። የሚቀናቀን ከሆነ ቶሎ የማጥፋት አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ መጠፋፋት አያቆምም። እርግጥ ነው፣ እንደሥርዓት ዛሬ አፄ የለም። በወንበር ላይ ግን መንግሥትም፣ ተቃዋሚም ሁሉም የአስተሳሰብ አፄ ነው። ትውልድ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለበት። እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም በወሰን፣ በክልል፣ በመጠንና በልክ ከተጠቀምንባቸው ሁለቱም የግድ አስፈላጊዎቻችን ናቸው።