Friday, July 15, 2016

ትወደኛለህን?


(ከነገ ድል አለ)
ምላሽ የሚያሻው የክርስቶስ ጥያቄ - ትወደኛለህን? (ዮሐንስ 21)
ይህን ጥያቄ ስናነብ ወደ አእምሮአችን በቶሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ብለን እናስብ ይሆናል፤ ወይም ጥያቄው የአፍቃሪ ጥያቄ አንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አሊያ እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ጥያቄው ረጅም ጊዜ ዐብሮን ከኖረ ሰው፥ በጣም ከሚያውቀንና ከምናውቀው ሰው፥ ለምሳሌ፥ ከባለቤታችን ወይም ከጓደኛችን ቢመጣስ ምን ይሰማናል? ያለ ጥርጥር ምን አይቶብኝ ይሆን? ወይም ምን አይታብኝ ይሆን? ምን ሰምቶብኝ/ምን ሰምታብኝ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል።
ጥያቄው “አዎን እወድሃለሁ” የሚል ምላሽን ለማግኘት ወይም መወደድን ለማወቅ የተጠየቀ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከፍቅረኛ፥ ከትዳር አጋር ወይም ከጓደኛ የመጣ ሳይሆን ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይም ለጴጥሮስ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በ21ኛው ምዕራፍ አንደ ዘገበልን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ያህል “ትወደኛለህን?” ሲል ጠይቆታል።

እወድሃለሁ
“ትወደኛለህን?” የሚለው ጥያቄ ፍቅርን ለማወቅ ወይም ለማረጋገጥ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ጥያቄው ከዚያ የሚያልፍ መልእክት አለው። በርግጥ ትወደኛለህን? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አልወድህም የሚል አይሆንም። በክርስቶስና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን ግንኙነት መለስ ብለን ስናስታውስ፥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሥጋ ልለያችሁ ነው፤ ልሄድ ነው ብሎ በነገራቸው ጊዜ፥ ጴጥሮስ ‘ተለይተኸን ወዴት ትሄዳለህ? የትም ብትሄድ ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ ሞት እንኳ ቢመጣ ከአንተ አልለይም’ ያለው ሰው ነበር (ዮሐ. 13፥36-38)። ጌታ ለጴጥሮስ ንግግር የሰጠው ምላሽ፥ ‘እንኳ ነፍስህን ልትስጠኝ፥ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ’ የሚል ነበር።

ፍቅር እንዴት ይገለጣል?
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የፍቅር መገለጫ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፥ ከባህል ባህል ይለያያል። የፍቅር መግለጫ ቋንቋ፥ የጋለ ጭብጨባ፥ እንባ፥ የቃል ንግግር፥ አበባ ማበርከት፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ መሳሳም ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍቅር ይገለጣል። ጌታ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቀው፥ ጴጥሮስም ሦሰት ጊዜ መላልሶ እወድሃለሁ ብሎታል። እንዲሁም በኋላ ላይ ግራ የገባው በሚመስል መልክ፥ በማዘንም ጭምር እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ ብሎታል።

ፍቅርና ተግባር
በአጠቃላይ በወንጌል በተለይም በጌታችን ትምህርትና ሕይወት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የፍቅር ዋና መገለጫ ቃላት ሳይሆኑ ተግባር ነው። ጴጥሮስ “እወድሃለሁ” ቢልም በተግባር ግን ይህን ፍቅር ማሳየት አልቻለም፤ እወድሃለሁ ያለውን ጌታውን ክዶታል። ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፥13 ላይ ነፍሱን ለወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር እንደሌለና ነፍስን መስጠት የፍቅር ጣሪያ መሆኑን እንዳስተማረ፥ በተግባርም ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ነው ጌታ ጴጥሮስን “ትወደኛለህን?” ሲል መላልሶ የጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ቀድሞው፥ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም” (ማቴ. 26፥35) አላለም። የራሱን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ነበር ያለው። ጴጥሮስ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ባይችልም፥ ኢየሱስ ፍቅሩን በተግባር ከገለጠና፥ የካደውን ጴጥሮስን በዚህ ፍቅር እንደ ገና ከመለሰው በኋላ አልከሰሰውም። ይልቁንም ሲመልሰውና ወይም እንደ ገና ሲያድሰው፥ ኀላፊነትንም ሲሰጠው እንመለከታለን።

መልእክቱ

“ትወደኛለህን?” የሚለው የጌታ ጥያቄ “አዎን እወድሃለሁ” ከሚል ምላሽ ያለፈ ቀጥተኛ መልእክት አለው። መልእክቱም የምትወደኝ ከሆነ አደራዬን ተወጣ የሚል ነው። ጌታ ሦስት ጊዜ፥ “ትወደኛለህን?” ሲል ከጠየቀው በኋላ ጴጥሮስ “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ፥ ግልግሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ የሚል ግልጽ አደራ ሰጥቶታል (ዮሐ 21፥15-17)። ይህ ኀላፊነት ወይም አደራ የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጨምር እንደሚሆን ቀጥሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ እናነባለን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጒልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ።” የዚህ ክፍል መልእክት በእኛም ሕይወት ሊተገበር የሚገባው ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል። ትወደኛለህን? ለሚለው ጥያቄ በቃል “እወድሃለሁ!!” የሚለውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳችንን መልሰን መጠየቅ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። በርግጥ ጌታን እንወደዋለን ወይ?

Monday, July 4, 2016

እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም አስፈላጊዎች ናቸው!

(ከኪሩቤል ሮሪሳ ጽሑፍ ተሻሽሎ የተወሰደ)
ነገሥታቶች በሪፐብሊካዊ መንገድ ሥልጣንን በእጃቸው ካስገቡ መሪዎች የበለጠ ቅቡል ነበሩ። የሥልጣን መሠረታቸው መለኮታዊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ሕዝብ በፈቃዱ ይገዛላቸው ነበር። እነርሱም ሕዝባቸውን ይወዳሉ... ሕዝብም ይወዳቸዋል። በንጉሣዊ አገዛዝ ንጉሡ አባወራ.., ንግሥቲቱ እማወራ... ሕዝብ ደግሞ ልጆች ናቸው። አዋጅ ሲነገር "የምንወድህና የምትወደን ህዝብ ሆይ" ብለው ንግግር ይጀምራሉ። ይኼ ጭምብል ያለው ማታለያ አይደለም። እውነት ነው። በእነዚህ አካላት መካከል እውነተኛ ፍቅር ነበር። ምክንያቱም በታዛዥ ልጅና አባት መካከል ፀብ አይኖርም። ፀቡ የሚጀምረው ልጅ እምቢ ሲል ነው።
ሕዝብ ሁሉንም ነገር እሺ ብሎ በሚቀበልባቸውና ንጉሣዊ አስተዳደር ባለባቸው አገሮች የተሻለ ሰላም አለ። ሕዝብ ጠግቦ ሊበላ ይችላል። ባይበላም ከላይ ከሰማይ የተሰጠን የ40 ቀን እድል ነው ስለሚባልና የመብት ጥያቄዎች ስለማይኖሩ የአገርም አንድነት አይናጋም። እዚህም እዚያም የቦምብ ፍንዳታና ግድያ አይኖርም። የትልቅ አገር (በተለየ አተያይ) ባለቤት የመሆን እድልም ሰፊ ነው። በኛም አገር ከነበሩት የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞች መካከል ከላይ የተጠቀሱት ይገኙበታል። ስለዚህ እነኚህን የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞችን የቀመሰም ሆነ የሰማ ሰው... ዛሬ ላይ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ነኝ ቢል ላይገርም ይችላል።
ሥልጣንን የመጋራትም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምርባቸው አገሮች ላይ ሰላም አይኖርም። ስደትና እንግልቶች ይኖራሉ። የረጋና ጸጥታ የሰፈነበትን ንጉሣዊ አስተዳደር ወደ ሌላ ሥርዓት የሚቀይረው እምቢታ ነው።
እምቢታ የለውጥ መጀመሪያ ነው። የዓለምን ቅርጽ የቀየረው እምቢታ ነው። የእምቢታ መሠረቱ ደግሞ እውቀት ነው። የንጉሣዊ አስተዳደሮች አገዛዝ ማዕበል አልባ ሐይቅ ነው። የማይንቀሳቀስ ውሃ ከሩቅ ሲታይ ፀጥታው ቢያስጎመዥም ውስጡ ላሉ አሣዎች ግን መራር ነው። ማዕበል ሲቆም አሣዎች መሞት ይጀምራሉ። እንቅስቃሴ አልባ የሆነ ነገር መልካም ቢመስልም ቆይቶ ግን ይገማል... ይሞታልም። ስለዚህ ንጉሣዊ አስተዳደሮች ለለውጥ የማይጋብዙ ስለነበሩ በኃይል መቀየራቸው ግድ ነበር። ሕዝብ በፀጥታው ውስጥ ተኝቶ ነበር። ሕይወት በድግግሞሽ የተሞላች አሰልቺ ነበረች።
በንጉሣዊ የአስተዳደር ሕግ ገዢው ግለሰብ እንጂ ሃሳብ አይደለም። ንጉሣዊ ባልሆነው ዓለም ደግሞ ገዢ የሚሆነው ሃሳብ ነው። የግለሰብ መኖር አስፈላጊ ላይሆንም ይችላል። ፓርቲዎች ሃሳቦችን ሲያመነጩ ሕዝቦች ደግሞ "ገዢ" ለሆነው ሃሳብ ድምፅ ይሰጣሉ። በዚህ የሥርዓት ሂደት... ሕይወት በምርጫ ውሳኔ ውስጥ ትወድቃለች። ለመምረጥ ሁለቱም መኖር አለባቸው። ሁለቱ ነገሮች ተነፃፃሪ እንጂ ተጻራሪ አይደሉም። መጻረር የሚባል ነገር የለም። ሁለቱም ትክክል ናቸው። የተሳሳተ የሚባል ነገርም የለም። አንዱ ከሌለ ምርጫ የሚባል ነገር ይጠፋል። አንዱ ፓርቲ ወንበር ይዞ ይቀርባል። አንዱ ደግሞ ሶፋ። ሕዝብ የፈለገውን መርጦ ያስቀመጥበታል። በዚህ መሃል ፓርቲዎች "ሶፋ ለእንቅልፍ ይጋብዛል" ወይም "ደረቅ ወንበር ለኪንታሮት ሕመም ይዳርጋል" ተባብለው ልዩነቱን ማጦዝ ይችላሉ። ነገር ግን ወንበር፣ ወንበር መሆኑ ሶፋም፣ ሶፋ መሆኑ እሙን ነው። ሁለቱም ይጠቅማሉ። ይህ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ፈጠራን አበረታቶ ለለውጥ ይጋብዛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የፖለቲካ አረዳድ ሶፋ ካለ ወንበር አያስፈልግም። ወንበርና ሶፋ ተጻራሪ እንጂ ተነጻጻሪ አይደሉም። ሁለቱም ጎራዎች ውስጥ በውስጣቸው የተቀበረ ንጉሳዊ መለዮ አለ። እኔ ብቻ ነኝ፣ የሥልጣን ምንጭ የሚል። ልዩነትን እንደጠላት የማየትና የእኔ ብቻ ትክክል የማለት አባዜ አገራችንን ጠፍንጎ ይዟታል። ከንጉሣዊ አስተዳደር ተላቀን ከለውጡ ልናገኝ የነበረውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እነዚህ ሁለት ጎራዎች መና አስቀርተውታል። የለውጡ ችቦ ከተለኮሰ ከ40 በላይ ዓመታት ቢቆጠሩም ዛሬም ፖለቲካችን አዙሪት ውስጥ ነው። የአዙሪቱ ምክንያት አንድ ነው። የመቀያየር ሳይሆን የመጠፋፋት አባዜ። ገዢው የተቃዋሚው.... ተቃዋሚው ደግሞ የገዢው ጠላቶች ናቸው። አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ መንገሥ ይፈልጋል።
ይህ በሽታ ወደ አዲሱ ትውልድም እየተዛመተ ነው። ወጣቱ ልዩነትን ባየ ቁጥር፣ ስም መለጠፍ ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ፍላጎቱ አይታወቅም።
የንጉሣዊ አስተዳደርን ባሕርያት በጥልቀት በማጥናት ለውጡ አስፈላጊ እንደነበረ መረዳትና ወደኋላ ተመልሰን እሱን የምንናፍቅበት መሠረት እንደሌለ ማመን ላይ ገና ብዙ ክፍተት አለ። በዚህ ዘመን ወደኋላ ተመልሶ ንጉሥ መናፈቅ ምን ይባላል?
መነሻው ባለው ላይ በትንሽ ነገር ተስፋ መቁረጥ... እልህና አጉል ጀብደኝነት ነው። የታሰረ ሁላ ጀግና.... ተቃዋሚ ሁላ ሽብርተኛ በማለት ፈርጆ ለመጠፋፋት ምሏል። ለዚህ ሁላ ምስቅልቅል የፖለቲካ ባህል ተጠያቂው ስንፍናና ድንቁርና ነው። በየጊዜው ዓላማችን ሥርዓት ለመቀየር እንጂ እኛ ለመቀየር ፍላጎት የለንም። ያልተቀየረ አስተሳሰብ ደግሞ የተቀየረ ሕብረተሰብ ሊፈጥር አይችልም። መለወጥ ያለበት አተያያችን ነው። እሳትና ውሃን አለቦታው ለመጠቀም መፈለግ የፈጣሪ ስህተት ሳይሆን የኛ ጉድለት ነው።
ውሃን እሳት ውስጥ ብንጨምር ወይም እሳትን ውሃ ውስጥ ብናስገባ ለመጠፋፋታቸው ስህተቱ የማነው? የበረደው ሰው እሳትን በብብቱ ይይዝ ዘንድ አይጠበቅም።
ነገር ግን ውሃንና እሳትን መጥነን በመደጋገፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንችላለን። ይህ የአስተሳብ ብስለት ነው። ፖለቲካችንን ግን ለምንኖርባት ቤታችን እንደሚመጥን አድርገን አስማምተን መጠቀም አልቻልንም። አጥፊና ጠፊ መሆኑ እስካላከተመ ድረስ አዙሪቱ ደግሞ አይለቀንም። ስለዚህ መለወጥ ያለበት ወንበሩ ሳይሆን ወንበሩን የሚፈልጉ ጭንቅላቶች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚነግረን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከቀረቡ ክሶች መካከል አንዱ "ንጉሥ ነኝ ይላል" የሚል ነበር። ይኽ ንግግር ደግሞ በወቅቱ በሕዝቡ ላይ ተሹሞ ለነበረው ሰው ትልቅ ራስ ምታት ነው። ምክንያቱም ሥልጣን የሚቀናቀን ሰው ቶሎ መጥፋት አለበት። ከሳሾቹም ይኽንን ያውቃሉ። በአደባባይም የተጠየቀው "አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህን?" የሚለው መቅደሙ መልሱን ለማወቅ ነው። የሚቀናቀን ከሆነ ቶሎ የማጥፋት አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ መጠፋፋት አያቆምም። እርግጥ ነው፣ እንደሥርዓት ዛሬ አፄ የለም። በወንበር ላይ ግን መንግሥትም፣ ተቃዋሚም ሁሉም የአስተሳሰብ አፄ ነው። ትውልድ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለበት። እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም በወሰን፣ በክልል፣ በመጠንና በልክ ከተጠቀምንባቸው ሁለቱም የግድ አስፈላጊዎቻችን ናቸው።

Wednesday, June 22, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ወንጌልን ማቆም ያልቻለው ለምንድነው?


ከዙፋን (ተስተካክሎ የቀረበ)
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሰረተ 25 አመት ሞላው። ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክና ሌሎች የክርስትና ክፍሎች የወንጌል ስብከት በፊት ከነበራቸው ውስንነት በበለጠ ሲሰፉ እንጂ ሲጠፉ አልታየም።
 በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የሆኑና ቤተክርስቲያኒቱ ከወንጌል ጋር አንዳንዴም ከወንጌል በላይ ስፍራ የምትሰጣቸው ትውፊቶች፣ ድርሳናት፣ ገድላት ከዚያም ባለፈ ልዩ ልዩ አስማትና ተረቶች የእግዚአብሔርን የክብር ስፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን ያስተዋሉና ከውስጥ የተነሱ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ከነበሩበት ሁኔታ እየሰፉና እያደጉ መጥተዋል። ግንዛቤያቸውን በሁሉም ዘንድ በማዳረስ ረገድ ሰፊ ተቀባይነት በማግኘታቸው ከነበሩበት የተወሰነ ሁኔታ ወጥተው ዛሬ ከማኅበሩ የ25 ዓመታት ቁጥጥር ውጪ ናቸው። ማኅበሩ የተሐድሶ እንቅስቃሴን ለመጨፍለቅ ያልቆፈረው ጉድጓድ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ከንግድ ድርጅቶቹ የሚያገኘውን ግዙፍ ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ማቴሪያልም ጭምር ለዚህ ስራ ያውላል። በተሐድሶ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ዐውደ ርእይ፣ ስብሰባ፣ ወርክሾኘ፣ በንግሥ በዓላት፣ በዐውደ ምሕረት፣ በፅሑፍ፣ በምስል ወዘተ ልዩ ልዩ መንገዶች ህዝቡን ያስተምራል፣ ያስጠነቅቃል ቪዲዮ ይበትናል፣ ካሴት ይለቃል፣ በራሪ ወረቀቶችን ያሰራጫል። በዩኒቨርሲቲዎች፣ በኮሌጆች፣ በሕጻናት፣ በወጣቶች፣ በጎልማሶች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ባሉ ሰንበት ት/ ቤት ተማሪዎች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሰርቷል። ተጽእኖውና መልእክቱ ያልገባበት ቤት የለም። ተሐድሶ፣ ሃራጥቃ፣ መናፍቃን፣ የአውሬው ተከታዮች፣ ፀረ ማርያሞች፣ ጠላቶች፣ ነካሾች፣ ቡችሎች…ወዘተ ብዙ ስም አውጥቶ ለማስጠላት ሞክሯል። በስለላ፣ በክትትል፣ በጥርጠራና በድጋፍ አብሮት ያልቆመውን ሁሉ ስም እየለጠፈ በማባረርና በማስፈራራት ብዙ ቢጓዝም ትምህርተ ተሐድሶ ግን ሊቀንስ አልቻለም። ከዚህ ሁሉ ልፋት በኋላ በውጤቱም በ25 አመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማታወቅ መልኩ 15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከኦርቶዶክስ አካውንት ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ጎርፏል።
ብዙ ሚሊዮን ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናን፣ መምህራን፣ ሊቃውንት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ጳጳሳት ሳይቀሩ ባሉበት ቤታቸው ሆነው የተሐድሶ እንቅስቃሴን ደጋፊና አራማጅ ሆነዋል። የተሐድሶ እንቅስቃሴ መጀመር ወደሌላ የእምነት ድርጅት የሚኮበልለውን ምዕመን ቁጥር መቀነስ ችሏል። ችግሩ ያለው ከኦርቶዶክስ መሠረታዊ አስተምህሮ ሳይሆን በጊዜ ብዛት በገቡ የስህተት ትምህርቶችና የፈጣሪን ሥፍራ የተረከቡ የክህደቶች አምልኰዎች የተነሳ መሆኑን ተሐድሶዎች ማሳወቅ በመቻላቸውና ይህንን ለማስወገድ ደግሞ እዚያው ሆኖ በማስተማርና በመለወጥ እንጂ በመኮብለል አለመሆኑን ብዙ በመሥራታቸው የተነሳ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ የሱን የኑፋቄ ጽዋ ለመጨለጥ ያልፈለጉት እዚያው ከሚቆዩ ይልቅ ኮብልለው የትም ገደል ቢገቡለት ይመርጣል። በጀትና ኃይል መድቦ ተሐድሶዎችን ከመከታተል ይልቅ ከበረት አስወጥቶ፣ በረቱ ውስጥ የቆዩለትን በጎች የራሱ የግል ንብረት አድርጎ ለመቆጣጠር ያመቸዋል። ያስቸገረውና ብዙ ድካሙን መና ያስቀረው ነገር የተሐድሶ ኃይል በእውቀት፣ በጥበብና በተዋሕዶ ቀደምት እውነት ሁሉን ማዳረስ መቻሉ ነው።
የማኅበረ ቅዱሳን ትልቁ ችግር ራሱን የእውነትና የእምነት ጫፍ አድርጎ መመልከቱ አንዱ ጉዳይ ሲሆን ሌላው ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተምህሮ ጥግ ላይ ከማኅበረ ቅዱሳን ውጪ ያለው ለማስተማር መሞከር ማለት አፍን ማሞጥሞጥ እንደሆነ አድርጎ ማሰቡ ነው። እውነታው ግን በተሐድሶ ምሁራንና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለው የእውቀት ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ተሐድሶ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ይቀመጥ ሲል ማኅበሩ ደግሞ በአሮጌው አቁማዳ አዲሱን የወይን ጠጅ ማስቀመጥ ይቻላል በሚለው የእምነት አስተሳሰብ ልዩነት የተነሳ በተደራጀ አቅምና ሥልጣን በሚያደርገው ሩጫ ተሐድሶን ማስቆም አልቻለም። ተሐድሶ የግለሰቦች አሳብ ሳይሆን የእግዚአብሔር አሰራር መገለጫ በመሆኑ ማንም ድርጅት በትግል ሊያቆመው አይችልም።
“ወልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ ዘሐደሶ እግዚአብሔር በጽድቅ፣ ወበርትዕ፣ ወበንጽሕ” ኤፌ 4:24
“ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” የሚለን እግዚአብሔር በቃሉ አማካይነት ነው። በተረታ--ተረትና በእንቶ ፈንቶ ጩኸት በመባከን ፈንታ የወንጌልን እውነት መጨበጥ፣ ባዶ ተስፋ ከሚያስጨብጡ ዝናብ አልቦ ደመናዎች ዝናብ ከመጠበቅ ይልቅ ባለቤቱ ራሱ የሕይወት ውሃ ምንጭ እኔ ነኝ ካለው እውነት ቃሉ በመጠጣት መርካት መቻል ማለት መታደስ፣ መለወጥ፣ አዲስ ሰው መሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር ሁሉም ሰው እንዲታደስለት ይፈልጋል። የተሰራነው አንድ ጊዜ ተሞልቶ ፈፅሞ ከማይደክም የባትሪ ኃይል አይደለም።
“ወዘንተ ውስጥነሰ ይትሔደስ ኩሎ አሚረ”
“... የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” 2ኛ ቆሮ 4:16 እንዳለው መታደስ በመንፈሳዊነት ኃይል እግዚአብሔር እንደሚወደው ሆኖ መሰራት ማለት ነው።
በዚህም የተነሳ ማኅበረ ቅዱሳን የሚታገለው የእግዚአብሔርን ሃሳብ ለማስቆም ነው። ነገር ግን እስካሁንም አልቻለም፣ ወደፊትም አይችልም። ምክንያቱም ተሐድሶ፣

1. የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው።

 በመጨረሻው ዘመን የክርስቶስ ወንጌል በምድር ሁሉ ሊሰበክ ግድ ነው። ሉቃ 12:49 “በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ “ እንደሚለው ጌታ የጣለው እሳት ይነዳል እንጂ አይጠፋም። ሐዋ 5-38
  “ይህ አሳብ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ እንዳትገኙ” እንዳለው ከእግዚአብሔር ስለሆነ ሊጠፉ አልቻሉም፣ አይጠፉምም ።

2. የአብርሖት (enlightenment) ዘመን በመሆኑ፣

ይህ ዘመን ትምህርት የተስፋፋበት ብዙዎች ከመሃይምነት ነጻ የወጡበት መረጃ የበዛበት ነው። የሰዎች መንፈሳዊ ረሃብ በማይረዱት ግእዝ የማያውቁትን ነገር ተቀብለው ወደቤት ከመሄድ ባለፈ መጽሐፍ ቅዱስና መንፈሳዊ ፅሑፎችን በማንበብ ማብራሪያና መልስ የሚፈልግበት ዘመን ነው። ትውልዱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልምምድን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይፈትሻል። ለእምነቱ በቂ ማብራሪያ ይሻል። ያነጻጽራል። መጽሐፍ ቅዱስን በሞባይሉ አስጭኖ የትም ቦታ ያነባል። እንደ መጨረሻ ባለሥልጣን ቃልም ያየዋል። ከዚህ ቃል ጋር የሚጋጭ ወይም ለማስታረቅ የሚሞክርን ማንኛውንም ውሸት ለመቀበል አይፈልግም። ይህንን ዘመነ አብርሖት ከእውነት ጋር በመስማማት እንጂ በመሸፋፈን ወይም ትቀሰፋለህ፣ በሰይፍ ትቆረጣለህ በሚል ማስፈራራት ማስቆም አይቻልም።

3. ዛሬም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳንና ፈውስ ስላለ፣

 እግዚአብሔር በአንድ ቃልና በጸሎት በአንዴ መፈወስ ያቃተው ይመስል ለሥጋዊ ፈውስ ሸንኮራ፣ ጻድቃኔ፣ግሼን፣ሚጣቅ፣ ሺፈጅ፣ ኩክየለሽ፣ ግንድአንሳ፣ ከድንጋይ አጣብቅ፣ መሿለኪያ፣ መንከባለያ፣ ገልብጥ፣ ሰንጥቅ ወዘተ አዳዲስ የፈውስ መደብር እየፈጠሩ የአንዱ ወረት ሲያልቅ ሌላ እየፈለሰፉ ገንዘብ ጉልበት ጊዜ ጨርሶ መፍትሄ በማሳጣት ተራራ ለተራራ መንከራተት ስለሰለቸው ሰው ከዚህ እንግልት ማረፍ ፈልጓል። ከ 5 ትውልድ ወደ10 ትውልድ፣ ወደ 30 የማይጨበጥ ቃል ኪዳን ለመጨበጥ ሲያበላልጥ በክርስቶስ ላይ ብቻ አንዴ ታምኖ በመኖር ዕረፍትን ፈልጓል።

4. ትውልዱ ከሱስ መፈታትን ስለሚፈልግ

የጫት፣ የሲጋራ፣ የሺሻ፣ የሃሺሽና የመጠጥ ሱስ በየመንደሩ ብዙ ወጣቶችን ተብትቧል። ሴተኛ አዳሪነት፣ ስርቆትና ዝሙት አንገቱ ላይ ያሰረው ክር ወይም መስቀል ነፃ ሊያወጡት አልቻሉም። የጠለንጅ ወይም የጊዜዋ ቅጠል ማጫጫስ መፍትሄ አልሆኑትም።
 44 ታቦት ባነገሠ ማግሥት ከነበረበት ሕይወት ሊፈታ ባለመቻሉ ከተስፋ መቁረጥ የሚያድነውን ይፈልጋል። ይኼውም ያልተቀላቀለበት የእውነት ወንጌል መስማት መቻሉ ነው።
2 ቆሮንቶስ 4፣2
“ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም፣ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን”

5. ለሥራ ስለሚያነሳሳ፣

 እምነቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያስተካከለ ሁሉ ለበጎ ሥራ የተነሳሳ ሰው ነው። ከወንጌል ሥራን እንጂ ስንፍናን አይማርም። ዐባይን ብቻዋን እንድትጠቀም ግብጽ በሕዝባችን ላይ የጫነችው የስንክሳር የበዐላት ሸክሟን ከራሱ ላይ አራግፎ በመሥራት ራሱንና ወገኖቹን የሚጠቅም ትውልድ እንጂ ስለአባ እገሌ እያለ የሚለምን ዜጋ ሊኖር አይችልም። ትንሽ ሠርቶ ያገኛትን ደግሞ በፍትሃት ድግስ እያራገፈ፣ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ዛሬ መልአከ እገሌ፣ ነገ አባ እገሌ፣ በዓታ፣ ጸአታ፣ ፍልሰታ፣ ልደታ፣ ግንቦታ፣ እያለ አበሻ ሥራ ቢሰራ የተለየ ቀሳፊ የተመደበበት ይመስል ዐዛሬ ቅጠል አልበጥስም” እያለ ይኖርበት ከነበረው ዘመን ተፈትቶ በዘመነ ተሐድሶ ነፃ እየወጣ የዕለት እንጀራውን ለማግኘት ሌሊትና ቀን እየሰራ ነው። በዐል ሳያከብር ፈረንጅ ያመረተውን ስንዴና ዘይት በእርዳታ የሚለምን በዐል አክባሪ እንደአበሻ ግብዝ የት ይገኛል?

ስለዚህ የዘመነ ተሐድሶ የክርስቶስን ወንጌል የሚቋቋም ማንም አይኖርም። የክርስቶስን ወንጌል የሚያቆም ከሰማይ በታች ምንም ዓይነት ኃይል ወይም ማኅበር የለም። ይሁን እንጂ ወርክሾፕ፣ ስልጠና ፣ አቅም ግንባታ፣ ሕንጻ ግንባታ፣ ኤግዚብሽን ግንባታ፣ ዐውደ ርእይ ወዘተ መደረጉ አይቀርም፣ ይኽ መደረጉ የእግዚአብሔርን የተሐድሶ ሐሳብ አያቆመውም። ማኅበረ ቅዱሳን የብር ኢዮቤልዩውን እንዲህ ካሳለፈ ዕድሜው ከሰጠው የወርቁን ደግሞ አመራሩ ራሱ ከኑፋቄ ወጥቶ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ በማምለክ ያከብረው ዘንድ የእግዚአብሔር የተሐድሶ እቅድ መሆኑን አንጠራጠርም።