( 4/4/ 2007 )
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቅት ወርን መባቻ ተከትሎ የአጠቃላይ ሰበካ ጉባዔ ዓመታዊ ስብሰባና የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህ ዓመት የተለየ የሚያደርገው ከሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የስብሰባ አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተደረገ የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ልዩ ልዩ ኃላፊዎች በተጠራ ጉባዔ ላይ የተካሄደው ውይይት ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ አልፏል። በወቅቱ ከተደረገው ውይይትና ከተሰብሳቢዎቹ ድምጽ ለማወቅ እንደተቻለው በአጭር ቃል «ማኅበረ ቅዱሳን» ስለተባለው ማኅበር እንቅስቃሴ ላይ ያጠነጠነ ውይይት መሆኑ የተለየ አድርጎታል።
ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ድርጅት እንቅስቃሴ፤ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያለው የሥራ ድርሻ፤ የአባላት ምልመላ፤ የገንዘብ አሰባሰብና ውጪን ስለማሳወቅ፤ ሊኖረው ሲለሚገባው ገደብና ሌሎች አሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው እንደነበር ይታወሳል። በማኅበሩ ዙሪያ በተነሱት የማኅበረ ካህናቱና የፓትርያርኩ ውይይት ደስተኛ አለመሆን ከማኅበሩ ዘንድ የሚጠበቅ ቢሆንም በአስገራሚነቱ የተመዘገበው ተቃውሞ የተነሳው ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራሉ ተብለው በከፍተኛ ስልጣን ላይ በተቀመጡት በዋና ሥራ አስኪያጁና ከዋና ፀሐፊው በኩል መሆኑ ነው። የማኅበሩ አባል የመሆን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማኅበሩን በተመለከተ ፓትርያርኩ ማኅበረ ካህናቱን የማወያየት አቅምና ሥልጣን የሌላቸው በማስመሰል መቃወም ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ማኅበሩ ምን እየሰራ ነው? እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? ቤተ ክርስቲያን የምትቆጣጠረው እንዴት ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች የማኅበረ ካህናቱን ድምጽ የመስማትና የማወያየት አቅም ፓትርያርኩ የላቸውም ከተባለ ዋና ሥራ አስኪያጁ ስለማኅበሩ የመጮህ ሥልጣንን ከየት አገኙ? የሚል አንጻራዊ ጥያቄን ማስነሳቱ የግድ ነው ።
ሌላው ስለማኅበሩ የጦፈ ክርክር ተደርጎ የነበረው ከአዲስ አበባው ሀ/ስብከት ጉባዔ በኋላ በተፈጸመው የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ላይ በድጋሜ መነሳቱ ነበር። በዚህ ጉባዔ ላይ ስለማኅበረ ቅዱሳን ያልተነገረና የቀረ አንዳች ነገር አልነበረም። የተናገሩትን ሰዎች ማንነት ለጊዜው ወደጎን ትተን በተነገረው ጉዳይ ላይ ስናተኩር ከተነገረው እውነት የቀረ ነገር ካልሆነ በስተቀር የተጨመረ አዲስ ነገር ምንም አልነበረም ማለት ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ጣልቃ ይገባል? ያልተፈቀደ ጉባዔ ይጠራል? የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባልነት ይመለምላል? ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቀውን ገቢ ይሰበስባል? የቤተ ክርስቲያኒቱን የኦዲት ምርመራ አልቀበልም ይላል? ለሁሉም አንድ መልስ «አዎን» ነው። በነዚህ አንኳር ነጥቦች ላይ የካህናቱና የፓትርያርኩ መነጋገር የሚያንገበግበው ቢኖር ማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለማኅበሩ ጥብቅና የሚቆሙ ወገኖች ብቻ ናቸው። ካልሆነ ስለማኅበረ ቅዱሳን ተግባር መነጋገር ለምን ያናድዳቸዋል?
ማኅበሩ የተሳሳተውን መንገድ አውቆ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብና የማኅበሩ ቅን አባላት ለተሻለ መንፈሳዊ ተግባር ትኩረት እንዲሰጡ የሚያስችል ውይይት ማድረግ ተገቢና ተቀባይነት ያለው መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለንም። ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። በጠራ ቃል «ማኅበሩን ይፈረስ ያለ ማንም የለም» ብለዋል። ከዚህ ውጪ እነዚህ ቡድኖች ምን እንዲሆን ይፈልጋሉ? በዚህ ዙሪያ የሚታመም ሊቀ ጳጳስ ወይም ተመሳሳይ ሰው ቢኖር ራሱን መመርመር ያለበት ራሱን ነው። ህመሙ የጤንነት ምልክት አይደለም። ዘረኝነት፤ ጥቅምና ጭፍን ደጋፊነት ብቻውን ማንነትን ከሚያጋልጥ በስተቀር የትም አያደርስም። ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አባ ማቴዎስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ የተናገሩት « ማኅበረ ቅዱሳንን ከነኩ እርስዎም እንደአባ ጳውሎስ ይሞታሉ» ማለታቸውን ሰምተን ጤንነታቸውን ተጠራጥረን ነበር። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር እንዴት አብረው ሊሰሩ እንደሚችሉ ስናስብ እጅግ ያስገርመናል። ዓይን ያወጣ ጥላቻና አንድን ቡድን መደገፍ አሳዛኝም አስገራሚም ነው። በዚህ ዓይነት ጉዞ ቤተ ክርስቲያን ወዴት እየሄደች እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለራስ ክብርና ለማኅበር መቆም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ውድቀት እየገፏት መሆኑን ለማወቅ ምርምር አይጠይቅም። ባለፉት 23 ዓመታትም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መካከል ከ16 ሚሊየን በላይ ልጆቿ ወጥተው የቀሩትም በዚህ ዓይነት ቡድናዊ አስተዳደርና ደካማ አስተምህሮ የተነሳ ነው።
የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ እንደተፈጸመ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ቀጥሎ ነበር። በዚህ የሲኖዶስ ጉባዔ ላይም በግንባር ቀደምትነት የተነሳው ጉዳይ ቢኖር ማኅበሩ ለምን ተነክቶ? የሚሉ የጳጳሳት ቡድን በአንድ በኩል፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ብቻቸውን በሌላ በኩል ሆነው የጦፈና የከረረ ውይይት ማድረጋቸውን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ሰምተን ነበር። ማኅበሩን የሚያወግዙና የሚወቅሱ የማኅበረ ካህናት አባላት እኛንም ከማኅበሩ ጋር ቀላቅለው ስለዘለፉን ቀኖና እንዲሰጣቸውና እንዲቀጡ ይደረግ የሚሉ አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ጳጳሳት የጉባዔውን አቅጣጫ ለማሳት ሙከራ አድርገው ነበር። ፓትርያርኩ ምንም እንኳን ለጉዳዩ መልስ በመስጠት ዝም ለማሰኘት ሞክረው የነበረ ቢሆንም «ወደ ገዳማችን እንሄድልዎታለን፤ ሲኖዶሱን ሊያከብሩ ይገባል፣ እርስዎ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው፤ ሲሉ የነበር ዛሬ እርስዎ ለምን ይሽሩታል?» ወዘተ መከራከሪያ ነጥብ ለማንሳት ተሞክሮም ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው የሲኖዶስ ውሳኔ ስለተሻረ ሳይሆን በሲኖዶሱ ሉዓላዊ ስልጣን ከለላ በማኅበረ ካህናቱ ዘለፋና ውግዘት የደረሰበትን ማኅበር ለመካስ ሲባል በማኅበሩ ላይ የተናገሩት ካህናት ሁሉ እንዲቀጡና ቀኖና እንዲሰጣቸው ለማስቻል ነበር።
ማኅበሩን አጋልጠው ለአጋላጭ ሰጥተዋል የተባሉት በዋናነት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፤ ሊቀትጉኃን ዘካርያስ ሐዲስ፤ መልዓከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ፤ ዲያቆን አበበ፤ ዲያቆን ዘመንፈስ አብርሃ፤ አባ ነዓኩቶ ለአብ የመሳሰሉት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና ቀኖና እንዲሰጣቸው እንዲሁም ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በተለይ ከፓትርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት እንዲባረሩ ይደረግ የሚል ውሳኔ ለማሳለፍ ተሞክሮ ነበር። በተካፈሉበት ጉባዔ ላይ ሁሉም አሳብ ሰጪዎች የተናገሩት በማኅበሩ ዙሪያ ብቻ ሆኖ ሳለ ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ በእነዚህ ካህናት ላይ የበቀል እርምጃ እንዲተላለፍ የተፈለገው ለምንድነው? ዋና የስም ማጥፊያ ማጠንጠንጠኛው ሙሰኞችና አማሳኞች ናቸው የሚል ቢሆንም ማን ምን ሰረቀ? ስንት ሰረቀ? መቼ ሰረቀ? የት ሰረቀ? ለሚለው የጥያቄ ጭብጥ መልስ የሚሰጥ አካል የለም። በወሬ ደረጃ የምናየውንና የምንሰማውን ይዞ ካልሆነ በስተቀር ማስረጃውን በነጥብ የሚያስረዳ አካል የለም። የተጠቀሱት ግለሰቦች በሥራቸው ያልተመሰረከላቸው መሆኑ ወይም የሙስና ተሳታፊ ስለመሆናቸው መጠርጠራቸው ብቻውን ስለማኅበረ ቅዱሳን መናገራቸውን ስህተት ሊያደርገው አይችልም። ታዲያ ቅዱስ ሲኖዶስ በነዚህ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወሰድ! የሚለው በምን መነሻ ነው? ሲኖዶስ ሊያደርግ የተገባው ሀቅ ቢኖር ማኅበሩንም ይሁን በማኅበሩ ዙሪያ ተቃውሞ ያነሱ ሰዎች ያጠፉት ነገር ካለ መርምሮ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም የእርምት እርምጃ መውሰድ ነበር። ነገር ግን አንዱን አጥፊ ደግፎ ሌላው አጥፊ ላይ ጣትን መቀሰር ቅንም፤ መንፈሳዊም አካሄድ አይደለም።
ይህንን ዘገባ እስካወጣንበት ጊዜ ድረስ ከላይ በጠቅስናቸውና በሌሎች ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማኅበሩ ከኋላ እየገፋ ብዙ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል። በአባ ማቴዎስና በአባ ሉቃስ አሳሳቢነት ቋሚ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ጉዳዩን እያነሱ የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደአንዱ ተቆጥሮ በተጠቀሱት ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ላለፈው አንድ ወር ሙሉ ጽኑ ክርክር ሲያደርጉ መቆየታቸው ተሰምቷል። ከተወሰኑ ጉባዔዎች በስተቀር ያልተነሳበት ስብሰባ አልነበረም። በተለይም አባ ሉቃስ «ሊቃነ ጳጳሳት ተዘልፈዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ክብር ሲነካ ዝም ማለት አይቻልም፤ ማኅበሩም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ እየሰራ ነው» በሚል መከራከሪያ በተቃዋሚ ካህናት ላይ እርምጃ ለማስወሰድ ብዙ ተጉዘው ነበር። ነገር ግን በፓትርያርኩ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ ተደርጓል።
የፓትርያርኩ አቋም ማኅበረ ካህናቱን ሰብስቦ ለማናገር የማንንም ፈቃድ አልጠይቅም። ቅዱስ ፓትርያርክ የሚመራቸውን ካህናት የማናገር መብቱን የሚያገኘው ሥልጣኑን ከተቀበለት ሰዓት ጀምሮ ነው። ካህናቱንም የተሰማቸውንና የታያቸውን ጉዳይ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማቅረባቸው ትክክልና ተገቢ ነው። አያስወቅሳቸውም። ከዚያ በተረፈ የሊቃነ ጳጳሳቱን ስም አንስቶ ጸያፍ ቃል የተናገረ ካለ በቦታና በስም ተለይቶ ይነገረንና ምክርና ተግሳጽ እንሰጠዋለን እንጂ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ የመሰለውን ሃሳብ ያንጸባረቀ ሁሉ ጥፋተኛ አይባልም» በማለት የማኅበሩን ደጋፊ ጳጳሳት ኩም አድርገዋቸዋል። በተለይም ባለፈው አንድ ሳምንት በማኅበሩ በኩል ከኋላ ይገፉ የነበሩትና አሳባቸው ውድቅ የሆነባቸው አባ ማቴዎስንና አባ ሉቃስን ያየ መጨረሻቸውን ለማየት ናፍቆ ነበር።
ሁልጊዜም የሚሸሸጉበት ስነ ሞገት «የሲኖዶሱ ውሳኔ ይከበር» የሚል ሲሆን ሲኖዶስ የማንን የመናገር መብት እንደከለከለ የሚገልጽ ማስረጃ ግን ማቅረብ አልቻሉም። ወደፊትም አይችሉም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳው ማኅበሩን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ካህናት መብታቸው በመሆኑ የትኛውም አካል ይህንን መብታችሁን ለምን ገለጻችሁ?ብሎ እርምጃ የሚወስድ አካል ቢኖር የሕግ ጥበቃ እንዲደደረግላቸው ለመንግሥት አካላት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ቃል የተገባላቸው መሆኑ ታውቋል።