Tuesday, May 21, 2013

«እግዚአብሔርን ወደማወቅ መድረስ


የሥነ አእምሮ፤ የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ምሁር የሆኑት ሪቻርድ ፕራት ሃይማኖትን ሰዎች የሚጠቀሙት ከሚመጣባቸው ቁጣና ቅጣት በማምለጥ ሰላምና ዘላለማዊ ዋስትና አገኝበታለሁ ብለው ለመጠለያነት ነው ይላሉ። ከዚያ ተቋም ውጪ ዋስትና አለ ብለው አያስቡም። ሰላምና ዋስትና መፈለግ በራሱ ጥሩ ቢሆንም ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በራሳቸው መንገድ የተገለጸውን ሰላምና ዋስትና መስጠት ወይም ማሰጠት አለመቻላቸው እውነት ነው። እንደሃይማኖቶቹ ልዩነት የተለያየ የደኅንነት መንገድ የለም። ምክንያቱም ዋስትናና ሰላም በተቋም ደረጃ ለተከታዮች የሚከፋፈል ስጦታ ሳይሆን  መስጠት ከሚችልና ዋስትና ካለው የሰላም ባለቤት ከራሱ ከእግዚአብሔር ለጠየቁትና ለለመኑት በቀጥታ የሚሰጥ እንጂ እግዚአብሔር ለሃይማኖት ተቋማት በተለይ አድሎ፤ እነርሱ ደግሞ በተናጠል ወደእነሱ ለመጣ እንዲያድሉ የተደረገበት መንገድ በፍጹም የለም። እግዚአብሔርን አባት ብለው ለሚጠሩት አማኞች ሁሉ አባት  የሚሆነው ልጅ የመባልን ጸጋ በነጻ ማግኘታቸውን አምነው ለተቀበሉ ብቻ ነው ይላሉ ዶ/ር ፕራት።
« በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና» ገላ 3፤26
በማመን የሚገኘውን ጸጋና ልጅነትን በሃይማኖት ተቋም በኩል መቀበል አይቻልም። ዛሬ በዚህ ዓለም ላይ የሃይማኖት ተቋማት መብዛት ዋናው ምክንያት ከሌላው የተሻለ ሰላምና ዋስትናን ለተከተለን ሁሉ እናድላለን ብለው ስለሚሰብኩ ብቻ ነው። በየድርጅቶቹ ውስጥ ያሉ ተከታዮችም በዚያ ተቋም በኩል ሰላምና ዋስትና ያገኙ ስለሚመስላቸው እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ፤ እኔ ካቶሊክ ነኝ፤ እኔ ይሁዲ፤ እኔ እስላም፤ እኔ ፕሮቴስታንት ነኝ፤  ጴንጤ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ሙሉ፤ ጎዶሎ፤ ቤዛ፤ መሠረት፤ሞርሞን፤ ወዘተ ነኝ እያሉ መታመኛና ዋስትና ያለበት የራሳቸውን ተቋም ትክክለኛነት ይናገራሉ። ሁሉም ራሱን ከሌላው የተሻለ የዋስትናና የሰላም ምንጭ የሆነውን ፈጣሪ ለመስጠት ብቃቱና ውክልናው አለኝ ብሎ ለራሱ ይመሰክራል።  እንዲያውም አንዱ ሃይማኖት የሌላውን ጉድለት በራሱ መንገድ እየዘረዘረ ራሱን ከማንም የተሻለ የእግዚአብሔርን ጎዳና መሪ አድርጎ በመደስኮር ወደእሱ ለመምጣት እንዲሽቀዳደሙ ሲሰብክ ይታያል። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚመዝነው ባሉበት የእምነት ተቋም ያለውን ህግና ደንብ ማክበራቸውን በማየት ሳይሆን እግዚአብሔርን አውቀው ከእርሱ ጋር ያደረጉትን እምነትና ኅብረት በመመዘን ብቻ መሆኑ እውነት ነው። አማኞች ያሉበት ሃይማኖት የሰራላቸውን አጥር አልፈው እግዚአብሔርን ለማወቅና ለማግኘት፤ ከእኔነት አዙሪት ወጥተው ለአንዱ እግዚአብሔር መገዛት ቢችሉ ኖሮ የሃይማኖት ተቋማት ባልኖሩም ነበር።  የመጀመሪያይቱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። ዛሬም ከድርጅትነት የተለየች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። የየሃይማኖቶች ጥምቀት፤ ጌታና አባት የለም። ሃይማኖቶች ግን የየራሳቸውን ጌታ፤ አባትና ጥምቀት ሲሰጡ ይታያሉ። ይህም የመጽሐፉ ተቃራኒ ነው።
«አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ»  ኤፌ 4፤5-6
 ይሁን እንጂ ያለው እውነት አንድ ብቻ በመሆኑ እኔ፤ እኔ ያለው ሁሉ እውነተኛ ሊሆን አይችልም። በዚህም ይሁን በዚያ የማይናወጥና የማያጠራጥር እውነት፤ ሰላምና ዋስትና ያለው ከምንጩ ባለቤት ከኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ክርስቶስም  ሰላምና ዋስትናን በውክልና እንዲሰጥ ያቋቋመው አንድም ተቋም እና ድርጅት በዚህ ምድር ካለመኖሩም በላይ ክርስቶስ በአማኞች ልቦና ላይ ሰላምና ዋስትናን ሊመሰርት መጣ እንጂ ድርጅት ሊያቋቁም አይደለም። ክርስቶስ ያቋቋመው እኔን ነው ማለት የሚቻለው  ባለሰርቲፊኬት ተቋም ባለመኖሩ ሁሉም እኔ ከሌላው የተሻልኩ ለክርስቶስ ቅርብ ነኝ እያለ ራሱን አጽዳቂ ከመሆን ውጪ ሰላምና ዋስትናን በዚህ ምድር ማምጣት አይችልም።
ሳይካትሪስትና የነገረ መለኮት ምሁር የሆኑት ዶ/ር ሪዩበን ዴቪድ  ደግሞ እንዲህ ይላሉ። ሁሉም ሃይማኖቶች እግዚአብሔርን የሚገልጹበት የየራሳቸው ዶግማና አስተምህሮ፤ የእግዚአብሔር ወዳጅ ለመሆን የሚያስችልም የየራሳቸው ሕግና ደንብ አላቸው። ያንን ዶግማና አስተምህሮ፤ ሕግና ደንብ በመጠበቅ ብቻ ትክክለኛው እግዚአብሔር ይገኛል ስለሚሉ  እያንዳንዱ የሚያምነውና ከእርሱ ዘንድ ብቻ በትክክል እንዳለ የሚገልጽበት የራሱ እግዚአብሔር አለው  ሲሉ  ያብራራሉ።  ዶ/ር ሪዩበን ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ ትክክለኛው እውነት ግን እግዚአብሔር ራሱን የገለጸበትና የሚለካበት መንገድ እያንዳንዱ ሃይማኖት በጻፈው ዶግማ፤ አስተምህሮ፤ ሕግና ቀኖና መሠረት አለመሆኑ ነው።  የእስላሞች ፈጣሪ «አላህ» ይባላል። እስላሞች ራሳቸው የተረጎሙትን ያንን «አላህ» ሰው ማመን ካልቻለ አይድንም ይላሉ። አላህ የሚገኘውም ቁርአን በተባለ መጽሐፋቸው ውስጥ ነው። ከዚያ ውጪ አላህ የለም።ካቶሊኮች የራሳቸው የሆነና ካቶሊካዊ ትርጉም  የተሰጠው እግዚአብሔርን የማወቅ ዐለምዓለቀፋዊነት አስተምህሮ፤ ዶግማና ቀኖና አላቸው። ሰዎች ትክክለኛውን እግዚአብሔርን ለማግኘት እነዚያ መጽሐፍቶች ውስጥ ገብተው በተተረጎመው ተቋማዊ እምነት ውስጥ መነከር አለባቸው። ካቶሊክ መሆን ካልቻሉ እግዚአብሔርን አያገኙትም፤ ወይም በተሳሳተ ጎዳና ላይ ናቸው ይላሉ።  ገሚሱም የቀደመችው መንገድ በዚህ አለች ይላሉ። አንዳንዶቹም ኢየሱስን ከእኛ ዘንድ ተቀበሉ፣ እንደግል አዳኝ ካልወሰድክ አትድንም ይላሉ። እርግጥ ነው፤ እምነት የግል ነው። የክርስቶስ የማዳን አገልግሎት የተሰጠው ግን ለግል አይደለም። ላመኑ ሁሉ እንዲያው የተሰጠ ጸጋ ነው። አንድ ሰው በግሉ ክርስቶስን ማመኑ ክርስቶስን የግል አዳኝ አያደርገውም። ማንም ለመዳን በዚህ የግል አዳኝነቱ መስመር ውስጥ የግድ ማለፍ የሚሉ እንደብቸኛ ወኪልነት ራሳቸውን  የሚቆጥሩ ናቸው።  ዶ/ር ሪዩበን፤ በእርግጥ ማንም ሰው ስለክርስትና መሠረታዊ የመዳን ትምህርትና ሕይወት የሚገኝበትን የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እውቀት ያስፈልጉታል። «ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል» 2ኛ ጢሞ 3፤5   «እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው» ሮሜ 10፤17
ቅዱሱን መጽሐፍ መማርና ማንበብ ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ለማግኘት እንጂ የድርጅት አባል በመሆን ለእግዚአብሔር ያሉበትን ተቋም እንደትክክለኛ ሥፍራ የማቅረብ ዓላማ አይደለም። ሐዋርያትም ወንጌልን እየተዘዋወሩ ሕዝቡን እያስተማሩና እያጠመቁ ወደ ሕይወት መንገድ መመለስ ቻሉ እንጂ  ድርጅትና የእምነት ተቋም በመመስረት ስለማገልገል አንድም ቦታ ወንጌል ላይ አልነገሩንም በማለት ያብራራሉ ዶ/ር ሪዩበን።  ሰው በመጠየቅ፤ በማንበብ፤ በመማር፤በመጸለይና በእግዚአብሔር ፈቃድ እውነቱን ወደማወቅ  ሊያደርስ ይችላል። በአንድ ድርጅት ውስጥ ተወትፎ መኖር ግን እውነት ምን እንደሆነ ከማወቅ ይከለከላል። ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የአይሁድ እምነት ተከታይ እንደነበረ የኦሪቱን ሕግ ሊፈጽም ኢየሩሳሌም የመገኘቱ ታሪክ ይነግረናል። ወደሀገሩ ሲመለስ ያልገባውን በመጠየቅ በሐዋርያው ፊልጶስ የኢሳይያስ መጽሐፍ ትርጉም ሲነገረው  እውነቱን ወደማወቅ ደረሰ፤ አመነ ተጠመቀም። ከአይሁዳዊ የእምነት ተቋም ወደክርስትና የመዳን ሕይወት ወዲያው ተሸጋገረ። በሕይወቱ ላይ የመጣው አዲስ ለውጥ ከአይሁድ ሕግና መመሪያ ድርጅታዊ ትእዛዝ ነጻ በመሆን ክርስቲያን የመባል የሐዋርያት እምነትጋር ኅብረት አደረገ እንጂ ከድርጅት ወደድርጅት አልተዘዋወረም። ያለኝ ኦሪታዊ ሕግና ደንብ ይበቃኛል፤ መዳን በዚያ ነው ያለው ብሎ በተቋማዊ ሕግጋቱ ላይ በድርቅናው ጸንቶ ቢሆን ኖሮ እውነቱን ወደማወቅ ባልደረሰም ነበር።  ክርስትና ማለት በክርስቶስ የተገለጠውን እውነት ማወቅና በዚያ ሕይወት ውስጥ መኖር በመሆኑ ጃንደረባው ከዚህ አዲስ እምነት ጋር ለማወቅ ባለው ትጋት ልክ ሊገባ በቃ።  የሃይማኖት ተቋማት አባል ሆኖ መቅረት ማለት በተቋሙ ጣሪያ ስር ተደፍኖ መቅረት ማለት ነው። በጣሪው ከተዘጋ ልቡና ወጣ ብሎ እውነቱን ለማወቅ ሰው ቢፈልግ ኖሮ እንደጃንደረባው ወደእውነቱ መድረስ በቻለ ነበር። ዛሬ በዓለማችን ላይ ያሉ ሃይማኖቶች ሁሉ በተለይም በክርስትናው ስም የሚንቀሳቀሱት በየራሳቸው ጣሪያ ስር ሚሊዮኖችን ነፍሳት ደፍነው በመያዝ ከዚያ እንዳይወጡ በሕግ፤ በመመሪያ፤ በደንብና በትዕዛዝ አጥር  እውነቱን ወደማወቅ እንዳይደርሱ ከልክለው ይገኛሉ።  እስልምና የተባለው እምነት ተከታዮቹን በሃይማኖት መጽሐፉ ላይ ከየትኛውም  ሌላ እምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉና በእምነት ከማይመስሏቸው ሰዎችም ጓደኝነትን እንኳን እንዳይዙ በጥብቅ ያስጠነቅቃል።  (ሱረቱ አል ኢምራን 3፤28) ከዚህ ጥብቅ መመሪያ የተነሳ ከዚህ እስር ለመውጣት አይችሉም። ከዚህም የተነሳ እውነት ምን እንደሆነ ወደማወቅ ለመድረስ ሊደርሱ አይችሉም። ኢየሱስ ክርስቶስ  በትንሣኤ ዘለሙታን ዳግም ሲመጣ በእሱ ላይ የነበረንን እምነትና ምግባር ይመዝናል እንጂ በነበርንበት የሃይማኖት ተቋም ልክና ማንነት አይፈርድልንም ወይም አይፈርድብንም።  እኔ ቀጥተኛይቱ ስላልን ቀጥተኛ አንሆንም። ቀጥተኛው የት እንዳለ በቃሉ ስንመረምር ብቻ እውነቱን ማወቅ ይቻለናል። አስተዋይ ልብም  በእውቀት፤ ጠቢብም በመሆን ሰሚ ጆሮ ካለን መንገዳችንን ያሰፋዋል፤ በታላቅም ሥፍራ ያደርሰናል። 
«የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች፣ የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች» ምሳሌ 18፤15-16
መንፈሳዊ ሰው መሆን ማለትም ያሉበትን ድርጅት ዓላማ መቀበልና መፈጸም ሳይሆን እግዚአብሔርን ማወቅ፤ እንደትእዛዙና ፈቃዱ መኖር ማለት ነው። ስለዚህ ከድርጅት በላይ እግዚአብሔርን ወደማወቅ አዲስ ሕይወት ልንሻገር ይገባል ።
1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥3-4
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።

Friday, May 17, 2013

ሰምና ወርቅ ! geezonline.com

 (The best ever Gold & Wax of the year ) dejebirhan
ጥጃዋ የሞተባትን ጥገት፤ አላቢዎች የቋንቋ ዕድርተኞች የጥጃውን ቆዳ ከጅራቱ እስከ አፉ ፈልቅቀው ሥጋውን አውጥተው በምትኩ 800 ቅርጫት ጭድ 500 ያኽሉን በጥጃው ቆዳ ጎስረው ጠቅጥቀው፤ የጥጃ ጎፍላ ወይም እንቡጣ (እንቦሣ) አስመስለው ሠርተው፤ ጸጕር ይብዛው እንጂ መንፈሰ ሕይወት በተለየው ቆዳ ገላው ላይ ጥቁር ጨው ነስንሰው፤ ለሷ ያንን እያላሱ፤ ለራሳቸው ወተቷን እያለቡ "ቴሌቫንጀሊዝም" እሚባል ቅላቸው ውስጥ ሲያንቆረቁሩባት፤ ላሚት እንዲህ አለች አሉ፦

ያለ እየመሰለኝ! ልጄ ሙቶ ሳለ
እንቦሣውን ባየው ልቤ ተታለለ!!

አላቢዎቹም ታዲያ እንዲህ ሲሉ መለሱላት ይባላል፦

ስንኳን አንቺ! ቤተ እስራኤል
ትታለል ነበረች በጥጃ ምስል!!

ሰሙ ጥጃዋ የሞተባትን ጊደር ኑሮ ለሚያውቅ ኹሉ ግልጥ ነው፤ ወርቁም ቢኾን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የምትገኝበትን ኹኔታ ለሚያውቅ የተሰወረ አይደለም። እንዲያውም ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በዓይነ ኅሊና ብቻ ሳይኾን እነሆ በዓይነ ሥጋም ጭምር ወለል ብሎ ይታያል።
http://www.eotc.tv/?q=node/65 ( ሊንኩን ከግዕዝ ኦን ላይን ይመልከቱ )
አዬ ቤተ ተዋሕዶ፤ አንቺም እንዲህ በትንሣኤው ምድር ልብሽ ሙቶ አእምሮሽ ደንዝዞ የለየልሽ ሞኝ ተላላ ላም ኾነሽ ታርፊው!!! "ከመ ዘንቃሕ እምንዋም" ትንሣኤውን ያሳየን አምላክ ያንችንስ ትንሣኤ የሚያሳየን መቼ ይኾን?!

Thursday, May 16, 2013

የማኅበረ ቅዱሳን ተላላኪና ሙሰኛው አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ከሥራ አስኪያጅነታቸው ታገዱ።

አባ ኅሩይ ወንድይፍራው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነቱን ከአባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል እጅ ተረክበው ማኅበረ ቅዱሳን በሚሰጣቸው መመሪያና ምክር መሠረት ለቤተ ክህነቱ ሸክም፤ ለማኅበሩ ግን ታማኝ አገልጋይ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል። በሥራው ላይ እያሉም በአንድ ወቅት አምነው የፈረሙበትን ደብዳቤ በጨለማ ተታልዬ ነው፤ አሳስተውኝ ነው፤ መዝገብ ቤቷ አሞኝታኝ ነው…………. ወዘተ፤ በሚል ማጭበርበሪያ ምክንያት የፈረሙትን ደብዳቤ መልሰው በመካድ የሰውዬው አቋመ ቢስና እምነት የማይጣልባቸው፤ እንደተልባ ስፍር የሚንሸራተቱ መሆናቸውን አይተን ከዚህ በፊት መዘገባችንም አይዘነጋም። ሰውዬው ማኅበረ ቅዱሳንን የሚያገለግሉት ስለሚወዱት ሳይሆን ስለሚፈሩት እንደሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ሲናገሩ ተሰምተዋል። ለምን እንደሚፈሩት የሚያውቁት እሳቸውና የኃጢአት መዝገብ ጸሐፊው ማኅበር ብቻ ናቸው። እንደክርስቲያን መፍራት የሚገባቸው የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን ብቻ መሆን እንደሚገባው  ብናምንም እንደሥጋዊ ሰው ድካማቸውን አይተን ማኅበሩ እዳ በደላቸውን አደባባይ እንዳያውለው ቢፈሩ በእርግጥም ሊታዘንላቸው ይገባል እንላለን።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አራት ቦታ ተበታትኖ ልዩ ልዩ ያልጠረቁ ጅቦችን ለማዳረስ ቅርጫው በሲኖዶስ በተወሰነ ጊዜ አባ ኅሩይም አንዱ እግር ደርሷቸው በምዕራብ ክፍለ ከተማ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ተመድበው ነበር። አባ ኅሩይ ብዙዎች ከሚያዝኑባቸውና ከሚያማርሩባቸው ምክንያቶች ዋናውና ግንባር ቀደሙ ጉዳይ ፈርሃ እግዚአብሔር የተለየው ጉቦኝነታቸው ሲሆን እስከዛሬም ብዙዎች እንባቸውን እንደራሔል ወደሰማይ የረጩባቸው ርኅራኄ የለሽ መሆናቸው ነው። አባ ኅሩይ እንኳን ሥራ አስኪያጅ የመሆን ብቃት ምንም የሌላቸው ይሁኑ እንጂ  ጉቦ / ዘረፋ/ በተባለው በሽታ ግን ፈጣንና ጥሩ የገፈፋ ልምድ ያካበቱ እንደሆኑ ገንዘባቸውን የገበሩ ሰዎች በምሬት ሲናገሩ ይደመጣሉ። እሰራልሃለሁ ብለው ሳይሰሩላቸው ያጉላሏቸውና አቤቱታ አቅርበው ከተባባሪ ሌባ አስተዳዳሪዎች ጋር ውስጥ ለውስጥ እየተገናኙ ባለጉዳዩን ያለሥራ ያንሳፈፈፉ፤ ማስጠንቀቂያ እንዲጻፍበት ያስደረጉ፤ የቤተ ክህነቱ ሸክምና የካህናቱ የልቅሶ ምንጭ መሆናቸው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው።
ይህ ግፍና መከራው የበዛባቸውና ሸክሙ የከበዳቸው ካህናት በአንድ ድምጽ ሆ ብለው ጩኸት በማሰማታቸው፤ ጉዳዩ እስከ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ድረስ ቀርቦ ማስረጃዎች በመገኘታቸው የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ የማኅበረ ቅዱሳኑ ተላላኪና የሙሰኞች አባት አባ ኅሩይ ወንድይፍራው በሊቀጳጳሱ ደብዳቤ ከሥራቸው ታግደዋል።
ከዚህ በፊት «ደጀሰላም» ብሎግ እኒህን ሙሰኛ መነኩሴ ሲያንቆለጳጵሳቸውና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተስማምተው ለመስራት ተነሳሽነቱ ያላቸው እያለ ለመካብ የሞከረ ቢሆንም በወቅቱ እንደዘገብነው ጊዜውን ጠብቆ ማንነታቸው ገሃድ ወጥቶ እነሆ በሙስና ተግባራቸው ከስራቸው እስከመታገድ ደርሰው የተሸፈነው ሲገለጥ ለማየት ችለናል። ጊዜው ቢረዝምም «ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው» እንዲሉ ከብዙ ጥፋት በኋላ ስራቸው  ማንነታቸውን ገልጦ ሰዓቱ ሲደርስ በመናገሩ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን ሲሸማቀቅባቸው፤ እውነታውን ሲለፈልፉ ያልተሰሙት ደግሞ ተግባሩ ራሱ ምስክርነቱን ሰጥቶላቸዋል።  እነማን የማኅበሩ አባላት እንደሆኑ እንደአንድ ማሳያ  ሆኖም ይቆጠራል።
በሌላ መልኩ በእነአሉላ ጥላሁን፤  በእነ መረዋ ዱከሌ በዘመናዊ ስሙ/ ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ/ እና በመሰሎቹ የሚዘወረው ከደጀ ሰላም ብሎግ ሞት በኋላ አዲስ የመጣው የማኅበሩ አገልጋይና የደብረ ብርሃን ወታደር የሆነው/ ሐራ ዘተዋሕዶ/ ብሎግ በአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫ ወቅት የምርጫው ሂደት ፍትሃዊ አይደለም ሲል እንዳልቆየ ሁሉ የፈለገው አለመሳካቱን ሲያረጋግጥ ፓትርያርኩ ከሰማይ የወረዱ መልአክ ናቸው ወደሚል ውዳሴ መሸጋገሩ ፍቅር ስለጸናበት ሳይሆን »ጅብን ሲወጉ……» እንዲሉ ሆኖ በፓትርያርኩ ሙገሳ ተተግኖ «የማኅበሩ መንገድ ይጠረግ፤ ስርጓጉጡም ይቅና» ለማለት ካልሆነ በስተቀር የንግድ ማኅበሩን ነጋዴነትና የሙሰኞች ወዳጅነቱን ሊሸፍነው አይችልም። ለቤተ ክርስቲያን ከማሰብ የመነጨ እንዳይደለም አሳምረን እናውቃለን። ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሙስና አለቃና የቤተክህነቱ ሸክም እንደሆነ የሚነገርለት ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃና  በዙሪያው ያሉ ሙሰኞች የስራ መሰናክል መሆናቸው ባይካድም ማኅበሩ ደግሞ ይህንን ግልጥ ጉድለት በሐራ ተዋሕዶ በኩል ፓትርያርኩን ተጠግቶ እየጮኸ፤  መንገዱን በመዝጋት ማኅበሩ ሰርጎ እንዳይገባ እንቅፋት የሆነባቸውን ሰው በስመ ሙስና አስወግደው  የራሳቸውን የቀን ጅቦች በቦታው ለመተካት ብሎጉ ሲዳክር ይታያል። ነገሩ «ከዝንጀሮ ቆንጆ ማን ይመራርጡ» ስለሆነ የእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ቡድንም ይሁን የደብረ ብርሃኑ ወታደር ቡድን ሁላቸውም በቤተክህነቱ ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደክሙና የፍትህና ርትዕ ዜማ እየጮሁ ቀበሮነታቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ አስመሳይ በላተኞች እንጂ ቤተክህነት የምትሄድበትን የቁልቁሊት መንገድ ለማቃናት ተፈጥሮም ዓላማም የላቸውም። ምክንያቱም  እነንቡረ እድ የሚታሙበትን ሙሰኝነት በተቃራኒው በማኅበሩ አባልና ደጋፊ በአባ ኅሩይም በኩልም እየተገለጸ ይገኛልና። ሁሉም ሙሰኞችና ነጋዴዎች ስለሆኑ ከቤተክህነት ዐውድ መገኘታቸው አንዱ አንዱን ለመጣል በሚደረገው የባለሥልጣናት ጥገኛ የመሆን አባዜ ውስጥ ቤተ ክህነቱን የመንፈሳዊነት ሳይሆን የጥቅም ጦር ዐውድማ አድርገዋታል።
ለፓትርያርኩ የምናሳስበውና የምንጠይቀው ዐብይ ነጥብ ማንም የቤተ ክህነቱ አዛኝ መስሎ የሚጮኸውን ሁሉ በግ ብለው እንዳይቆጥሩና እንዳይታለሉ ሲሆን የመዋቅር ለውጥ፤ የአስተዳደር ሪፎርም፤ የሥራና ሠራተኛ ግንኙነትን ማሻሻል፤ ሕግና ደንብ ገዢ ማዕከል እንዲሆን በማስቻል አዲስ የሥራ መንፈስን በመፍጠር እንጂ በጥገናዊ ለውጥ አንዱን በማቅረብ ሌላውን በማራቅ ላይ አይጠመዱ ድምጻችን ነው። የአባ ኅሩይን የእግድ ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ