ጽሁፍ፤ በተስፋ አዲስ (ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት የቀረበ ነው)1
ክፍል አንድ
ተሐድሶዎች እነማን ናቸው?
ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ የስብከት ካሴት ሳዳምጥ፤ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን ሳነብ ፡ተሃድሶዎች ተሐድሶዎች፡ የሚል ጩኸት እሰማለሁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የተቋቋመው ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅት አባላቱም ሆኑ አመራሮቹ ስለተሃድሶዎች በስብከታቸው እና በጽሑፋቸው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ ሳያነሱ አያልፉም።
እኔም ተሐድሶዎችን ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ። ምን ዓይነት አቋም እንዳልቸውና የት እንደሚገኙ፤ አላማቸው ምን እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ ፈለግሁ። እነርሱ ግን ተሃድሶ የሚለውን ስም አይቀበሉትም። እኔ ተሃድሶዎች ስል አንባቢ በሚገባው ቋንቋ ለመጠቀም እንዳሰብሁ ይረዳልኝ። ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ማህበርም ከተሐድሶዎች ጋር ያለውን ቅራኔ ለማቅረብ እሞክራለሁ። አንባቢ የራሱን ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ እንዲሠጥ አንዳችም ሳልቀንስ እና ሳልጨምር ትክክለኛውን መረጃ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መነሻየ ግን ከማህበረ ቅዱሳን እና ከተሐድሶዎች ሥነ ጽሑፎች ነው። የሁለቱንም ቡድን እንቅሥቃሴ በተከታታይ አቀርባለሁ መልካም ንባብ።
ተሀድሶ ማለት ይላሉ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉ ወገኖች ማደስ፣ መጠገን፣ ማጽዳት፣ ማለት ነው ይላሉ።ለምሳሌ ቤት ከተሠራ በኋላ ሳይታደስ ብዙ ከቆየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊፈርስ ይችላል ስለዚህ ከመፍረሱ በፊት የሚደርግለት እንክብካቤ ቤቱን ያጸናዋል። እንደሸረሪት ድር፤ የጢስ ጠቀርሻ ያሉ ነገሮችም ከቤቱ ላይ ሊጠረጉ ይገባል። ማደስ ማለት ማፍረስ አይደለም በቤቱ ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፤ ማስወገድ እና በፈረሰው በኩል መጠገን ነው በሌላ አነጋገር መሠረቱን ሳይነኩ እና ሳያናውጡ ጥንታዊነቱን እንደያዘ ቤቱን ማሳመር ማለት ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ ዘመን ከመኖሯ የተነሣ ብዙ ስሕተቶች ይገኙባታልና መጽዳት አላባት፤ ባህሉን ከሃይማኖቱ፤ ውሸቱን ከእውነቱ፤ ክፉውን ከደጉ መለየት አለባት የሚል ራእይ ያላቸውና ለዚህ ሌት ተቀን ያለ እረፍት የሚሠሩ ናቸው።
የሚገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ጳጳሳት፤ ቀሳውስት፤ ዲያቆናት፤ መምህራን፤ የድጓ፤ የቅኔ የቅዳሴ መምህራን የሰንበት ተማሪዎች፤ እንዲሁም ምእመናን ሁሉ ያሉበት የአስተሳሰብ ኃይል ነው። የታወቀ ማህበር ግን የላቸውም። አንዳንዶች ማህበር መሥርተዋል ። ኑራቸው እና ሥራቸው በዚያው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሲሆን በተለያየ ቦታ ጽ/ቤት እና በርካታ ማሰልጠኛዎች አሏቸው። በርካታ መነኮሳት እና ሰባኪዎች በነዚህ ቦታዎች ይሰለጥናሉ። ይህን ሁሉ እንቅሥቃሴ የሚያደርጉት ግን ቤተ ክህነቱ ሳይውቅ ነው። ቀሳውስቱ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በየቤተክርስቲያናቸው ሌሎች ቀሳውስት በመመልመል ያሰልጥናሉ። ከጳጳሳትም ውስጥ ለዚሁ ሥራ የሚውል በግላቸው ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋሉ። ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታና ስልጣን አላቸው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሚሊዮኖች በብዛት ይገኛሉ። በገጠር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና በገዳማት ሁሉ አሉ። ደሞዛቸውን የሚያገኙት ከዚያው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። ግን ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም እርዳታ ያገኛሉ ተብለው ይታማሉ። ተሐድሶዎች እንደቀደምት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አማኞች እንጂ እራሳቸውን ተሃድሶ ብለው አይጠሩም። ስማቸው በሥራቸው ምክንያት ከሚጠሏቸው ወገኖች የተሰጣቸው ነው። በቤተ ክርስቲያን ባሕላዊ ትምህርት ጥልቅ የሆነ ዕውቀት ያላቸው ስለሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተና ደካማ ጎንም ሆነ ጠንካራ ጎን ለይተው የሚያውቁ ሊቃውንት ናቸው። የተሃድሶዎች እንቅሥቃሴ ከባድ እንቅሥቃሴ ነው ምክንያቱም እስከሞት ድረስ የቆረጡ ሲሆኑ ታላቅ ራዕይ ያላቸው ናቸው። በማኅበር መደራጀት ሳይሆን በግል እያንዳንዱ አውቆ መስራት አለበት ስለሚሉ እዚህ ጋ ወይም እዚያ ጋር ናቸው ያሉት አይባልም። በአጭሩ የሌሉበት ቦታ የለም።
የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ነን የሚሉ ጳጳሳት ሳይቀሩ የዚህ ተሐድሶ የሚባለውን እንቅስቃሴ በስውር ይደግፋሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ተሐድሶ የሚባሉት ክፍሎችን ከቤተክርስቲያኒቱ ማስወገድ በፍጹም አይቻልም። ከላይ እስከታች በተያያዘ ሰንሰለት የሚሰሩ ናቸው።