በይትባርከ ገሠሠ
(ይህ ጹሑፍ በሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 389 ረቡዕ የካቲት 13/2005 ታትሞ የወጣ ነው)
በመጀመሪያ የጠራ እምነትና ቃልን መሠረት ማድረግ ይገባል። ስለ እምነት ስንናገር የቁልምጥ ቃላትን ልንጠቀም አይገባም። ዘወትር የክርስቶስ ትምህርት 4ቱ ወንጌላትን ማንበብ ይገባል። ፈሪሳዊያንና ሰዱቃዊያን በስሕተት ጥያቄ ሲዳፈሩት ክርስቶስ ኃይለ ቃል ያለበትን መልስና ትምህርት ያቀርብ ነበር።
በቴክሳስ የተደረገው ጉባኤ እንደ እምነት ወግ የዘገየ ቢሆንም ሙከራው መልካም ነበር ማለት ይቻላል። መሠረተ ይዘቱ ስንመረምር ግን የተጣላች ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡ አንድ ናትና። የተጣላ እምነት አይደለም። እምነት ወይም አምላክ አንድ ነውና። እኔ ልሾም እኔ ልበልጽግ በማለት የተጣሉት መነኮሳት ናቸው እንጂ። ህዝበ ክርስቲያኑ በማያውቀው ምሥጢር እርስ በራሱ ተለይቶ ይኖራል። ምንኩስና ሥርዓት ለሥልጣኑ ሲል በሚፈጥረው ሰበብ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ህዝበ ክርስቲያኑ ሲጨፈጨፍ ሲጣላ ኖሮአል። እንዲህ ሊሆን የቻለውም የምንኩስና ሥርዓት ያለ ታሪኩ፡ ያለ መደቡ፡ ያለ ቦታው፡ ያለ ውሉና……የመሳሰሉትን ሁሉ ረግጦ ከቤተ ክርስቲያንዋ ቁንጮ ወጥቶ ስለ ተከመረ ነው። አሁንም የሚነታረኩ ለራሳቸው ሥልጣን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ለምእመናን አንድነት እንዳይደለ በድርድራቸው ኂደት ማወቅ ይቻላል። መነኩሴና መነኩሴ ተደራድረው የሚፈይዱት ውጤት እንደማይኖር አስቀድሞ ማወቅም ብልህነት ነው። ለዚህ መድኀኒቱ ሌላ ነው። እሱም ሊቃውንት፣ ካህናትና ህዝበ ክርስቲያን አንድ ኃይል ፈጥረው ተዋሕዳዊ መሠረተ ሕግ ካልጣሉበት በቀር እየተድበለበሉ፡ ህዝበ ክርስቲያኑን እያሳዘኑና በነጣቂዎች እያዘረፉ መኖር ነው።
ለመሆኑ አቡነ መልከጼዴቅ ማን ናቸው?
በኢትዮጵያ ኪነ ጽሑፍ ሥርዓት ጽሑፉ ቦታ እንዳያጣ የቀድሞ የክብር ስማቸው ተቀምጦአል። የተዋሕዶ እምነትና የንጉሡም ክብደት ተጨምሮበት ሊሆን ይችላል፡ አንድነትዋንና ክብሯን ሊጠብቁላት የመጨረሻው የክብር ቦታዋ አንድ ደረጃ በቀረው ላይ ሰየመቻቸው፤ አከበረቻቸው። ይሁን እንጂ አገር ውስጥ ሳሉም ለግላቸው ይጠቀሙባት እንደ ነበሩና ለተዋሕዶ እምነት አስተዳደር የማይታዘዙ እንደነበሩ ሕይወት ታሪካቸውን መመልከት ያስፈልጋል። አሁንም ውጪ ሀገር ኄደው ከመጀመሪያ ግንጠላው ጀምሮ የግንጠላው ተጠያቂ እሳቸው ራሳቸው ብቻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ለክብራቸው ለኑሮአቸው ሲሉ ቤተ ክርስቲያንዋን የከፈሏት እሰቸው ናቸው። አቡነ መርቆሬዎስ በፍጹም በዚህ ጉደይ ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም። ግንጠላው ሲከናወን አልነበሩምና። አገር ውስጥ ነው የነበሩ። ኋላ ከጥቁሩ ባሕር ኄደው ተቀላቀሉ እንጂ። አዘጋጁ እንደሚያውቀው አቡነ ይስሐቅም በእሳቸው ተገፋፍተው ፈጸሙት እንጂ አላሰቡበትም ነበር።
ወደ መሠረታዊ አጭር ታሪክ እንግባ። በ1983 ዓ.ም የውጪው ተደራዳሪ ሲኖዶስ ነኝ የሚለው ሲገነጠል በመጀመሪያ የዘመኑ ምስክር አዘጋጁ እንደ ሆነ ማስቀደም ይገባል። ሐምሌ ወር 28 ሐሙስ ቀን ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ሰሚናሪ ኮሌጅ ከሚባል ቦታ ስብሰባ ተጀመረ። በየዓመቱ የአሜሪካ ርክበ ካህናት በአቡነ ይስሐቅ መሪነት ስንሰበሰብ ነበርንና ነው። በየዓመቱ የማይቀሩ የነበሩ በጣም የሚመለከታቸው ካህናት ቄስ አስተርአየ ጽጌና መምህር ፍሥሐ ጽዮን ካሣ የሚባሉ የዋሺንግቶን ዲሰ. ኑዋሪዎች ኢንፎርሜሽን ሳይኖራቸው አይቀርም ፤አንኄድም ብለው ቀሩ። አዘጋጁ ግን ከሥራው ያለ ክፍያ የሳምንት ፈቃድ ወስዶ ከዋሽንግቶን ዲሲ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ኄደ።
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ስብሰባው የተጀመረው ሐሙስ ቀን ነበር። ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ስብሰባው ሲከሃኄድ ተሠውሮበት ነው መሰል የሰማው ነገር አልነበረም። ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ እንገነጠላለን የሚል ሐዲስ ሐሣብ ሰማ። ሀላፊነቱ የአቡነ ይስሐቅ የነበረ ቢሆንም ተገንጣይ ስብሰባውን የመሩት ሊቀጳጳስ መልከጼዴቅ ነበሩ። ለግንጠላው ትልቅ ምክንያት ሆኖ የቀረበውም አባ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው (በነሱ አቀራረብ ሆኖ) ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ኅብረት አይኖረንም ነበር። ከዚህ ችግር የደረሰው የሰሜን አሜሪካ፣ የደቡብ አሜሪካና የኢሮፕ ሀላፊ ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ሳያስቡትና ሳይፈልጉት በአቡነ መልከጼዴቅ ግፊት ግንጠላው ተፈጽሞአል። እኛ ራሳችን ጠንቅቀን የምናውቀው ቢሆንም ኋላ ራሳቸው አቡነ ይስሐቅ ሳላስበው አሳስተውኛል ብለዋል። በመጀመሪያ በዚሁ ግንጠላ የተቃወሙት 1ኛ. አባ ሐዲስ ግደይ ከኒውዮርክ አሁን ሲያትል። 2ኛ. ስም ዘነጋሁ የቤርሙዳ ተወካይ ካህን። 3ኛ. ታናሹ አባ ይስሐቅ ከሚኒሶታ የመጡ። 4ኛ. ራሱ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዋሺንግቶን ዲሲ ነበርን። ደጋፊዎች፡ 1ኛ አቡነ ይስሐቅ 2ኛ. ሊቀጳጳስ መልከጼዴቅ 3ኛ. ሊቀ ካህናት ምሳሌ ከካናዳ 4ኛ. ቄስ ከበደ ከምዕራብ ስቴቶች 5ኛ. ስማቸውን የረሳሁት ከኒውዮርክና ከሌላም። እነዚህ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት 5ኛው ፓትርያርክ እንዲመረጥ በቅድሚያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስማምተው ፈርመው እንደ ነበሩ በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ይታወቃል።
ግንጠላው ሲፈጸም አቡነ መርቆሬዎስ አገር ቤት ስለነበሩ የግንጠላው መሪ ወይም ተባባሪ ሊባሉ አይገባም።