Friday, August 24, 2012

የተወጋ ሲረሳ (ክፍል አንድ)


        የጽሁፍ ምንጭ፤ betefikir.blogspot.com
የወደደንን መውደድ፣ የጠላንን መጥላት፣ ለዋለልን መስጠት፣ ለነፈገን መንሣት፣ ላሰበልን መራራት፣ ለዘነጋን መክፋት የብዙኃኑ የሰው ልጅ የአኗኗር መመሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን በጸጋ ዘመን ላይ ብንገኝም ዓለም ገና ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ ከሚለው ምላሽ አልጸዳችም፡፡ እንዲያውም በዚህ ሕግ ግልጽ ሆኖ ከሚስተዋለው ለጠሉኝ እሬት አይነት አካሄድ በበለጠና በረቀቀ መንገድ ሰዎች የልባቸውን ፈቃድ እያረኩ ነው፡፡ ለብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን እሾህን በእሾህ፣ ደምን በደም የመመለስ ኑሮ ከእምነት ጋር አቻችሎ ማስኬድ አልከበዳቸውም፡፡ ክፉውም ጋር ደጉም ጋር ቋሚ ተሰላፊ የሆኑ ጥቂት ሆድ ሲብሳቸውያስቀመጥኩትን ቆንጨራ እንዳላመጣው?” በማለት የሚዝቱ ሁሉን ትተው ሳይሆን ሁሉን ለክፉ ቀን አስቀምጠው የተከተሉት አይናችን ስር ናቸው፡፡
         አብዛኞቻችን ሰው በሚለውና ክርስቲያን በሚለው መጠሪያ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ አንለውም፡፡ ሰው ከምድራዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ ሲሆን፤ ክርስቲያን የሚለው ደግሞ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ ነው፡፡ ሰው በመሆን ውስጥ በምድራዊ ስፍራና በሥጋዊ በረከት መርካት ሲስተዋልበት፡፡ (ማለትም በዚህ ምድር የምንሰበስበው ሁሉ ከፀሐይ በታች ሲሆን) ክርስቲያን በመሆን ውስጥ ደግሞ በሰማያዊ ስፍራና በመንፈሳዊ በረከት መባረክን እናስተውላለን (ኤፌ. 1÷3)፡፡
         ሰው በመሆን ልደት ይህንን ዓለም በሥጋና በደም አቋም ሆነን እንቀላቀላለን፡፡ ክርስቲያን በመሆን (ዳግም በመወለድ) ደግሞ የዘላለም ሕይወትን መቀላቀል ደግሞም የተዋረደው ሥጋችን የጌታን ክቡር ሰውነት መስሎ በሰማይ ከእርሱ ጋር እንነግሳለን፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ሁሉ ሰው መሆንን ቢጋራም ሰው ሁሉ ግን ክርስቲያን አይደለም፡፡ በዚህም ክርስቲያን መሆን ሰው ከመሆን በእጅጉ ከፍ ያለ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
         ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፣ እንዲከስህም እጀ ጠባብህን እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፣ ማንም ሰው አንድ ምእራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” (ማቴ. 5÷38-42)፡፡ ጌታ በዚህ ክፍል  ላይ ያስተማረው ትምህርት ሰው በሚለውና ክርስቲያን በሚለው ስያሜ መካከል ያለውን ተግባራዊ ልዩነት ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ለሚያዘን ነገር ሁሉ የምንፈጽምበትን ኃይል እንደሚሰጠን መተማመን በዚህ ክፍል የተገለጸውን ትምህርት በቅንነት ለመረዳት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ቀኝ ጉንጭን በጥፊ መመታት ውስጥ ያለው ክርስትና ሳይሆን ሰው መሆን ነው፡፡
            እጀ ጠባብን ለሚወስድ ያንኑ መተው ሰው በመሆን ደረጃ የሚከናወን ተግባር እንጂ ክርስቲያን መሆንን አይጠይቅም፡፡ አንድ ምእራፍ በመሄድ ውስጥም እንዲሁ ከክርስትና ይልቅ ያለው ሰው መሆን ነው፡፡ የክርስትናው የአኗኗር ልኬት የሚጀምረው ታዲያ የቱ ጋር ነው? ካልን ሁለተኛውን ጉንጭ በመስጠት፣ መጎናጸፊያን በመጨመር፣ ሁለተኛውን ምእራፍ በመሄድ የሚል ይሆናል፡፡ ከዚህ ያነሰው ግን ማንም ሰው ከሰብአዊ ርኅራኄ በመነሣት አልያም ከሥጋ ሕግ በመነጨ ሁኔታ የሚከውነው ነው፡፡የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ. 5÷46)፡፡
         የነከሰንን ማጉረስ፣ የበደለንን መካስ፣ የተጣላንን ገፍቶ መታረቅ፣ የረገመንን ከልብ መመረቅ ተወግቶ እንደ መርሳት ነው፡፡ ጉዳቱ እያለ በደልን አለመቁጠር፣ ስቃዩ እየታየ ጥፋትን መተው፣ ጉድለቱ እየተስተዋለ ኪሳራን አለማስላት መንፈሳዊ የኑሮ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡ ክርስትና የተወጋ ሲረሳ ነው!
         ከብሉይ ኪዳን በዳዊትና በሳኦል መካከል የነበረው የገፊና ተገፊ፣ ያሳዳጅና ተሰዳጅ፣ የጠዪና ተጠይ ታሪክ ለተነሣንበት ርእስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ወደ ንግሥና የመጣበትን መንገድ የስነ መለኮት አዋቂዎች ሲያስረዱእግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የተስማማበት ሂደት ነውይላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሳኦል የእስራኤል ንጉስ የሆነው እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት ሳይሆን በሕዝቡ ፍላጎት ተመርጦ በእግዚአብሔር አጽዳቂነት መሆኑ ነው፡፡
          እግዚአብሔር ሳሙኤልንእንደጠየቁ ቀባላቸውበማለት ከሕዝቡ አሳብ ጋር ተስማማ፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቸኛው ክፍል እንደሆነ ይነገራል (1 ሳሙ. 15)፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ከአሳባችን ጋር ከተስማማ ኪሳራው የሰው ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን ያለፈውን ፍላጎታችንን እና ዛሬ በዚያ ፍላጎት ላይ ያለንን አተያየት ብንመለከተው ለየቅል ነው፡፡ ያኔ እግዚአብሔር በፊቱ ካቀረብነው አሳብ ጋር ተስማምቶ ቢሆን፤ እንደጠየቅነው ሁሉን ቢሰጠን ኖሮ ዛሬ ከምናፍርበት ነገር ጋር ለመኖር  በተገደድን ነበር፡፡
          እግዚአብሔር ሲሰጥ ብቻ ሳይሆን ሲከለክል፣ ሲመልስ ብቻ ሳይሆን ዝም ሲል፣ ሲያኖር ብቻ ሳይሆን ሲገድልም አይሳሳትም፡፡ የእርሱ ጌትነት ምቾትን ብቻ ሳይሆን ጉስቁልናንም ያጠቃልላል፡፡ ክርስትና መብዛትን ብቻ ሳይሆን መዋረድን፣ መጥገብን ብቻ ሳይሆን መራብን፣ ከፍታን ብቻ ሳይሆን መጉደልንም ማወቅ ጭምር ነው (ፊል. 4÷12)፡፡ 

Thursday, August 23, 2012

የቅዱስነታቸው ቀብር በደማቅ ሁኔታ ተፈጸመ።


የጽሁፍ ምንጭ፤ ዓውደ ምሕረት

76 ዓመታቸው ያረፉት የብጹዕ ወቅዱስ / አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአለም የአብያተክርስትያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የዓለም ሰላም አምባሳደር ስርዓተ ቀብር ዛሬ ነሐሴ 17 2004 .. ከቀኑ 730 ላይ በደማቅ ሁኔታ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የቅዱስነታቸው ስርዓተ ቀብር ላይ ቁጥሩ እጅግ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የተገኘ ሲሆን ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የእህት አብያተ ክርስቲያናት አባቶች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ ምክትል አፈጉባዬ / ሽታዬ ምናለ፤ አምባሳደሮች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትና በአክሱም ካሕናት እምቢልታ የታጀበ የቀብር ስነ ስርዓት ተደርጎላቸዋል።
አቡነ ገሪማ የህይወት ታሪካቸውን ያነበቡ ሲሆን የእህት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እና የመንግስት ባለስልጣናትም ንግግር አድርገዋል። ሥነ ስርዓቱ በፖሊስ ማርሽና የሰንበት ተማሪዎችም ዝማሬ የታጀበ ነበረ።
በትናንትና ዕለት የጀመረው እጅግ ደማቅ የነበረው ስነስርዓትም በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል። ትናንትና ከቅዳሴ በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን በሰረገላ ሆኖ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በርካታ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት የእህት አባተ ክርስታናት ተወካዮች፤ የመንግስት ባለስልጣናት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በሊቃውንተ ቤተክርስትያን በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በአዲስ አበባ ፖሊስ ሰራዊት ባንድ በምዕመናንና በምዕመናት በክብር ታጅቦ በደመቀ ስነስርዓት የተካሄደውን የሽኝት ስነስርዓት ተመልካችን እጅግ አስደሳች ነበረ።
ከምሽቱ 200 ጀምሮ እስከ ንጋቱ ድረስ ለሊቱን በሙሉ ጸሎተ ማህሌት ሲከናወን አድሯል ንጋት 1230 ላይ አስከሬኑ ባለፈበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና አኅት አብያተክርስትያን ተወካዮች ባሉበት ስርዓተ ቅዳሴው ተከናውኗል ጸሎቱ እንዳበቀ የቅዱስነታቸው አስከሬን በክብር ታጅቦ ወደ አውደ ምህረት ወጥቷል በተዘጋጀለት ቦታ ላይ ለሰዓታት አርፏል፡፡
ይህን ተከትሎም ስነስርዓቱ የጀመረ ሲሆን የደመቀ የሚለው ቃል ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ባማረ ሁኔታ የቀብሩ ስነስርዓት ተፈጽሟል።

Wednesday, August 22, 2012

የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር ሐሙስ ይፈጸማል፤ መጪው ዘመንስ ምን ይመስል ይሆን?


ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ እነሆ አንድ ሳምንት ሊሆናቸው ነው። የሚወዷቸው አዝነዋል፤ የሚጠሏቸውም ደስ ተሰኝተዋል። አንዳንዶች ቢጠሏቸውም እንኳን ሞት የጋራ ርስት መሆኑን በማመን እግዚአብሔር እረፍቱን ይሰጣቸው ዘንድ ከልባቸው ተመኝተዋል።
አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ መጪው ዘመን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገሪቱ ምን ይመጣ ይሆን? በሚል ሃሳብ ረጅሙን ጊዜ በማስላት ይጨነቃል። በእርግጥም ሟቾች ጥፋትም ይስሩ ልማት ላይመለሱ ሄደዋል። የነበሩበት ቦታ ትልቅ የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሥልጣን ደረጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ አባትነት ሊመራ የሚችልን ሰው በማግኘት አንጻር ቢያሳስበን አይገርምም። በስጋዊ ሥልጣን ደረጃም እንደዚሁ በሀገር መሪነት ደረጃ የሚመጣው ሰው የነበሩ ድክመቶችን በማስተካከል፤ የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ስለመቻሉ ቢያሳስበን እንደዜጋ ከተገቢነቱ የወጣ አስተሳሰብ አይደለም።
 ቀና ቀናውን አስበን፤ መጪውን ጊዜ ብንፈራ ሰው ነንና ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ክፉም ሆነ ጨካኝ ገዢ የሚመጣብንና የመጣብን መሪዎች ክፉ ወይም ደግ ለመሆን ስለፈለጉ ሳይሆን ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተላልፎ የተሰጠ አምልኰ ስላለን መሆኑን አምነን ልንቀበል ይገባል።
እግዚአብሔር ለዳዊት በተናገረው ቃል ላይ ከወገቡ የሚወጣው ልጅ እንደሕጉ ከሄደ መልካም የሆነው ነገር ሁሉ ከፈጣሪው እንደሚሆንለት፤ ክፋትን በፈጸመ ጊዜ ደግሞ የሰው መቅጫ በትር እንደሚላክበት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጾ ይገኛል።
2 ሳሙ 714
እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ
እኛ ደጎችና የእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጻሚዎች ሆነን ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በቅጣት ወይም በመከራ ውስጥ አይተወንም ነበር። ስለዚህ ለሆነውና ለሚሆነው ሁሉ ጥፋተኞች እኛ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። 
ኢዮብ 3412    
በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።
የሚያሳዝነው ነገር ኢትዮጵያውያን በማንነታችን ስንመዘን ፊታችንን ወደእግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች ያልሆንን እልከኛ ህዝቦች መሆናችን ሲታይ መከራ የምንለው ነገር ማብቂያው ገና ረጅም ነው። ከጣዖት አምልኰ ገና አልተላቀቅንም። አምልኮቶቻችን ብዙዎች ናቸው። እግዚአብሔርን በከንፈሩ የሚያከብር በልብ ግን ከፊቱ የራቅን ሕዝቦች ነን። ከመበላላት ገና አልወጣንም። ሥልጣንን ጠልፎ ለመውሰድ ከሚደረግ የሽንገላና የተንኮል ተግባር ገና አልተላቀቅንም። ቤተክህነቱም ሆነ ቤተመንግሥቱ ለእግዚአብሔር ይገዛ ዘንድ ለፈቀደ ሕዝብ ገና ዝግጁ አይደለም።  ሁሉም ያሰፈሰፈው ለወንበሯ ነው። ሀገሪቱ በሃሳብ ነውጥ ተወጥራለች። ሰላም ነን እያልን ራሳችንን ካልሸነገልን በስተቀር አየሩ በሁከትና በሃሳብ ተበክሏል። ይህ ካልጸዳ የሀገሪቱ ችግር አላባራም ማለት ነው። አዎ መጪው ዘመን ያስፈራል። አመላችንና አኗኗራችን ገና አልተስማማም።