በፍቄ ከአዲስ አበባ፣
ባሕር ማዶ ካሉ ሰዎችጋ ስናወራ አንዳንድ የማይገቡን ወሬዎችን እየሰማን ጭንቅላታችንን እየናጥን “ወቸ ጉድ!” ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡ ለኛ ባዳ ከሆነው ከቀላሉ “GPS” ጀምሮ፣ credit card ቢሉ፣ ምን ቢሉ ሁሉም ለኛ እንቆቅልሾች ናቸው፡፡ ወጉ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ “GPS” ቀርቶብኝ እበላው ባገኘሁ የሚለው እስኪታወሰን ድረስ እንደመማለን፡፡ እዚህ GPS የለም፣ credit card የለም፣ ባቡር (ወይም subway
station ብሎ ቋንቋ) የለም፣ smart phone የለም፣ wi-fi የለም (አለ እንዴ?) ለነገሩ የዚህ ጫወታ ጉዳዮች እነዚህ ሁሉ ስላልሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ በርግጥ ግን ወደጫወታው አጀንዳ ለመድረስ አሁንም ዳር፣ ዳሩን መነካካት የግድ ነው፡፡ ‹አሜሪካኖች ለምን ወፋፍራም ሆኑ? ኢትዮጵያውያኖች ለምን ቀጫጭን ሆኑ?› ብለን ብንጀምርስ!
ያልተመጣጠነ ውፍረት ለ75 በመቶ አሜሪካውያን የጤና እክል እየፈጠረ ነው፤ ለ75 በመቶ ኢትዮጵያውያን ደግሞ (ይህ ቁጥር በጥናት አልተረጋገጠም እንጂ፣) ችግራችን ቅጥነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በobesity ሳይሆን በምግብ እጥረት፣ በጨጓራ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎችን ነው ማግኘት የሚቻለው፡፡ ለምን ብለን የጠየቅን እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣናቸው አፍላ ዘመን ቃል በገቡት መሠረት “በቀን ሦስቴ መብላት” ባለመቻላችን ነው፡፡ በቀን ሦስቴ መብላት ማለት አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ማለት አይደለም፡፡ በሦስተኛ ክፍል ሳይንስ ላይ እንደተማርነው የተመጣጠነ ምግብ መብላት ማለት ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ደግሞ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት፣ ፋት፣ ቫይታሚኖችና ማዕድኖችን መያዝ አለበት፡፡
የኢትዮጵያውያንን አመጋገብ በጥቅሉ በአንድ መስመር መተረክ ይቻላል፡፡ ቁርስ፤ ዳቦ በሻይ (ሻይ ከተገኘ!)፣ ምሳ፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፣ እራት፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፡፡ በዚህ የአመጋገብ ልምድ ውስጥ የሚካተቱት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ እና ውሃ ናቸው፡፡ በርግጥ በስንዴ ውስጥ ካርቦሃይድሬት፣ በጤፍ ውስጥ iron (ብረት ነክ ማዕድን)፣ በባቄላ ውስጥ ፕሮቲን አለ፡፡ ፋት ግን ምናልባት እንደሽሮፕ በማንኪያ በምትጨመረው ዘይት ውስጥ ካልሆነ በቀር የለም፤ ስለዚህ የሚያወፍረን ምንም ነገር የለም፡፡ በምግብ ዝርዝራችን ውስጥ የሚያወፍር ነገር አለመኖሩ እሰዬው፣ ነገር ግን በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚያጎለብት÷ የፍራፍሬና የአትክልት dessert እንዳይኖር እርጥብ አገራችንን ያደረቃት ማነው?
የልምድ Vegetarians
ኢትዮጵያውያን የኑሮ ነገር ሁኖብን ከጥንትም ጀምሮ የምንመገበው የምግብ ዓይነት vegetarian የሚያሰኘን ነው፡፡ የጤፍና ባቄላ ድምር!!! በርግጥ ብዙዎቻችን የምግብ ምርጫችን ምን እንደሆነ ስንጠየቅ ቁርጥ ወይም ክትፎ ልንል እንችላለን፡፡ የምግብ ምርጫችን ግን አምሮታችን እንጂ÷ ‘የምናዘወትረው የምግብ ዓይነት ነው’ የሚል ትርጉም እንደሌለው ሁላችንም ይገባናል፡፡
ቬጂቴሪያንነትም ሆነ ቅጥነት ዕድሜን እንደሚቀጥል ምሁራኑ ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ የወፋፍራሞቹ አሜሪካውያን አማካይ ዕድሜ 70ን ሲዘልቅ፣ የቀጫጭኖቹና የልምድ ቬጂቴሪያኖቹ ኢትዮጵያውያን ዕድሜ ግን ሃምሳ መድረስ አቅቶታል፡፡ ‹የዘመኑ ምርጫ፣ ምን እና ቀጫጫ› የተባለውን እውነታ አፈርድሜ አስበልቶ፣ ውፍረትን እንደምቾትና እንደጤነኝነት ባገራችን እንዲቆጠር ያደረገው ማነው?
“ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው”
ይህች አባባል አገልግሎት ላይ የምትውለው ብዙ በሊታ ከሲታዎችን ለመተቸት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‹እውን በሊታ ከሲታዎች አሉ?› ብለን ከጠየቅን ውዥንብር ውስጥ መውደቃችን አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዴ አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ሆድን ከመቆዘርና፣ ጨጓራን ለበሽታ ከመዳረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡
“ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው” የሚለው አባባል እንደየሃገሩ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን እኛጋ ብዙ የሚበሉት ናቸው የሚከሱት ብሎ ለመሳለቅ ቢያገለግልም፤ ወፋፍራሞቹ ዓለም ግን ብዙ መብላት ለውፍረት፤ ውፍረት ደግሞ ለበሽታ ወይም ሞት ይዳርጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው፡፡
እኛ አገር ግን ምግብ ይከበራል፡፡ “ገበታ ንጉሥ ነው” ነው ከነአባባሉ፡፡ ሁሉም ንጉሥ ከሚሊዮን አንድ ነው፤ ታዲያ ገበታን ከንጉሥ እኩል ምን አደረገው ብለን ስንጠይቅ መልስ ሊሆን የሚችለው “ገበታ በሃገራችን ከሚሊዮን አንድ ነው” የሚል ይሆናል፡፡ ሌላው ዓለም በሌለ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ ከንጉሥ እኩል ይከበራል፣ ይዘፈንለታል፡፡ በዘፈን ክሊፖቻችን ሳይቀር ለእንቁልልጭ ይቀርባል፡፡ ለምን? ምግብ ብርቅ ነዋ! ምግብን ከጥንት እስከዛሬ በሃገራችን ብርቅ ሆኖ እንዲቀር ያደረገው ማነው?