ስለምልጃ ( ክፍል አንድ )


መጽሐፍ ቅዱዊ የአማላጅ ትርጉም
መግቢያ
እውነትን ማወቅ እጅግ መልካም ነገር ነው። ለማይኖርበት ሰው ግን እውነትን ማወቅ ምን ይጠቅመዋል? ለሚኖርበት ግን እውነተኛውን የሕይወት ነጻነት ያጎናጽፈዋል፤ ነፍሱንም ያሳርፋል (ኤርምያስ 616 ማቴዎስ 1128)፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «…ያመኑትን አይሁድ፡- እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» ያላቸው (ዮሐንስ 831-32)፡፡
እኛም እውነት ከኃጢአት ባርነት ነፃ እንደሚያወጣ ካመንን እውነቱን ከራሱ ከባለቤቱ ወይም ከምንጩ መስማትን የመሰለ ነገር እንደሌለም መዘንጋት የለብንም፡፡ ከምንጩ መስማትን መውደድና መምረጥ ስሜትን ሳይሆን እውቀትን መሠረት ያደረገ የሕይወት ጉዞን ወደ መምራት ያደርሰናል፡፡ የነጠረው እውነት ሲገለጥም ከማፈር ይታደጋልከሁሉም በላይ ከዘላላም ጥፋት ያድናል (ምሳሌ 119)::
ነገር ግን የራስን ግንዛቤ ወይም ከሌሎች የተቀዳን የተሳሳተ እሳቤ እንደ መልካም እውቀት ይዞ መጓዝ የኃጢአት ባሪያ አድርጎ ያኖራል። አንድ ሰው ያለው እውቀትና ማንነቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እውቀቱ ማንነቱንና አመለካከቱን ይወስናልና፡፡
እውቀት ጥቅሙ ሥራ ላይ ሲውል በተግባርም ሲተረጎም አይደል፡፡ በዚህ ከተስማማን ደግሞ እውነቱ ሲገለጥ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ደርሶ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አስተዋይነት ነው፡፡ እውነትን በእውነትነቱ ተቀብለው መታዘዝን የሚፈቅዱ ሁሉ የቀድሞ አመለካከታቸው ልክ አለመሆኑን ተገንዝበዋልና ስህተታቸውን ለማረም አያንገራግሩም፡፡ በተለይ ወደ ዘላለማዊው ሕይወት ስለሚያደርስ የጽድቅ መንገድ ሲነሳና እውነቱ ሲገለጥ ውሳኔውም ብርቱና የጸና ሊሆን ይገባዋል፣ የዘላለም ሕይወት ነውና!
ስለዚህ ስለ ቀጥተኛ መለኮታዊ መንገድ ለማወቅና ለማሳውቅ የእውነት ምንጭ ከሆነውና አማራጭ ከሌለው ሕያው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እውነትን በማወቅና ባወቁት እውነት በመኖር ከኃጢአት ባርነት ነፃ ወጥተው ወደ ዘላለም ሕይወት ለመጓዝ ለሚፈቅዱ ሰዎች ሁሉ ይህ ትምህርት ስለ አማላጅና ከምልጃ ጋር ተዛማጅነት ስላላቸው ነጥቦች እውነቱን ለማሳየት ቀርቦአል።
ክፍል አንድ
በዚህ ክፍል «አማላጅ» ምን ማለት እንደሆነ የቃሉን ፍቺ በመመልከት እንዲሁም «ምልጃ» እንደ እግዚአብሔር ቃል በስንት እንደሚከፈል እናያለን።
1. አማላጅ  ምን ማለት ነው?
«አማላጅ» የሚለው ቃል የተገኘው «ማለደ» ከሚል ግስ ሲሆን «ማለደ» ማለት ደግሞ «ለመነ» ወይም «ጸለየ» ማለት ይሆናል። « መማለድ ማማለድ… » ማለት  «መለመን ማስታረቅ» ሲሆን «አማላጅ» ደግሞ ይህን ተግባር የሚያከናውን ነው፡፡ ተግባሩ ደግሞ «ምልጃ» ይባላል፡፡
ነገር ግን «ማለደ» የሚለው ቃል ሁለተኛ ትርጉምም አለው፡፡ ይኸውም «ማለዳ ተነሳ» ወይም «በጠዋት ተነሳ» ለማለት ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦
     «አቢሜሌክም በነገታው ማለደ፥ ባሪያዎቹንም ሁሉ ጠራ…» (ዘፍጥረት 208)
    «ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ»
(1ሳሙኤል 1512)፡፡
ማለዳ (በጣም በጠዋት) የሚነሳ ሰው «ማላጅ» ይባላል። ስለዚህ በኤርምያስ 725 «እየማለድሁ» የሚለው ቃል «ማለዳ፥ በጠዋት ወይም ሳይረፍድ ወይም ጊዜው ሳያልፍ» ከሚል ትርጉም ውጭ ከምልጃ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እንዲሁም በመዝ. 119148 «ቃልህን አስብ ዘንድ ዓይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ» ሲልም «ለመማለድ» ማለቱ ሳይነጋ ለመነሳት ማለት ነው እንጂ በጸሎት ፈጣሪውን መለመኑን ለማመልከት አይደለም፡፡
2. ምልጃ በስንት ይከፈላል?
«አማላጅ» ማለት ምልጃን የሚያቀርብ ቢሆንም «ምልጃ» ሁሉ ግን አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቃል ምልጃን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች መድበን ልንመለከተው እንችላለን:-
¨ የክርስቶስ ምልጃ /ኢሳይያስ 531-12/
¨ በአጸደ-ሥጋ ያሉ ሰዎች የጸሎት ምልጃ /2ቆሮንቶስ 914/
¨ የእጅ መንሻ /የጉቦ/ ምልጃ  /ዘዳግም 1016/ ናቸው።
እነዚህን የምልጃ ዓይነቶች በቅደም ተከተል ሰፋ አድርገን በቀጣይ ክፍሎች እንመለከታቸዋለን።
ክፍል ሁለት
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር «ማለደያማልዳልይማልዳል…» ብሎ በግልጽና በተደጋጋሚ ይናገራል። ነገር ግን ክርስቶስ «አምላክ ነውና ወደ ማን ይማልዳልብሎ መጠየቅ ተገቢ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልሱን ደግሞ አሜን ብሎ መቀበል መንፈሳዊ ብስለት ነው፡፡
በክርስቶስ የተከናወኑ ሁለት ዓይነት ምልጃዎች አሉ። እነርሱም የክርስቶስ የጸሎት ምልጃ እና በክርስቶስ የመስቀሉ ሥራ (መስዋዕትነት) የተፈፀመ የኃጢአት ሥርየት ምልጃ ናቸው።
1. የክርስቶስ የጸሎት ምልጃ
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ሆኖ ሳለ፣ በሥጋ ተገልጦ ጻድቅ ሰው ለጌታው እንዴት መገዛት እንዳለበት በተግባር ያሳየ፤ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ሰው አንዴት አምላኩን ማምለክ እንዳለበት ያስተማረ ነው (ማቴዎስ 1128 ዮሐንስ 1313)
ለምሳሌ በማቴዎስ 313-15 የተጻፈውን ቃል እንመልከት «ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት።» ሰው ሁሉ ኃጢአቱን እየተናዘዘ ሲጠመቅ ክርስቶስ ግን «እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና» በማለት የጽድቅን  አፈጻጸም በተግባር አሳይቶአል።
በመሆኑም ዕብራውያን 31 “…ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤በማለት የክርስቶስ የጸሎት ምልጃ፣ ከሰዎች የጸሎት ምልጃ የሚለየው የማዳን ሥራውን እየሠራ ለተከተሉት ሁሉ ምሳሌ ለመሆን የጸለየ በመሆኑ ነው።
ስለዚህም አይደል 1ጴጥሮስ 221 ሐዋርያው ጴጥሮስ  «የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና» ብሎ የጻፈው?
ኢየሱስ ለሐዋርያው በሉቃስ 2231-32 «…ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና…» ብሎት ስለነበር ነው (ዮሐንስ 171-26 ማቴዎስ 2638-45 ዕብራውያን 57)፡፡
2. በክርስቶስ የመስቀሉ ሥራ (መስዋዕትነት) የተፈፀመ ምልጃ
በክርስቶስ የቀረበውን የኃጢአት ስርየት ምልጃ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያብራራው፣ የክርስቶስን ጸሎት በማመልከት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በአጠቃላይ ያከናወናቸውን የእርቅ ሥራዎች የሚያካትት አድርጎ ነው፡፡
የሰው ሁሉ አባት ወይም በኩር የሆነው አዳም (ሐዋ. 1726-27) በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት በሰው ሁሉ ላይ የሞት እዳ ወደቀ፤ በሰውና በፈጣሪ መካከልም ጥል ሆነ፡፡ ሰው ከአምላኩ ተለይቶ ይጥፋ ካልተባለ በስተቀር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የኃጢአት መጋረጃ የሚቀድድና ሰውን ከአምላኩ ጋር የሚያስማማ ወይም በመካከል ገብቶ የሚያስታርቅ የግድ ማስፈለጉ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን የኃጢአትን መጋረጃ ማን ይቅደደው? ማንስ በመሐል ይግባ? ማንስ ያስታርቅ?
ለመሆኑ ሰው እግዚአብሔርን የበደለው እንዴትና መቼ ነው? የዚህን መልስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 እና 3 እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጅቶና በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎ ሕያው ነፍስ ያለው ካደረገው በኋላ (ዘፍጥረት 27) በዔድን ገነት አኖረው (ዘፍጥረት 28)፡፡ የፈጠረውንም ሰው (አዳምን) እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- «ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና» (ዘፍጥረት 216-17)፡፡ የምትረዳውንና አብራውም የምትሆንን ሴት (ሔዋንን) ፈጠረለት። ነገር ግን ሰው የተሰጠውን ትዕዛዝ አላከበረምና አዳምም ሆነ ሚስቱ ሔዋን ከፍሬው በሉ፣ ከእግዚአብሔርም ፊት ሸሹ፡፡ «…ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ» (ዘፍጥረት 38)፡፡
የተጣሉትን ለማስታረቅ፣ በበዳይና በተበዳይ መካከል ቆሞ የሚያስማማ ወይም የሚያስታርቅ መካከለኛ ማስፈለጉ ከማንም የተሰወረ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መለኮታዊውን ትእዛዝ የተላለፉትን አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ መካከለኛ ግድ ማስፈለጉ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ማን በመካከል ይግባ? መላእክት ነበሩ ነገር ግን ምንም ሊይደርጉ አልቻሉም። ከሰው ማንም አልነበረም! በምድር ላይ ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩና፡፡ አዳምና ሔዋን ብቻ፡፡ ሁለቱም ኃጢአትን ሠርተው ወደቁ «እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡- ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፣ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፣ አንድ ስንኳ የለም» (ሮሜ 310-12)፡፡
ስለዚህ አዳም የራሱ ኃጢአት እያሳደደውና እርሱም እየሸሸ ባለበት ሰዓት ደርሶ መርዳት የሚችል ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ሆነና እርሱ ራሱ በቃሉ ፍለጋ መጥቶ «…አዳምን ጠርቶ፡- ወዴት ነህ?…» ሲለው፣ አዳምም «በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፣ ተሸሸግሁም» በማለት መለሰ (ዘፍጥረት 39-10)፡፡
እግዚአብሔር የአዳምንና የሔዋንን ውድቀት ተመልክቶና ራቁታቸውን መሆናቸውም እንዳሳፈራቸው አይቶ እንደ ነበሩ አልተዋቸውም፡፡ በቃሉ አማካይነት ፍለጋ መጣ። አማላጅ እስኪልኩ አልጠበቀም። ቢጠብቅም ማንን ሊልኩ ይችላሉ? (ኢሳይያስ 5915-17) በመቀጠልም «…ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፣ አለበሳቸውም» (ዘፍጥረት 321)፡፡ በዚህም ለዘለቄታው የሚሆን የማዳን ልብስ ለሰው እንደሚያለብስ ሲያመለክት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያስገባውን እቅዱን በማሳወቅና የዲያቢሎስን ሥራ የሚያፈርስበትን መንገድ በመግለጽ ለዲያቢሎስ መርዶ ለሰው ዘር የምሥራች ተናገረ (ዘፍጥረት 315 ኢሳይያስ 6110)፡፡ ያለማንም እርዳታ እርቁን /ምልጃውን/ ራሱ እንደሚያከናውነው በተስፋ ቃል ኪዳን አመለከተ፡፡ ምክንያቱም ማንም ጣልቃ የማይገባበት የእርሱ ሥራ ብቻ ነውና፡፡
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበትና መዘንጋትም የሌለበት ዋና ነጥብ የብሉይ ኪዳን ትምህርት በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ለሚያከናውነው የማዳን ሥራ በጥላነት የሚያገለግል መሆኑ ነው።እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነውተብሎ ተጽፎአልና (ቆላስያስ 217)
ስለዚህ የዘፍጥረት 38-21 መልእክት በእግዚአብሔር ብቻ ሊከናወን የሚችል የእርቅ ሥራ /ምልጃ/ መኖሩን ያስገነዝባል። በኤርምያስ 5034 «ተቤዢአቸው ብርቱ ነው፣ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርንም ያሳርፍ ዘንድ በባቢሎንም የሚኖሩትን ያውክ ዘንድ ሙግታቸውን ፈጽሞ ይምዋገታል» የተባለለት የነፍሳችን ጠበቃ ራሱ ጌታ እግዚአብሔር ነው (1ዮሐንስ 21)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን የሚቤዠው ከኃጢአት ሁሉ፣ የሚቤዠውም ራሱ፣ ለራሱና በራሱ ስለሆነ በሮሜ 1136 “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜንይላል።
በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው ፍጥረትን ሁሉ ብቻውን በቃሉ የፈጠረ አምላክ (ዮሐንስ 13) በዘላለም የሞት ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀውን ሰው ለመፈለግና ለማዳን የተጠቀመውም ያንኑ ቃሉን ነውና በመዝ. 10720 “ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸውተብሎ ተጻፈ (ኢሳ. 5511-12)፡፡
«የጠፋውን ለማዳን» (ማቴዎስ 1811) በአዲስ ኪዳን ቃሉን ሥጋ በማድረግ ተገለጠ (ዮሐንስ 114)፡፡ ቃል ሥጋ ሆኖ ሲወለድ የእግዚአብሔር ቃል የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ (ሉቃስ 135 ራእይ 1913)፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ቃል ሥጋ መሆን መቻሉን ለማሳየት ሳይሆን ደም ሳይፈስስ ሥርየት እንደሌለ በዕብራውያን 922 ስለተጻፈ ለሰው ልጆች የኃጢአት ሥርየት መስዋዕት ለመሆን የእግዚአብሔር በግም ተብሎአል፡፡
እግዚአብሔር ተማላጅ /ታራቂ/ ማለትም አምላክ ሆኖ ሳለ ራሱ በሥጋ በመገለጥ አስታራቂ ሆኖአል (1ጢሞ. 316)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በግልጽ እንዲህ ብሎ ጽፎአል «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፣ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ» (2ቆሮንቶስ 519-20)፡፡ ከላይ እንዳየነው ጥለኞች በአማላጅ ማለት በሽማግሌ /በአስታራቂ/ መታረቃቸው የተለመደ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ዓለሙን ከራሱ ጋር በራሱ አስታረቀ! በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋገጠውና የመሰከረለት የኃጢአት ይቅርታ ያስገኘልን አማላጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፤ «የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ተብሎ ተጽፎአልና (ሮሜ 834)፡፡
ቅዱስ ቃሉ በሰው መረዳት አሊያም በትርጉም ሳይሆን ቃል በቃል ማለደ፣ ይማልዳል ይለናል፡፡ ስለዚህ «አማላጅ አይደለም» ወይም «ክርስቶስ አያማልድም» ብሎ ማመንም ሆነ መናገር ለእግዚአብሔር ቃል ባዕድ መሆንን ከማመልከት አይዘልልም።
ለሐዋርያቱም ይህንኑ የምስራች /የእርቅ መልእክት/ ይናገሩ ዘንድ የማስታረቅን ቃል ሰጣቸው፡፡ ዛሬ በመልእክቶቻቸው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው ይለምናሉ (2ቆሮንቶስ 519-20)፡፡ እንዲህ በማለት «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው» (ኤፌሶን 214-16) የምስራች! የጥሉ ግድግዳ በሥጋው ፈርሶአል ይሉናል፡፡ ጥልን በመስቀል መግደል የሚችል ከመላእክትም ሆነ ከሰው ከቶ ስላልተገኘ ሥጋውንም ቆርሶ ደሙን አፍስሶ በኃጢአተኛ ምትክ ራሱን ማቅረብ የቻለ ክርስቶስ ብቻ ነው (ማቴዎስ 2626-27)
ለአዳም ዘር ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት በመሆን ለሰው ዋስ፣ ጠበቃ፣ አማላጅም ተማላጅም ሆኖ ከራሱ ጋር የሚያስታርቅ በምድርም ሆነ በሰማይ ከእግዚአብሔር ክንድ ሌላ በመጥፋቱ «…እግዚአብሔርም አየ፣ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ፡፡ ሰውም እንደሌለ አየ፣ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፣ ጽድቁም አገዘው፡፡ ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፣ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፣ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ» የሚል ቃል በኢሳይያስ 5915-17 ተጻፈ፡፡ በሌላ አነጋገር «የበቀልንም ልብስ ለበሰ» ማለት አምላክ በሥጋ ተገለጠ (1ጢሞቴዎስ 316) ወይም ሥጋ ለብሶ ተገለጦ ጠላትን ተበቀለው ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ክንድ ለማዳን፣ የኃጢአት መስዋእት ለመሆን፣ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት እንደሚገለጥ ሲናገር «እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ» ብሎ በኢሳይያስ 5312 የሰውን ኃጢአት መሸከም የሚችሉ መላእክት ወይም ጻድቃን ወይም ሰማዕታት ሳይሆኑ ራሱ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ተናገረ (መዝሙር 797-9) ገና በብሉይ ኪዳን ዘመን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ኢሳይያስ «ማለደ» በማለት ነው ስለ ክርስቶስ የተነበየው፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው ትንቢቶች በመፈጸማቸው እግዚአብሔር በሥጋ ከተገለጠ በኋላ በአዲስ ኪዳን በግልጽ እንዲህ ተብሎ ተጻፈ «እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፣ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና» (ቆላስይስ 119-20)፡፡
ይህም ቃል ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ያስጨብጠናል፡፡ አንደኛው እግዚአብሔር በሥጋ ተገልጦ በምድር ሲመላለስ መማለዱን ወይም ከራሱ ጋር ማስታረቁን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወደፊትም «ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና…» የሚለው ነው (ዕብራውያን 725)፡፡ ይህም በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ክቡር ደሙ ዛሬም ሆነ እስከ ክርስቶስ ዳግም መመለስ ማንም ኃጢአተኛ ንስሐ ገብቶ በሞተለት ጌታ የሚያድን ስም ቢጠመቅ የኃጢአትን ሥርየት እንደሚሰጠውና ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበትም ብቸኛ መንገድ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ደሙን ያፈሰሰው ለእርቅ ነው። የኃጢአት ይቅርታና እርቅ ደግሞ የሚገኘው /የሚፈፀመው/ በክቡር ደሙ ብቻ ነው።
ይህ የሆነው ከላይ እንዳየነውም በዕብራውያን 922 «እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም» ስለሚል፣ የኃጢአት ይቅርታ የሚያሰጥ አማላጅ በምድር ላይ በመጥፋቱ ምክንያት እግዚአብሔር የገዛ ክንዱን መድኃኒት አድርጎ ስለተገለጠ ነው (ኢሳይያስ 5915-17) በኢሳይያስ 635 እንደተጻፈው ራሱ እግዚአብሔርተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝብሎአል። ይህ የትንቢት ቃል የተፈጸመው እግዚአብሔር የገዛ ክንዱን /ልጁን/ ከዘላለም ሞት የሚታደግ መድኃኒት እንዲሆን በሰጠ ጊዜ ነው (ዮሐ. 129 36 ሮሜ 81-4 ሐዋ. 2028 ይመልከቱ)፡፡ ስለዚህም «ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ» ተባለ (መዝ. 981)
በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (ዕብራውያን 925-28) ላይ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ይላል «ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፣ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፣ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፣ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሠዋ በኋላ፣ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል»፡፡ ሰውንና እግዚአብሔርን የለያየ ኃጢአት ነው፡፡ የሰውን ኃጢአት በማንጻት ከአምላኩ ጋር እንዲታረቅ ማድረግ የሚችል ደግሞ የክርስቶስ ክቡር ደም ብቻ ነው (1ዮሐንስ 17-10 ኤፌሶን 216-18)፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ፍርድና ኃጢአት ይሸከሙ የነበሩና በጥላነት ያገለገሉ ካህናት ነበሩ (ዘጸአት 2830 ዘሌዋውያን 420 263135 1617-19)፡፡ ነገር ግን «እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ (ክርስቶስ) ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል» (ዕብራውያን 723-25)፡፡ ይህም ስለነፍሳችን ቤዛ ሊቆም የሚችል በሥጋውና በደሙ የተሠራው ሥራ ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሊቀርብም ሆነ ሊያቆመን የሚችል ዋስትና እንደሌለው በእጅጉ ያስረዳል፡፡
  «አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ» (1ጢሞቴዎስ 25-6) ሲል በእኛና በእግዚአብሔር መካከል መቆም የሚችል የጥሉን ግድግዳ ያፈረሰበት ሥጋው (የእግዚአብሔር በግ ማለት ክርስቶስ) ብቻ ነው።
  እርሱ ራሱ «በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» (ዮሐንስ 146) ስላለ ዘላለማዊ ቃሉን በማመን ለሚታዘዙ የቀረበው ጥሪ፡- «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ» የሚል ነው (ማቴዎስ 1128)፡፡ ቀጥታ «ወደ እኔ ቅረቡም…» ብሎ የሚጣራውን የፍቅር አምላክ ያለ አማላጅ ይቅርታን የማያውቅ ጨካኝ አምላክ አድርጎ መገመት ትልቅ ስሕተት ነው። አባት ስለሆነ በልጅነት መንፈስ «አባ አባት» ብለን እንድንጠጋው ይፈልጋል (ሮሜ 815 ያዕቆብ 47-8 ይመልከቱ)፡፡
  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ለተከተሉት ለደቀ መዛሙርቱ በማቴዎስ 2122 ላይ «አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ» አላቸው እንጂበአማላጅ የለመናችሁትን ትቀበላላችሁአላለም (ዮሐንስ 1413-14)፡፡ «አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፡፡ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ» ብሎ በግልጽ ተናግሮ የለ? ከዚህ ትምህርት የወጣ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ መሠረት ወደ ምን ያዘነበለ መንገድ እንደሆነ ለማወቅ ከፈለጉ በግልጽ በቆላስይስ 216-18 ተጽፎ ያለውን ቃል ይመልከቱት፡፡
ይህን አባባል እንደ ድፍረት የሚቆጥር ይኖር ይሆን? ካለም ትክክለኛና ቅዱስ ቃሉ የሚደግፈው ድፍረት ነው፡፡ እንዲህ በማለት፡- «የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡ በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመንነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን» (1ዮሐንስ 513-15)፡፡
ክፍል ሦስት
1. በአጸደ-ሥጋ ያሉ ሰዎች የጸሎት ምልጃ
ይህ ምልጃ  በአጸደ-ሥጋ ማለት በምድር ላይ በሕይወት ያሉ ሰዎች ስለ ሌሎች በአጸደ-ሥጋ ስላሉ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚጸልዩትን ጸሎት ወይም የሚያቀርቡትን ልመና የሚያመለክት ነው፡፡ ሰዎች በምድር በሕይወት ሳሉ ወደ እግዚአብሔር ስለሌሎች ሰዎች ይማልዳሉ (ይጸልያሉ)፡፡ «ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፣ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፣ ቁርባኔን ያመጡልኛል» (ሶፎንያስ 310) በማለት ወደ እግዚአብሔር የሚማልዱ እንዳሉና እርሱም ምልጃቸውን እንደሚቀበል ያሳያል፡፡
እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ «ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ» (ፊል. 46) ብሎአል፡፡ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት ደግሞ «እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፣ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ» (1ጢሞቴዎስ. 21-2) በማለት ጽፎአል፡፡
ሐዋርያው ያዕቆብም «ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት፡፡ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች» (ያዕቆብ 514-16) ስላለ አንዱ ስለሌላው ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ (እንዲያማልድ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጸሎት ሥርዓት ነው፡፡ «…ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፣ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል» (2ቆሮንቶስ 914) በማለት በምድር ላይ በአጸደ-ሥጋ ያሉ ቅዱሳን ብቻ አንዱ ስለሌላው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው ልመናና ጸሎት ምልጃ እንደሚባል ያሳያል፡፡
ለምሳሌ፦
  አብርሃም ስለ ሰዶምና ስለ ገሞራ በውስጥዋም ስለነበሩ ቅዱሳን (ለሎጥና ለቤተሰቡ) ወደ እግዚአብሔር እንደ ማለደ (ለመነ) እንመለከታለን (ዘፍጥረት 1823-32)
   ከነናዊቷ ሴት ጋኔን ክፉኛ ይዞአት ለነበረች ልጅዋ ጌታ ኢየሱስን ለምናለች (በማቴዎስ 1522-28) በተጨማሪም በዚሁ ክፍል ላይ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚች ሴት ጌታ ኢየሱስን መለመናቸውን እናያለን፡፡
     የአይሁድ ሽማግሎችም እንኳ ብላቴናው ስለታመመበት የመቶ አለቃ አማልደዋል፡፡ የመቶ አለቃውም «ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው፡፡ እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው፡- ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኩራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት» (ሉቃስ 72-5)፡፡
    ማርያም በዮሐንስ 21-4 ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል   ወይን ጠጅ ማለቁን ለጌታ ኢየሱስ በመንገሩዋ ምክንያት የሠርጉን ቤት ጉድለት ለመሙላት ጌታ ኢየሱስ ውኃው ወይን ጠጅ እንዲሆን አድርጎአል (ዮሐንስ 25-10)
ሐዋርያው ጳውሎስ በአዲስ ኪዳን የጌታ ኢየሱስ መንፈስ በአማኞች ልብ አድሮ ለቅዱሳኑ በጸሎት እንደሚማልድ በሮሜ 826-27 ሲጽፍ «…መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና» በማለት በቅዱሳን ልብ ያደረ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለቅዱሳን እንደሚማልድ ያስተምረናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛውን ማለትም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አጸላለይ ይመራናል። አጥብቀንና አዘወትረን እንድንጸልይም ያግዘናል ያበረታንማል፡፡
ይህም በይሁዳ . 20-21 እንዲህ ተብሎ ተገልጾአል እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ» ይላልና ክርስቲያን በዚህች ምድር ሲኖር ለራሱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ስለ ቅዱሳን ሁሉ ስለ ባለሥልጣናትና ስለ አገር በአጠቃላይ ስለ ሰዎች ሁሉ ወደ አምላኩ መማለድ ይኖርበታል (1ጢሞቴዎስ 21-2)፡፡