Wednesday, April 4, 2018

«አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና»



ዕብራውያን פֶּסַח «ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው። በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል። ደሙን ደግሞ የበሩን ሁለት ረድፍ «መቃንና ጉበኑን» ይቀቡታል። ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።